የተቃዋሚ ፓርቲዎች ኮከስ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ አሰራጭቷል። የኮሪደር ግንባታን “ቀለም ቅብ” በማለት፣ የአገራዊ ምክክሩን በማጣጣል፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮችን ዘርዝሮ በማውገዝ የተሰራጨው መግለጫ፣ የአፍሪቃ ቀንድን፣ የህዳሴ ግድብንና የኢትዮጵያን የወደብ ፍላጎትም ወርፏል። መንግስት ጦርነትን የመግዣ ስልት አድርጎ እንደሚጠቀምም አስታውቋል። ሙሉ መግለጫው ከስር ያንብቡ
ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ኮከስ (ኮከስ) በወቅታዊ ሁኔታ ላይ የተሰጠ መግለጫ
የብልጽግና መንግስት ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ የአገራችን ፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ተጨባጭ ሁኔታዎች ከዕለት-ወደ ዕለት ‹‹ ከድጡ ወደ ማጡ›› በሚያስብል ደረጃ ለሁለንተናዊ ምስቅልቅሎሽ እየዳረጉን ነው፡፡ ፖለቲካችን የተለመደውን የአፈናና አግላይነት፣ የአንድ ፓርቲ የበላይነትና ጠቅላይነት አጠናክሮ ቀጥሏል፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከአጃቢነት፣ ህዝብ ከአገልጋይነት ያለፈ የፖለቲካ መብታቸውን የማንሳት ህገመንግስታዊ መብት ተገፎ፣በወንጀል ተቆጥሮባቸው ሰጥ-ለጥ ብለው እንዲገዙ ተፈርዶባቸው በከፍተኛ ድብርት ውስጥ ናቸው፡፡
ኢኮኖሚያችን ወደ ጦርነት ኢኮኖሚ ተሸጋግሮ ለተለያዩ የልማት መሰረተ ልማት አውታሮች ሊውል የሚችል የዓመታዊ በጀታችን ከፍተኛው ድርሻ ለጦርነትና ጸጥታ ማስከበር ግብዓቶች እንዲውል፣ልማትና ዕድገት ከቀለም-ቅብ ያለፈ መሰረት እንዳይኖረው ተገደናል፣ የኑሮ ውድነቱ ከህዝብ አቅም በላይ ሆኖ ምሬትና ተስፋ መቁረጥ በአደገኛ ሁኔታ የመሰደድን ምርጫ እያጎላው መጥቷል፡፡ ማኅበራዊ ህይወታችን በሥራ አጥነት፣መፈናቀል፣የማኅበራዊ ተቋማት መዳከምና የአገልግሎት መቋረጥ ወይም መቀንጨር፣ የሠራተኞች ብሶት መገለጫቸው ከሆነ ውሎ አድሯል፤ በየአቅጣጫው የሚነሱ ጥያቄዎችም የሚያረጋግጡት ይህንኑ ነው፡፡ ከትምህርትና ጤና አገልግሎት ተቋማትና ሠራተኞች የሚሰማው ጩሄት በእጅጉ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ይህንኑ ለህዝብ፣ ለመንግስትና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚያቀርቡ የሲቪል ማኅበረሰብ ፣የመገናኛ ብዙሃን፣ የሰብዐዊና ምግባረ ሰናይ ተቋማት ድምጻቸውን የማሰማትና ዓላማቸውን ለማስፈጸም በነጻነት መንቀሳቀስ መብታቸው ከጥያቄ ውስጥ ገብቷል፡፡
በአጠቃላይ የህዝቡን ኢኮኖሚ አቅም ማዳከም፣ የማኅበራዊ ግንኙነት መሥመሮችንና ተቋማትን በመበጠስ ማፈናቀልና በዘር/ቋንቋና ሃይማኖት በመከፋፈል፣ በትብብር፣መከባበርና መተሳሰብ በተቃራኒ በጥርጣሬና ጥላቻ እንዲተያይ የማድረግ አካሄድ፣ እነዚህንና ሌሎች ተፈጥሮኣዊ ልዩነቶችን ለፖለቲካ በማዋል ህዝብን በመከፋፈል ለተገዢነት በማዘጋጀትና ማመቻቸት ላይ መሆኑ የገዢው ፓርቲ ድንበር ተሻጋሪ የአደባባይ መታወቂያው ሆኗል፡፡ በዚህ ተጨባጭ ሁኔታ ውስጥ ብልጽግና ‹‹ከተጨፈኑ ላሞኛችሁ›› አካሄዱ አልተላቀቀም፤ይልቁንም ሽግግር በሌለበት ስለሽግግር ፍትህ፣ከመለያየትና መከፋፈል አጥፊ፣ አፍራሽና አጫራሽ ፕሮፖጋንዳ ባልተላቀቀበት ህዝብን ለግጭት እያነሳሳ ባለበት፣ለመወያየትና ድርድር ቁርጠኝነት በሌለበትና ከመገዳደል ወደ መደራደር ፖለቲካ ለመሸጋገር ወገቤን ባለበት ስለ ምክክር ኮሚሽን አብዝቶ ይደሰኩራል፡፡ ይሁን እንጅ ከባዶ የፕሮፖጋንዳ ድስኩሩ ውጪ ያለውን እውነታ ስንመረምር የሚከተሉትን በግልጽ መረዳት የሚያስችል ተጨባጭ ሁኔቶችን እናገኛለን፡፡
1)ግጭትና ጦርነትን እያስፋፉ- የይስሙላ አግላይ የምክክርና ውይይት ስብከት- ላም ባለዋልበት ኩበት ለቀማ መንከራተት፤
በአገራችን ሁሉም ክልሎች ማለት በሚያስደፍር በተለይ ደግሞ በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ትግራይ፣ ሱማሌና አፋር ክልሎች በደቡብና ምዕራብ የአገራችን ክፍሎች በክልሎች መካከልና በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ውስጥ ጤናማውንና ዘመን ተሻጋሪ ግንኙነት እያፈረሱ የጥላቻና ጥርጣሬ መንፈስ እየቀሰቀሱ ህዝብን በፈጠራ አፍራሽ ፕሮፖጋንዳ ለጦርነትና ያለመረጋጋት እየቀሰቀሱ የፖለቲካና የግንኙነት ችግሮቻችንን በውይይት፣ምክክርና ድርድር ስለመፍታት ‹መስበክ ከአልኩ ባይነት› ያለፈ ትርጉም የሚሰጥ አይደለም፡፡ በዚህ ዓይነቱ በመንግስትና ህዝብ መካከል ያለውን የእምነት ሚዛን የሚያዛንፍ አካሄድ የሚሊዮኖች ህይወት በተቀጠፈበት፣ ሚሊዮኖች የተፈናቀሉበት፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ትምህርታቸውን ባቋረጡት፣ ሚሊዮኖች የማኅበራዊ አገልግሎት ባጡበት፤ በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር ለወቅታዊና አስፈላጊ ልማት የሚውል አንጡራ ሃብት በሚጋይበት እውነታ ውስጥ እያለን በሺ ዓመትም ‹‹አታሸንፉኝም›› በማለት እየፎከሩ ‹እንመካከር› ማለትም ሆነ ‹በእኔ ሥር ሆናችሁ እንደራደር› ማለት ከባዶ ፕሮፖጋንዳ ያለፈ ትርጉም የለውም፤ ለማይጠቅም የፖለቲካ ፍጆታ ካልዋለ በቀር ለዘላቂ ሠላምና መረጋጋት ቁርጠኘኝነትን አያመለክትም፡፡ በመሆኑም መንግስት/ገዢው ፓርቲ ከማስመሰል ተላቆ ራሱንና የአገሪቱን የፖለቲካ መድረክ ለሁሉን አካታችና አሳታፊ ተዓማኒና በባለድርሻ አካላትና አስፈጻሚዎች ተቀባይነት ያለው ሃቀኛ የምክክር ፣ድርድር ፣ውይይት መድረክ እንዲያመቻችና ሽግግሩ በመጨናገፉ የቀጠለውና የተስፋፋው ጦርነት በአስቸኳይ እንዲቆም እንጠይቃለን፡፡
የፖለቲካ መብት ጥያቄ አፈናውና በጋራ ምክር ቤት ሥም አሰልቺው የመድብለ-ፓርቲ ፕሮፖጋንዳ ፤
በአገራችን የሥልጣን ጥያቄ በሠላማዊና ዲሞክራሲያዊ ትግል ይሆን ዘንድ የገዢውን ፓርቲ ጨምሮ ጉዳዩ ያገባናል በሚል የተደራጁ የፖለቲካ ኃይሎች በመሰረታዊ አገራዊ አጀንዳዎች ዙሪያ በትብብርና በመነጋገር የጋራ መድረክና አሰራር በማበጀት ለመንቀሳቀስ ያቋቋሙት የጋራ ምክር ቤት በምስረታው ከተቋቋመበት የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ማጠናከር ዓላማና ተልዕኮ እየራቀ የገዢው ፓርቲ ታዛዥ- ጉዳይ ፈጻሚና አስፈጻሚ እንዲሆነ ከፍተኛ ጫና እየተደረገበት ነው፡፡ ገዢው ፓርቲ በአገሪቱ ያሉትን መንግስታዊ ተቋማት ሙሉ በሙሉ በተቆጣጠረበት የዲሞክራሲና ሠላም ግንባታን ለፈተና የዳረገበትን ተጨባጭ ሁኔታ ላመስተካከልና በሃቀኛ የመድብለ ፖለቲካ ሥርዓትና አሰራር ለመተካት በፈቃደኝነት የመሰረትነው የጋራ ምክር ቤት ከዓላማው ውጪ በመንቀሳቀሱ አካሄዱ እንዲታረምና ምርጫ ቦርድ እንዲሰበስበን ያቀረብነው ጥያቄ ሳይመለስ ዕድሜወን አራዝሞ. ብልጽግናን ያለውድድር ሰይሞና ሌሎችን በምርጫ ሥም አስቀምጦ አዲስ አመራር መምረጡንና፣ደንብ መቅረጹን ለመቀበል እንቸገራለን፡፡ ይህ አካሄድ ከተጨባጭ ሁኔታችን የተሰናሰለ የዘመነ ፖለቲካ አካሄድ ስለሚቃረን ወደተመሰረተለት ቃልኪዳን እንዲመለስ አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡
ኃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን የሚዲያ ህግ በማሻሻል ሥም ማቀንጨርና ተቋማቱን የማፈን እርምጃ፤
ብልጽግና በአደባባይ ኃሳብን በነጻነትና ያለመሸማቀቅ የመግለጽ መብት መከበርን ቢሰብክም በተግባር ግን ህገመንግስታዊ ድንጋጌዎችን በአዋጅ፣በመመሪያና ደንብ እያፈነ ይገኛል፤ በቅርቡ የወጣው የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ ማሻሻያም የዚሁ የአፈና እርምጃ መገለጫ መሆኑን ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው እየገለጹ ነው፡፡ ይህም ለሚዲያ ማዕከላት ከመድረክ መውረድ፣ የሚዲያ ባለሙያዎችን፣የመብት ተቆርቋሪዎችን፣ አክቲቪስቶችንና ፖለቲከኞችን ለሥቃይ፣እስራትና እንግልት ሲያልፍም ስደትና ሞት እየዳረገ ነው፡፡ ይህ ለዲሞክራሲና ዘላቂ ልማት ለአገር ግንባታና ማህበራዊ አገልግሎት መስፋፋትና መረጃ፣ ዕውቀት፣ ልምድና ቴክኖሎጂ ልውውጥና ሥርጭት ከፍተኛ ሚና ያለውን ሠላማዊና ገንቢ ልምምድ የሚያቀነጭር፣የተዋናዮችን ነጻነት የሚያፍን አሰራርና አፈጻጸም በአስቸኳይ እንዲቆም አበክረን እናሳስባለን፡፡
ሽግግር በሌለበት የሽግግር ፍትህ ውዳሴ፤
የህግ የበላይነት መከበርና ነጻና ገለልተኛ ከመንግስት/ የገዢ ፓርቲ ተጽዕኖ ነጻ የሆነ የፍትህ ሥርዓት ግንባታ የዲሞክራሲ ሥርዓታችንና የሠላማችን አስኳል መሆኑ፣ለዚህም ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ሥር ለሰደደው ከእውነታችን ያልተሰናሰለ የፖለቲካ አስተሳሰብ ውርሳችንና ልምዳችን ሽግግር ማድረግ ቢሰበክም በተግባር ግን የተለመደውን ከማስቀጠል አልተላቀቅንም፡፡ ከትናንት እስከዛሬ- የታዋቂ ግለሰቦች- ፖለቲከኞች፣የመብት ተሟጋቾች፣አርቲስቶች፣ጋዜጠኞች፣ አክቲቪስቶችና ንጹሃን ዜጎች ላይ በአደባባይ ለተፈጸሙ የመብት ጥሰቶች ተገቢው ህጋዊ ማጣራት ተደርጎ በአስፈጻሚዎችና ፈጻሚዎች ፍትሃዊ እርምጃ ባለመወሰዱ ደመ-ከልብ በመሆናቸው በገቢር ‹‹እኔን ያየህ ተቀጣ›› መልዕክት አስተላለፉ እንጂ ፍትህ አልተሰጣቸውም፡፡
የመንግስት ባለሥልጣናትና የተለየ ሃሳብ ያንጸባረቁ የምክር ቤት አባላትና የገዢው ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮችም ከዚህ በትር አላመለጡም፡፡ ለዚህ በመንግሥት አደራጅነት የሚቋቋም የሽግግር ፍትህ ተቋም ከዚህ በፊት ከተቋቋሙትና ያለውጤትና ሪፖርት ከተበተኑት ኮሚሽኖች የተለየ ውጤት አይጠበቅም፡፡ በተጨማሪ መደበኛ የመንግስት አስተዳደር ወቅት ተግባራዊ ያልተደረገ የፍትህ ሥርዓት በሽግግር ፍትህ አሰፍናለሁ ማለት ከቧልት ያለፈ ስሜት አይሰጥም፡፡ ስለሆነም ለአካታች፣ አሳታፊና ተዓማኒ የሽግግር ሂደትና ተቀባይነት ያለው ህጋዊ የፍትህ ሥርዓት እንዲዘረጋ፣እንዲተገበርና ሠላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
የሰብዐዊ መብት ተሟጋቾችና የዲሞክራሲ አጋሮች – እየተበረታቱ ወይስ እየተሸማቀቁ ፤
የሠብዐዊ መብት ተከራካሪዎችና ጠበቃዎች እንዲሁም የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አቀንቃኞችና ጋዜጠኞች ስለምን በህዝብ ላይ የምንፈጽመውን በደልና ግፍ ትከታተላላችሁ፣ለዓለም ህዝብ ታስተጋባላችሁ፣…በሚል አመራሮችና ሠራተኞቻቸው ለሌላው ዋስ ጠበቃ መሆናቸው ቀርቶ ራሳቸው መስክ በወጡበት ሲገደሉ፣ሲታሰሩ፣ሲሳደዱና ሲሰደዱ፣ቢሮዎቻቸው ሲታሸጉና ንብረቶቻቸው ሲወረሱና ሲዘረፉ፣በጥቅሉ ለሥቃይና መከራ፣ ለእንግልትና ወከባ ሲዳረጉ እየታዘብን ነው፡፡ ይህን ሁሉ መከራና ስቅይት አድርሶ ‹‹ይቅር ብያችኋለሁ›› በማለት አድንቁኝና አወድሱኝ ከሚባልበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፣ አልፎም ይቅርታ ብናደርግም አልተሻሻላችሁም በማለት ማስፈራራት በተግባር ሲፈጸምም ተመልክተናል፡፡ በዚህ አሸማቃቂና አፋኝ እውነታ የሰብዐዊ መብት መከበርም ሆነ የዲሞክራሲ ልምምድ በቅርብ ርቀት የሚታይ አልሆነምና ባለድርሻ አካላት ለሰብዐዊ መብት መከበር እንዲረባረቡ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
ለፈተና የተዳረገው የአጎራባች አገሮች፣ የአፍሪካ ቀንድ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲና ግንኙነት፤
አገራችን ከጎረቤት እስከ ዓለምአቀፍ መድረክ የንግድና ልማት፣ የፖለቲካና ዲፕሎማሲ፣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትና በድንበርና ሉዓላዊነት ጉዳይ ግንኙነት ታደርጋለች፡፡ እነዚህም በወደብና የባህር በር ባለቤትነትና ተጠቃሚነት፣በድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ላይ በሚገነቡ ግድቦች- በአሁኑ ጊዜ የኅዳሴው ግድብ፣ የሠላምና መረጋጋት ጉዳይ በሚመለከት ከጎረቤት አገራት- ኤርትራ፣ ሱዳን፣ ሱማሊያ ጋር ያለው ወቅታዊ ሁኔታ፣ በአካባቢያችን የሚታዩት የአሻባሪ እንቅሰቃሴዎች፣ ከዓለም ንግድ ድርጅት እስከ መገበያያና ዓለም አቀፍ የኃይል አሰላለፍ መስመር በሙሉ የዚህ ማሳያዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ግንኙነቶች በድምር ሲመዘኑ በጥልቅ ያልተጠኑና ያልተተነተኑ፣ በጊዚያዊ ሁኔቶች የሚዘወሩና ዘላቂ ስትራቴጂካዊ ዓላማና ግብ ያላገናዘቡ በመሆናቸው ለፈተና የተዳረጉና አደጋ የተጋረጠባቸው ናቸው ማለት ያስደፍራል፡፡ ስለዚህ ማንኛውም አካባቢያዊ/ቀጠናዊ፣ አህጉራዊም ሆነ ዓለም አቀፋዊ የውጪ ግንኙነታችንና ዲፕሎማሲያችን በየዘርፉ በባለሙያ ዝርዝር ጥናቶች ላይ የተመሰረተና የአገርን ዘላቂ ጥቅም፣ ልማትና ሉዓላዊነት፣ የህዝብን መብትና ክብር፣ ያገናዘበና የሚያስከብር እንዲሆን በአንክሮ እናሳስባለን፡፡
የመድብለ ፓርቲና ብዝሃ አስተሳሰብ ወይስ በአምባገነናዊነት የተቀፈደደው የፖለቲካ ምህዳር፤
ዕለት ከዕለት የገዥው ብልጽግና አምባገነዊነትና አማቂነት እየጎላና እየተበራከተ ነው የመጣው። የፖለቲካ ምህዳሩ እየጠበበ መጥቶ ተኮማትሯል።በተቃዋሚነት የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች ነፃነትና ሊጫወቱ የሚችሉት ሚና በመግለጫዎች እንዲወሰን ተደርጓል። ሠላማዊ ሠልፍ ለመጥራት መዘጋጀት፣ህገመንግሥት የሚፈቅደው መብት ሆኖ ሳለ- ያሳስራል፣ ለከፋም ጉዳት ይዳርጋል። የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮችና አባላት፣ ገዥዎችን የማያወድስ ወይም ጉድለቶቻቸውን የሚጠቁም ዜና ወይም ትችት ያቀረቡ ጋዜጠኞች ላይ አፈና፣ድብደባ፣ ዛቻ፣ማስፈራራት፣ ዘወትራዊ ሆነዋል። በርካቶች ታስረው ይማቅቃሉ። የፖለቲካ ድርጅቶች ሃሳብ መለዋወጫ እንዲሆን የመሠረቱትን የጋራ ምክር ቤትን ብልጽግና ቀስ በቀስ በስልታዊውና በሚታወቀው የኢህአዴግ አካሄድና ዘዴዎች አሽመድምዶታል። ህወሓት መር የነበረው ኢህአዴግ ይሠራቸው የነበሩት ዕመቃዎች፣ጥሰቶች፣ተንኮልና ደባዎች፣አስርጎ የማስገባትና የመከፋፈል ሤራዎች፣አሁን በወራሹ ብልጽግና ደምቀውና ጎልተው ያለድብብቆሽና ይሉኝታ እየተደገሙ ነው። ይህ የፖለቲካ ምስቅልቅል ለማን ይበጃል፣ ከመጠፋፋት ውጭ ምን ያስገኛል?!ብለን ስንጠይቅ ምላሹ ‹‹ ለማንም አይበጅም፣ ማንንም አይጠቅምም ›› የሚል ነውና መንግስት ከዚህ አፍራሽ አካሄዱ እንዲታቀብና በህገመንግሥታዊ የኃላፊነትና ተጠያቂነት ሥርዓት እንዲሰራ እንጠይቃለን፡፡
ዜጎችን ለመፈናቀል የዳረገ ያልተጠና ግብታዊ ‹ልማት› ፣
በገዥው የብልጽግና ፓርቲ ሹመኞች፣ ሃላፊነት በጎደለው ፍላጎትና ውሳኔ፣ በዋና ከተማችን ‹የኮርደር ልማት› በሚል የተጀመረው የመኖሪያና ንግድ ቤቶችንና ህንጻዎችን በማፍረስ ህዝብን በማፈናቀል ለከፍተኛ ማኅበረ-ኢኮኖሚ ቀውስና ለጎዳና ተዳዳሪነት አጋልጧል፡፡ ይህ ኅብረተሰቡንና ባለድርሻ አካላት ተሳትፎና ከፖለቲካ ገለልተኛ ሙያዊ ጥናት ውጪ የሚደረገው ዜጋ አሰቃይ እርምጃ ወደ ክልል ከተሞች እየተዛመተና ሥቃዩን በመላ አገሪቱ እያዳረሰ ነው፡፡ በሂደቱ የንግድ ቤቶች ትምህርት ቤቶች፣ ክሊኒኮችና የጤና ተቋማት፣ ቤተ-ዕምነቶች ፈርሰዋል። ግቡ ለቀጣዩ ምርጫ የቅስቀሳ ግብዓት መሆኑ እየተገለጸ ያለው ይህ ‹የኮርደር ልማት› በገዥዎች የረጅም ጊዜ አብሮነታቸውና ማኅበረ-ኢኮኖሚ ቁርኝታቸው የማይፈለገውን የማኅበረሰብ አባላት ማፈናቀልና መበተን ስለሆነ ሥራው ያለምንም ተጠያቂነት፣ በማናለብኝነት መንፈስ፣ በጥድፊያ እየተካሄደ ነው። የፈረሱትን ማቋቋምና የቅድሚያ ቅድሚያ የሚጠይቁ በርካታ የመሰረተ ልማት ፍላጎቶችንና ጥያቄዎችን ወደ ጎን በማለት ውዱን የአገርና ህዝብ ሃብት ከመንገድ ማስፋትና፣ ህንጻ መቀባትና ሣር መትከል አልፎ ለቤተመንግሥት ግንባታ ጭምር እየዋለ መሆኑ ለዜጎች ህይወትና ኑሮ ደንታ ማጣት- ኢሰብዐዊነት ነው፡፡
ይህ የአገርን ዘላቂና ቀጣይነት ያለው ልማት ቅድሚያ ትኩረትና የዜጎችን ህይወት ያላገናዘበ አካሄድ በአስቸኳይ ተገትቶ ወደህዝብ ፍላጎትና አገራዊ አንገብጋቢ ሠላምና ዘላቂ ልማትና ጥቅም እንዲዞር እንጠይቃለን፡፡
የአገራችን ከነባራዊ እውነታው የተወለደውን ተጨባጭ ፖለቲካዊና ማኅበረ-ኢኮኖሚ ተጨባጭ ሁኔታ እንደሚከተለው ማጠቃለል ይቻላል፡፡
በህዝብ መካከል የተገነባውንና ከትውልድ ትውልድ በቅብብሎሽ ሲሸጋገር የመጣውን የመተሳሰብ፣መከባበር፣ መረዳዳትና ለተለያዩ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዓላማ የመደራጀትና አብሮነት ስሜት በዜጎችና ህዝብ መካከል የተዘራው የጥላቻ፣አለመተማመን፣ ጥርጣሬና ክፋት የጥፋት ዘር አራሙቻ እየበላው ጤናማ የህዝብ-ለህዝብ ግንኙነት ለጥያቄ ተዳርጓል፡፡ የአጥፊ የተበዳይነት ፕሮፖጋንዳው በሰረጸባቸውና ሰለባ ባደረጋቸው አካባቢዎች ግጭቶችና ጥፋቶች እየተስተዋሉ ሲሆን በቀጣይም የማይሽር ጠባሳ እንዳያስከትል ለከባድ ሥጋት ዳርጓል፡፡ ይህ አስቸጋሪና አሳሳቢ ክስተት ከፖለቲካ ልዩነት ተሻግሮ በገዢው ፓርቲ አባላት መካከልም መስተዋሉ ጉዳዩን የበለጠ አሳሳቢ አድርጎታል፡፡ ከዚህ የውስጥ ችግር ባለፈም ከአጎራባች አገራትና ከዓለምአቀፍ ማኅበረሰቡም በተለያዩ ጉዳዮች ያለን በጥናትና ጥልቅ ምልከታ ይልቅ በግልብ ስሜት ላይ የተመሰረተው የማኅበራዊ፣ የንግድና ኢኮኖሚያዊ፣እንዲሁም የልማትና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በግብታዊነትና ጠባብና አጭር ቅርብ-አዳሪ ምልከታው ከወዳጅነት ለጥርጣሬ ዕይታ ዳርጎን ዘላቂ ሠላማዊ የትብብር ጤናማ ግንኙነት ላይ ከባድ ፈተና ጋርጦብናል፡፡ በመሆኑም መንግስት የውስጥ ግንኙነታችንም ሆነ ከውጪ ጎረቤቶች አጋሮች፣ ወዳጆችና ዓለምአቀፍ ማኅበረሰብ ጋር ያለን ግንኙነት የተጠናና በዘላቂ ጥቅምና ሠላም ፣ ተቀባይነት፣ የድጋፍና ትብብር ስሌት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን አበክረን እናሳስባለን፡፡
በመጨረሻም አገሪቱ ከገባችበትና ካለችበት እጅግ አሳሳቢና ፖለቲካዊ ማህበረ-ኢኮኖሚ ምስቅልቅል እንድትወጣ፣ በየአቅጣጫው ከሚሰማውና ህዝባዊ የህልውና ጥያቄ፣ከሚታየው የትጥቅ ትግል መፍትሄ ለመስጠት ተኩስ ቆሞ ሃቀኛ፣ሁሉን-አቀፍ፣አሳታፊ፣ብሄራዊ መግባባትና ዕርቅ ለማውረድ ተዓማኒ ውይይት/ምክክርና ድርድር እንዲደረግ የፖለቲካ ኃይሎች፣ባለድርሻ አካላት፣ ህዝቡና ዓለምአቀፍ ማህበረሰብ በመተባበር እንደየድርሻቸውና ሚናቸው እንዲረባረቡ ጥሪ እናደርጋለን//
ጦርነትን እንደ መግዣ ሥልቱ የሚጠቀም መንግሥት የሠላምና ልማት ጠንቅ ነው//
የተቃዋሚ ፓርቲዎች ኮከስ ( ኮከስ)
ታህሳስ 09 /2017 ዓ.ም ፣ አዲስ አበባ፤