ዶናልድት ሦስት ጊዜ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ለመሆን ሙከራ ከማድረጋቸው በፊት በአሜሪካ ታዋቂ እና አነጋጋሪ ቢሊየነር ነበሩ።
ትራምፕ ለመጀመሪያ ጊዜ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ለመሆን የተወዳደሩት በአውሮፓውያኑ 2016 ነው። ነገር ግን በኒው ዮርክ ግዙፍ የሪል ስቴት ኩባንያ ባለቤት የሆኑትን ባለሀብት ከዚያም በፊትም የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ትኩረት ነፍገዋቸው አያውቁም።
ስማቸው ገናና መሆኑ እና ከዚህ ቀደም ለየት ባለ መልኩ የምርጫ ቅስቀሳ ማድረጋቸው ጉምቱ ፖለቲከኞችን በመርታት ፕሬዝዳንት እንዲሆኑ ሳያደርጋቸው አልቀረም። ቢሆንም አነጋጋሪው ፕሬዝደንት ከአራት ዓመታት በኋላ በምርጫ ተሸንፈው ከሥልጣን ተወግደዋል።
ሥልጣን የለቀቁበትን ሽንፈታቸውን አሁን ድረስ በፀጋ ያልተቀበሉት የ78 ዓመቱ የሪፐብሊካን ፓርቲ ዕጩ ትራምፕ ድጋሚ መንበረ-ፕሬዝደንቱን ለመቆጣጠር እየተወዳደሩ ይገኛሉ።

ውርስ
ዶናልድ ትራምፕ የኒው ዮርክ ጉምቱ የሪል ስቴት ባለሀብት የሆኑት ፍሬድ ትራምፕ አራተኛ ልጅ ናቸው።
ምንም እንኳ ቤተሰቡ ገንዘብ የተረፈው ባለፀጋ ቢሆንም እሳቸው ግን በልጅነታቸው ዝቅ ያለ ሥራ ይሠሩ ነበር። በ13 ዓመታቸው ፀባያቸው አልገራ ብሎ በማስቸገሩ ወደ ወታደራዊ ካምፕ ተላኩ።
ከፔንሲልቬኒያ ዩኒቨርሲቲ ዋርተን ስኩል የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከጨበጡ በኋላ ግን አባታቸውን ተከተው የቤተሰቡን ንብረት እንዲያስተዳድሩ ታጩ።
ታላቅ ወንድማቸው ፍሬድ በአልኮል መጠጥ ሳቢያ በ43 ዓመቱ ሞተ። ትራምፕ በዚህ ምክንያት “አንድም ቀን አልኮልም ቀምሼም ሆነ ሲጋራ ነክቼ አላውቅም” ይላሉ።
ትራምፕ ከአባታቸው በተበደሩት አነስ ያለች የአንድ ሚሊዮን ዶላር መነሻ ገንዘብ አማካኝነት ወደ ሪል ስቴት መስክ እንደገቡ ይናገራሉ። ቀጥሎም የአባታቸውን ኩባንያ ተቀላቀሉ።
በኒው ዮርክ ግዛት በርካታ ንብረት ያለው የአባታቸውን ግዙፍ ኩባንያ እያስተዳደሩ ከቆዩ በኋላ በአውሮፓውያኑ 1971 ሙሉ በመሉ ኩባንያውን ተቆጣጥረው ትራምፕ ኦርጋናይዜሽን ሲሉ ሰየሙት።
ትራምፕ “ያነሳሳኝ እሱ ነው” እያሉ የሚያወድሷቸው አባታቸው በ1999 ሞቱ።

ባለሀብቱ ትራምፕ በተለያዩ መስኮች
በትራምፕ ዘመን የቤተሰቡ ኩባንያ ብሩክሊን እና ኩዊንስ ከሚገነባቸው መኖሪያ ቤቶች አልፎ ማንሃተን በመግባት የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ማስፋፋት ጀመረ።
ትራምፕ ታወር የተባለው ሕንፃ ኒው ዮርክ የሚገኘው ፊፍዝ አቬኒዩ የተሰኘው ጎዳና ላይ የሚገኘው ሲሆን፣ ጉምቱው ባለሀብት ለበርካታ ዓመታት ኖረውበታል። ቀጥሎ የሚገኘው ኮሞዶር ሆቴል ደግሞ ግራንድ ሃያት ተብሎ ተሰየመ።
ትራምፕ በስማቸው ከአትላንቲክ ሲቲ እስከ ቺካጎ እና ላስ ቬጋስ እንዲሁም በሕንድ፣ በፊሊፒንስ እና በቱርክ በርካታ ዘመናዊ የመቆመሪያ ቤቶች (ካዚኖ)፣ ኮንዶሚኒየሞች፣ የጎልፍ መጫወቻ ሜዳዎች እና ሆቴሎችን ገንብተዋል።
በሪል ስቴት ገበያው ስማቸው የገነነው ትራምፕ ወደ መዝናኛው ዓለም መጡ። መጀመሪያ የሚስ ዩኒቨርስ፣ ሚስ ዩኤስኤ እና ሚስ ቲን ዩኤስኤ የተባሉት የቁንጅና ውድድሮች አዘጋጅ ነበሩ። ቀጥሎ ደግሞ ‘ዘ አፕሬንቲስ’ የተባለ በኤንቢሲ የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ የሚተላለፍ ፕሮግራም ይዘው ብቅ አሉ።

በተለያዩ ምዕራፎች ተከፋፍሎ 14 ክፍሎች የዘለቀው ‘አፕሬንቲስ’ ተወዳዳሪዎች መጥተው የትራምፕ ቢዝነስ አስተዳዳሪ ለመሆን የሚወዳደሩበት ነው።
ትራምፕ በዚህ ፕሮግራም ላይ የሚታወቁበት አጠር ያለ ንግግር አለ። “ዩ አር ፋየርድ” አሊያም “ተባረሀል/ተባረሻል” ሲሉ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ተወዳዳሪ የሚያሰናብቱበት መንገድ የበለጠ ታዋቂ አደረጋቸው።
ትራምፕ በርካታ መጻሕፍት ፅፈዋል። የተለያዩ ፊልሞች ላይ ተጋባዥ ተዋናይ ሆነው ሠርተዋል። የነፃ ትግል ስፖርት ላይ ተሳትፈዋል። ከመጠጥ እስከ ክራቫት ሸጠዋል።
ነገር ግን በቅርብ ዓመታት የተጣራ ገቢያቸው እየወረደ መጥቷል። ፎርብስ መጽሔት በቅርቡ ባወጣው ዘገባ ሀብታቸው 4 ቢሊዮን አካባቢ ይሆናል ይላል።
ዶናልድ ትራምፕ ስድስት ጊዜ ኪሳራ ገጥሞኛል ሲሉ በይፋ ለመንግሥት ማሳወቂያ አስገብተዋል። እንደ ትራምፕ ስቴክስ እና ትራምፕ ዩኒቨርሲቲ የተባሉ ተቋሞቻቸው ደግሞ ከስረው ተዘግተዋል።
ግብር አይከፍሉም እየተባሉ የሚታሙት ትራምፕ የግብር መረጃቸውን ይፋ ባለመድረጋቸው ብዙ ወቀሳ ደርሶባቸዋል። ኒው ዮርክ ታይምስ በ2020 ባወጣው ዘገባ ባለሀብቱን ፖለቲከኛ ግብር ባለመክፈል በማስረጃ አስደግፎ ከሷቸዋል።

የቤተሰብ ታሪክ
የትራምፕ የቤተሰብ ታሪክ ለሕዝብ ይፋ የሆነ እና ብዙ ውዝግቦች ያለቡት ነው።
የመጀመሪያ እና ታዋቂ የሆነው ትዳራቸውን የመሠረቱት ከኢቻና ዜልኒኮቫ ጋር ነው። የቼክ አትሌት እና ሞዴል የነበሩት ኢቫና እና ትራምፕ ሦስት ልጆች አሏቸው። ዶናልድ ጁኒር፣ ኢቫንካ እና ኤሪክ። ጥንዶቹ በአውሮፓውያኑ 1990 ሰማናያቸውን ቀደዋል።
የጥንዶቹ ፍቺ የመገናኛ ብዙኃን መነጋገሪያ ነበር። ሚስታቸው በቤት ውስጥ በሚፈጽሙት ጥቃት ትራምፕን ከሰዋቸዋል የተባለ ቢሆንም፣ ኢቫና ከመሞታቸው በፊት ይህ ሐሰት ነው ሲሉ አስተባብለዋል።
ትራምፕ በ1993 ከተዋናይት ማርላ ሜፕልስ ጋር ሌላ ትዳር መሠረቱ። ጥንዶቹ በ1999 ብቸኛ ልጃቸው ቲፋኒ በተወለደች በሦስተኛ ወሯ ተፋቱ።
የአሁኗ የትራምፕ ሚስት የቀድሞዋ ስሎቬናዊት ሞዴል ሜላኒያ ክናውስ ናቸው። በ2005 የተጋቡት ሜላኒያ እና ትራምፕ አንድ ወንድ ልጅ አላቸው። ባሮን ዊሊያ ትራምፕ አሁን 18 ዓመቱ ነው።
ትራምፕ ወሲባዊ ጥቃት ይፈጽማሉ፤ ከትዳራቸው ውጪ ይማግጣሉ የሚሉ ወቀሳዎቹ ተለይተዋቸው አያውቁም።
በዚህ የአውሮፓውያኑ ዓመት መባቻ ኢ ጂን ካሮል ያቀረቡባቸውን ወሲባዊ ጥቃት ክደዋል በሚል ለከሳሻቸው 88 ሚሊዮን ዶላር እንዲከፍሉ ታዘዋል። ትራምፕ ውሳኔውን ተቃውመው ይግባኝ ጠይቀዋል።
ትራምፕ በ2006 ከወሲብ ፊልም ተዋናይቷ ስቶርሚ ዳንኤልስ ጋር በነበራቸው ግንኙነት ምክንያት ቢዝነሳቸውን በተለመከተ የተዛባ መረጃ ሰጥተዋል በሚል በ34 የክስ መዝገቦች ጥፋተኛ ሆነው ተገኝተዋል።

የትራምፕ ጉዞ ፕሬዝደንት ለመሆን
ትራምፕ በአውሮፓውያኑ 1987 ነው አንድ ቀን ፕሬዝደንታዊ ዕጩ ሆነው ብቅ ሊሉ እንደሚችሉ ፍንጭ መስጠት የጀመሩት። በ2000 ሪፎርም ፓርቲን በ2012 ደግሞ ሪፐብሊካን ፓርቲን ወክለው ለመወዳደር አስበው እንደነበር ተናግረዋል።
“የትውልድ ቦታ” የሚል ሐሳብን በማራመድ የሚታወቁት ትራምፕ፣ ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ አይደለም የተወለዱት በማለት ወሬ ነዝተዋል። እስከ 2016 ድረስ ይህን ሐሳባቸውን ይዘው ቆይተው በኋላ ሐሰት መሆኑን ቢያምኑም እስካሁን ይቅርታ አልጠየቁም።
ትራምፕ በይፋ ለመጀመሪያ ጊዜ ዋይት ሐውስ ለመግባት ዕቅድ እንዳለቸው ያሳወቁት በ2015 መገባደጃ ላይ ነው።
ይህን ይፋ ባደረጉበት ወቅት የቢዝነስ ስኬታቸውን አውርተው፤ ጎረቤት አገር ሜክሲኮ የዕፅ አዘዋዋሪዎችን እየላከችብን ነው ሲሉ ወቅሰው በሁለቱ አገራት መካከል አጥር ለመገንባት እና ወጪውንም ሜክሲኮ እንድትሸፍነው እንደሚያደርጉ ቃል ገብተው ነበር።
በምርጫ ክርክሮች ወቅት ተቀናቃኞቻቸውን ዝም በማሰኘት የሚታወቁት ትራምፕ ያልተጨበጡ የሴራ ትንታኔዎችን በማስፋፋት በርካታ ደጋፊዎችን ቢያፈሩም፤ በተመሳሳይ በርካታ ተቺዎች ገጥመዋቸዋል። በዚህ ሳቢያ የመገናኛ ብዙኃን ትኩረት ተነፍጓቸው አያውቅም።
‘ሜክ አሜሪካ ግሬት አጌይን’ (አሜሪካንን መልሶ ታላቅ ማድረግ) በተሰኘው የዘመቻ መለያቸው ብቅ ያሉት ትራምፕ የሪፐብሊካን ፓርቲ ዕጩ ሆነው ከዲሞክራቷ ሂላሪ ክሊንተን ጋር ለመፎካከር ብዙ አልተቸገሩም።
እርግጥ ነው የምርጫ ዘመቻቸው በውዝግብ የተሞላ ነበር። ወሲባዊ ጥቃትን በተመለከተ የተናገሩት በድብቅ ተቀድቶ ወጥቶ በቅድመ-ምርጫ የሕዝብ ድምፅ መለጊያዎች ከሂላሪ ዝቅ ብለው እንዲታዩ አድርጓቸው ነበር።
ነገር ግን በስተመጨረሻ በምርጫው ቀን ድሉን በማጣጣም የዩናይትድ ስቴትስ 45ኛው ፕሬዝደንት ሆነው ብቅ አሉ።

የትራምፕ የፕሬዝደንትነት ዘመን
ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ በድራማ የታጀበው የትራምፕ የፕሬዝደንትነት ዘመን ለአራት ዓመታት መነጋገሪያ ከመሆን ያገደው አልነረበም። በቀድሞው ትዊተር በአሁኑ ኤክስ ገፃቸው ላይ በሚፅፏቸው መመሪያዎች እንዲሁም ከውጭ አገራት መሪዎች ጋር በይፋ የሚፈጥሩት እሰጥ አገባ የሚረሳ አይደለም።
በሥልጣን ዘመናቸው ዋነኛ ከሚባሉ የአየር ንብረት ለውጥ እና የንግድ ስምምነቶች አገራቸውን ከማግለላቸው ባለፈ፣ ከሰባት የሙስሊም አገራት ዜጎች ወደ አሜሪካ እንዳይመጡ ማገዳቸው፣ ከቻይና ጋር በግልፅ የንግድ ጦርነት ውስጥ መግባታቸው እና ከመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማሻሻላቸው አይዘነጋም።
የትራምፕ የምርጫ ዘመቻ ቡድን እና ሩሲያ ግንኙነት ነበራቸው በሚል በቀረበ ክስ ምክንያት 34 ሰዎች በወንጀል ቢከሰሱም ትራምፕ ግን ስማቸው አልተካተተበትም። በመጨረሻም ምርመራው ወንጀል አልተፈፀም በሚል ተጠናቋል።
ትራምፕ በአሜሪካ ፕሬዝደንቶች ታሪክ ሥልጣን ላይ ሳሉ የተከሰሱ ሦስተኛው ሰው ናቸው። ይህ የሆነው የውጭ አገራት መንግሥታት ጆ ባይደንን በተለመከተ ምሥጢራዊ መረጃ እንዲያወጡ ግፊት አድርገዋል በሚል ነው።
በዲሞክራቶች በሚመራው የአሜሪካ ተወካዮች ምክር ቤት የተከሰሱት ትራምፕ በሪፐብሊካኖች በተያዘው የላይኛው ምክር ቤት (ሴኔት) ነፃ ተብለዋል።
በ2020 ለምርጫ ድጋሚ የመጡት ትራምፕ በኮሮናቫይረስ ምክንያት አወዛጋቢነታቸው ቀጥሎ በዓለም ዙሪያ አነጋጋሪ የሆኑ በርካታ ጉዳዮችን አንስተው ነበር።
በኮሮኖቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት ሳይንሳዊ ያልሆኑ አስተያየቶች በመስጠት የሚታወቁት ትራምፕ ለወረርሽኙ በቂ ምላሽ አልሰጡም የሚል ወቀሳ ይቀርብባቸዋል። በአንድ ወቅት በቫይረሱ ተይዘው ከምርጫ ቅስቀሳ ራሳቸውን ለማግለል ተገደውም ነበር።
በ2020 ምርጫ በመንበራቸው ላይ ለሁለተኛ ዙር የሥልጣን ዘመን ለመቆየት የተፎካከሩት ትራምፕ ከ74 ሚሊዮን በላይ የመራጮች ድምፅ ቢያገኙም በተቀናቃኛቸው ጆ ባይደን በ7 ሚሊዮን ተበልጠው ከፕሬዝዳንትነት ለመውረድ ተገደዱ።
ከውጤቱ በኋላ ምርጫው ተጭበርብሯል የሚል ክስ ያቀረቡት ትራምፕ በአውሮፓውያኑ ጥር 6/2021 ደጋፊዎቻውን ሰብስበው የጆ ባይደን አሸናፊነት ከመፅደቁ በፊት የአሜሪካ ምክር ቤት መቀመጫ ወደሆነው ካፒቶል ሂል እንዲዘምቱ አበረታትተዋል።
በዚህ ምክንያትም በተነሳ ግርግር የገዛ ምክትላቸውን ጨምሮ በርካታ ፖለቲከኞች ወቀሳ ሰንዝረውባቸው ለሁለተኛ ጊዜ ተከሰው አሁንም በጠባብ ድምፅ በሴኔቱ አማካይነት ነፃ ተብለዋል።

ዳግም ወደ ዋይት ሐውስ?
ከካፒቶል ሂል አመፅ በኋላ የትራምፕ የፖለቲካ ሕይወት ያበቃ መስሎ ነበር። ደጋፊዎቻቸውን ጨምሮ የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርጉላቸው ሰዎች በይፋ በትራምፕ ላይ ቅሬታቸውን እና ወቀሳቸውን አሰምተው ነበር።
ነገር ግን ይህ ያላገዳቸው ትራምፕ በታማኝ ደጋፊዎቻቸው ታግዘው እነሆ በ2024 የአሜሪካ ምርጫ ለመሳተፍ እያሟሟቁ ይገኛሉ።
ትራምፕ ለሁለተኛ ጊዜ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ለመሆን እየተወዳደሩ ያሉት በአራት የተለያዩ የክስ መዝገቦች 91 ክሶች ቀርቦባቸው እያለ ነው።
በምርጫ ቅስቀሳ ላይ ሳሉ በቅርቡ የግድያ ሙከራ የተደረገባቸው ትራምፕ በጥይት ተጨርፏል የተባለ ጆሯቸውን አሽገው ነው ፓርቲያቸው በይፋ ዕጩ አድርጎ በሰየማቸው መድረክ ላይ የቀረቡት።
የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝደንትን ተክተው ከትራምፕ ጋር በመጪው ጥቅምት ማብቂያ ላይ በሚካሄደው ምርጫ ላይ የሚፋጠጡት ምክትል ፕሬዝደንቷ የዲሞክራቶች ዕጩ ካማላ ሃሪስ ናቸው።
ምንም እንኳ ካማላ በቅድመ ምርጫው ከሕዝብ በተሰበሰቡ ድምፆች ትራምፕን እየመሩ ቢገኙም፣ ከሳምንታት በኋላ የሚካሄደውን የምርጫ ውጤት መገመት እጅግ አዳጋች ነው።