የቻይና ሕዝብ ጥረት ሌላ ዓለም ያደረጋት የመቶ ደሴቶች ከተማ።
ወቸው ጉድ። አይ ጁሃይ ሄኖክ ስዩም እንግዳሽ ይሁን?
በፔርል ወንዝ ዴልታ ደቡብ ምስራቃዊ ጠርዝ ላይ የምትገኘው ጁሃይ በደቡብ ጓንግዶንግ አውራጃ ማዕከላዊ የባህር ጠረፍ ላይ ከፒርል ወንዝ በስተ ምዕራብ ዳርቻ ተዘርግታለች።
ከጓንጇ ደቡብ ምዕራብ 140 ኪሎ ሜትሮች ተጉዘናል። ወደ ጁሃይ፤ ቻይናዎች ስሟን “pearl sea” ይሏታል። ስምን መልአክ ያወጣዋል። “የእንቁ ባህር” ማለት ነው ትርጓሜው። ደግሞ ለጁሃይ ልክክ ይላል። እ.ኤ.አ በ2014 በተደረገ አንድ ጥናት በቻይና የማኅበራዊ ሳይንስ አካዳሚ የተለቀቀ አንድ ዘገባ እንደሚያሳየው ጁሃይ በቻይና ውስጥ በጣም ለኑሮ ምቹ ከተማ በሚል ተገልፃለች።
በረዥሙ ውብ የባህር ዳርቻዋ በጎበኟት ምናብ ትኖራለች። የዘንባባ ዛፎችን አውለብልባ እንግዶቿን የምትቀበል። ዝቅተኛ የህዝብ ብዛት፤ ብዙ ቁጥር ያለው ደሴት ያላት። ከእነስሟ የመቶ ደሴቶች ከተማ እያሉ የሚጠሯት፣ የፍቅር ከተማ።
ጁሃይ ምዕራባዊ ክፍሏ ፐርል ወንዝ ዴልታ ላይ ያረፈ ባለ ወደብ ከተማ ናት። ሁለቱ ዓለም አቀፍ ወደቦች ናቸው። 690 ኪሎ ሜትር የሚደርስ የባህር ዳርቻ ግዛት አላት። 217 ደሴቶች ባሏት ግዛት እገኛለሁ።
ትንሿ ሲንጋፖር ይሏታል፤ ውብ እና ረጋ ያለች ግን ደግሞ ፈጣን ከተማ። ጁሃይ ጥብቅ የአካባቢ ህጎችን አስተዋውቃ ከተማዋን ለማዘመን የከተማዋን ፕላን ለማገዝ ከሲንጋፖር ጭምር መሐንዲሶችን ቀጥራ የተሰራች ከተማ።
የዛሬ አርባ አምስት ዓመት ከተማ ሆነች። የቻይና ሕዝባዊ ሪፐብሊክ መንግሥት እ.ኤ.አ. በ 1980 ነበር ጁሃይ ከተማ ከአራት ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች መካከል አንዷ እንደምትሆን ይፋ ያደረገው።
የእጽዋት ከተማዋ ጁሃይ ቱሪዝምን መሰረት ያደረገ ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማምጣት የአየር ንብረቷ አግዟታል። ከአምራች ኢንዱስትሪዎች የሚደርሰው የአካባቢ ብክለትን ለመቀነስ አረንጓዴ አብዮት አቀጣጠለች። እንደ እናቷ እንደ ቻይና ምድር።
ከሃያ አምስት ዓመት በፊት የወጣ የ chain.org መረጃ
በደቡብ ቻይና የምትገኘው ይህቺ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን በ10 ዓመታት ጊዜ ውስጥ በአረንጓዴ ቀለም የደመቀች ከተማ እንድትኾን ወጠኑ። ዛሬ ተሳክቶ ያ ይታያል።
በመሀል ከተማ ያለው እያንዳንዱ ሰው አሁን 7.22 ካሬ ሜትር የወል አረንጓዴ መሬት እና 7.14 ካሬ ሜትር የፓርክ ቦታ ያለው ሲሆን አረንጓዴው መሬት ከጠቅላላው የመሀል ከተማው ስፋት 26 በመቶ ድርሻ ይይዛል። እንዲህ ነው መሰልጠን እንጂ።
ወደ ማንግሩቭ ደን ወሰዱን። Zhuhai Qi’ao Mangrove Wetland Ecological Park በፒርል ወንዝ ዴልታ ላይ ከሚገኙት 10 ምርጥ መልክዓ ምድሮች አንዱ የተባለ መስህብ ነው።
ማንግሩቭ ዌትላንድ ከፍተኛ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያለው የስነ-ምህዳር መልክአ ምድር እና መስህብ ኾኗል ነው። በቻይና ውስጥ ከጥፋት የተመለሰው ትልቁ ቦታ። 700 ሄክታር የሚያህል የማንግሩቭ ደን አለው። ስለ ማንግሩቭ ወደ ሰንጀን ስጓዝ አወጋችኋለሁ።
(ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም – ለድሬ ቲዩብ)