ጁባላን ወታደሮቿ የሞቃዲሾውን መንግስት ኃይል ድል እያደርገ እንዳለ መረጃዎች በሚወጡበት በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ መሪዎች በፕሬዝዳንት ኤርዶዋን ግብዣ ቱርክ እንደሚገኙ ተገለጸ። ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ እና ልዑካቸው አንካራ ቱርክ መግባታቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
የቱርክ ፕሬዚዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በጽሕፈት ቤታቸው አቀባበል ያደረጉላቸው ሲሆን ሁለቱ መሪዎች ከልዑካን ቡድናቸው ጋር የሁለትዮሽ ውይይት ማድረጋቸው ተሰምቷል። የሶማሊያው ፕሬዜዳንት ሼክ መሐመድ አንካራ በተመሳሳይ ውይይት ማድረጋቸው በተለያዩ መገናኛዎች ተዘግቧል።
መሪዎቹ አንካራ የሄዱበት ሶማሊያ እና ኢትዮጵያ የገቡበትን ውጥረት ለማርገብ እንዲቻል ኤርዶጋን የንግግር መድረክ አመቻችተውላቸ እንደሆነ ተመልክቷል። በግል ውይይት ከተደረገ በሁዋላ ሁለቱንም መሪዎቹ ፊት ለፊት እንደሚነጋገሩ እየተዘገበ ነው። ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ለውይይት ዝግጁ መሆኗን ስታስታውቅ፣ ሶማሊያ በበኩሏ ከሶማሊላንድ ጋር የተደረገው የባህር በር ስምምነት ቅድሚያ መቀደድ አለበት የሚል ቅድመ ሁኔታ ስታስቀምጥ ቆይታለች።
ሮይተርስ የሶማሊያ ዜና አገልግሎት ሶናን ጠቅሶ እንደዘገበው የሁለቱ መሪዎች የፊት ለፊት ንግግር እየተካረረ የሄደውን የሁለቱን ሃገራት ዲፕሎማሲያዊ ቀውስ ለማርገብ ያስችላል የሚል ግምት አኑሯል።
ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ባደረገችው የመግባቢያ ስምምነት መሰረት በወደቡ ላይ ስራ የሚያሳልጥ ህጋዊ ቢሮ መክፈቷን ከቀናት በፊት ማስታወቋ አይዘነጋም።
እንደ ተባለው ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ከሀሰን ሼክ መሀመድ ጋር ፊት ለፊት የሚገናኙ ከሆነ ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ሶማሌ ላንድ ጋር የወደብ ባለቤት የሚያደርጋትን ስምምነት ከተፈራረሙ ወዲህ ይህ የመጀመሪያዉ ይሆናል።