በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀፅ 49 ላይ ባል እና ሚስት መከባበር፣ መተጋገዝ እና መደጋገፍ እንዳለባቸው እና ይህን ግዴታቸውን በሚያደርጉት ስምምነት ሊያስቀሩት እንደማይችሉ ይደነግጋል። ይህ ማለት አንደኛው ተጋቢ ሠርቶ ገቢ ማግኘት የማይችል ሆኖ በሚቸገርበት ጊዜ በቤተሰብ ህጉ በአንቀፅ 210(ሀ) መሰረት ሌላኛው ተጋቢ እንደ አቅሙ ለኑሮ አስፈላጊውን ወጪ የመሸፈን (ቀለብ የመስጠት ግዴታ) አለበት ማለት ነው። ጋብቻው በሞት ቢፈርስ አንኳን በጋብቻ ዘመዳሞች መካከል ያለው ቀለብ የመስጠት ግዴታ ይቀጥላል፡፡ ሆኖም ጋብቻው በፍቺ ወይም ሕገ-ወጥ በመሆኑ በፍርድ ቤት ውሳኔ ከፈረሰ በጋብቻ ዘመዳሞች መካከል ያለው ቀለብ የመስጠት ግዴታ በቤተሰብ ሕጉ አንቀፅ 199 መሠረት ቀሪ ይሆናል።
መግቢያ
ቀለብ የመስጠት ግዴታ በኢትዮጵያ ማሕበራዊ መስተጋብር የቆየ ባሕላዊና ሀይማኖታዊ እሴት ሲሆን አስገዳጅነት ኖሮት በሕግ ከመደንገጉ አስቀድሞም የማህበረሰቡ ባህል አካል ሆኖ ቆይቷል። በሥራ ላይ ያሉት የፍትሐብሔርና የወንጀል ሕጎቻችን ድንጋጌዎች ለጉዳዩ አፈፃፀም ህጋዊ መሰረት እንዲኖረው አድርጓል። በዚህ ጽሁፍ ስለቀለብ ምንነት፣ ቀለብ ስለሚገባቸው ሰዎችና ቀለብ የመስጠት ግዴታ ስላለባቸው ሰዎች ማንነት፣ ቀለብ የሚሰጥበትን ሁኔታና ቀለብ የመስጠት ግዴታውን በማይወጣው ሰው ላይ ስለሚኖር የሕግ ተጠያቂነትና በአጭሩ እንመለከታለን።
ቀለብ ለሚለው ቃል የተሰጠ ቁርጥ ያለ የሕግ ትርጉም የለም። ይሁን እንጂ በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 197 ጠቅላላ አንድምታ በመነሳት “አንድ ወይም ብዙ ሰዎች በሕግ በተቀመጠው የሥጋ ወይም የጋብቻ ዝምድናቸው መሠረት ወይም በሟች በሚሰጥ የኑዛዜ ቃል ተጠቃሚ ለሆነ ሰው ወይም ሠርቶ ለኑሮው አስፈላጊ የሆነውን ገቢ ለማግኘት አቅም ለሌለው በችግር ላይ ላለው ቀለብ ጠያቂ እንደ ቀለብ ሰጪው እና ተቀባዩ ሁኔታ እና እንደ አካባቢው ልማድ የሚስማማውን በመከተል ለምግብ፣ ለመጠለያ፣ ለልብስ፣ ለጤናው መጠበቂያ እና እንደ ሁኔታው ለትምህርቱ አስፈላጊ የሆነውን ነገር የመስጠት ግዴታ ነው።
ቀለብ ስለሚገባቸው ሰዎች
ከላይ እንደተገለፀው ቀለብ የሚሰጠው ለኑሮው አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ማሟላት ለማይችል ሰው ነው። ማንኛውም ሰው በችሎታው የመተዳደር መብት ቢኖረውም በተለያዩ ምክንያቶች ይህን መብቱን ተጠቅሞ የእለት ጉርሱና ልብሱን ማሟላት የሚያዳግተው ሰው ይኖራል። በቤተሰብ ሕጉ አንቀጽ 201 መሰረት ቀለብ የመስጠት ግዴታ ተፈፃሚ የሚሆነው ቀለብ ጠያቂው ሠርቶ ለኑሮው አስፈላጊ የሆነ ገቢ ለማግኘት አቅም የሌለውና በችግር ላይ የወደቀ ሲሆን ብቻ ነው። ገቢ ለማግኘት አቅም የሌለው ሰው የሚባለው በእድሜው ለጋነት ወይም በእርጅና ወይም በጤና ጉድለት ምክንያት ሠርቶ መተዳደር አለመቻልን ያመለክታል። ቀለብ መስጠት የግድ የሚለውም ይህን መሰል ሰው ለመርዳት ይሆናል። የሚሰጠው ቀለብ መጠንና አይነትም ቢሆን እንደሕጉ አነጋገር እንደ ባለጉዳዮቹ ሁኔታና እንደ አካባቢው ልማድ የሚስማማውን በመከተል ለቀለብ ተቀባዩ ምግብ፣ መኖሪያ፣ ልብስ፣ ጤናውን የሚጠብቅበትና እንደሁኔታው ለትምህርት አስፈላጊ የሆነውን ነገር ለማሟላት ያህል እንደሆነ ከሕጉ አጠቃላይ ድንጋጌ መገንዘብ ይቻላል።
ቀለብ የመስጠት ግዴታ ስላለባቸው ሰዎች
ቀለብ የመስጠት ጉዳይ ማሕበራዊ እንድምታ ያለው እንደመሆኑ መጠን፣ የዝምድና ትስስርንና ሌላ ማህበራዊ ግንኙነትን ታሳቢ ያደርጋል። ቀለብ የመስጠት ግዴታ ያለባቸውን የቅርብ ዘመዶች ደግሞ የቀለብ መብት ያለው ሰው ባል ወይም ሚስት፣ የሥጋ ዘመዶቹና የቀጥታ የጋብቻ ዘመዶቹ ተብለው በ3 ተከፍለው የሚታዩት ዘመዳሞች ይሆናሉ።
ባል ወይም ሚስት
በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀፅ 49 ላይ ባል እና ሚስት መከባበር፣ መተጋገዝ እና መደጋገፍ እንዳለባቸው እና ይህን ግዴታቸውን በሚያደርጉት ስምምነት ሊያስቀሩት እንደማይችሉ ይደነግጋል። ይህ ማለት አንደኛው ተጋቢ ሠርቶ ገቢ ማግኘት የማይችል ሆኖ በሚቸገርበት ጊዜ በቤተሰብ ህጉ በአንቀፅ 210(ሀ) መሰረት ሌላኛው ተጋቢ እንደ አቅሙ ለኑሮ አስፈላጊውን ወጪ የመሸፈን (ቀለብ የመስጠት ግዴታ) አለበት ማለት ነው። ጋብቻው በሞት ቢፈርስ አንኳን በጋብቻ ዘመዳሞች መካከል ያለው ቀለብ የመስጠት ግዴታ ይቀጥላል፡፡ ሆኖም ጋብቻው በፍቺ ወይም ሕገ-ወጥ በመሆኑ በፍርድ ቤት ውሳኔ ከፈረሰ በጋብቻ ዘመዳሞች መካከል ያለው ቀለብ የመስጠት ግዴታ በቤተሰብ ሕጉ አንቀፅ 199 መሠረት ቀሪ ይሆናል።
የሥጋ ዘመዶች
ይህ የወደታች ተወላጆችን (ልጅ፣ የልጅ ልጅ)፣ የወደላይ ወላጆችን (እናት እና አባት፣ አያት፣ ቅድመ አያትን) የሚመለከት ሲሆን ቀለብ የሚገባው ሰው የጋብቻ አጋር ከሌለው ወይም ቀለብ መስጠት የማይችል ከሆነ በሁለተኛ ደረጃ ልጆቹ፣ የልጅ ልጆቹ (ተወላጆቹ) ቀለብ የመስጠት ግዴታ አለባቸው።
የወደታች ተወላጅ ከሌለ ደግሞ ወላጆቹ፣ እነሱ ካልቻሉ አያቶቹ እያለ ቀለብ መስጠት የሚችሉ እስካሉ ወደ ላይ ይቀጥላል። ቀለብ የሚገባው ሰው ከላይ የዘረዘርናቸው ዘመዶች ከሌሉት ወይም ቢኖሩም ቀለብ መስጠት የማይችሉ ከሆኑ ደግሞ ወደ ጎን የሚቆጠር የሥጋ ዝምድና ያላቸው ወንድም እህቶቹ በአራተኛ ደረጃ ግዴታ እንዳለባቸው የቤተሰብ ሕጉ በአንቀፅ 210(መ) ላይ ደንግጓል።
የጋብቻ ዘመዶች
የቀለብ ጠያቂው ባል ወይም ሚስት ከሌላ የወለዷቸው የእንጃራ ልጆች፣ ልጅ ልጆች (ተወላጆች) በአምስተኛ ደረጃ ለእንጀራ አባታቸው ወይም እናታቸው ወይም አያቶቻቸው ቀለብ የመስጠት ግዴታ ተጥሎባቸዋል። በቅደም ተከተሉ በመጨረሻው የስድስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ደግሞ አማቾች (የባል ወይም የሚስት ወላጆች፣ አያቶች…) ናቸው።
ብዙ ቀለብ ሰጪዎች ያሉት ቀለብ ጠያቂ ከመካከላቸው አንደኛቸውን መጠየቅ ይችላል። በቀለብ አሰጣጡ ላይ ክርክር ከተነሣ የቀለብ ሰጪውን የዝምድና ቅርበት እና የገቢ መጠኑን በማየት ፍርድ ቤቱ በቤተሰብ ሕጉ አንቀፅ 209(1) መሠረት በሙሉ ወይም በከፊል ቀለቡን እንዲሸፍን ሊወሰን ይችላል።
ሌላው በዚህ ርእሰ ጉዳይ መጠቀስ ያለበት የጉዲፈቻ ዝምድና ከቀለብ አሰጣጥ አንጻር የሚኖረው ተፈጻሚነት ይሆናል። የጉዲፈቻ ውል የተፈጥሮ ልጅ ያለውን መብት እና ግዴታ በጉዲፈቻ ተደራጊው እና በጉዲፈቻ አድራጊው መካከል የሚፈጥር ስምምነት ነው። ቀለብን በተመለከተ ግን በቤተሰብ ሕጉ አንቀፅ 212 መሠረት ጉዲፈቻ የተደረገው ልጅ፣ ባል ወይም ሚስት ወይም ተወላጆቹ የጉዲፈቻ አድራጊውን ቤተዘመዶች ከላይ በጠቀስነው ቅደም ተከተል መሠረት ቀለብ መጠየቅ ይችላሉ። ሆኖም እነኝህ የጉዲፈቻ ቤተሰቦቹ ቀለቡን መስጠት ካልቻሉ ብቻ የተፈጥሮ ወላጆቹን ቤተዘመዶችም ቀለብ የመጠየቅ ሁለተኛ ዕድል አላቸው። የጉዲፈቻ ልጅ የተፈጥሮ ወላጆቹ፣ አያቶቹ፣ ቅድመ አያቶቹ (የወደ ላይ የሚቆጠሩ ወላጆቹ) ከዘመዶቻቸው አንዱን ቀለብ ለመጠየቅ የማይችሉ ካልሆኑ በስተቀር በጉዲፈቻ የሰጡትን ልጅ ቀለብ መጠየቅ አይችሉም።
ከላይ የተመለከቱት የሕግ ወይም የስጋ ዝምድና ሳይኖር በሌሎች ማህበራዊ ግንኝነቶችም ቀለብ የመስጠት ግዴታ ሊኖር ይችላል። ይኸውም በፍትሐብሔር ሕጉ የተለያዩ ድንጋጌዎች የሚገኝ ሲሆን በተለይም ከስጦታ፣ ውልና በኑዛዜ የሚሰጠውን ቀለብ የማግኘት መብት ማስታወስ ያስፈልጋል። ለምሳሌ በፍትሐብሔር ሕጉ ቁጥር 2458 እንደተመለከተው በግልጽ የተነገረ የውል ቃል ባይኖርም ስጦታ ሰጪው በድኅነት ላይ ወድቆ ሲገኝ ስጦታ ተቀባዩ ለሰጭ ቀለብ መስጠት ግዴታ አለበት፡፡ ሰጭ እንደመረጠ ቀለቡን እርሱ ስጦታ ካደረገለት ሰው ወይም ሕግ ለርሱ ቀለብ ለመስጠት ግዴታ አለባቸው ከሚላቸው ሰዎች ላይ ለመጠየቅ ይችላል፡፡ በተጨማሪም አንድ ሰው ንብረቱን በውርስ ሲያስተላልፍ ኑዛዜ የማድረግ መብቱን ተጠቅሞ ወራሹ እስከ አገባ ወይም እንደገና እስከአገባ ድረስ የአንድ የተወሰነ ሀብትን ሪም ወይም አንድ የተወሰነ ቀለብ በኑዛዜ ስጦታ የተደረገለት ያገኛል ብሎ ተናዛዡ መወሰን እንደሚችል ከፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 917 መረዳት ይቻላል።
ቀለብ የሚሰጥበት ሁኔታ
ቀለብ የመስጠት ግዴታን መወጣት የሚቻለው ቀለብ ሰጪው ለቀለብ ተቀባዩ የቀለቡን ገንዘብ በመስጠት ነው፡፡ የቀለቡ መጠን የሚወሰነው ቀለብ ጠያቂው ያለበትን ችግር እና የቀለብ ሰጪውን አቅም በማመዛዘን ፍርድ ቤት በሚሰጠው ውሳኔ መሰረት ይሆናል። ይሁን እንጂ ቀለብ ሰጪው ወይም ተቀባዩ በሚያቀርቡት ጥያቄ መሠረት ስለቀለቡ መጠን ወይም ስለቀለብ ተቀባዩ መኖሪያ የተሰጠውን ውሳኔ በማናቸውም ጊዜ ማሻሻል የሚቻል ሲሆን ቀለቡ የሚከፈለው በተቻለ መጠን ለቀለብ ተቀባዩ በሚያመቸው ቦታ ይሆናል፡፡ ይህ ቢኖርም ቀለብ ተቀባዩ ለኑሮው አስፈላጊ መሆኑን ካላረጋገጠ በስተቀር የቀለቡን ገንዘብ መቀበል ካለበት ቀን ጀምሮ በተከታዮቹ ሦስት ወራት ውስጥ ያልተቀበለው ወይም ሳይጠይቀው የቀረ እንደሆነ የተጠራቀመው ቀለብ እንዲሰጠው መጠየቅ እንደማይችል ከቤተሰብ ህጉ አንቀፅ 206 ተደንግጓል፡፡
በሌላ በኩል ቀለብ ሰጪው ቀለብ ተቀባዩን በመኖሪያ ቤቱ ተቀብሎ በማስቀመጥ ቀለብ የመስጠት ግዴታውን ሊፈፅም ይችላል፡፡ ቀለብ ተቀባዩን በመኖሪያ ቤት ተቀብሎ የማስቀመጡ ጉዳይ ክርክር ያስነሳ እንደሆነ ፍርድ ቤቱ የነገሩን የአካባቢ ሁኔታዎች በመመልከት ተገቢ መስሎ የታየውን ይወስናል፡፡ ለቀለብ ተቀባዩ ቀለብ የመስጠት ግዴታ ያለባቸው ሰዎች ብዙ የሆኑ እንደሆነ ቀለብ ተቀባዩ ከእነርሱ መካከል አንዱ ቀለቡን እንዲሰጠው ሊጠይቀው ይችላል፡፡
ቀለብ የመጠየቅ መብት ቀሪ የሚሆንበት ሁኔታ
ቀለብ የማግኘት መብት ቢኖርም በቀለብ ተቀባዩ ያልተገባ ድርጊት ቀለብ የማግኘት መብት የሚታጣበት ሁኔታ ይኖራል። ይኸውም በቤተሰብ ሕጉ አንቀፅ 200 እንደተገለፀው ቀለብ ተቀባዩ በቀለብ ሰጪው ወይም በዚህ ሰው ወደላይና ወደታች በሚቆጠሩ ወላጆች ወይም ተወላጆች ወይም ባል ወይም ሚስት ሕይወት ወይም ንብረት ላይ የወንጀል ተግባር የፈፀመ ወይም ለመፈፀም የሞከረ እንደሆነ ቀለብ የመቀበል መብቱን ያጣል፡፡
ቀለብ የመስጠት ግዴታን አለመወጣት የሚያስከትለው የሕግ ተጠያቂነትና መፍትሔው
በሕግ የታዘዘውን አለመፈጸም ወይም በሕግ የተከለከለውን ድርጊት ፈፅሞ መገኘት በሕግ እንደሚያስጠይቅ ይታወቃል። የተጠያቂነቱ ሁኔታ ደግሞ ፍትሐብሔራዊ ወይም የወንጀል ወይም በሁለቱም ሊሆን ይችላል። በያዝነው ጉዳይ ላይም ሕጉን ተላልፎ የተገኘ ቀለብ ሰጪ ህጋዊ ተጠያቂነት ይኖረዋል።
ስለሆነም በወንጀል ሕጉ አንቀፅ 658 ስር እንደተደነገገው፡-
ማንም ሰው ያለበቂ ምክንያት፡-
በሕግ መሠረት ሊሰጥ የሚገባውን ቀለብ ለባለመብቶች፣ የፍቺ ውሳኔ እስከ ሚሰጥበት ጊዜ ድረስ የፍቺ ጥያቄ ላቀረበ የትዳር ጓደኛም ቢሆን አልሰጥም ያለ ወይም መስጠትን ያስተጓጐለ እንደሆነ ወይም
በሕግ ወይም በውል በገባው ግዴታ መሠረት ከጋብቻ ውጭ ላስረገዛት ሴት ወይም ከጋብቻ ውጭ በግብረ ሥጋ ግንኙነት አብሮት ለኖረ ሰው ወይም ከጋብቻ ውጭ ለተወለደው ልጅ ሊያሟላ የሚገባውን የገንዘብ ግዴታ ያልተወጣ እንደሆነ የግል አቤቱታ ሲቀርብበት በመቀጮ ወይም ከስድስት ወር በማይበልጥ ቀላል እሥራት ይቀጣል፡፡
ከዚህም ሌላ የፌደራል ሰበር ሰሚ ችሎት መጋቢት 14 ቀን 2007 ዓ/ም በፍትሐብሔር ህግ ቊጥር 2458 ለሰጭ ቀለብ የመስጠት ግዴታውን ያልተወጣ የስጦታ ውል ተጠቃሚ በስጦታ ያገኘውን በዚሁ ሕግ ቁጥር 2464 መሰረት ስጦታውን በመሻር ለባለሀብቱ እንዲመልስ ወስኗል[የሰ-መ/ቁ. 107990]።
ማጠቃለያ
በአጠቃላይ በተለያዩ ምክንያቶች ሰርቶ መሰረታዊ ፍላጎቶቹን ማሟላት ላልቻለ ሰው ቀለበ የመስጠት ግዴታ ከማህበራዊ መስተጋብር ባለፈ በህግም የተጣለ ግዴታ እንደመሆኑ በህጉ መሰረት ቀለብ የመስጠት ግዴታ ያለባቸው ሰዎች ግዴታቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይገባል፡፡
በንቃተ ህግ ትምህርትና ስልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ