ዘፈኑ ሁሉ “ዋ” ነበር። ዘፈኑ ሁሉ “ወዮልህ” ነበር። ፉከራው ሁሉ የዛርና የቆሌ ዓይነት ነበር … ዛር፣ ቆሌ፣ አቴቴ፣ አወሊያ፣ አዳልሞቴ፣ ሃይላሎ ላሎ ወዘተ እና እነ “ወጋሁት” የዘመኑ ኪስ አውላቂዎች፣ እነ ባለ ድግምቶች … የዘር አምልኮ አምላኪዎች፣ የዘር መንፈስ አውራጆች፣ የጎሰኝነት መንፈስ ጠሪዎች፣ የትርምስ ጠማቂዎች፣ በትርምስ ውስጥ ደም እየሰፈሩ ስኬት የሚቆጥሩ የሳይበር አዋጊዎች … ተዘርዝሮ አያልቅም!! “ያለምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም” ተብሎ ተጀምሮ … ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስን ጠይቁት!!
እንደምን ከረማችሁ። ደሞዝ የተንጠባተበላችሁም እድሜ ልክ ሁለት ብር ከሃምሳ የቤት አበል እየተቀበሉ ለሚኖሩት እማማም … ያበደው ሰላምታ ያቀርባል። ሰላምታውን ዘለለው። ድንገት እማማ ልቡናውን ወሰዱት። አንዴ፣ በአንድ ተስያት አውድ ዓመት ቤታቸው ነበር። ቦሰናም አብራው ነበረች። እማማ ደሳሳ ጎጇቸው መካከሉ ላይ በተከሉት ጉልቻ ዙሪያ ህይወታቸውንም ተክለዋል።
ደርግ አንድ የጭቃ ቤት “ትርፍ ነው” ብሎ ነጥቋቸው በወር ሁለት ብር ከሃምሳ አበል ይሰታቸዋል። ያበደው ሲጠይቃቸው ለሃያ አምስት ዓመት ደሞዛቸው በወር ሁለት ብር ከሃምሳ ነበር። እተወሰደው ቤታቸው የሚኖረው ተከራይ አምስት ብር የቤት ኪራይ እየከፈለ ዙሪያውን አጥሮ እንደ ባለ ርስት … ይቅር ታሪኩ ብዙ ነው። ዛሬ ግቢ አድርጎ ጠቅልሎታል አሉ … አንድዬ ሚስጥሩን ይይና ይፍረድ? ፈርዶም ከሆነ … ቦሰና ያለችው ነው። ደርግ ጓዳ “ትርፍ እያለ ይሰርቅ የነበረ ማጅራት መቺ ነበር።
እማማ ከተናገሩት መካከል፣ ሸምተው አያውቁም። መብራት ቤታቸው የለም። መክፈል ሰማይችሉ ቆጣሪው ሲቀር አገልግሎቱን ተነጠቀዋል። ጥራጥሬ እየለመኑ በመወዘቻ ወዝተው ከመመገብ ውጪ ሌላ ወግ ረስተዋል። የሚለበስ ነገር ለመጨረሻ ጊዜ መቼ እንደገዙ አያስታውሱም። ለነብስ ያሉ ከሚያጎርሷቸው ውጭ አቁላልተው አያውቁም። ድህነትና እድሜ ተማክረው ሰብረዋቸዋል። ቦሰና እንደነፈረቀች ውላ እየነፈረቀች ገላቸውን አጥባቸው …. እማማ “ኢትዮጵያዊ” ናቸው።
ያበደው አውሮፓ በረዶ እንደ ኩስ የሚዘንብበት ቀን መዳረሻ ምልክቱ በፈጠረበት ድብርት ተውጦ፣ የብሄር ዛር የሚጋልባቸውን አሰበ። እንደ እማማ ዓይነቶቹን ማሰብና ተረባርቦ መርዳት እያለ የትርምስ አጅንዳ ላይ የተተከሉትን ሳላቸው። ትርምስ ጠማቂዎች ከዚህም ከዚያም በደሃ ደም የሚነግዱ ናቸው። የትርምሱ አቀጣጣዮች በ1997ም ነበሩ። ያን የመስለ ምርጫ አፍርሰው ዛሬም ድረስ በዚያው ጎዳናቸው ላይ ናቸው።
ያበደው መስቀል አደባባይ መበልና ሱናሚን አይቷል። መለስ ደጋፊዎቻቸውን “ማዕበል” ሲሉ ባወደሱ ማግስት አዲስ አበባ ጠጠር መጣያ አጣች። “ሱናሚው” የመለስን ማዕበል የብልቃጥ ውሃ አደረጋት። ድራማ ነበር ” የንብ ቆዳ ያለው. የንብ ቆዳ ያለው” የሚሉትን ጨምሮ ኢህአዴግን ህዝብ አደባባይ በሰላማን በፍቅር ሰቀለ!!
የዛሬ ተንታኞች ያን ግዜ ተቧድነውና ተቀጥረው ጋዜጣ ያትሙ ነበር። ዕለት እለት የሚያትሙ ነበሩ። ህዝብ ለሊት ላምባዲና ይዞ በድምጹ ያገነውን ድል ” ዋ ፓርላማ ትገቡና” በሚል ዜማ አጀቡት። ከኢህአዴግ ውንብድና ጋር ተዳምረው ምርጫውን በዜሮ አባዙ። መለስ ባመኑት ከግማሽ ያላነሰ ያፓርላማ ወንበር፣ አዲስ አበባን ሙሉ ያሸነፈ ፓርቲ የያዘውን ይዞ ለቀታዩ እንዳይጫወት ቀሰቀሱ። እኒህ የዛሬ ተንታኞች የያዙትን መያዝና የቀረውን ለመረከብ መታገልን “ክህደት” ብለው ህዝብን አሳመጹ። ያን የመስለ ምርጫ መጨረሻው ዕልቂትና እስር ሆነ። “ዋ ፓርላማ ትገቡና” ሲሉ የነበሩ ከፊሉ ታሰሩ፣ ከፊሉ ሸሹ። አንዳንዶቹም ለማስመሰል ታስረው ተፈቱ። ለእነ እማማ ጠብ ያለ የለም።
ቦሰና የዛሬዎቹን ተንታኞች ስታይ “ይሉኝታ ድሮ ቀረ” ትላለች። እውነት ነው ይሉኝታና ፈርሃ አምላክ ላይመለሱ ከኢትዮጵያ ምድር ተሰናብተዋል። መንግስት ውስጥም ተመሳሳይ ነው። ዛሬ ድረስ ያልተቀየሩ የለሊት ጋላቢዎች አሉ። ሞት ጠሪዎች። ቀን ብልጽግና ማታ ሞት ጠሪዎች!!
ጃዋር ” ቢያንስ አንድ ትልቅ ስኬት አሳክተናል” የሚለው ለዚህ ነው። ጃዋር በናይሮቢ ቅምጥል ያለ ህይወት እያስለፈ ነው። በቂ ሃብት አለው። አዲስ አበባም …. ጃዋር አመስን ለመቆስቆስና በፍጥነት አብዮት ለማቀጣጠል የዘር ፖለቲካ አጅግ ተመራጭ እንደሆነ ያምናል። በራሱ ሚዲያዎች አምልጦት ይሁን ድንገት አፍሷል።
የብሄር አመጽ ማስነሳት ቀላል እንደሆነ ሲናገር ጎን ለጎን ” መንግስት ከተኮነ በሁዋላ የብሄር በብሄር ነዳጅ ያነሳሱትን ደጋፊ ማብረደና መደበኛ ነዋሪ ማድረግ ከባድ ነው” ሲል በተደጋጋሚ ተድምጧል።
“ጃዋር አማራን ብሄረተኛ ሆኖ ማየት ትልቅ ስኬት ነው” ሲል የገባቸው ጥቂት ነበሩ። አማራን ብሄረተኞ ማድረግ የወያኔ ቁልፍ አጀንዳ ነበር። ወያኔ ያላሳካውን ህልሙን ያሳኩለት እነጃዋር ናቸው። እነ ጃዋርን ያገዙዋቸው ደግሞ ምርጫ 97ን አክሽፈው ዛሬ የአማራ ተቆርቋሪ ሆነው እየተነተኑ ያሉት ናቸው። አማራን ብሄረተኛ አድርገው ከኦሮሞ ጋር ለማጋደል ያተፈነቀለ ድንጋይ አልነበረም ዛሬ ….
ጃዋር በስኬትና በድል አማራን አንስቶ “ሃይሎሃዬ ሆ!” ሲል መባነን የማይቻለው እንዴት ነው? አማራ ክልል አሁን ለገባበት ውጥንቅጥ መውጫው እነ ጃዋር ስኬት ባሉት መንገድ ማጋለብ ወይስ ቆም ብሎ ማሰብና ፍሬይማ ስልት መንደፍ?
ያበደው ዘለለ። የበደው ምራቁ አፉን ሞላው። ተፋው። ተመናቀረ። የአማራ ክልል እንዲህ የማንም ውርጋጥ ፖለቲከኛ፣ የዛጉ ባንዳዎች መጫወቻ ይሁን? ጠየቀ? አማራን በልኩ የሆኑ ብስል ፖለቲከኞች እንዳይነሱለት ችግር የሆነው ምንድን ነው? አማራ ከሌሎች ሳይጣላ፣ ሌሎችም በደሉን በደላቸው አድርገው አብረውት እንዲቆሙ የሚያስችሉ ጥበበኞች አማራ ማህጸን ውስጥ አልተፈጠሩም? ያበደው አንገቱን ደፋ!!
አማራ ማንም እየተነሳ የሚያንቦጫርቀው፣ የሚያማስለው፣ ጀግና የሚባልበት፣ በየቀበሌው በተነሱ የጎበዝ አለቆች የሚተራመሰው እስከመቼ ነው? ያበደው ቆፈኑ ለቀቀው። እርምጃውን ጨምሮ ኢትዮጵያ ኮሙኒቲ ደጅ ደረሰ። አልገባም። ስሙ እንጂ ቋንቋው አንድ አይደለም። ተመለሰ። የአማራ ህዝብ የሚዘፈንለት ሁሉ እያጠፋው ነው። ዕርቅ እንዳይሞከር የሚገፉት ብዙ ናቸው። ቢያንስ ዕርቅ ቁጭ በማለት ሞክሮ “ይህን አቅርበን ይህን ተከለከልን። መፍትሄው ጠብ መንጃ ነው” ለማለት ያመቻል።
ድሮ ገባ በንጭጩ – ዘፈኑ ሁሉ “ዋ” ነበር። ዘፈኑ ሁሉ “ወዮልህ” ነበር። ፉከራው ሁሉ የዛርና የቆሌ ዓይነት ነበር … ዛር፣ ቆሌ፣ አቴቴ፣ አወሊያ፣ አዳልሞቴ፣ ሃይላሎ ላሎ፣ መጫኛ ገትር፣ ድግምት፣ ወዘተ እና እነ “ወጋሁት” የዘመኑ ኪስ አውላቂዎች፣ እነ የለሊት ጋላቢዎች ጥምረት ፈጥረዋል። ዘንዶ የሚቀልቡትም ዘንዶውን አደባባይ እሳት እይስረጩ ታይተዋል። … የዘር አምልኮ አምላኪዎች፣ የዘር መንፈስ አውራጆች፣ የጎሰኝነት መንፈስ ጠሪዎች፣ የትርምስ ጠማቂዎች፣ በትርምስ ውስጥ ደም እየሰፈሩ ስኬት የሚቆጥሩ የሳይበር አዋጊዎች … ተዘርዝሮ አያልቅም!! “ያለምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም” ተብሎ ተጀምሮ እንዴት እንዳለቀ … ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስን ጠይቁት!! ዳዊት ዛሬም ታግሎ አታጋይ ነው። ተንታኞቹም ነዛው የሚታወቁት ናቸው። በድሮው መንፈስ ተጀምሮ እንደቀደመው መንፈስ እየሆነ ነው። ልዩነቱ ክላሽና ቆሞ ጥበቀኝ በመትርየስ፣ ታንክና ድሮን ተቀይረዋል። ሁሉም አጥፊ ናቸው። መንግስት ዲጂታል ጦረኛ ሲሆን፣ ሌሎች ስራስር ተተቃሚ ሆነው ” የጃዋርን ሃይሎጋዬ” እያወረዱ ነው። ልብ ያላችሁህ ስሙ!! አሁን አመሻሽ ነው። ሰላም ክረሙ። ደጎልንና ያበደው ቀጠሮ አላቸው።