በዘመናዊ የህግ ሥርአት የተፈጥሮ ሰው ብቻ ሳይሆን በህግ በግልፅ በተደነገገ ጊዜ ህጋዊ ሰውነት የተሰጠው ድርጅትም የወንጀል ተጠያቂነት ያለበት መሆኑን ማወቅና ድርጅቶችን በወንጀል ተጠያቂ ከሚያደርጉ የወንጀል ተግባራት መታቀብ ያስፈልጋል፡፡
መግቢያ
በሕግ ሁለት ዓይነት ሰዎች አሉ፡፡ እነሱም የተፈጥሮ ሰው እና በሕግ ሕጋዊ ሰውነት የተሰጠው ሰው ናቸው፡፡ በሕግ ህጋዊ ሰውነት የተሰጠው ሰው ማለት የንግድ ድርጅቶች፣ ማህበራት እና መሰል ሌሎች ድርጅቶችን የሚመለከት ነው፡፡ የተፈጥሮ ሰው ወንጀል ሲሰራ በህግ እንደሚጠየቅ ሁሉ የህግ ሰውነት የተሰጠው ድርጅት በወንጀል የሚጠየቅበት ሁኔታ በህጉ ተመልክቷል፡፡ በዚህ ፅሁፍ በሀገራችን ድርጅት በወንጀል የሚጠየቅበትን ሁኔታ እና ተያያዥ ጉዳዮችን እንዳስሳለን፡፡
የድርጅት ምንነት
በሀገራችን የድርጅት የወንጀል ተጠያቂነትን በተመለከተ መነሻ የሆነው የወንጀል ህጉ አንቀፅ 34 ሲሆን ለድንጋጌው አላማ የድርጅትን ምንነት ትርጓሜ ሰጥቶ እናገኛለን፡፡ በዚህ ድንጋጌ ንኡስ አንቀፅ 4 መሰረት “ድርጅት” ማለት መንግስታዊም ሆነ መንግስታዊ ያልሆነ ወይም ሕዝባዊም ሆነ ግላዊ መዋቅር ያለው አካል ሲሆን ለንግድ፣ ለኢንዱስትሪ፣ ለፖለቲካ፣ ለሃይማኖት ወይም ለሌላ ሕጋዊ ዓላማ የተቋቋመንና በመንግስት ዕውቅና ያገኘን ማናቸውንም ማኅበር እንደሚያጠቃልል ደንግጓል፡፡ ሆኖም የመንግስት አስተዳደር አካላት ወይም ተቋማት በህግ ሰውነት የተሰጣቸው ቢሆንም በዚህ ድንጋጌ ውስጥ በድርጅትነት የሚሸፈኑ አይደሉም፡፡
ድርጅት በወንጀል የሚጠየቅበት ሁኔታ
የሕግ ሰውነት የተሰጠው ድርጅት በወንጀል ተጠያቂ ሊሆን የሚችለው በወንጀል ሕጉ አንቀፅ 34 በተመለከቱት ሁኔታዎች ነው፡፡ ይኸውም
አንድ የወንጀል ድርጊት በድርጅት ከተፈፀመ አስቀጪ እንደሆነ በህጉ በግልፅ ሲደነገግ እና
ከሀላፊዎቹ ወይም ከሰራተኞቹ አንዱ ከድርጅቱ ሥራ ጋር በተያያዘ የድርጅቱን ጥቅም በህገወጥ መንገድ ለማራመድ በማሰብ ወይም የድርጅቱን ህጋዊ ግዴታ በመጣስ ወይም ድርጅቱን በመሳሪያነት ያለአግባብ በመጠቀም በዋና ወንጀል አድራጊነት፣ በአነሳሽነት ወይም በአባሪነት ወንጀል ካደረገ ነው፡፡
የድርጅትን የወንጀል ተጠያቂነት ያካተቱ ህጎች
ድርጅት በወንጀል ሊጠየቅ የሚችለው አንድ ወንጀል በድርጅት በተፈፀመ ጊዜ ድርጅቱ በወንጀል ሊጠየቅ እንደሚችል በህጉ በግልፅ ሲደነገግ ነው፡፡ ይህን መነሻ በማድረግም በሀገራችን በሥራ ላይ ያሉ በርካታ የወንጀል ድንጋጌዎችን ያካተቱ ልዩ ህጎች ድርጅት በወንጀል ተጠያቂ የሚሆንባቸውን ሁኔታዎች ደንግገዋል፡፡ ለአብነት የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣ አዋጅ ቁጥር 881/2007 በአዋጁ አንቀጽ 5፣ በፌደራል የታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2008 አንቀፅ 132፣ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብን እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ ቁጥር 780/2005 አንቀፅ 33፣ በሰው የመነገድ እና ሰውን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ ቁጥር 1178/2012 አንቀፅ 18፣ የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀፅ 17 እና የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥር አዋጅ 1177/2012 አንቀፅ 22(11) ይጠቀሳሉ፡፡
ህጋዊ ሰውነት በተሰጠው ድርጅት ላይ የሚጣል የወንጀል ቅጣት
ድርጅት በወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ ቢገኝም ድርጅትን እንደተፈጥሮ ሰው ማሰር ስለማይቻል በድርጅት ላይ በዋናነት የሚጣለው ቅጣት በወንጀል ህጉ አንቀፅ 90(3) የተመለከተው የገንዘብ መቀጮ ነው። ይህ ማለት አንድ ወንጀል በተፈጥሮ ሰው ሲፈፀም በእስራት የሚያስቀጣ ከሆነ እና ወንጀል ፈፃሚው ህጋዊ ሰውነት የተሰጠው ድርጅት ሆኖ ከተገኘ ለእስራቱ ተመጣጣኝ ነው ተብሎ በህጉ በተደነገገው የገንዘብ መቀጮ ይቀጣል ማለት ነው፡፡ ከመቀጮ በተጨማሪ በወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘ ድርጅት እንዲታገድ፣ እንዲፈርስ፣ እንዲዘጋ ሊወሰን እንደሚችል ከወንጀል ሕጉ አንቀፅ 34(2) መረዳት ይቻላል፡፡
በወንጀል ህጉ አንቀጽ 90(3) መሰረት የመንግስት የአስተዳደር አካላትን ሳይጨምር የህግ ሰውነት የተሰጠው ድርጅት በወንጀል ተካፋይ ሆኖ ሲገኝ የድርጅቱ ሀላፊዎች ወይም ሰራተኞች በየግላቸው መጠየቃቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ድርጅቱ ወንጀል ተጠያቂ ተደርጎ
1. እስከ 5 አመት ቀላል እስራት ለሚያስቀጣ ወንጀል እስከ አስር ሺህ ብር
2. እስከ 5 አመት ፅኑ እስራት ለሚያስቀጣ ወንጀል እስከ ሀያ ሺህ ብር
3. እስከ 10 አመት ፅኑ እስራት ለሚያስቀጣ ወንጀል እስከ ሀምሳ ሺህ ብር
4. ከ10 አመት በላይ ፅኑ እስራት ለሚያስቀጣ ወንጀል እስከ አምስት መቶ ሺህ ብር፣ መቀጮ እንዲከፍል ይወሰንበታል፡፡
የህግ ሰውነት የተሰጠው ድርጅት ጥፋተኛ የተባለበት ድንጋጌ በመቀጮ ብቻ ሚያስቀጣ በሆነ ጊዜ ደግሞ በድርጅቱ ላይ ሚጣለው ቅጣት የመቀጮውን አምስት እጥፍ እንደሚሆን በወንጀል ህጉ አንቀፅ 90(4) ተደንግጓል፡፡
ሆኖም ይህ በወንጀል ህጉ አንቀፅ 90 የተደነገገው ቢኖርም በልዩ ህጎች የተለየ ቅጣት ሊቀመጥ ይችላል፡፡ ለምሳሌ በሰው የመነገድ እና ሰውን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ ቁጥር 1178/2012 አንቀፅ 18 መሰረት
1. በቀላል እስራት ወይም እስከ 5 አመት ፅኑ እስራት ለሚያስቀጣ ወንጀል እስከ አምስት መቶ ሺህ ብር
2. ከ5 አመት እስከ 15 አመት ፅኑ እስራት ለሚያስቀጣ ወንጀል ከአምስት መቶ ሺህ እሰከ አንድ ሚሊዮን ብር
3. ከ15 እስከ 20 አመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ለሚያስቀጣ ወንጀል ከአንድ ሚሊዮን እስከ ሁለት ሚሊዮን ብር
4. ከ20 አመት በላይ በሆነ እስራት ወይም ሞት ለሚያስቀጣ ወንጀል ከሁለት ሚሊዮን እስከ ሶስት ሚሊዮን ብር በሚደርስ መቀጮ ይቀጣል፡፡
በተመሳሳይ የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ ቁጥር 1176/2012፣ የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ 1177/2012 እንዲሁም የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣ አዋጅ ቁጥር 881/2007 ለድርጅት ተፈፃሚ የሚሆን የየራሳቸውን የመቀጮ መጠን ደንግገዋል፡፡
ማጠቃለያ
በአጠቃላይ በዘመናዊ የህግ ሥርአት የተፈጥሮ ሰው ብቻ ሳይሆን በህግ በግልፅ በተደነገገ ጊዜ ህጋዊ ሰውነት የተሰጠው ድርጅትም የወንጀል ተጠያቂነት ያለበት መሆኑን ማወቅና ድርጅቶችን በወንጀል ተጠያቂ ከሚያደርጉ የወንጀል ተግባራት መታቀብ ያስፈልጋል፡፡
ፍትህ ሚኒስቴር