ማሟሻ…
ከምድራችን ግንባር ቀደም ተናፋቂ አብያተ መንግሥታት መካከል ቬርሳይ አንዱ ነው። ከፈረንሳይ ርዕሰ መዲና ፓሪስ በስተምዕራብ ወጣ ብሎ ይገኛል። ‘የሩስያዋ ቨርሳይ’ የሚሰኘው በቅዱስ ፒተርስበርግ ከተማ የሚገኘው ፒተርሆፍ አብያተ መንግስሥታት ሌላው ነው።
ሁለቱም አብያተ መንግሥታት ዛሬ አብያተ-መዘክሮች ሆነዋል። ተፈጥሮ፣ ታሪክና ቅርስ የተዛነቀባቸው የዕልፍ አዕላፍ ቱሪስቶች መነሀሪያ ናቸው። በአንድ ስፍራ የሀገር መልክ እና ልክ የተገለጠባቸው።
የአዲስ አበባው ብሔራዊ ቤተ መንግሥትም የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ‘የአፍሪካ ቨርሳይ’ መባሉ አይቀሬ ነው። ለምን ቢሉ ዘመንና ስፍራ ቢለያቸውም የታሪክ ዑደታቸው፤ የዘመን ቀለማቸው፣ የብዝሃ ቅርስ ባለቤትነታቸው ያመሳስላቸዋልና!
የፈረንሳይ ንጉሳዊያን ቤተሰቦች በፈረንሳይ አብዮት ከቨርሳይ ቤተ-መንግሥት ተባረዋል። የሩስያ ዘውዳዊ ስርዓት (ፃሮች ስርዓት) በኮሚኒስቶች አብዮት ከፒተርሆፍ ቤተ-መንግሥት ላይመለስ ተገርስሷል። በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ሠለሞናዊ ዘውዳዊ ስርዓት ከብሔራዊ ቤተ መንግሥት ፍጻሜውን አግኝቷል!!
ቨርሳይ ቤተመንግሥት ለፈረንሳይ
ከአራት ምዕተ ዓመታት በፊት ነው። ቨርሳይ ላይ የፈረንሳይ ግዛተ አፄ ንጉሥ ሉዊ 13ኛ ለአዳኞች ዕልፍኝ ገነባ። ልጁ ንጉሥ ሉዊ 14ኛ ደግሞ የቨርሳይ ቤተ መንግሥትን መሰረተ። በጊዜው ቅንጦት ተብሎ ፈረንሳያዊያን ‘እግዚኦ’ አሉ። በፈረንጆቹ 1661 የነገሰው ንጉሥ ሉዊ 14ኛ ግን ለመንግስቱ ክብር ዕፁብ ድንቅ የሆነውን የቨርሳይ ቤተ መንግሥቱን አነፀ። ሌሎች ነገሥታትም አሻራቸውን እያከሉ ኖሩበት። በተለያዩ አገልግሎቶችን አስተናግዶ፣ የፈረንሳይን አብዮት ጨምሮ መልከ ብዙ ታሪካዊ ሁነቶችን አስተናግዶ ዘመናት ተሻገረ። በጎርጎሬሳዊያኑ 1837 በወቅቱ ንጉስ ሉዊ ፕሊፕ የቨርሳይ ቤተ-መንግሥት ወደ ቤተ መዘክርነት ተለወጠ። እነሆ የቀድሞው ቨርሳይ ቤተ-መንግሥት ከነግርማ ሞገሱ 400 ዓመታትን ዘለለ።
ዛሬ ከዓለማችን ምርጥና ዝነኛው ቤተ መዘክሮች አንዱ ነው። በአውሮፓዊያኑ ዘመን ቀመር በ1979 ዓ.ም ከጎንደሩ የፋሲል ቤተ መንግሥት ጋር በዩኔሰኮ የዓለም ቅርስነት ተመዘግቧል። በፈረንሳይ ባህልና ቅርስ ሚኒስቴር ስር ይተዳደራል። የቨርሳይ ቤተ-መዘክር ኪነ ሕንጻ ብቻ አይደለም። ስነ ውበት፣ ኪነ ሕንጻና ኪነ ጥበብ ጥግ የሚነበብበት ከ800 ሄክታር በላይ የሚሸፍን ሠፊ ምድረ ግቢ ነው። ቤተ መንግሥቱ 63 ሺህ 154 ካሬ ሜትር ላይ ያረፉ 2 ሺህ 300 ቤቶች አቅፏል። የንጉስ ማደሪያ ቤት፣ ቋሚ ዐውደ ርዕዮች፣ ፋፏቴዎች፣ ሙዚየም፣ አረንጓዴ ስፍራ፣ የፈረሰኞች አካዳሚ፣ የገበያ ስፍራ፣ መናፈሻዎች፣ የቴኒስ መጫዎቻ ቦታ እና ሌሎች የተለያዩ ክዋኔ ስፍራዎችን በውስጡ አምቆ ይዟል። ቨርሳይ በጌጣጌጦቹ፣ በቅርፃ ቅርጾቹ፣ በስዕል ጥበቦቹ ሁሉ አጃይብ የሚያሰኝ ስፍራ ነው።

ቨርሳይ ቤተ መንግሥት
ቨርሳይ የፈረንሳይ የኩራት ትዕምርት ነው። የዓለማችን ቀዳሚዋ የቱሪስት መዳረሻ በሆነችው ፈረንሳይ ከተወዳጅና ተመራጭ የሀገሪቷ የቱሪስት መዳረሻዎች መካከል ቨርሳይ አንዱ ነው። በየዓመቱ 15 ሚሊዮን ሕዝብ ይጎበኘዋል። ይህ ማለት ከምስራቅ አፍሪካዋ ሩዋንዳ ጠቅላላ ሕዝብ ቁጥር የበለጠ ጎብኚ ቨርሳይ ላይ በየዓመቱ ይጎርፋል ማለት ነው። ከ2 ሺህ 500 በላይ ቀጥተኛ፣ ከ10 ሺህ በላይ ተዘዋዋሪ ስራ ዕድል ፈጥሯል። ቨርሳይን ጨምሮ ፈረንሳይ በዓመት እስከ መቶ ሚሊዮን ዶላር ገቢ ታመነጫለች- በትናንት ታሪክና ቅርሷ።
ፒተርሆፍቤተ-መንግሥት
የዘመናዊት ሩስያ መስራች ታላቁ ፒተር ቀዳሚ በንጉሥ ሉዊ 14ኛ ዘመን ወደ ፈረንሳይ ተሻገረ። በቨርሳይ ቤተ-መንግሥትን በክብር ተስተናገደ። በተመለከተው ትዕይንት ተደነቀ፤ ተገረመ። የፒተርሆፍ ቤተ መንግሥትን እንዲያንጽ ምክንያት ሆነው።
ፒተርሆፍ ቤተ መንግሥት በቅዱስ ፒተርስበርግ ከተማ ይገኛል። ቀዳማዊ ፒተር በአውሮፓዊያኑ 1709 ታነጸ። ብዙሃኑ ፒተርሆፍን ‘የሩስያው ቨርሳይ’ ይሉታል። የክረምቱ ቤተ መንግሥትም ይሰኛል። የሩስያ ታሪክ፣ ጥበብና ቅርስ ማዕከል ነው። የሩስያ ጣሪያ አለባ ቤተ መዘክር(Open air musuem) በምትሰኘዋ ቅዱስ ፒተርስበርግ ከተማ ከሚገኙ ቀዳሚ የቱሪስት መነሃሪዎች መካከል አንዱ ፒተርሆፍ ነው።

ፒተርሆፍ ቤተ መንግሥት
በ3 ሺህ 934 ሄክታር ላይ ያረፈው ፒተርሆፍ በውስጡ ግዙፍ ቤተ መንግሥት፣ ዕውቁ የሳምሶን ፋውንቴን፣ አረንጓዴ ስፍራዎች፣ ፏፏቴዎች፣ መናፈሻዎች፣ ማራኪ ኪነ ሕንጻዎች፣ ጥንታዊ ስዕላት፣ ቤተ መዘከር እና ሌሎች የከበሩ ቅርሶችን ይዟል። የዚህ ጽሁፍ ጸሀፊ ፒተርሆፍን ምድረ ግቢ የማየት ዕድል ያገኘሁ ሲሆን ታሪክ፣ ቅርስና ተፈጥሮ እንዴት መሳ ለመሳ ተሰናስነው ሀሴትን እንደሚያላብሱ ታዝቤያለሁ። ሩስያዎች ታሪክና ቅርሳቸውን እንዴት ለዘመናት ጠብቀው እንጀራ እያበሰሉበት እንዳለም እንዲሁ።
በአውሮፓዊያኑ በ1990 በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት ተመዝግቧል። በየዓመቱ በአማካይ ስድስት ሚሊዮን ቱሪስቶች ይጎበኙታል። ከቅዱስ ፒተርስበርግ ብቻ ሳይሆን ከመላዋ ሩስያ ምርጥ ቱሪስት መዳረሻዎች መካከ አንዱ ነው።
ፒተርሆፍ ቤተ መንግሥት በኢትዮ-ሩስያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የራሱ ታሪካዊ አሻራ እንዳለው መጥቀስ ተገቢ ነው። ይሄውም ከአድዋ ድል አንድ ዓመት ቀደም ብሎ በ1887 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ በፊታውራሪ ዳምጠው ከተማ(የራስ ደስታ አባት) የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ ሩስያን ሲረግጥ ደማቅ አቀባበል የተደረገለት በፒተርሆፍ ቤተ መንግሥት ነበር።

በፊታውራሪ ዳምጠው ከተማ ልዑክ በፒተርሆፍ ቤተ መንግሥት
ፊታውራሪ ዳምጠው ከተማ ከአጼ ምኒልክና ከእቴጌ ጣይቱ የተላኩ ስጦታዎችን ለንጉስ(ጻር) ኒኮላስ ዳግማዊ እና ለባለቤታቸው ቀዳማዊት አሌክሳንድራ ያስረከቡት ፒተርሆፍ ቤተ መንግሥት ነበር። ከሩስያ ሲመለሱም ለአድዋ ጦርነት ስንቅ የሆኑ የጦር መሳሪያዎች እና የቀይ መስቀል አባላትን አስከትለው ተመልሰዋል። ይህም የሩስያው ቨርሳይ(ፒተርሆፍ) ከኢትዮጵያ ጋር የሚያስተሳስራት ሌላ ታሪካዊ ገመድ እንዳለ ያረጋግጣል።
ብሔራዊ ቤተ መንግሥት ለኢትዮጵያ
የምድረ ቀደምቷ ሀገር ኢትዮጵያ ብሄራዊ ቤተ መንግስት የአአፄ ኅይለሥላሴን 25ኛ ዓመት(የብር ኢዮቬልዮ) የንግሥና ክብረ በዓል ምክንያት በማድረግ የተገነባ ነው። በ1953 ዓ.ም የመፈንቀለ መንግሥት ሙከራ በኋላ ንጉሠ ነገሥቱ ገነተ ልዑልን(አሁን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) ለቀው እስከ ሕልፈተ ሕይወታቸው ድረስ መኖሪያቸው ይሄው ቤተ-መንግሥት ነበር። በደርግ ዘመን ወደ ‘ብሔራዊ ቤተ መንግሥት’ነት ስሙ ከመለወጡ በፊት ‘ኢዮቬልዮ ቤተ መንግሥት’ እየተባለ ሲጠራ ቆይትል። ከታላቁ ወይም ከዳግማዊ ምኒልክ ቤተ መንግሥት ጋር በማነጻጸር ደግሞ የታችኛው ቤተ-መንግሥትም ይባል ነበር። በደርግ ዘመን ፋውንቴኖችና ሌሎች መዝናኛ ስፍራዎች ተገንብተውለታል።


በኢሕአዴግ መንግሥት ደግሞ የርዕሰ ብሔሮች መኖሪያና እንግዳ መቀበያ ሆኖ አገልሏል። ሀገራዊ የክብር ክዋኔዎች መስተናገጃ ነው። የእንግሊዟን ንግስት ቪክቶሪያ ጨምሮ በርካቶች የዓለማችን ዕውቅና ዝነኛ መሪዎች ተስተናግደውበታል። በዚህ ቤተ መንግሥት የንግስቷ እልፍኝ የተባለ ክፍልም እንዳለ መረጃዎች ያሳያሉ። በኢጣሊያናዊው የኪነ ሕንፃ ባለሙያ ራፋዔል ፔትሮን የተነደፈው ቤተ መንግሥቱ፤ የኢትዮጵያን ባህላዊ የኪነ ሕንፃ እሴት እና የዘመናዊ ኪነ ህንፃ ለዛ አጣምሮ የያዘ እንደሆነ ይነገርለታል።

አፄ ኅይለሥላሴ በብሔራዊ ቤተ መንግሥት
አፄ ሃይለሥላሴ (ያኔ ልዑል አልጋወራሽ ራስ ተፈሪ) በፈረንጆቹ 1924 የተመረጡ 39 አባላትን ያቀፈ ልዑክ መርተው መካከለኛው ምሥራቅና አውሮፓን መጎብኘታቸው ይታወሳል። በአውሮፓ ሀገራትም የዓለማችን ምርጥ አብያተ መንግስታትና ታሪካዊ ስፍራዎችን ተመልክተዋል። ራስ ተፈሪ ከጎበኟቸውና ቀልባቸውን ከሳባቸው የፈረንሳይ ታሪካዊው ስፍራዎች መካከል የቬርሳይ ቤተ መንግሥት ይገኝበታል። አልጋ ወራሹ የመጀመሪያ የውጭ ሀገር ጉዞ በሆነው በዚሁ ጉብኝት ወቅት ከፈረንሳይ መሪዎች ጋር ተወያይተዋል። በውይይታቸውም ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ዋስትና ጉዳይ ቀዳሚው አጀንዳ እንደነበር ታሪክ ያወሳል።
አስገራሚው ነገር ከአንድ ምዕተ ዓመት በኋላ በቅርቡ በብሔራዊ ቤተ መንግሥት ንግግር ያደረጉት የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት አማኑኤል ማክሮን ‘ኢትዮጵያ የባህር መውጫ በር ያስፈልጋታል የሚለው ንግግር ታሪካዊ ግጥምጥሞሽ ያሰኘዋል።

የቤተ መንግስቱ ስፋት፣ ዘመናዊነትና ኪነ ሕንፃ ውበት ብቻ ሳይሆን በውስጡ የያዛቸው ቅርሶችና ያስተናገዳቸው ታሪኮች የተለዬ መልክ እንዲኖረው ያደርጋል። የዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ መነሻ ሀብቶችን አቅፏል።
የቤተ መንግስቱ መገኛ ስፍራ የአዲስ አበባ ከተማ የተወጠነበት አስካል በመሆኑ ከሌሎች ታሪካዊ ስፍራዎች ሌላው ልዩ ገጽታው ያላብሰዋል። ቤተ መንግሥቱ የኢትዮጵያ ብዝሃ ታሪክ ባለቤትነትና የምንጊዜም ነጻ ሀገርነት ማሳያ ትዕምርትም ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከአራት ዓመት በፊት ቤተ መንግስቱንና ቅርሶቹን እያስጎበኙ፤ ያልተገለጠው ሀብት እሴት ተጨምሮበት ለጎብኚዎች ክፍት የማድረግ ሃሳባቸውን ማጋራታቸው ይታወሳል። ቤተ መንግስቱ ታድሶ ለሕዝብ ክፍት ቢደረግ ለሀገር ምን ያህል በረከት ይዞ እንደሚመጣ የሰጡት ማብራሪያም የብዙሃኑን ቀልብ የሳበ ነበር።
ብሔራዊ ቤተ መንግሥት ከፍልውሃ፤ ከፊንፊኔ ባሕል አዳራሽ፣ ከግዮን ሆቴል እና ከአፍሪካ አዳራሽ ጋር የተያያዘ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት የቤተ መንግሥት ምድረ ግቢ ከፍልውሃና ፊንፊኔ አዳራሽ ጋር ተዳምሮ ከ70 እስከ 80 ሄክታር ስፋት አለው። በትልልቅ ዛፎች ውብ ሀመልማላዊ ገጽታ የተላበሰ፤ ድንቅና ብርቅ ታሪካዊ ሀብቶች ይገኙበታል።
“መሀልከተማ ላይ ትልልቅዛፎች ያሉት፣ በጣምየሚገራርሙ ታሪካዊሀብቶችን የያዘ ስለሆነሙሉስራከተሰራለትበምንም መመዘኛበየትኛውምየዓለምክፍልካሉካፒታልሲቲዎችሊወዳደርየሚያስችልበቃትአለው” ነበር ያሉት።
ለአብነትም በቤተ መንግስቱ ውስጥ የሚገኙ መኪናዎችን የ’ካር ሙዚዬም’ ገንብቶ ለጎብኚዎች ክፍት ቢደረግ ኢትዮጵያ ምን ያህል ተጠቃሚ እንደምትሆን ጠቁመው ነበር።
“እነዚህመኪኖችእኛከተማምይሁንሌላዓለምበቀላሉየሚታዩአይደሉም።አይታዩም፤ ብርቅናቸው።እነዚህንበጣምውብበሆነመንገድየመኪናኤግዚቪሽንብንሰራበጣምብዙሰውመጥቶያያቸዋል። አንደኛየንጉሥ መኪናናቸው። ሁለተኛአፍሪካውስጥ የዛሬ 50 ዓመት 60 ዓመትበዚህደረጃየደረጀሀብት እንደነበርየሚያሳይነው።… አፍሪካውስጥኢትዮጵያውስጥጥንታዊታሪክያላትከ50 ዓመትበፊትእንደዚህአይነትውቅርየደረጀመንግስቷየሚንቀሳቀስሀገርናተየሚለውቀላልትርጉምየሚሰጠውአይደለም”
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስላስደመመቻቸው ‘አምፊካር’ ስለተሰኘችዋ ተሽከርካሪ ሲያብራሩም “በጣምከገረመኝ ነገርአምፊካርየምትባለውዋ መኪና ናት።በፊልምካልሆነበስተቀርኢትዮጵያውስጥበቀላሉየምናየውነገር አይደለም።አምፊካርመሬትላይመኪናነው፤ውሃላይጀልባነው።እንደጀልባምእንደመኪናም የሚያገለግል የዛሬ 50 እና 60 ዓመትኢትዮጵያነበራት።የዛሬትውልድአያውቀውም።ይህንታሪክማሳየትእንችላለን” ብለዋል።
የብሔራዊ ቤተ መንግሥት ሀብቶችን ለትውልድ ለማስተማርም ለተቀረው ዓለም በማሳየትም የኢትዮጵያን ልክ ማሳየት እንደሚቻል “ይህንን በደንብ ለቱሪስቶች በማሳየት፣ በማስተማር የኢትዮጵያን ልክማሳየት ይቸላል።
ይህን ለማድረግ እኛ አዳዲስ ታሪክ መፍጠር አይጠበቅብንም፤ ያለውን በወግ እና በልኩ ቦታው ካስቀመጥን በራሱ ከበቂ በላይ የሚያስደንቅና የሚያስደምም ብዙዎችን የሚማርክ ሆኖ እናገኘዋለን። … እዚህ ቤት ውስጥ ተራ የሚባል ዕቃ የለም። እያንዳንዱ ዕቃ ውድ ነው። ዙፋን ብንመለከት የማን ነበር ብለን ጥያቄ የምናነሳው አይደለም። ስም አለበት እንደማህተም።
በጣም ብዙ የሚገርሙ ብዙ ሀብቶች እዚህ ውስጥ አሉ። ብዙዎቹ በጣም በውድ የተሰሩ በወርቅ የከበሩ ናቸው።ሰው ቢያቸው ውብ የሆኑ ግን ስቶር ቢቀመጡ ትርጉም የሌላቸው” ሲሉ ነበር ያብራሩት።
ቀጥለውም የብሔራዊ ቤተ መንግሥት ያዘላቸው ታሪኮች፣ ቅርሶችና የስነ ጥበብ ውጤቶች ለኢትዮጵያዊያን ኩራትም እራትም እንደሚሆኑ ጠቅሰዋል። ከኢትዮጵያ አልፎም የአፍሪካዊያን ታሪክ ማዕከል እንደሆነም እንዲሁ።
“የኢትዮጵያን ታሪክ ለማሸጋገርዕድልይሰጣል። የትኛውየአፍሪካሀገርነውበዚህልክመጽሀፍአለኝብሎማሳየትየሚችለውብላችሁመጠየቅነው። ጥንታዊታሪክአለንስንልይህንየሚያህልመጽሀፍቅዱስአለኝየሚልየአፍሪካሀገር ከየትም ሊያመጣአይችልም።
ብዙሊነገርየሚችልታሪክበሚሳዝንመንገድታጭቆተቀምጧል። ሰብሰብአድርገንጸዳ፣ ጸዳ አድርገንቦታውላይብናስቀምጥልጆቻችንታሪካቸውን፣ማንነታቸውንለማወቅዕድልያገኛሉ። … እዚህቦታላይሰፊሰዓትሊነገሩየሚችሉታሪኮች፣ ቅርሶችናፒክቸሮችአሉ።
በዓለም ላይ ስመ ጥር መሪዎች ፎቶዎች ይታያሉ። ማሀተመጋንዲ አለ፤ ማርቲንሉተር ኪነግ አለ። የአፍሪካ ታላላቅ መሪዎች አሉ። እያንዳንዱ የአፍሪካ ሀገር ነጻ ሲወጣ መጀመረያ መጥቶ የሚጎበኘው የአፍሪካዋን ነጻሀገር ኢትዮጵያን ነው። ሁሉም ሀገር ታሪኩ እዚህ አለ። የኛ ታሪክ ብቻ አይደለም። እያንዳንዱ የአፍሪካ ሀገር መሪው የመጣበት ጊዜ፤ ለምን መጣ ብለን በትክክል ቀምረን ማስቀመጥ ከቻልን እያንዳንዱ ሀገር ነጻ የወጣበትን እና ነጻ እንዲወጣ የረዳችውን ሀገር ታሪክ፣ የራሱንም ታሪክ ያይበታል። ይህ እንግዲህ ከኛም አልፎ የሌሎች የአፍሪካ ሀገሮችታሪክምእዚህ ውስጥእንዳለናለእነርሱለማሳየትምበጣምምቹይሆናል። ለእኛ ብቻ ሳይሆን እነሱም ታሪካቸውን መጥተው እንዲያዩ ማድረግ ያስችላል ማለት ነው።
በአንድ ክፍል ውስጥ ይህ ሁሉ ታሪክ ታጭቋል። ሕንጻ አድሰን እያንዳንዱን ክብር ባለው ቦታ ብናስቀምጠው ታሪክ ለማወቅ ያግዛል፤ ገንዘብ እንድናገኝበትም ይረዳል፤ ቱሪስት ይስባል” በማለት ነበር ያጠቃለሉት።

ብዙ ሀብትና ታሪክ በጉያው የያዘው ብሄራዊ ቤተመንግስት ለዘመናት የተደበቀው ሀብትና ታሪኩ ተገልጦ እንደ ፈረንሳዩ ቨርሳይ፤ እንደ ሩስያው ፒተርሆፍ የሚሆንበት ጊዜ ደረሰ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር ባደረጉት ንግግር መሰረት ብሔራዊ ቤተ መንግሥቱ በፈረንሳይ መንግሥት ድጋፍ ወደ ዕደሳት ገብቷል። የቨርሳይ ቤተ መንግሥት የዕድሳት ባለሙያዎች እገዛ መኖሩም ሌላ ዕድል ነው።

አንድ ምዕተ ዓመት በላይ ያስቆጠረውን ይፋዊ የኢትዮ-ፈረንሳይ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትና ዘመን ተሻጋሪ ወዳጅነትም በጽኑ መሰረት ላይ ያቆመ መሆኑን ያሳዬ ነው። የአፍሪካ ቨርሳይ ያልኩት ብሔራዊ ቤተ መንግሥትም ታድሶ እንደ ፈረንሳዩ ቬርሳይ፣ እንደ ሩስያዋ ፒተርሆፍ የዕልፍ አዕላፍ ቱሪስቶች ሰርክ የሚርመሰመሱበት መዳረሻ ሊሆን እነሆ ቀኑ ደረሰ!!
በአየለ ያረጋል addis zemen
ሙሉውን ለማንበብ 👉https://www.ena.et/web/amh/w/amh_5706095