የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ ህወሓት ያለበትን ውስጣዊ ችግር በመግባባት ፈትቶ እንዲቀርብ የፌደራል መንግሥት ማሳሰቡን ተናገሩ። ለሁለት በተከፈሉ የትህነ አመራሮች እየታመሰ የሚገኘው የክልሉ የፓለቲካ ሁኔታ ከመሻሻል ይልቅ ተባብሶ መቀጠሉም ተናግረዋል።
በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት ምርጫ እስከሚደረግ ድረስ ትግራይን በጊዚያዊነት በማስተዳደሩ አግባብ የፌደራል መንግስት ድርሻ ቢኖረውም፣ መንግስት ሆን ብሎ ለትህነግ መልቀቁን በተደጋጋሚ ማስታወቁ አይዘነጋም። በስምምነቱም ላይ በግልጽ የተቀመጠ ነው። አቶ ጌታቸው ይህንን ዘርዝረው ሳይገልጹ ነው ትህነግ መስማማት ካልቻለ ፌደራል መንግስት ክልሉን እንደሚረከብ የተናገሩት።
” በምንገኝበት የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ የፓለቲካ የአሰላለፍ ለውጥ እየተፈጠረ ነው” ያሉት አቶ ጌታቸው፣ የሚታየውን ለውጥ ተያይዞ ከትግራይ አንጻር ያሉ ዕድሎችና ፈተናዎች መተንተን ያስፈልግ እንደነበር አመልክተዋል። አቶ ጌታቸው ይህን ሲሉ ትግራይ ከክልልነት በዘለለ በአፍሪቃ ቀንድ አገራት በሚጫወቱት ፖለቲካ ከኢትዮጵያ ተነጥላ ወይም በግል ምን ሚና እንደሚኖራት፣ ምን ዓይነት ዕድል ለመጠቀም እንደምትችል ግን አላብራሩም።
” የትግራይ ፓለቲካ ሀገራዊ ፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ መገንዘብ ትቶ በአመራሮቹ እየታመሰ ነው ” ያሉት አቶ ጌታቸው ንግግራቸውና ቁጭታቸው በኢትዮጵያ ማዕቀፍ ውስጥ እንደ ክልል ሊያደርጉ የሚገባቸውን ተሳትፎ ማነሱን ይሁን ሌላ ማለት የፈለጉት ጉዳይ ስለመኖሩ አሁንም ዝርዝር መናገራቸው አልተሰማም።
” የፌደራል መንግስት ውስጣዊ ችግራችንን እንድንፈታ እየገለፀ ነው። ካልተቻለ ግን የማስተዳደር ስልጣኑን ብልፅግና በብቸኝነት እንደሚይዘው ግልፅ አድርጓል ” በማለት የፕሪቶሪያውን ስምምነት ካርድ መንግስት እንደሚመዝ በገደምዳሜ ገልጸዋል።
በትህነግ አመራሮች መካከል የተፈጠረው መከፋፈል ተባብሶ መቀጠሉን የገለጹት አቶ ጌታቸው ረዳ ፤ በቅርቡ በአፍሪካ ህብረት ለሚካሄደው በፕሪቶሪያ የሰላም አፈፃፀም የሚመለከት የግምገማ መድረክ ላይ ከወዲሁ ” እኔ ነው መሳተፍ ያለብኝ ” ወደ ሚል መሳሳብ መጀመሩን ተናግረዋል።
” የትህነግ አመራር ሉዓላዊ የትግራይ ግዛት ከፌደራል የሀገር መከላከያ ሰራዊት ውጭ ያሉ ታጣቂዎች ነጻ ሆኖ ተፈናቃዮች ወደ ቄያቸው የመመለስ ዋና አጀንዳ ዘንግቶ የጊዚያዊ አስተዳደሩ የእለት ተእለት ስራዎች በማድናቀፍ ተጠምዷል ” ሲሉም ከሰዋል። አቶ ጌታቸው “ሉዓላዊ” ሲሉ የሚገልጹት አገላለጽ አሰራርን የሚጥስ፣ በክልል ደረጃ ሉዓላዊ የሚባል ነገር እንደሌለ እንዲያርሙ ከዚህ ቀደም መገሰጻቸው አይዘነጋም።
የውስጥ ችግሩን መፍታት ካልቻለ፣ የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደር የፌዴራል መንግሥት እንደሚረከበው ማሳሰቡን አቶ ጌታቸው ከመናገራቸው በቀር መንግስት በይፋ ያለው ነገር የለም። መንግስት በትህነግ ሰዎች መከፋፈል ዳተኛ መሆኑ አግባብ አይደለም የሚሉ ትችቶች አልፎ አልፎ ቢሰማም እንደ አቶ ጌታቸው ገለጻ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ቡድኖች ከአንዴም ሶስቴ ካልተስማሙ ክልሉን እንደሚነጠቁ ነግሯቸዋል። ውሳኔውም ከፕሪቶሪያው ስምምነትና ከህገ መንግስቱ እንደሚቀዳ ታውቋል።
አቶ ጌታቸው ረዳ በትግራይ ክልል ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ ትላንት እሁድ፣ ህዳር 15 ቀን 2017 ዓ.ም፣ የትግራይ ክልልን ባንዲራ ከጀርባቸው አድርገው ስድስት ለሚሆኑ የመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ ይፋ እንዳደረጉት በዶ/ር ደብረጽዮን የሚመራው የትህነ ቡድን በጊዜያዊ አስተዳደሩ ሲቪላዊ አስተዳደሮች ላይ መፈንቅለ መንግሥት እየፈጸመ መሆኑን አስታውቀዋል።
” ከፕሬዜዳንት ስልጣን ወርደዋል ፤ ወደ ውጭ አገር ሊወጡ እያመቻቹ ነው ፤ ውጭ ሀገር ወጥተው እንዲቀሩ መንግሥት እያመቻቸላቸው ነው ” ተብሎ ሲወራባቸው ስለ መሰንበቱ የተጠየቁት አቶ ጌታቸው ረዳ ” ለስራ በምወጣበት ጊዜ ከሁለቱ ምክትሎች አንዱ መወከል የተለመደ አሰራር ነው መወከሌም እቀጥላሎህ ፤ ‘ ከሀገር ሊወጣ ነው ‘ ተብሎ የተነዛው ወሬም ከሃቅ የራቀ መሰረተ ቢስ የውሸት ወሬ ነው ” ሲሉ መልሰዋል።
‘ ለስልጣን መቆራቆስ ትተን በጦርነት እና ጦርነት ወለድ ችግሮች የተጎሳቆለው ህዝባችን መካስ ማስቀደም አለብን ” ያሉት አቶ ጌታቸው ረዳ በእሳቸው የሚመሩ የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች በደብረፅዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ከሚመራው የህወሓት ከፍተኛ አመራር ጋር የሃይማኖት አባቶች በጀመሩት የእርቅ ጥረት ችግሮቻቸው ለመፍታት ቁርጠኛ እንደሆኑ አረጋግጠዋል።
“ስልጣን ሙሉ ለሙሉ የመቆጣጠር ፍላጎት ነው ያላቸው” ያሏቸው የህወሓት ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ ወደ ፌደራል መንግሥት በመመላለስ “ስልጣን እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል” ሲሉ አቶ ጌታቸው ገልጸዋል።
“ሦስት ጊዜ ወደ ፌደራል መንግሥት ሄደዋል፤ አንድ ላይ ሆናችሁ መምጣት አለባችሁ ተብለዋል። ያካሄዱትን ስብሰባም እንደ ጉባኤ አንቆጥረውም ተብለዋል” በማለት ድርጅቱ ችግሩን ውስጣዊ ድርድር በማድረግ እንዲፈታ እንደተነገረው አስታውቀዋል፡፡
አቶ ጌታቸው በሰጡት መግለጫ፣ በትግራይ ያለው ፖለቲካዊ ሁኔታ ወደ አሳሳቢ ደረጃ እየደረሰ መሆኑን በመጠቆም፣ ህወሓትን ለማዳን ንግግር ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አመልክተዋል።
የፌደራል መንግሥቱ ህወሓት የውስጥ ችግሩን እንዲፈታ ጥሪ እያቀረበ መሆኑን ጠቁመው፤ ካልሆነ ግን የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደር የፌዴራል መንግሥት እንደሚረከበው ማሳሰቡን ተናግረዋል።
ዜናው ከተለያዩ ሚዲያዎችና ማህብራዊ ጸሃፊዎች ትርጉም የተሰባሰበ ነው