አሳድ ሞስኮ ከአባታቸው በወረሱት ስልጣን ላለፉት 24 ዓመታት ሶሪያ ላይ ሲገዙ የኖሩት በሽር አላሳድ አማጺዎች ከመንበራቸው ገፍተረዋቸዋል። እሳቸውም ሲያልቅ አያምር እንዲሉ ሸሽተው በሞስኮ ስደተኛ ሆነዋል።
የሩስያ ዜና ምንጭ ታስ እንደዘገበው በሽር አላሳድ ከነቤተሰባቸው ሩስያ፣ ሞስኮ ጥገኛ ሆነዋል።ሩስያ ለአላሳድ እና ለቤተሰባቸው በሰብዓዊነት ምክንያት ጥገኝነት እንደሰጠች ተነግሯል።
አማጺዎች ደማስቆን ከተቆጣጠሩ በሁዋላ ሕዝብ የአሳድ ቅንጡ ቤተመንግስታቸው ዋኝተውበታል። የዘረፉም አሉ። እየተዟዟሩ ቤቱን በመገረም ሲመለከቱ የነበሩ አሉ። በአንድ ጋራዥ ውስጥ የታዩት ቅንጡእ መኪናዎች አስገራሚ ናቸው። ምንም ተባለ ምንም በሩሲያና ኢራን ትከሻ ስልታናቸው ላይ የከረሙት አላሳድ ዛሬ ስደተና ሆነዋል። በሳምንት ጦርነት ጦራቸው ተፍረክርኮ ወደ ኢራቅ ጎርፏል። በቃ ታሪክ ሆነዋል።
አሁን ጨዋታው ተቀይሯል። ከጂሃዲስትነት ፣ በኢስላሚክ ስቴት (አይኤስ) በኩል ከአል-ቃይዳ እና ከኢስላሚክ ስቴት ኢራቅ (አይኤስአይ) ጋር ትስስር የነበረውና የሶሪያ አማጽያን መሪ አቡ አሕመድ አል-ጃውላኒ ከጂሃዲስት ንቅናቄ ጋር ያለውን ግንኙነት ማቋረጡን ቢናገርም፣ ቀጣይዋ ሶሪያ ምን ልትመስል እንደምትችል አስቀድሞ መተንበይ አይቻልም። በዚሁ ሰው የሚመራው ታጣቂ ቡድን ሃያት ታህሪር አል-ሻም (ኤችቲኤስ) የሶሪያ መዲና ደማስቆን ጨምሮ ዋና ዋና ከተሞችን ተቆጣጥሯል። በውስጡ የተለያዩ አማጺ ቡድኖችን ተካተዋል። እነዚህ አማጺዎች አብዛኛውን የአገሪቱን ክፍል መቆጣጠራቸውንም አስታውቀዋል። እንግዲህ ስጋቱ የሚመነጨው ይህን ተከትሎ ነው።
የአማጽያኑ ደማስቆን መቆጣጠርና የፕሬዝዳንት አሳድ አገዛዝ ማክተም በመላው ዓለም በስደት ላይ የሚገኙትን ሶሪያውያንን አስፈንድቋል፤ የአውሮጳና አሜሪካ መሪዎችንም ይበል አሰኝቷል። ተሰናባቹ የአሜርካ ፕሬዝዳንት ባይደን የአሳድ መንግስት መወገድ ሶሪያውያን አገራቸውን ዳግም እንዲገነቡ የሚያስችል ጥሩ አጋጣሚ መሆኑን በመግለጽ፤ ሆኖም ግን አደጋዎችም ሊከተሉ ስለሚችሉ ጥንቃቄ የሚያስፈልግ መሆኑን አሳስበዋል።
የአውሮጳ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮን ዴርላይንም፤ “ አምባገነኑ አሳድ ተወግዷል፤ ይህ ታሪካዊ ለውጥ ጥሩ አጋጣሚዎች ያሉትን ያህል አደጋዎችም ሊኖሩት ይችላል” በማለት የአውሮጳ ህብረት፤ የሶሪያ አንድነትና ሉላዊነት እንዲከበርና የህዝቦቿ ነጻነት እንዲረጋገጥ የበኩሉን የሚያደርግ መሆኑን ባወጡ መግልጫ አስታውቀዋል።

ከሳምንት በፊት ይህ ይሆናል ብሎ በርግጥ ማን አሰበ? ማንስ ገመተ? ይህ የአምባገነኖች መጨረሻ የሌላኛው ታሪክ ማሳያ ነው ። የአል- አሳድ ስረወ መንግስትም ተገረሰሰ ። አሁን ጥያቄው ለሶሪያ አዲስ ጸሐይ ይወጣላታል? ወይስ ፤ እንደ ጋዳፊው ሊቢያ በጦር አበጋዞች ተከፋፍላ የጠለቀችው ጸሐይ ወደ ድቅድቅ ጨለማ የሚያመራባት ሶሪያ ትሆናለች ?
ትናንት እሁድ ከወደ ደማስቆ የተሰማው ዜና በርግጥ ለተቀረው ዓለም ይቅር እና ለሶሪያዉያኑ ራሱ የማይታሰብ ይመስል ነበር ። ሃያት ታህሪር አል ሻም በተሰኘው እስላማዊ ታጣቂ ቡድን የሚመራው የሶሪያ አማጽያን ጥምረት ትናንት እሁድ ማለዳ መዲናዋ ደማስቆን በቁጥጥሩ ስር አውሏል።
የአል አሳድ መንግስት መውደቅን ተከትሎ በርካታ ሶሪያዊያን በመዲናዪቱ ጎዳናዎች ወጥተው ደስታቸውን ሲገልጹም ታይተዋል። የመንግስት ወታደሮች ጥለዋቸው በሸሹ ታንኮች ዙሪያ ተሰባስበው ሲጨፍሩ የሚያሳዩ የቪዲዮ ምስሎች ተለቀዋል።
አማጽያኑ መዲናዋ ደማስቆን በቁጥጥራቸው ስር ሲያውሉ ፕሬዚደንት በሽር አል አሳድ አስቀድመው ሀገር ጥለው ወደ ሁነኛ ወዳጃቸው የፑቲን ሀገር ሞስኮ ሩስያ መሸሻቸው ተሰምቷል።
ብሄራዊ ቤተመንግስቱን ጨምሮ የሀገሪቱ መንግስታዊ የመገናኛ ብዙኃንን በቁጥጥር ስር ያዋሉት አማጽያኑ «ሶሪያ ከጨቋኙ ስረዓት ነጻ ወጥታለች» ሲሉ አውጀዋል።
አማጽያኑ መዲናዋን ከተቆጣጠሩ በኋላ በነበረው የመጀመሪያው እርምጃቸው በግዙፉ ሳይንድንያ እስር ቤት የታጎሩ በሺዎች የሚቆጠሩ እና ተቃዋሚዎችን የሚደግፉ እስረኞችን ከእስር ፈትተው ለቀዋል።
በመዲናዋ የሚገኙ የመንግስት ኃይሎች አስቀድመው መሸሻቸውን ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ዘ,ግበዋል። የሀገሪቱ መከላከያም ኃይሎቹ ከዚህ በኋላ ተልዕኮ አይኖራቸውም ብሏል። አማጺ ቡድኑ ሃያት ታህሪር አል ሻም ወይም ኤች ቲ ኤስ በቴሌግራም ገጹ ባሰራጨው መረጃ “የጨለማው ዘመን አብቅቶ አዲስ ዘመን ተጀምሯል” ብሏል።
በአምባገነኑ የአሳድ መንግስት የተፈናቀሉ ሶሪያዊያን ወደ ቤታቸው እንዲመለሱም ጠይቋል።
“ሁሉም ሰው በሰላም የሚኖርባት እና ፍትሕ የሚሰፍንባት አዲሲቷ ሶሪያ ናትም” ብሏል ቡድኑ በመግለጫው ። በርግጥ ነው ፤ ሶሪያዉያን ቀጣዩን ጊዜ በተስፋ ይጠባበቃሉ ። ከዚያ በፊት ግን እነዚያ 13 የጨለማ ዓመታት መለስ ተብለው መቃኘታቸው አይቀርም ። የደረሰው ሰብአዊ ቀውስ እንዲሁ በቀላሉ የሚረሳ እና አዲስ ህይወት የሚጀመርበት አይደለምና ።
የዶቼ ቬለ ዘጋቢ ሶሪያዊቷ ጋሲያ ኦሃኔስ እንደምትለው የአል አሳድ መንግስ በዚህ ፍጥነት መገርሰሱ በሀገር ውስጥ እና በመላው ዓለም ተበትነው ለሚገኙ ሶሪያዉያን የምስራች ነው ።

«የ13 ዓመታት ጦርነት እና ያደረሰው ውድመት ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ በተደረገ ጦርነት በፍጥነት ነበር ወደ ፍጻሜው የደረሰው ። ይህ የፈጠረው ደስታ አሁን በጋራ ደስታቸውን የሚገልጹ ሰዎች ሶሪያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በጎረቤት ሊባኖስም ጭምር ጎዳና መውጣታቸውን ተመልክተናል።
ይህ በሽር አልአሳድ እና አባታቸው ከሃምሳ ዓመታት በዘለቀው መንግስታቸው ምን ያህል ጠላት እንዳፈሩ አሳይቶናል »
የመካከለኛው ምስራቅ ጉዳይ ተንታኙ ሮድገር ሻናንም የጋሲያን ሃሳብ በሚጋራ መልኩ ለዶቼ ቬለ እንዳለው ከጥቂት ቀናት በፊት አማጽያኑ የጀመሩት ዉግያ እርሱን ጨምሮ ሶሪያዉያኑ እንዲህ በፍጥነት ይጠናቀቃል ብለው አልጠበቁም።
« አማጽያኑ መግፋት መጀመራቸው እኔን ጨምሮ ብዙ ሰዎች ብርቱ ጦርነት እንደሚደረግ እና ደም አፋሳሽ ሊሆን እንደሚችል ይሆናል ብለው ነበር የጠበቁት ። የሆነው ግን ከዚህ በእጅጉ የተለየ ነው። »
በጎርጎርሳዉያኑ 2011 የተቀሰቀሰው የሶርያ ግጭት ሀገሪቱን ቀውስ ውስጥ ከቷት ያለፉትን 13 ዓመታት ገደማ የደም ምድር አድርጓታል። በጦርነቱ ግማሽ ሚሊዮን ያህል ሶሪያዉያን ተገድለዋል፤ ከስድስት ሚሊዮን የሚልቁቱ ደግሞ ሀገር ጥለው በመላው ዓለም በስደት ተበትነዋል። በጦርነቱ ሶሪያ ከደረሰባት ሰብአዊ ውድመት እና ማህበራዊ ቀውስ ባሻገር በገንዘብ ሊገመት የማይችል የንብረት ውድመት ደርሶባታል።
ዉብ ከተሞቿ በደረሰባቸው ውድመት እንዳልነበር ሆነው በትዝታ ሲቀሩ ፤ ታሪካዊ ፣ ዓለም ያደነቃቸው እና በቅርስነት የመዘገባቸው በርካታ ታሪካዊ ቅርሶች ወደ ፍርስራሽነት ተቀይረዋል። በጦርነቱ ምክንያት ኢትዮጵያን ጨምሮ በመላው ዓለም ተበትነው የሚገኙ ሶሪያውያን በምን ያህል ፍጥነት ወደ ሀገራቸው ይመለሳሉ የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ጊዜው ገና ቢሆንም ለአምባገነኑ ስረዓት መፍረስ ግን ደስታቸውን ከመግለጽ አላገዳቸውም።
ይህ ግን ከፖለቲካ ተንታኞች ባሻገር ተራ ሰዎችን ጨምሮ በብዙ አነጋጋሪ የሆነው የ13 ዓመታት ደም አፋሳሽ ጦርነት እንደምን በአስር ቀናት ውስጥ ፍጻሜ አገኘ የሚለውን ጥያቄ ማስነሳቱን አያስቀርም ።
የመካከለኛ ምስራቅ ጉዳይ ተንታኙ ሮድገር ሻናን እንደሚለው የሶሪያ መንግስት መዳከም ፤ በሶሪያ መንግስት ወታደሮች ውስጥ የተፈጠረው የጦርነት መሰላቸት እና የውጭ ኃይሎች ድጋፍ መቀዛቀዝ ለአል አሳድ ውድቀት ፍጥነት አበርክቶ እንዳለው ነው።
«የአሳድ አስተዳደር ለጦርነት የሚያውለው ሃብት እየተዳከመ መሄድ ፣ የጦር ኃይሉም ቢሆን የመዋጋት ብቃተቸው መውረዱ አገዛዙ አማጽያኑን ማስቆም የማይችልበት ደረጃ ላይ አድርሶታል። በዚህ ላይ ደግሞ ሁነኛ አጋሮች የነበሩ ሩስያ እና ኢራን በራሳቸው ጉዳይ ተይዘውም ይሁን በሌላ ገሸሽ ማለታቸው የአል አሳድ አገዛዝ በመጨረሻ አማጽያኑን መግታት የማይችልበት ደረጃ ላይ አድርሶታል። »
የሶሪያ አማጽያን ኃይሎች ጥምረት ወይም ናሽናል ኮአሊዥን ኦፍ ሲሪያን ሪቮሉሽን ኤንድ ኦፖዚሽን ፎርስስ የተባለው ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ የሆኑት አል-ባሕራ ፣ «በደማስቆ የነዋሪዎች ደኅንነት የተጠበቀ » መሆኑን በ ኤክስ ገጻቸው ባጋሩት መረጃ አስታውቀዋል።
«በሁሉም ሃይማኖት እና ቡድኖች ውስጥ ያሉ ዜጎቻችን ከዚህ በኋላ እርስ በእርስ መዋጋት የለባቸውም» ያሉት አል ባህራ ። «ዜጎች ቤታቸው እስከሆኑ ድረስ ደህንነታቸው የተጠበቀ ነው ፤በቀል አይኖርም፤ የሰብአዊ መብትም አይጣስም፤ የሰዎች ክብር ይጠበቃልም» ብለዋል።
የበሽር አልአሳድ መንግስት ውድቀት እና የአማጽያኑ መዲናዪቱ ደማስቆን መቆጣጠር ከሶሪያ ፣ብሎም ከመካከለኛው ምስራቅ ባሻገር የምዕራቡ እና የምስራቁን ዓለም በጎራ የከፈለ አንድምታ አስከትሏል።
ውድቀቱ ለሩስያ እና ኢራን ብሎም ለአፍቃሬ ኢራን የመካከለኛው ምስራቅ አማጽያን ጥሩ ዜና ይዞ አልመጣም ። ለአስራ ሶስት ዓመታት እስትንፋሱን ይዘው ያቆዩት የወዳጃቸው የአልአሳድ መንግስት መጨረሻውም ያላማረ ሆኗል። ሶሪያ ውስጥ ተጠልሎ የሰነበተው የሄዝቦላ ታጣቂ ቡድን ገና ከወዲሁ ሶሪያን ለቆ ለመውጣት ተገዷል። በመካከለኛው ምስራቅ ሁነኛ ሚና የመጫወት ዕድል በእጇ ያስገባችው ቃጣር ህዝቡን እና ሃገራቸውን መታደግ ያልቻሉ ሰው ስትል በሽር አል አሳድ ላይ ብርቱ ነቀፌታ አሰምታለች።
በጦርነት ውስጥ የሰነበተችው እስራኤል የደማስቆ ውድቀት ደስታ እንደፈጠረላት እየተሰማ ነው ። ምክንያቱም አሜሪካ እና የአውሮጳ ህብረት ከአልቃኢዳ ተነጥሎ እንደተቋቋመ የሚነገርለትን አማጺ ቡድኑን ከሽብርተኝነት ፍረጃ አላቀው ምናልባትም ወታደራዊ ድጋፍ አድርገውለት ለስልጣን አብቅተውታል ለእርሷ ሰርግ እና ምላሽ ሊሆንላት ይችላል ፤ የኋላውን ለኋላ አስቀርተን
የበሽር አል አሳድ ሁነኛ አጋሯ ኢራን ሶሪያዉያን ያለአንዳች የውጭ ጣልቃ ገብነት መጻኢ ጊዜያቸውን በራሳቸው ይወስኑ ስትል ምክር አዘል መልዕክት አስተላልፋለች። ከሶሪያ ጋር ያለን ወንድማዊ ግንኙነታችን ተጠናክሮ ይቀጥላል ስትል ያላትን ተስፋም ገልጻለች። እስራኤል በበኩሏ በተባበሩት መንግስታት የሰላም አስከባሪ በሚጠበቀው የጎላን ኮረብቶች የሶሪያ ግዛት ላይ ወታደሮቿን እያሰፈረች መሆኗን አስታውቃለች። እርምጃውን ሶሪያ ውስጥ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ በጎላን ኮረብቶች የሚኖሩ ዜጎቼን ከማንኛውም ጥቃት ለመከላከል ያለመ ነው ብላለች።
ሌላዋ የመካከለኛው ምስራቅ ኃያል ሀገር ሳዑዲ አረቢያ በሶሪያ የተፈጠረው ሁኔታ ወደ ሌላ ቀውስ እንዳያመራ በቀጣናው ካሉ ባለድርሻ ሃገራት ጋር ግንኙነት እያደረገች መሆኗን ገልጻለች።
ልዕለ ኃያሏ ሀገር አሜሪካም ብትሆን ከሳዑዲ አረቢያ የተለየ ነገር አላለችም ። ተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ከዋይት ሃውስ በሰጡት መግለጫ እርሳቸው እና ቡድናቸው በሶሪያ እየሆነ ባለው ነገር ላይ ከአጎራባች ሀገራት ጋር በቅርበት እየተነጋገሩበት እንደሆነ ነው የገለጹት ። ተመራጩ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ ግን ጠንከር ያለ አቋም ይዘዋል። አሳድን በመወረፍ በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት ሃሳብ አሳድ « ሀገሩን ጥሎ ሸሽቷል፤ ታዳጊው ሩስያ ፤ በቭላድሚር ፑቲን የምትመራዉ ሩስያ ልትታደገው አልቻለችም » ሲሉ መሳለቃቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ሞስኮ በበኩሏ ባሽር አላሳድ ስልጣናቸውን ለቀው ከሀገር መውጣታቸውን ከመግለጽ ባለፈ የት እንዳሉ አልገለጸችም ። ነገር ግን የዜና ምንጮች አል አሳድ ሞስኮ መግባታቸውን ለክሬምሊን ቅርበት ካላቸው ታማኝ ምንጮች ማረጋገጣቸውን ጽፈዋል። ክሬምሊን ግን ይህንን አምኖ መቀበል የፈለገ አይመስልም ። ቃል አቃባይ ዲሜትሪ ፔስኮቭ ዛሬ ከጋዘጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ «አሳድ የት እንዳለ የማውቀው ነገር የለም።» ሲሉ ሞስኮ አልአሳድን አስጠልላለች ተብሎ አስቀድሞ የወጣውን መረጃ አጣጥለዋል።
በሶሪያ የሚገኘው ጦሯም በከፍተኛ ተጠንቀቅ እንዲቆም መታዘዙን የሩስያ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር አስታውቋል። ሚኒስቴሩ በትናንት መግለጫው ለጊዜው ለጦሩ የሚያሰጋው አንዳች ነገር የለም፤ ብሏል።
ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሶርያዉያን ስደተኞችን ያስጠለለችው ጀርመን የበሽር አል አሳድ መንግስት ውድቀትን መልካም ዜና ብላዋለች። መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልዝ ትናንት እሁድ በሰጡት መግለጫ «ይህ መልካም ዜና ነው ፤« ሀገሪቱን ወደ ተረጋጋ ሁኔታ ለመመለስ ፖለቲካዊ መፍትሄ ሊበጅ ይገባል»፤ ብለዋል።
ይህ በእርግጥ ለአስራ ሶስት አመታት ለአለቀው የሶሪያውያን ሰቆቃ ማብቂያ ጊዜ የደረሰ መስሏል። ጋዜጠኛ ጋሲያ እንደምትለው ሶሪያውያን አሁን ወደ ሃገራቸው የሚመለሱበትን መንገድ መመልከት የሚጀምሩበት ነው።
«አሁን ከአስራ ሁለት ሚሊዮን የሚልቁ ስደተኞች አሉ ፤ አብዛኞቹ በዚህ አካባቢ ነው የሚገኙት እና አብዛኞች ሊባል በሚችል መልኩ ወደ ሃገራቸው እንዴት አድርገው መመለስ እንደሚችሉ መመልከት እንደሚጀምሩ ነው የምረዳው ፤ ሊባኖስ ድንበሯን ከፍታለች፤ ሰዎች ለመመለስ እየተጠዳደፉ እንደሆነ የሚያሳዩ ምስሎችም እየተለቀቁ ነው። ይህ ሰው ምን ያህል ለመመለስ እንደፈለገ ነው የሚያሳየው “
በጎርጎርሳዉያኑ በ2010 በቱኒዚያ ተቀስቅሶ አብዛኛውን የመካከለኛው ምስራቅ የአረብ ሃገራት ያዳረሰው የአረብ አብዮት በአብዛኞቹ ሃገራት የመንግስት ለውጥ ሲያስከትል እንደ ሶሪያ ያሉትን ደግሞ ከማይወጡበት የርስ በርስ ጦርነት አስገብቷቸው አልፏል።
አንድ አፍታ ወደ ጎርጎሪዎሱ 2015 ወደ ኋላ ልመልሳችሁ ፤ ከላይ ቀይ ሹራብ ከስር ጥቁር ሰማያዊ ቁምጣ የለበሰ አንድ የአራት አመት ሶሪያዊ ህጻን አስክሬን በሜድትራንያን ባህር በቱርክ የባህር ዳርቻ ተገኘ ። ህጻኑ ስሙ አላን ኩርዲ ይሰኛል ፤ የዚህ ህጻን አስክሬን በባህር ወጀብ ተገፍቶ ባህር ዳር ከተገኘ በኋላ ዓለም የሶሪያን ስደተኞች ቀውስ ምን ደረጃ እንደደረሰ የተረዳበት ወቅት እንደነበረ መገመት አያዳግትም ።
ሶሪያውያን በጦርነቱ ከተራ የጦር ወንጀል እስከ የተከተከሉ የኬሚካል መርዞችን እስከ መጠቀም ያደረሱ የጦር ወንጀል እና በሰብአዊነት ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች አስተናግደዋል። መንግስትን የተቃወሙቱ በየእስር ቤቱ ታጉረው የደረሰባቸውን ከዚህ በኋላ ምናልባት ይናገሩ ይሆናል።
በሶሪያ አሁን አዲስ ቀን የመጣ መስሏል። ነገር ግን ሊቢያን ያየ ሶሪያን ለማመን ይከብደዋል እና አዲሱ ቀናቸውን ብሩህ የማድረግ የሶሪያዉያኑን ቁርጠኝነት መጠየቁ አይቀርም ። በህዝባዊ አመጽ እና በኃይል ፕሬዚዳንቷን ያስወገደችው ሊቢያ ከበርካታ ዓመታት በኋላ እንኳ የቀድሞውን ፕሬዚዳንት ዘመን ትናፍቃለች።
የመካከለኛው ምስራቅ በእርግጥ ቀውስ ውስጥ ነው ፤ የእስራኤል ሃማስ ጦርነት ያስከተለው የጋዛ ቀውስ እንደቀጠለ ነው። የሁቲ አማጽያን በእስራኤል ላይ ሚሳኤል መተኮሳቸው እንደቀጠለ ነው። የእስራኤል ኢራን ግጭት የተዳፈነ እሳት ነው። ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ ከመካከለኛው ምስራቅ አንጻር የሚይዙት ጠንከር ያለ አቋም ቀጣናውን ወዴት ሊያመራ እንደሚችል መገመት ይከብዳል።
በዚህ ሁሉ ውስጥ በመካከለኛው ምስራቅ እምብርት ላይ የምትገኘው ሶሪያ ያገኘችውን የለውጥ አጋጣሚ ትጠቀምበታለች ወይ ጊዜ ይመልሰዋል።
የበሽር አልአሳድ መዳረሻ ለጊዜው ባይታወቅም እንደ ቀደሙቱ አምባገነኖች ሁሉ መጨረሻቸው ሽሽት እና ውርደት ሆኖ ለሌሎች አምባገነኖች ትምህርት ሆኖ አልፏል።
ዘገባው ከጀርመን ድምጽና የተለያዩ መገናዎች የተወሰውደ ነው