በኢትዮጵያ “ይዞ መገኘት” የሚለው ትውልድን ያጨነገፈ መፈክር ይፋ የሆነው ” ሸራተን” እሚባለው “ትልቁ” ቤት ውስጥ ነው። ይህ እሳቤ “ትህነግ” በሚባለው መንግስት ሙሉ ድጋፍና ከለላ የተሰጠው ስለነበር በፍጥነት መንደር ድረስ ዘለቀ። እሳቤው አገሪቷን ከመወረሩ በላይ ማሻሻያም እየተደረገበት ዘልቆ ” ጥሎ ማለፍ” የሚል ማዕረግም ተመረጠለት። “ይዞ መገኘትና ጥሎ ማለፍ” ልክ እንደ ዛሬው ” የሌማት ቱርፋት፣ የኮሪዶር ልማት፣ የምግብ ሉዓላዊነት”፣ የበጋ መስኖ፣ አብርሆት ላይብረሪ፣ የሳይንስ ሙዚየም፣ ህጻንትና አረጋዊያንን መመገብ … ወዘተ ፓኬጅ የተሰራለት መዋቅራዊም ነበር። ያማል!!
በዚህ መርህና ፓኬጅ ስር የተሰባሰቡ ይዞ ለመገኘት ራስን እስከማዋረድ፣ ሚስትን አሳልፎ ለገበያ እስከማቅረብ ወይም የክብር ሚስትን ለሰጪና ሰጪ ዘንድ ለሚያደርሱ ውሽማ ለማድረግ መስማማት… የውሽሞች ቀን ብሎ በገሃድ መሪዎችን ጋብዞ መዛሞት፣ አንድ ፍሬ ህጻናትን አጥቦ፣ ወልውሎና አድምቆ ለገበያ ማቀረብ፣ በአደባባይ መሳቂያ መሆንን ወዘተ ያካትታል … ብዙ ለጽሁፍም ለንግግርም የማይመቹ ተግባራትን ፈጽመዋል። እርስ በርስ ኩዴታ እስኪደራረጉ ድረስ አንዱ የሌላው አለቅላቂና ታዝዥ እንደነበሩም ማስረጃ ማቅረብ አይጠይቅም። ወንበር ከመለዋወጥ በቀር በግብርም ሆነ በአቋም አንድ ናቸው።
በዚህ “ሸራተን” ተብዬው ሆቴል ውስጥ ከመሪዎች ጋር ቶራቦራ ሰርተው ሲረክሱና ሲያራክሱ የምናውቃቸው በኢትዮጵያ ህዝብ ብሄራዊ ቴሌቪዥን ቀርበው ታላላቅ የአገር ፕሮጀክት አራማጆች፣ የመጪው ትውልድ መጻዒ ዕድል የሚያሳስባቸውና ኃላፊነት የሚሰማቸው፣ የአገር ክብርና ልዕልና የሚያስጨንቃቸው መስለው ሲታዩ ማንነታቸውን ለሚያውቃቸው የምን ግዜም ሃፍረታቸው ነው።
በክራባት ታንቀው፣ ከሰረቁትና ለማጭበርበሪያ እንዲረጩ ከተፈቀደላቸው የግፍ ሃብት እየቦጨቁ የሚመጸውቷቸው አዝማሪዎች፣ ዘፋኖች፣ ቲያትረኞች፣ ቧልተኞች፣ በየአልኮል መቸርቸሪያው ስም እንዲገነቡ በተመደቡ የባንኮኒ አክቲቪስቶች፣ የላም አለኝ በሰማይ ዓይነት ባለሃብቶች፣ በጥቅሉ “በይዞ መገኘት፣ በጥሎ ማለፍ” ማህበርተኞች የሚጮህላቸው ወይም እንዲጮህላቸው የሚደረገውም ይህንኑ የረከሰ ማንነታቸውን ለመሸፈን እንጂ ለሌላ አይደለም።
መነሻዬ ስለሸራተን ወይም ቶራቦራ ለመጻፍ ሳይሆን እሳቤው እንዴት አገርን እንዳመነዠገና አሁንም እያነከተ መሆኑን ለማሳየት ነው። (ያልተነቀለው ሰንኮፍ – ዩሪ ቢስሜኖቭ እንዳለው፣ እኛም እንዳየነው…) በሌላም በኩል እዛ ሰፈር የወንበር ለውጥ ቢኖርም ሁሉም አንድ ዓይነት መሆናቸውን ጠቆም አድርጎ የ”ትልቅነት ደህና ሰንብት” አጀንዳዬ ለማምራት ነው። ጉዳዩን የለካከፍኩት ከሩጫውም ሰፈር ትልቅነት ወድሟል ብዬ የደፈርኩበትን ምክንያትም ለማሳየትና ጉዳዩ በዝምታ የሚታለፍ እንዳልሆነ ለማስረዳት ነው።
ከፓሪሱ የኦሊምፒክ ውድድር በሁዋላ የታመሰው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ውጤት ጉዳይ የሚያሳየን ከላይ ለመነሻ ያቀረብኩትን የጥሎ ማለፍ አስተምህሮት አጀንዳ እንጂ ሌላ አይደለም። ንግድ፣ ንግድ፣ ንግድ፣ ንግድ …. አሁንም እላለሁ ንግድና ንግድ ብቻ ነው። ከፓሪሱ ኦሊምፒክ ጅማሮ አንድ ሳምንት በፊት የተጀመረው ሁከትና የተቀናጀ ድራማ ይህ ጽሁፍ እስከታጻፈበት ሰዓት ድረስ የችግሩን ቴክኒካዊና ታክቲካዊ፣ አስተዳደራዊና ቡድንተኛነት የተጣባው አካሄድ መርመሮ ለመለየት የተደረገ ሙከራ የለም። ጉዳዩ በቴክኒክ ግምገማ ኦሊምፒክን ይመለከተዋል ብዬ ስለማላስብ፣ የነውጥ ጠንሳሾቹም ስለሚያምኑ ችግሩን ነቅሶ ለማውጣት ፍላጎቱ የላቸውም። ምክንያቱም ውጤቱ ከዓላማቸው መነሻ ጋር እይገጥምምና ነው።
የተደራጀው ሴራ
ከላይ ለምሳሌነት እንደተጠቆመው ሰዎቹ ርኩሰታቸውንና ግልሙትናቸውን ለመሸፈን ዳንኪራ ረጋጮችን ያስጮሁ ነበር። ከባንክ በቢሊዮን እየወሰዱ “አንድ ሚሊዮን ለህክምና ድጋፍ ሰጡ” በሚል አየሩን አስወጥረው በምስጋጋና በገጽታ ግንባታ ጠበል ይታጠቡ ነበር። ዙሪያቸው ያሉ ግልገል ተከፋዮችና ካድሬዎች ምስኪን ህጻናትን ዱባይ ወስደው እንዲዛሞቱ ስለተደረጉ በሄዱበት ባገደሙበት ” ሰው ብሎ ዝም” ይዘፍኑላቸዋል። የተሰጣቸውን ኃላፊነት ትተው ኢትዮጵያ ላይ እንዲፈነጭባት ይፈቅዱላቸዋል። በዚህም ኩራት ይሰማቸዋል። ይህ ልምድ አትሌቲክሱ ውስጥ ሰተት ብሎ ከገባ ከርሟል። ብዙ ብዙ ዋጋም አስከፍሎናል። በባንዲራና በክብር ስም የተጠቀለሉት ሳይቀሩ ሸራተንኛ እያዜሙ ነው። ለጊዜው ጫጫታው ቢጋርድም ቀስ እያለ እውነቱ እንደሚወጣ ይታመናል። በኦሊምፒክና ዓለም ሻምፒዮና የተለመደው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ውጤት ላለፉት አስራ ስድስት ዓመታት ቁልቁል ሲወርድ መናገር እንዳይቻል ተደርጎ የነበረውም በዚህ ስሌት ነው። ገንዘብ ሲናገር እንዲሉ!!
ዱቤ ጅሎና ደራርቱ ቱሉ
ሁለቱም ካድሬዎች ነበሩ። ናቸው። ዕድሜ ከሰጣቸው ወደፊትም የሚመጣውን አሜን ብለው እንደሚቀበሉ ጥርጥር የለውም። ደራርቱ ቱሉና ዱቤ ጅሎ እጅግ በሚዘገንን ደረጃ የምስኪን አትሌቶች ስብዕና፣ መብት፣ ችሎታ፣ ዕድል፣ የላባቸውን ዋጋ እንዳያገኙ፣ ተስፋና የአገር ክብር ወዘተ ላይ በገሃድ ወንጀል ሲፈጽም በኖረው የቀድመው ፌዴሬሽ ውስጥ ባለ ሙሉ ድምጽ ስራ አስፈጻሚዎች የተደረጉት ለተበዳዮች ድምጽ እንዲሆኑ ነበር። አንድም ጊዜ ግን የወከላቸውን አትሌት ወግነው ለፍትህ የቆሙበት ጊዜ አልነበረም።
የአትሌቶችን መብት እንዲያስከብሩ ተመርጠው ስራ አስፈጻሚ ውስጥ የተሰየሙት ደራቱ ቱሉና ዱቤ ጅሎ / የዛሬው የፓርላማ አባል/ ከነበረው የካድሬ ስብስብ ጋር አንድ ዓይነት መለያ ለብሰው ምን ይወስኑ እንደነበር ለመረዳት ሚዲያዎች ከላይ በተገለጸው መሰረት ሰለባ ካልሆናችሁ የተገፉትን አትሌቶች አነጋገሩ። “ለዕውነት ቆመናል፣ ከቀደመው አገዛዝ እንሻላለን” የምትሉ የመንግስት ሚዲያ ቦርድ አመራሮችና የስራ ኃላፊዎች ይህ እንዲሰራ መመሪያ ስጡ። የዛኔ ጉዱን ለማውራት ኢቲቪ ልክ እንደ ኤምግሬሽን በተበደሉ ወገኖች ወረፋ ይጥለቀለቃል።
ደራርቱ ጀግና ሯጭ ናት። ንብ ናት። ብቃቷ ድንቅ ነው። ይህ አይካድም። አኩርታናለች። ልክ እንደ ሩጫው ጮሌነትና ዕምባ አብረው ታድለዋታና እግር ሲደክም ተጠቅማበታለች። ሩጫው ሲቆም በጮሌነትና በለቅሶ ጠግርራናለች። በዚሁ ተሰጥዎዋ እሷ ብቻ ተለይታ ውድ መኪና፣ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብና ወርቅ እንድትሸለም ሆኗል። ያለ አቅሟ ትልቅ ተቋም መሪ ለመሆንም በቅታለች። ” ሽልማቱ ጥሩ ነው። ግን ጌጤስ? እነ እገሌስ? …ወዘተ ለምን ሳይሸለሙ ቀሩ? ብሎ የጠየቀ አለመኖሩ አያስደነግጥም? ግን ለምን እሷ ብቻ? በሜዳሊያ ብዛት ከሆነ ቀነኒሳ ለምን ተዘለለለ? ጥሩነሽ ዲባባስ … ሌሎችም አሉ። ብዙ መከራከሪያ ሊነሳ ይችላል። ወደ መነሻዬ ልመለስ። ይህ የማይሆነው ከላይ እንደተባለው የይዞ መገኘት ፓኬጅ አካል በመሆኑ ነው።
ዱቤ ሩጫ አይችልም። የሩጫ ጥሩ ታሪክ፣ የሚወራ ገድል የለውም። በበረሃ አገሮች እየተሳተፈ ትርፍራፊ ገንዘብ ይልቀም እንደነበር ከሚታወቀው ውጪ እሱም የሚነገረን ወርቃማ ገድል የለውም። የስራ አስፈጻሚና የቴክኒክ ኮሚቴውን ሃላፊ ሆኖ ፌዴሬሽኑን ሲመራ በነበረበት ወቅት ኮተቤ ኮሌጅ ትምህርት ጀመረ። የፍየል ስጋ በጠጅ እያወራረደ ትምህርቱን እንዴት እንደጨረሰ፣ ስንት ቀን ትምህርት ገበታው ላይ እንደተገኘ አበል እየወሰዱ የውጭ ጉዞ ሲመቻችላቸው የነበሩ አስተማሪዎቹን ጠይቁ። ይህም ሙያን አራክሶ በይዞ መገኘት መርህ ማምለክ ካልሆነ ምን ይባላል? የቴክኒክ ኮሚቴ አባላት የነበሩ የኮተቤ ኮሌጅ መምህራን ዘንድ መረጃ ሰብሰቡ። ይህ ለጥቆማ ያህል ነው። ዱቤ የትሌቲክስ ፌዴሬሽን የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሆኖ የጀመረውን ኃላፊነቱን አቶ እንዳልክ ሲሞቱ በቴክኒክ ኃላፊነት ጠቅልሎ ሲይዝ ወዲያውኑ ዶናዶኒ ከሚባሉ ጣልያናዊ የአትሌት ማናጀር ጋር በጋራ መስራት ጀመረ። ይህ ማለት በፌዴሬሽኑ የሹመት ወነበር ላይ ሆኖ ኮሚሽን ኤጀንት ሆነ ማለት ነው። ይህ ወንጀል መሆኑ ተጠቅሶ ሲጠየቁ “የተከበሩ” ዱቤ ጅሎ ከላይ እንደተገለጸው በይዞ መገኘት የተቀኙትን ሚዲያዎች ተጠቅሞ አስተባበለ።
እዚህ ላይ ለማንሳት የፈለኩት ዱቤ በተቀመጡበት ወንበር በተፈጸሙት ያልተገባ ተግባራት የተፈጠረው የጥቅም ግጭት አገርን፣ ፌዴሬሽኑንና አትሌቶችን በምን ያህል ደረጃ እንደጎዳቸው ነው። ዱቤ ካልፈረመና ካልፈቀደ ውጭ አገር ሄዶ መሮጥ ስለማይቻል፣ አትሌቶች ከቀደመው ማናጀራቸው ለቀው ወደ ዶናዶኒ እንዲዛወሩ በይፋ ይጠየቁ ነበር። ይህ የሚሆነው እሱ ከአንድ አትሌት ከማሸነፊያ፣ ከስፖንሰር፣ ከመግቢያና ከሰዓት ክፍያ የሚያገኘው የውጭ ምንዛሬ እንዲጨምር ብቻ ነው። በዚህ መነሻ ጥያቄውን ያልተቀበሉ ከብሄራዊ ቡድን ተቀንሰዋል። እንዳይመረጡ የተደረጉ አሉ። ውድድር የተከለከሉ ብዙ ናቸው። በዚሁ ግፍ ተማረው አገር ጥለው የኮበለሉ ብዙ ናቸው። ፈቃደኛ በመሆናቸው ደግሞ ያለ አግባብ የተጠቀሙ ጥቂት አይደሉም። እንግዲህ ሚዲያው የሚጮኸው እኚህን ሰው ድጋሚ የፌዴሬሽኑ ፐሬዚዳንት ለማድረግ ነው። እንግዲህ በዚህ መልኩ ነው የተበላሸውን ውጤት ለመታደግ እየተሮጠ ያለው።
የዱቤና የደራርቱ ጉዳይ ብዙ ነው። ቢዘረዝሩት መጽሃፍ ይሆናል። እንደነ ሲፋን ዓይነት ትንታግ ሯጮች አገር ጥለው የሄዱት እነሱ ጭምር ጣታቸውን በሚቀስሩበት የስራ አስፈጻሚ ውሳኔ በሚፈጸም በደል መነሻ ነው። ሲፋን ስንት ሜዳሊያ ነጠቀችን? ለዚህ የዳረገን ማን ነው? ይህ ወንጀል አያስጠይቅም ወይ? ሲፋን ብቻ አይደለችም ብዙ ናቸው ኦሊሞፒካ ዓላም ዋንጫ ላይ እያለቀስን ያየናቸው…. ይህ ሁሉ ወንጀል ሲፈጸም ደራርቱም ሆነች ዱቤም አሉበት። ከአምባገነን ካድሬዎችና የውጭ ምንዛሬ ሲለቅሙ ከነበሩ ነጋዴዎችና የጊዜው ባለጠጋዎች ጋር አብረው ለፈጸሙት ጥፋት ይቅርታ አልጠየቁም። ፍትህ ያዛቡባቸውን የሙያ ባልደረቦቻቸውን በግልጽ “አፉ በሉን” አላሉም። ስም በመጥቀስ ብዙ ማለት ይቻላል።
ደራርቱ ደጋፊ ያሰባሰበች ካድሬ በመሆኗ፣ ከላይ እንደተገለጸው “ይዞ መገኘት” በሚለው መፈክር የተመረዘ የሚዲያ መኖሩ ችግር ስላልፈጠረባት እንጂ ከስፖርቱ አካባቢ በግዞት መገለል የነበረባት ሰው ነበረች። በብዙ ምክንያቶች እሷና ዱቤ ጅሎ አትሌቲክሱን በከፋ ደረጃ ለመበደላቸው ኃይሌ፣ አሰፋ መዘገቡ፣ ስለሺ ስህን፣ጌጤ ዋሚ፣ ገዛኸኝ አበራ / የዛሬን አያድረገውና/ ብርሃኔ አደሬ፣ መሰረት ደፋር / አቴንስ ኦሊምፒክ/ እልፍነሽ አለሙ ወዘተ ገሃድ መናገራቸውን በመረጃ የምናውቅ እናውቃለን። እነሱም አይክዱም። እንዲሁም ከውድድር የታገዱ፣ የተሰደዱ፣ ውድድር የተከለከሉ፣ በዘር ሳቢያ የተገለሉ፣ በአድልዎ ከምርጫ የወጡ፣ በርካታዎች ምስክር ናቸው።
ከዱቤ ጅሎ ጀርባ ማን አለ?
ለዚህ ጽሁፍ አቅራቢ ሚስጢር ያይደለው ሚስጢር ኃይሌ ከዱቤ ጀርባ መሆኑ ነው። ኃይሌ ከሩጫ ታሪኩና ገድሉ ባልተናነሰ ከሰራቸው ትልልቅ ተግባራት መካከል “ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያን” መመስረቱ ነው። ልክ እንደ አንድ አገራዊ እሴት የሚቆጠር ሃብትም ነው። ለዚህ ይመስላል ከፋና ጋር ያለውን ውል ሰርዞ የዘንድሮውን ውድድር ከኢቲቪ ጋር ለመስራት ሲስማማ ባለስልጣናቱ “አገራዊ ፕሮጀክት ነው በጥንቃቄ ይሰራ” በሚል መመሪያ ያወረዱት። በዚሁ መመሪያ መሰረት ከውድሩ ቀን አንድ ወር በፊት የኢቲቪ ሰዎች ድርጅታቸው ከተከፈለው አንድ ሚሊዮን ብር በላይ በታላቁ ሩጫ ቢሮ በመመላለስ ሲሰሩ የነበረው።
ይህ ታልቅ ግብረስናይ ድርጅት ሲቋቋም አትራፊ ስላልነበር ቀረጥም ሆነ ማናቸውንም የግብር ክፍያ አይከፍልም ነበር። ኃይሌ የዚያን ጊዜ መስመር ረግጧል። የረገጠው መስመር አደገኛ ነው። መረጃው ያላቸው አደገኛነቱን ያውቃሉ። “አትራፊ ያልሆነ ድርጅት ነው” በተባለው ታላቁ ሩጫ ኃይሌ ከብር እስከ ውጭ ምንዛሬ ሲያርስበት እንደነበር የድርጅቱን የውጭ አካውንቶች የግድ ማየት አይስፈልግም። ይህ ለመሆኑ ዱቤ ጅሎ በቂ መረጃ ያካፈላቸው አሉ። ሌሎችም የድርጅቱ ተቀጣሪዎች የነበሩ መረጃውን ጠንቅቀው ያውቁታል። እናም ዱቤ ወደ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለመመለስ ኃይሌ ድጋፍ እንዲያደርገለት ሲጠይቅ “እሺ” የተባለው በዚህ አግባብ አይደለም ማለት አይቻልም።
ጊዜውን በውል ማስታወስ ባልችልም ብሶት የወለዳቸው አትሌቶች ተሰባስበው ለመብታቸው የሚከራከር የአትሌቶች ማህበር አቋቁመው ነበር። ሊቀመንበር ያደረጉት ኃይሌን ሲሆን አሰፋ፣ ስከሺ፣ ጌጤ፣ ገዛኸኝ፣ ብርሃኔ፣ ፋቃዱ የስራ አስፈሳሚ አባላት ሆነው ጊዜያዊ ቢሮ ዓለም ሲኒማ ውስጥ ከፍተው ነበር። ፍትህ ሚኒስቴር ተመዝግቦ ህጋዊ የሆነው ማህበር አራራት በተቋቋመና ይፋ በሆነ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ኃይሌ ፌዴሬሽን ተጠራ። ማህበሩን ካላፈረሰ ታልቁ ሩጫ ዙሪያ ባሉ ጉዳዮች እርምጃ እንደሚወሰድና አለ አግባብ የተከናወኑ ተግባራት ይፋ እንደሚሆን ሲገለጽለት በበነጋው ፈቃዱን መልሶ ማህበሩን እንዳፈረውሰው በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ማንበቤን አስታውሳለሁ። እናም የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን ውክልና ውዝግብ ተከትሎ ከገኘሁት መረጃ ጋር ገጠመልኝ። ዱቤ ጅሎ!!
አዲስ አበባ ዱቤ ጅሎን ትቶ ስለሺ ስህንን በፕሬዚዳንትነት ለመወዳደር ሲያቀርብ የቴክኒክ ኮሚቴው ውስጥ ሁሉም አንፈርምም ያሉት ኃይሌ በቀጥታ ጣልቃ በመግባቱ ነው። በዚሁ መነሻ ስለሺ ወደ ኦሮሚያ ለማምራት ተገዷል። ይህ ከፓሪስ ኦሊምፒክ መከፈት ቀደም ብሎ የተጀመረው የ”ውጤቱ አሳሰበን” ሽፋን ያለበት ውዝግብ መነሻውም መዳረሻውም ደራርቱን አስወግዶ ገብረ እግዚአብሄር ገብረማሪያምን ለመተካት ነበር። ይህም ሲሆን ኃይሌ ሂሳብ ነበረው። ዱቤ የመጣው በውስጥ ለውስጥ የአዲስ አበባን ድምጽ ገብሬ እንዲወስድ ታስቦ ነበር። ዱቤን ” ያው የምችለውን አደረኩልህ” በሚል ሂሳብ ለማጃጃል እና ዝምድናን “ሞክሬያለሁ” በሚል ታቤላ ለመጠበቅ … ይቅር!!
የኦሊምፒክ ኮሚቴ ጉዳይ በፍርድ ቤት የተያዘ በመሆኑ ብዙ ባይባልለትም፣ እስከ ሎሳንጅለስ ድረስ መቀጠሉ የማይቀር በመሆኑ አሁን ላይ መነታረኩ አይበጅም። እንደውም የሚበጀው ዶክተር አሸብር “በቃኝ” እንዲሉ ጾም ጸሎት በማወጅና መማጸን ብቻ ነው። ይህ ንግግር ህግ ለሚያውቁ ይገባቸዋል። በጥላቻና በፍቅር የሚሆን ነገር የለም። ቀደም ሲል ህግ ሲያረቁና ሲያጸድቁ፣ ሆቴል ሰጥተው ሲደንሱ የነበሩት እነ ኃይሌም ሆኑ ሌሎች ሁሉም ሃቁን ያውቁታል። ዓላማቸው አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን አፍርሰው መስራት ነውና ድራማው እዚህ ጋር ያበቃል።
ሸራተኖች የሚዲያ ቡድን አላቸው። ምንም ነገር አያስጨንቃቸውም። የሚነካካቸውን “ጃስ” ያስብሉበታል። ከተፈጠረው ጉዳይ ጋር የማይዛመድ ዘመቻ ይከፍቱበታል። የግል ህይወት፣ የቤተሰብና ሌላም ጉዳይ እየተመዘዘ እንደ ዶፍ ስም ማጥፋት ይወድበታል። ተከፋዮች ኪሳቸው በሚሞላበት መጠን ስም ያጨቀያሉ። ሌሎች ፈርተው በመሻማቀቅ እንዲኖሩ ያደርጋሉ።
ስም ማጥፋትና ማቆሸሽ ብቻ አያበቃም። ከዛም አልፈው አረቄ ጠግበው ” ይደረግ” ብለው ይማማሉበታል። ከራሩ በዱላ፣ ካልራሩም እስከወዲያኛው ያስቀጫሉ። የባለስልጣባት ችግር የለባቸውም። ህግና ፍትህን ከአገሪቱ ባንኮች በተበደሩት ብድር ያናገራሉ። በእዳ ባከማቹት ሃብት ፍትህን ጭጭ ይሰቅሏታል። እነዚህ ቡድኖች ግብር በመክፈል፣ ጨዋ ግብር ከፋይ ሆነው ለትወልድ አርዓያ የመሆን ቅንጣት አሳብ ስለሌላቸው በዝና፣ በዘፈን፣ በሙገሳ፣ በሳንቲም ድጎማ ሰው ሆነ ይታያሉ። ግን አይደሉም። ዕርም የከበባቸው፣ በግፍ የደነደኑ፣ ክብረ ነክ ተግባራት ሁሉ የተዋሃዱዋቸው፣ ፈጣሪን የዘነጉ በፈጣሪ ስም የሚያምታቱ ለምድ ለባሾቹን ዓይነቶች ናቸው።
አሁንም በስፖርቱ ቤት እየሆነ ያለው ይህ ነው። ሮጠው ብቻ ሃብታም እንደሆኑ እንድናስብ የሚያደርጉን ክፍሎች፣ በባንክ ብድር አናታቸው ድረስ የተዘፈቁ ናቸው። ጨዋ ግብር ከፋይ ሆነው አናያቸውም። በጨዋ ግብር ከፋይነት አርዓያ ሆነው ፊት ሲቀመጡ አንታዘብም። ብልጭ ድርግም በሚሉ ጥቃቅን ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር በበጎ ተግባርም ቢሆን ተሳታፊ ሆነው አናይም። ለተችገሩ አንሶላ ሲያለብሱ የሚያሳይ ቪዲዮ የላቸውም። የአንድ ድሃ ጎጆ ቆርቆሮ ሲያለብሱ ሰምተን አናውቅም። የሚያምርባቸው ይህ ሆኖ ሳለ ዝናቸውን እየቆጠርን እንድናመልካቸው፣ እንድንሰግድላቸው፣ አይነኬ መሆናቸውን እንድናስብ በሸራተን ቅጂ መሮጥ መርጠዋል። እንደ አቅማቸው ሚዲያ እየደጎሙ “ገንዘብ ሲናገር” ዜማ እያዜሙ ነው። ነገ ከነገ ወዲያ ልክ እንደ ሸራተን አውሬዎች ማስቀጨት እንደማይጀምሩ ማረጋገጫ የለም። ይህ አካሄድ አያዋጣም። ብዙ የሚታዘቡ ሰዎች አሉ። ብዙ እውነቱን የሚረዱና የሚጠይቁ ዜጎች አሉ። በማህበራዊ ሚዲያ ከሚጮሁት በላይ በርካታ ሚዛን ያላቸው ይጠይቃሉና ጠንቀቅ ማለት ደግ ነው። መንግስትም የሚርመጠመጡ ኃላፊዎችህን ቃኝ!!
ሞገስ ተፈራ ቃሊቲ ዝግጅት ክፍሉ – ይህ ጽሁፍ የጸሃፊው አሳብ ብቻ ነው