ሲትየዋ ለቃሉ ይቅርታ በገላዋ የምትተዳደር ቀንና ፖለቲከኞች እድልዋን ያበላሹባት ዜጋ ናት። አንድ ቀን ምንም አልነበራትም። ከሰል አያይዛ የቡና ጀበናዋን ውሃት ትቀቅልበታለች። ቡና የለም። ፈንዲሻ የለም። ቂጣ የለም። ዕጣን አልፎ አልፎ ታጨሳለች። እንዲሁ ውላ ድንገት አንድ ደንበኛዋ ” ሸጌ” ብሎ ዘው አለ።
ሰላምታ ከተለዋወጡ በሁዋላ አምስት ብር ሰጣት። ወጣ ብላ ስትመለስ ቤቱ ቡን ቡና ሸተተ። ፈንዲሻ ተንጣጣ። ዳቦ ተቆረሰ። ይህኔ ደንበኛ በልቡ ” አህያም ካናፋ በኛ ቤት ዘፈን ነው” አለ አሉ። የሰሙ እንዳሉት ” ወግ ወጉ ተይዟል ችግር አንቆ ይዟል” ሲልም አክሏል» ሰየው ይህ ያለው ከአምስት ብር በፊትና በሁውላ የነበረውን የሸጌን ቤት ድባብ አይቶ ነው።
በግድ፣ በባዶ ቂጥ ፈረንጅ የመሆን አባዜ፣ እዛና እዚህ መርዝ እየረጩ ጋላቢዎችን በማስደሰት ትልቅ የመልሰል ቅዠት፣ አረብ የመሆን የበታችነት ስሜትና የተላላኪነት መንፈስ፣ የኢሳያስና የሻዕቢያ መለያቸው ነው። ትህንሽ ነገር ሲገኝ “ሃይላሎ” በከበሮ ” አህያም ካናፋ በኛ ቤት ዘፈን ነው” እንዳለችው ምስኪን!!
መከረኛው የነጮቹ አዲስ አመት ሲቃረብ፣ ፍሬው ድንቁርናና ጨለማ የሆነው ቀን ሲቃረብ፣ ወይም ራሳቸውን ላይችሉ የተገነጠሉበትን ቀን ሲያከብሩ ብቅ እያሉ የሚቃዡት የኤርትራና የሸዕቢያ መሪ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፉወርቂ፣ ሰሞኑንም እንደተለመደው ቀባጥረዋል። ህገ መንግስት ሳይኖራቸው በጨበጣ አደር እየመሩ፣ የሚተችም ቢሆን ህገ መንግስት ያላቸውን ለመተቸት ሲወራጩ ታይተዋል። እሳቸው ያለ አንድ አንቀጽና ህግ ጋላቢዎቻቸው ኤርትራና ምስራቅ አፍሪቃ ላይ ድንኳን ጥለውላቸው እያተራመሱ ጻድቅ ለመምስለ ይውተርተራሉ። ምርጫ፣ ፓርላማ፣ ነጻ ሚዲያ፣ የእምነት ነጻነት የማይታሰበት፣ በተለይም ” ኢየሱስ ያድናል” ማለት እሚያስረሽንባትን አገርና ስርዓት ከነክርፋቱ ተሸክመው፣ሰዎች ያለፍርድ ቤት ታስረው፣ እስር ቤት የሞሞቱባትን አገር መስርተው፣ ምንም እንዳልሆነ፣ እንዳልተፈጠረ አድርገው የሚሰጡት ዲስኩር “ጥርሴስ ልማዱ ነው፣ አይኔን አታስቂው” እንዲሉ ነው። ሃፍረት እሳቸው ቤትና የኢሳቶቹ ታዛዦቻቸው ሰፈር ድርሽ እንደማይል ማሳያም ነው።
ኤርትራ ባለፉት ሰላሳ ዓመታት አምራች ዜጎቿን ከስራለች። አሮጊት ሽማግሌ፣ ልጅ የልጅ ልጅ ሳይቀር በስደት አገር ለቀው የአውሮፓና አሜሪካን ጎዳና ሞልተዋል። የተረፉትም በአገር ቤት ጣታቸውን ቃታ ላይ አድርገው ከመኖር ያለፈ ዕድል እንደሌላቸው በስደት የሚወጡት በገሃድ የሚናገሩት ሃቅ ነው።
መቀመጫ፣ መጋረጃና ምንጣፉ ሳይቀየር ሁለት ሰዎች አስቀምጠው በቴሌቪዥን ያለገደብ የሚያወሩት ኢሳያስ፣ ንግግራቸው፣ ትችታቸው፣ ግምገማቸውና ውሳኔ ሰጪነታቸው ዓለም ላይ ታይቶ የማይታወቅ ድንቅ መሪና ድንቅ አገር የፈጠሩ እስኪመስሉ ነው። ከድንጋይ ዘመን በፊት ባለ እሳቤ የዲጂታል ዘመንን የሚሞግቱት ኢሳያስ፣ በዚሁ በሳሎናቸው ባሰሙት ንግግር ስለ ኢትዮጵያ፣ ስለ ምስራቅ አፍሪቃ፣ ስለ ሱዳን፣ ስለ ዓለም፣ ስለ አሜሪካ አዲሱ ፕሬዚዳንት የለውጥ ሂደት ወዘተ ደስኩረዋል። ትችተዋል። ሊመክሩም ካጃሏቸዋል።
ጥያቄ አንብቦ ጸጥ ብሎ የመስማት እንጂ፣ የመሞገት አሳብም ፈቃደም በማይታሰብበት የወሬ ክፍለ ጊዜ “ኤርትራ በፍፁም ኢትዮጵያ ያለመረጋጋት ውስጥ ገብታ የማየት ፍላጎት የላትም” ሲሉ ኢሳያስ መናገራቸውን ንግግራቸውን ወደ አማርኛ የመለሰው ቢቢሲ ገልጿል። ይህ አስቂኝ፣ ብሎም ለሳቸው ሳይሆን ለኢትዮጵያዊያን አሳፋሪ የሆነው ንግግራቸው የተወሰኑ ጥያቄዎች ለሚያነሱ እንዴት ይወራረዳል? ሲንጋፖርን የመሆን ቅዠት በኢትዮጵያ አንድ ክልልን እንኳን ከመሆን ጋር መወዳደር ወደ ማይችል እውነታ ሲቀየር ያወራጫል እንዲሉ ነው ነገሩ …
በመጀመሪያ “ኤርትራ በፍፁም ኢትዮጵያ ያለመረጋጋት ውስጥ ገብታ የማየት ፍላጎት የላትም” ካሉ ለምን የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ተቃወሙ ብንልዎትስ? ሊያስሩን? ወይስ ሌላ አካል በንዴት ሊያደራጁ? ወይስ ከትግራይ የዘረፉትንና ያዘረፉትን ማንቆርቆሪያ፣ በር፣ ትሪ ቆርቆሮ፣ መስኮት፣ ቲቪ፣ ማብረጃ፣ የከስለ ምድጃ፣ ከብቶች፣ ምን ቅጡ … የፋብሪካ ማሽኖችና የህክምና መሳሪያዊች እንዲሁም የቢሮ ዕቃውፕች፣ መሳሪያና …. ከስምምነቱ በሁዋላ “መልሱ” የሚል የክስ ፋይል የከፈታል ብለው ሰግተው ነው? ልንገርዎ መመለስዎ አይቀርም።
ኢሳያስ የኢሳትን ሰራተኞች አስመራ ካነጋገሩና የዓይን አባት ከሆኑዋቸው በሁዋላ ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ ልክ እንደ እነሱ ይመስላቸዋል። ነገሩ ግን እንደሱ ዓይደለም። እሳቸው በጋላቢዎቻቸው ትዕዛዝና በበታችነት ስቃይ ተነሳስተው ትህነግን አደረጁ፣ ትህነግን አሳብጠው፣ ከወቅቱ የዓለም የስርዓት ለውጥ፣ እንዲሁም እንደነ ሻለቃ ዳዊት ዓይነት ራሳቸውን የሸጡና ሲአይኤ አብረው የኢትዮጵያን ጀነራሎች የበሉት በዚህ ትውልድ ዕድሜ ነው።
እንዲከሽፍ ታስቦና ታቅዶ በተዘጋጀው መፈንቅለ መንግስት (ሻለቃ ዳዊት ሳያስበው ምስክርንርቱ ሲሰሰጥ ሱዳን ሆኜ እከታተለው ነበር ማለቱን ልብ ይሏል) የኢትዮጵያን ምርጥ መኮንኖች እንዲያልቁ ተደርጓል። ሰራዊቱ መሪ እንዲያጣ ተደረገ። በአስመራም የኢትዮጵያ ጀግኖች አስከሬናቸው አደባባይ እንዲጎተት ሲደረግ ጋላቢዎችዎና አሁን ድረስ እርስዎ ነጠላ ጫማ ስር የሚንደባለሉ ለማኞች እጅ እንዳለበት ይህ ትውልድ ያውቃል። ትህነግ ምስጋና ይግባውና የሚመራትን አገር አዋርዶ እንደ እርስዎ ያለውን አቅመ ቢስ፣ ባንዳ አገዘፈዎት እንጂ በባድመ ጦርነት ወቅት በቀናት የከበብዎት ጀግና የዛኔ ይፈጽምዎት ነበር። እድሜ ለመለስ ተረፉ። እንዳይሸወዱ የአሁኑ ግን ” እረ የአሁን ይባስ” የሚያዘፍን ነው። ትንሽ ታገሱ!! የሚበጅዎ ከቅዠት መውጣት ብቻ ነው።
“ኤርትራ በፍፁም ኢትዮጵያ ያለመረጋጋት ውስጥ ገብታ የማየት ፍላጎት የላትም” ሲሉ የተናገሩት ምን ለማለት ፈልገው ነው? ባይባልም፣ ኢሳያስ በፍፁም ኢትዮጵያ ያለመረጋጋት ውስጥ ገብታ የማየት ፍላጎት ባይኖራቸው ኖሮ ገና በረሃ እያሉ ጀምሮ ሲያደራጁ የነበረውን ትተን፣ ስልጣን ላይ ከወጡ በሁዋላ እነማንን ነበር ዛሬ ድረስ ያደራጁብን? ለሚለው ሁሉም ኢትዮጵያዊና ፍትህ ወዳድ ኤርትራዊያን ግልጽና ቀላል መልስ አለው። እርስዎና ጋላቢዎችዎ ናቹህ።
ማን ነው አንዱን ኦነግ አምስት ቦታ ከፋፍሎ ” ሸኔን” የሞሸረበን? ማን ነው የሸኔን ታጣቂዎች ሱዳን በኩል ሲለቅብን የከረመው? አርበኞች ግንባርን ማነው ሲያደራጅና ሲያስታጥቅ የነበረው? ማን ነው ሊሉን ነው? በትግራይ አድርጎ አገር እንዲያተራምስ ትህዴንን መልምሎ፣ አደራጅቶና አስልጥኖ ያበቃው የኢትዮጵያ የጸብ መጥመቂያዋ እስርዎ አይደሉም? ካልሆኑ ኤርትራ ምድር ላይ ያለውንና ይህን ሁሉ የሚፈጽመውን ” የሃይላሎ መንፈስ” ስም ይነገሩን!!
ምን ይህ ብቻ አልሳካ አለ እንጂ ግንቦት ሰባትንም እኮ አደራጅተዋል። ትህነግ “አገር ምራ” ቢባል ክብር ጠልቶ ረክሶ ስላራከሰን በወቅቱ ደገፍን እንጂ፣ እርስዎ ኢትዮጵይ ላይ የሚረጭ መርዝ መጥመቅ የተካኑበትና ” በሃይላሎ መንፈስ” ምሪት የሚወስዱበት ዋና ተግባርዎ እንደሆነ የምንዘነጋ አይምስልዎ። ይህ ትውልድ እኮ “ሰላም ወርዷል መሳሪያ አውርዱ” ከተባሉ በሁዋላ እርስዎ በጅምላ ያስጨፈጨፉቸው የኢትዮጵያ ወታደሮች ቤትሰብ፣ ልጅ፣ ወገን፣ የወንዝ ልጅ እንደሆነ አይዘንጉ። ነገሩ ” ከሞኝ ደጃፍ” እንዲሉ ሆነና ደጋግመው ሞከሩ፣ አሁን ግን ቁርጡ ቀርቧል። እርስዎና ትህነግ ያፈረሳችሁት የኢትዮጵያ ኃይል ዳግም ሁሉንም መረብ በጣጥሶ እያገሳ ነው። ይህን እርስዎ በውል ስለሚያውቁት ዝርዝር አያስፈልገውም።
የኢትዮጵያን ምርት መዝረፍ፣ ዶላር ማጠብ፣ ተደራጅቶ ኮንትሮባንድ ላይ መሰማራታቸሁን አስመልክቶ ድሩ እየተቆራረጠ ቢሆንም ወደፊት እመለስበታለሁ። “ኤርትራ በፍፁም ኢትዮጵያ ያለመረጋጋት ውስጥ ገብታ የማየት ፍላጎት የላትም” ለሚለው ስላቅ ” ያልወለድኩት ልጅ” የሚለውን ተረት አስታውሶኛልና ወደዛው ልመለስ።
“ኢሱ” ብዬዎት አላውቅም። በወቅቱ መንግስት ባዶ ቂጡን ስለነበር “ያዘመርልዎት፣ ወይም አዝማሪ የሆነልዎት” ጊዜ፣ አዲስ አበባ ላይ ሲንጎባለሉ፣ የሲንጋፖርነት ቅዠትዎ ዳግም የለመለመ እንደመሰለዎ ወዳጆችዎ አጫውተውኛል። አስመራ ” ገአት/ ገንፎ” ከጋበዙዋቸው መካከል አንዱ ቅዠትዎ እርስዎ መቃብር ሳይወርዱ እንደማይለቅዎት በብዙ ማስረጃ ነግሮኛል። የልማትና የዕድገት “ህልም” ቢኖርዎትማ ለኤርትራ ህዝብ ስደትን ጠቅልለው እንደ ገና ስጦታ ባለከናነቡ ነበር። እርስዎ እንደ ፍየል ወጠጤ እዛም እዚህም እየዘለሉ፣ በቅዠት ሲንጋፖር በተግባር ኤርትራን ነዎት።
ኢእርስዎ ኢትዮጵያን በክፋት ወስፋት አንጀቷን ፣ በምቀኘት እንደ አልቅት ላንቃዋ ላይ፣ እንደ ቫይረስ መላ ሰውነቷን የሚያግሉ ለመሆንዎ አንድ ማሳያ ልጨምር፣ ኢትዮጵያ በሶማሊያ ሰላም ለማስከበር ልጆቿን ስትገብር እርስዎ ስንት ጊዜ አሸባሪ አስለጥነው ወደ ሶማሊያ ላኩ? በቅርቡ እንኳስ ስንት ጊዜ ሚሊሻ እያስታጠቁ ሶማሊያ አፈሰሱብን? ይህም ይቅር
ከልወጡ በሁዋላ እርስዎ ሚሌኒየም አዳራሽና አራት ኪሎ ሲንጎራደዱ የሻዕቢያ ኤምባሲ ሰዎችና አምባሳደሩ ባህር ዳር ለምን ጉዳይ ነበር ቢሮ የከፈቱ ያህል በየቀኑ ሲመላለሱ የነበሩት? በውቀቱ መንግስት ገና አቅሙ ባለመደርጀቱና እንደመንግስት ለመቆም እየተውተረተረ በመሆኑ እንዳላየ መሰለ እንጂ የባህር ዳሩን መፈንቅለ መንግስት የወጠኑት “ዳውድ ኢብሳ ናቸው” እንደማይሉን እሙን ነው። ቢሉም “አይቼሽ ነው ባይኔ፣ ወይስ በቴሌቪዥን ..” የሚለውን ቅኔ ከመቀኘት ውጭ አማራጭ የለም። ጊዜ ሲገልጸው የአማራ ክልል መሪዎች መቃብር ስር ሊገኙ የማይችልበት ምክንያት የለም። ጊዜ ድኛው !!
ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ያደረገችውን የባህር በር ስምምነት አስመልክቶ እርጅናዎን ረስተው እባብ እነዋጠች ወጠጤ ፍየል እዛና እዚህ ያዘለለዎት፣ የግብጽ ተላላኪና አለቅላቂ የሆኑበት ጉዳይ “ለኢትዮጵያ በጎ እንመኛለን” ከሚለው መርዛማ ንግግርዎ ጋር አብሮ ሲገጥም የሚፈጥረውን ህብረ ቀለም የዚህ ጸሃፊ ሲያስበው ይዘገንነዋል።
እርስዎ በእውን ሊያዩዋት የሚመኙዋት ኢትዮጵያ 130 ሚሊዮን ህዝብ ይዛ የተዘጋች፡፡ የታፈነሽ። የታሸገች፣ የተከረቸመች ሆና እንድትቀር ነው። ኢትዮጵያ በስጋትና በግብር ሃብቷን እየገፈገፈች እንደ እርስዎ ዓመዳም የሆነች፣ ፖለቲካዊ ፋይዳዋ የደበዘዘ፣ የቀይ ባህር ተመልካች ሆና የምትታይ አገርን ሆና እንድተቀር ነው ፋልጎትዎ።
በቅናትና በበታችነት ስሜት ሰሚሰቃዩ ኢትዮያን በርስዎና እግራቸው ስር በሚነደባለሉላቸው ጌቶችዎ ምኞት ወደሁዋላ ለመጎተት ሲፈነቅሉ የነረው ድንጋይ አሁን ላይ እያለቀ ይመስላል። ይህ ደግሞ ዛሬ አይቻልም። “ቀይባህር ላይ ተፈጥረናል፣ ነበርን፣ እንኖራለን” የሚል ትውልድ ተነስቷል። ኢትዮጵያ ይህን እንዳታሳካ አንዴ ሱዳን፣ አንዴ ሶማሊያ፣ አንዴ የመን፣ አንዴ ገዢዎችዎ ግብጾች ዘንዳ እንደ አህያ ቢንደባለሉም መልሱን የሚሰጡ ጀግኖች ስራቸውን እየሰሩ ነው አያስቆሙዋቸውም።
ይህ ሳዘጋጅ ኢንሳን የጎበኙት የእርስዎ ባለስልጣኖች ታወሱኝ። ህንጻው በተጠጉት ቁጥር እታሱ ወለል እያለ፣ ግድግዳው በራሱ እየተፈረሰና እየተሰበሰበ ኢትዮጵያ የደረሰችበትን የአርተፊሻል ኤንተለጀንስ ደረጃ ሲያዩ ” ይህ እውነት ኢትዮጵያ ነው?” ብለው የጠየቁ ሁለት ባርኔጣ ያደረጉ ወኪሎችዎት ጥያቄ ያላችሁበትን መንግስታዊ ቁመና አስረድቶኛል። እንደ ድሮ በሴት፣ በዕድር ፣ በሰንበቴ፣ በማህበርና እምባሻ በሚቆረጥበት ቀናት ላይ የተቸከለ ደህንነትና አቅም ይዞ በዚህ ደረጃ መደስኮር …. ይቅር!!
ለማንኛውም ኦነግ ወደ ሰላም ጠረጲእዛ አምርቶ ሰላም አውርዷል። አማራ ክልልም ችግሩ በቅርቡ በዕርቅ ይፈታል። ዝግፍቱ አልቅቱንና ወስፋቱን ለማጽዳት ነው። ይህ አይቀርም። ከትሀንግ አንዳንድ ልክስክሶች ጋር ለመሻረክ ደፋ ቀና ቢባልም፣ የትግራይ ህዝብ የሆነውን ሁሉ ስለሚያውቅ በባድመ መንፈስ ….
የኢሳያስ ስላቅ – ለግማሽ ምዕተ ዓመት ኢትዮጵያ ላይ ሽፍታ፣ ነጻ አውጪና አኩራፊ ሲያመርቱ ኖረው ” የኢትዮጵያን ስትረበሽ ማየት አንፈልግም” ብለው ከአሁን በሁዋላ ስንቴ ይሸረድዱን ይሆን? የሚበጅዎት ከኢትዮጵያ ጉሮሮ ላይ መላቀቅ ብቻ ነው። ህዝብ እንዴት እንደሚኖር ያውቅበታልና እርስዎ መንገድዎን ካስተካከሉ ቀሪውን ለህዝብ መተው ነው። ሌላውና ወሳኙ ጉዳይ ከሞቃዲሾው የአንድ ጎሳ ወረዳ አስተዳዳሪ ሓሰን ሼኽ ጋር የጀመሩት የእፉኝት ጉዞ ክፉኛ ዋጋ ሳያስከፍልዎት እጅዎን ቢሰብሰቡ ብዬ እመክራለሁ። ወገን የሆነው የኤርትራ ህዝብም ያስብበት። በሁዋላ ተንኩሰው እንደሚያለቅሱት እንዳይሆን!!
ኢሳት ስል ያነሳሁት አሁን ላይ የኢሳያስን አቋም የሚያራምዱና እዛ ድረስ ሄደ ቡራኬ የተቀበሉትን “ነአምናዊያኖቹን” ነው።
በሌላናው ጽሁፌ እንገናኝ – ጽሁፉ የጸኃፊው አቋምና እምነት ብቻ ነው
ሞገስ ወልደጻድቅ
ለሚዛን እንዲረዳ
ቢቢሲ ስለ ኢትዮጵያ ተናገሩ ብሎ የጻፈ ይህን ነው
ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የባሕር በር የማግኘት የመግባቢያ ስምምነት ከተፈራረመች በኋላ ከሶማሊያ ጋር እንዲሁም በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ምክንያት ከግብፅ ጋር አለመግባባት ውስጥ እንዳለች ይታወቃል።
በተለይ ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ መተላለፊያ እንዲሁም ሚና እንዲኖራት ያላትን ፍላጎት ይፋ ካደረገች በኋላ በቀጥታም ባይሆን ኤርትራ ደስተኛ አለመሆኗን ስታሳይ ነበር። በዚህም የሶማሊያው ፕሬዝዳንት አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በኤርትራ ከሦስት ጊዜ በላይ ጉብኝት አድርገዋል።
በተጨማሪም ሶማሊያ ከግብፅ ጋር የወታደራዊ ስምምነት መፈራረሟን ተከትሎ አሥመራ ላይ የተፈረመው የሶስትዮሽ ስምምነት ከኢትዮጵያ አንጻር መሆኑ በተደጋጋሚ ሲነገር ቆይቷል። ነገር ግን የኤርትራው ፕሬዝዳንት ይህንን አስተባብለዋል።
ፕሬዝደንት ኢሳያስ “የውጭ ኃይሎች እና አቀንቃኞች በመገናኛ ብዙኃን እና በማኅበራዊ ሚዲያ የሚያሠራጩት የተዛባ መረጃ እና ዘመቻ በቀጣናው ግጭት ያባብሳል” ሲሉ ኮንነዋል።
“ይህ [በመገናኛ ብዙኃን ላይ የሚሠራጨው] የመነጨው ከልብ ለኢትየጵያ ከማሰብ አይደለም” ያሉት ፕሬዝደንቱ በሦስቱ ሀገራት መካከል የተደረሰው ስምምነት “ዋና ዓላማው በቀጣናው መረጋጋትን ማስፈን” እንደሆነ ተናግረዋል።
የኤርትራ ዋና ፍላጎት “በመላው የአፍሪካ ቀንድ፣ በአባይ ተፋሰስ እና በቀይ ባሕር አጎራባች ሀገራት መረጋጋት እና ትብብር እንዲኖር ነው” ብለዋል ፕሬዝደንቱ።
“ኤርትራ በፍፁም ኢትዮጵያ ያለመረጋጋት ውስጥ ገብታ የማየት ፍላጎት የላትም” ያሉት ኢሳያስ፣ በቀጣናው ሀገራት መካከል የሚደረሱ ስምምነቶች ያለመተማመንን እንዲሚቀርፉ እና ፍሬያማ እንደሆኑ አስምረዋል።