በጸጥታና ደህንነት ተቋማት ያከናወነው የሪፎርም ስራ ኢትዮጽያን የሚመጥንና ዘመን ተሻጋሪ ተቋማትን ለመገንባት ጠንካራ መሰረት የጣለ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ገልፀዋል። የኢትዮጵያ አየር ኃይል ደግሞ በዚህ ረገድ ተጠቃሽ መሆኑንም ተናግረዋል።
አየር ኃይሉ 89ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን እያከበረ ባለበት በዚህ ወቅት ”ጸሐይ 2 ” የተሰኘችና በአየር ኃይሉ የተሰራች አውሮፕላን ለበረራ ብቁ አድርጓል።
አውሮፕላኗ ግዳጅን በብቃት መፈጸም የሚያስችል ቴክኖሎጂ የታጠቀች ናት። ይህም አየር ኃይሉ በ2030 በአፍሪካ ስመጥር አየር ኃይል ለመሆን የያዘውን ራዕይ እውን ለማድረግ በትክክለኛ ጎዳና ላይ መሆኑን የሚያመላክት ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ።
በአፍሪካ ሀገራት አየር ኃይሎች መካከል ጠንካራ ትስስር እንዲኖር የኢትዮጵያ አየር ኃይል በትኩረት ይሰራል።
ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ
በአፍሪካ ሀገራት አየር ኃይሎች መካከል ጠንካራ ትስስር እንዲኖር የኢትዮጵያ አየር ኃይል በትኩረት ይሰራል ሲሉ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ተናገሩ።
“የተከበረች ሀገር የማይደፈር አየር ኃይል” በሚል መሪ ቃል ለ89 ጊዜ የሚከበረው የኢትዮጵያ አየር ኃይል የምስረታ ቀንን በማስመልከት የአፍሪካ ሀገራት የአየር ኃይል አዛዦች በተገኙበት ሁለተኛው የአፍሪካ አየር ኃይሎች ፎረም በአየር ኃይል መኮንኖች ክበብ ተካሄዷል።
በፎረሙ ላይ የሞሮኮ፣ የዩጋንዳ፣ የታንዛኒያ፣ የማሊ፣ የኬንያ፣ የሩዋንዳ፣ የጂቡቲ፣ የናይጀሪያ፣ የኮንጎ ብራዛቪል እና የኒጀር አየር ኃይል አዛዦችን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት ወታደራዊ አታሼዎች፣ የአቭዬሽን ካምፓኒ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል።
ፎረሙን በንግግር የከፈቱት የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ይልማ መርዳሳ ፤ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ቴክኖሎጂ በየእለቱ እየዘመነና አዳዲስ መልኮችን እየተላበሰ የሚገኝ በመሆኑ የሀገር ሉዓላዊነት ማስጠበቅ የሚችል ጠንካራና ዘመኑን የዋጀ አየር ኃይል መገንባት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል።
ፎረሙ በዘርፉ ያለውን ልምድ እና ተሞክሮ ለመለዋወጥ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያበረከትም ተናግረዋል።
በፎረሙም የአፍሪካ አየር ኃይሎች ማህበር ለመመስረት በሂደቱም ላይ በጋራ ለመስራት ጠንካራ መሰረት የምንጥልበት ነው ብለዋል።
ለአፍሪካ አየር ኃይሎች መጠናከር እና እድገት የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከአፍሪካ አገራት አቻዎቹ ጋር በትብብር ለመስራት ያለውን ቁርጠኝነትም አንስተዋል።
በተለይም አየር ኃይሉ በቴክኖሎጂ አቅም ግንባታና በሰው ኃይል ልማት ረገድ ከተለያዩ አቭዬሽን ተቋማትና ከአፍሪካ ሀገራት አየር ኃይሎች ጋር በጋራ ለመስራት ተነሳሽነት ያላቸው መሆኑንም ተናግረዋል።
ለፎረሙ ተሳታፊዎች ስለ አየር ኃይል አካዳሚ ገለፃ ያደረጉት ምክትል አዛዥ ለአየር ኃይል አካዳሚ ኮሎኔል ገዛኸኝ ነጋሽ አካዳሚው በውስጡ የመሠረታዊ ውትድርና ትምህርት ቤት፣የቴክኒክ ትምህርት ቤት ፣ የበረራ ትምህርት ቤት እና የአመራር ትምህርት ቤትን ያቀፈ መሆኑን ገልፀዋል።
ከዚህ ቀደም የተለያዩ አፍሪካ ሀገራት አብራሪዎችንና ቴክኒሽያኖችን አሠልጥኖ ከማስመረቁም በተጨማሪ በቀጣይም በአፍሪካ ተመራጭ የስልጠና ማዕከል በመሆን የአፍሪካ ኩራት የሆነ አየር ኃይል ለመገንባት በትኩረት እንደሚሰሩም ተናግረዋል።
በፎረሙ ላይ የተሳተፉ የተለያዩ ሀገራት አየር ኃይል አዛዦች የሚመሩትን የአቭዬሽን ተቋም ወቅታዊ ሁኔታ እና የደረሱበትን የዝግጁነት ደረጃ በሚመለከት ገለፃ አድርገዋል።
በፎረሙ ላይ የተሳተፉት የወታደራዊ የአቭዬሽን ትጥቆች አምራች ተቋማት ኃላፊዎች በበኩላቸው የአቭዬሽን ኢንዱስትሪው የደረሰበትን ፈጣን እድገትና ዘመናዊ አየር ኃይል ለመገንባት ተቋሞቻቸው ያላቸውን ፍላጎትና አቅም በተመለከተ ለፎረሙ ተሳታፊዎች ገለፃ አድርገዋል።
በአየር ኃይል መኮንኖች ክበብ ሲካሄድ የነበረው ፎረም የተጠናቀቀ ሲሆን ከሰዓት በኋላ በሐረር ሜዳ ሲኒማ አዳራሽ ከፎረሙ ተሳታፊዎች ጋር በሚከናወን የፓናል ውይይት የአፍሪካ አየር ኃይሎች ፎረም የሚጠቃለል መሆኑ እና 89ኛው የአየር ኃይል የምስረታ ቀን በዓል ህዳር 20 ቀን 2017 ዓ.ም በቢሾፍቱ ከተማ በሚገኘው የአየር ኃይል ሐረር ሜዳ ስታዲየም በሚከናወኑ የተለያዩ መርሃ ግብሮች የሚጠናቀቅ መሆኑም ተገልጿል።
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ህዳር 18 ቀን 2017 ዓ.ም