በኦሮሚያ ክልል መንግስትና በኦነግ አመራሮች መካከል የተደረገውን ስምምነት ተከትሎ የሰራዊቱ አባላት ወደ ተዘጋጀላቸው ካምፕ እየገቡ እንደሆነ ታውቋል። ስምምነቱ ይፋ መሆኑን ተከትሎ ቀደም ሲል ” ገዳይ” በማለት ሲከሱትና በሰላማዊ ሰልፍ ሳይቀር ሲያወግዙት የነበረውን ኦነግ መልሰው “ከሃጂ” ማለታቸው፣ ኦነግና ፋኖ ተናበው እንደሚሰሩ ምስክር የመሆን ያህል እንደሆነ እየተገለጸ ነው።
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥትና የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት አመራሮችን ስምምነት ተከትሎ የሰራዊቱ አባላት ወደ ካምፕ መግባት መጀመራቸውን በምስል አስደግፎ ያስታውቀው የክልሉ ብልጽግና ጽህፈት ቤት ነው።
ወደ ካምፕ እየገቡ ያሉት ልዩነትን በምክክር እንጂ በጠመንጃ መፍታት እንደማይቻል ከግንዛቤ በማስገባት በተደረገው ስምምነት አማካኝነት የሰላም ጥሪውን የተቀበሉና በተለያዩ አካባቢዎች ሲንቀሳቀሱ የነበሩና በጃል ሰኚ የሚመራው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት አባላት ናቸው።
ጃል ሰኚን ባለፈው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት አመራር የነበሩት ያላቸው ዜና፣ ባለፈው ሳምንት እሁድ የሰላም ስምምነት መፈረሙ አስታውሷል።
በዚህ ስምምነት መሰረትም የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አባላት ወደ ተዘጋጀላቸው ካምፕ እየገቡ መሆኑን በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት መረጃ አመላክቷል።
ወደ ኤርትራ ሲያቀና አንድ አመራርና መዋቅር የነበረው ኦነግ ኤርትራ ውስጥ ራሱን አምስት አድርጎ ወጣ። አቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመሩት አምስተኛው ክፋይ፣ በኦሮምኛ “ሸን” ወይም አምስትን እንደ መለያው አድርጎ “ኦነግ ሸኔ” መባሉ አይዘነጋም።
ኦነግ ሸኔ አዲስ አበባ የሚቀመጥ የፖለቲካ ክንፍና፣ ጫካ ገብቶ የጠብ መንጃ ትግል የሚያካሂድ ኃይል ሆነው መከፈላቸው ቢነገርም በርካቶች አይቀበሉትም ነበር። ያም ሆኖ ጫካ ያለው ኃይል ራሱን “የኦእሮሞ ነጻነት ሰራዊት” በሚል ስያሜ ጠርቶ ጦርነት ከጀመረ በሁዋላ ቆይተው የአሰላለፍ ልዩነት እንዳላቸው ይሰማ ጀመር።
ይህ ሁሉ ሲሆን በተቃውሞ ጎራ የተሰለፉ መገናኛዎች ስለ ልዩነታቸው ሳይሆን ” ሸኔ ገዳይ ነው” በሚል ነበር ሲያራክሱት የቆዩት። በግፍ ለተገደሉ የአማራ ተወላጆች ግንባር ቀደም ተግጠያቂ የተደረገው ሸኔ፣ በጅምላ ግድያ የተከሰሰውን ያህል ሁለት ቦታ መከፈሉ ሲቃወሙትና ሲያራክሱት ለነበሩት ክፍሎች ለወሬነት እንኳን የሚበቃ ጉዳይ አልሆነም።
“ገዳይ” በሚል ተፈርጆ ሲወገዝ ከነበረው ሸኔ አንደኛው ወገን (በጃል ሰኚ) የሚመራው ” በሰላም ለመነጋገር ዝግጁ ነኝ” ሲልም እነዚህ ክፍሎች ሞትን ሲዘግቡ በነበረበት መጠን ቀርቶ የእግረ መንገድ መረጃ ያህል እንኳን ሽፋን አለመስጠታቸው ” እነዚህ ሰዎች ለየትኛው ወገን ነው የሚቆረቆሩት” የሚል ጥያቄ አስነስቶ ነበር።
ጃል ሰኚ በሰላም መነጋገር እንደሚፈልጉ ባስታወቁት መሰረት በይፋ ከጃል መሮ ተለይተው፣ በገሃድ ህዝብ እያየ ከኦሮሚያ ፕሬዚዳንት ጋር የሰላም ስምምነት ፊርማ ሲያኖሩ ” ግድያ ባይቆምም ይቀንሳል። ተመስገን” ከማለት ይልቅ ” የጨረቃ ስምምነት ተደረገ” በማለት ከጮሁት መካከል መሳይ መኮንን ቀዳሚው ነው።
መሳይ የአስተያየት መስጫ ሳጥኑን ቆልፎ ያሻውን በሚለጥፈበት የፌስ ቡክ ገጹ “ዛሬ ሽመልስ አብዲሳና ጃል ሰኚ የጨረቃ ስምምነት አድርገዋል። በሚቀጥሉት ቀናት ወይም ሳምንታት ባህር ዳር ላይ ተመሳሳይ ነገር እንደሚኖር ሹክ ተብለናል። የብልጽግና ፋኖ ከአረጋ ከበደ ጋር ድል ባለ ድግስ ፋኖ ከመንግስት ጋር የሰላም ስምምነት ተፈራረመ የምትል ዜና ከአሚኮ ዋና ማዘዣ ጣቢያ ለብሄራዊ ቴሌቪዥኖች ይበተናል። ጥቃቅንና አነስተኛ የብልጽግና ሚዲያዎች ያስተጋቡታል። በቅርቡ ባህርዳር ላይ ‘የጨረቃ ስምምነት’ እንደሚኖር ከግምት በላይ መናገር ይቻላል። ሟች በመጨረሻው ሰዓት ያንቀዠቅዠው ነበር ያለው ማን ነው? ” ሲል ስጋት፣ ንዴት፣ ለቀጠሩት ክፍሎች ታማኝነቱን ለመግለጽ የተላላጠበትን አስፍሯል። ሌሎችም በተመሳሳይ ስምምነቱን ተቃውመዋል። መሳይ የጋበዛቸው እንግዳም ጃል ሰኚ ኦነግን እንደማይወክል ገልጸው መሳይን አስደስተውታል።
መሳይ አማራ ክልል ሰላም ቢነግስ ምን አስጨነቀው? ምን አስፈራው? ምንስ አስቀድሞ ለቅሶ ደራሽ አደረገው? ሌሎችም ልክ እንደመሳይ ይህ ስምምነት ለምን አናደዳቸው? አማራ ክልል በጨረቃም ይሁን በጠራራ ጸኃይ፣ በጨለማም ይሁን በብርሃን ሰላም ቢያገኝ የሚከፉ እውን ኢትዮጵያዊ ስሜት አላቸው? ለማን ነው የሚሰሩት? አማራ ክልል ሰላም ቢሆን ኢትዮጵያ ምን ልትሰራ እየተዘጋጀች እንደሆነ ስንቶች ገብቶናል? ቢግባን ኖሮ ለማክሸፍ የሚደረገው የቅጥረኞች ርብርብ ወለል ብሎ በታየን ነበር።
“ሻምቡ፣ ወለንጪቲ ዙሪያ፣ ፊንጫና አንገር ጉቲን ሂዱና ህዝብ አነጋግሩ፣ ቢያንስ ሃምሳ ከመቶ ወደ እውነት ትደርሳላችሁ” በየቀበሌው፣ በየሰፈሩ ዱካ እየቀያየሩ ንጽሃንን የሚዘርፉ፣ የሚያገቱ፣ የሚያፍኑና የሚገድሉ አካላት አንዳንዴም ፖለቲካዊ ተልዕኮ አላቸው ብሎ መቀበል እንደማይቻል የሚገልጹ ” ህዝብን ምሬት ውስጥ ለመክተት የተደራጁ ተከፋይ ገዳዮችና አፋኞች ናቸው፣ አለያም የራሳቸውን አደረጃጀት ፈጥረው አፈናና እገታን ስራ ያደረጉ የማፍያ ቁጥቋጦ ናቸው” ይላሉ። …..
ይህን ያንብቡ የጠራ ሰእል ያገኛሉ
ከስምምነቱ ሳምንት በፊት ወለጋ ከህዝብ ጋር በተደረገ ስብሰባ ላይ አቶ ሸመልስ አብዲሳ
“ጽንፈኛ” ያሉት ኃይልና ሸኔ ያላቸውን መደጋገፍና ጥምረት እንዲሁም እንዴት አብረው እንደሚሠሩ አራት ነጥቦችን ጠቅሰው አስረድተዋል። ከስምምነቱ በሁዋላ የተሰማው ጩኸትና እሪታ ይህንኑ የሚያረጋግጥ ምስክር እንደሆነ ንግግሩ ያደመጡ እየገለጹ ነው። ፋኖ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ሲንቀሳቀስ ሸኔ በአራት መንገዶች ድጋፍ እንደሚያደርገለት ገልጸዋል።
፩ኛ- ሸኔ ሕዝቡን ትጥቅ ያስፈታል፤ ሕዝቡ ለራሱ መከላከያ ያለውን መሣሪያ በየቤቱ እየዞረ ሸኔ እየነጠቀ ሕዝቡን ባዶ ያደርጋል።
፪ኛበየቀበሌና ወረዳ ያለውን መዋቅር ማፍረስ፤ ይህ በተከታይ የሚደረግ ነው፤ ትጥቁን የፈታ ሕዝብ የቀበሌ መዋቀሩ ሲፈርስበት ጠባቂ አይኖረውም፤ ለጥቃት የተጋለጠ ነው። ሲጋለጥ የሚደርገው ይታወቃል።
፫ኛ፤ በየቦታው ሸኔ ጥቃት በሚፈጽምበት ጊዜ ጥቃቱን ለመከላከል የመንግሥት ኃይል ወደ ቦታው ሲንቀሳቀስ ፋኖ መንገድ ላይ ጠብቆ ጥቃት ያደርሳል። ይህ በተለያዩ ቦታዎች ማለትም በጊዳ፣ ሀሮ ሊሙ፣ አሙሩ ዳጋምሣ፣ ወለጋ ሆሩ፣ ወዘተ ቦታዎች የታየ ተግባር ነው። ትጥቁን የፈታውን ሕዝብ ለመታደግ በሚመጣው የመንግሥት ኃይል ላይ ጥቃት ይሰነዘራል
፬ኛ፤ ሸኔ ጽንፈኛው ኃይል ላይ የትም ቦታ፣ መቼም፣ አንድም ቀን ምንም ዓይነት ጥቃት አይሠነዝርም፤ ጽንፈኛው
ኃይልም በተመሳሳይ ሸኔ ላይ አይተኩስም። እንዲያውም መሣሪያ ይቀባበላሉ፤ መረጃ ይለዋወጣሉ፤ ራሳቸውን ከእርስ በርስ ጥቃት ይጠብቃሉ።
“ሸኔ ማለት የጭን ቁስል ነው” የሚሉ ወገኖች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ አቶ ሽመልስ ያሉትን የሚጋሩት ” ግድያ ሲታቀድ፣ ሲፈጸም፣ ከተፈጸመ ደቂቃዎች በሁዋላ በሚዲያ ሲረጭ፣ ያለው መስተጋብር ነገሩ በጥምረትና በመናበብ የሚሰራ ለመሆኑ ጥርጥር እንደሌላቸው በመግለጽ ነው።
በመሰረቱ በኦሮሚያ በተለይም ወለጋ ውስጥ የሚኒሩ ወገኖች ከዚህ ሰላም እንደሚጠቀሙ እይታወቀ ቢያንስ ማድነቅ ቢያቅት፣ ዝም ማለት ያልተቻለው ቁማሩ፣ የደም ንግዱ ሌላ ዓላማ ስለለው ብቻ ነው። በተጠቀሰው አካባቢ የሚኖሩ ዜጎች ዕረፍት ማግኘታቸው የቀደመው ጩኸት ከልብ ቢሆን ኖሮ ባስደሰተም ነበር።
ለማጣጣል የተሞከረው ስምምነትና የምናውቀው ዕውነት
በመጀመሪያ ኦነግ ውስጥ መከፋፈል የተለመደና የድርጅቱ ልዩ ታሪኩ ነው። ሌንጮ ለታ፣ አባ ቢያ፣ ከማል ግለቾ፣ ገላሳ ዲልቦና ዳውድ ኢብሳ ሆኑም የኦነግ ባለ “አክሲዮን” ናቸው። ሁሉም የየድርሻቸውን ይዘው ኦነግ ናቸው። ከኤርትራ ወደ አዲስ አበባ ከመጡ በሁዋላ እንደ ዳውድ ሁለት ቦታ ተከፈሉ። አንደናው ወገን ጦርነት ይብቃ ባይ መሆኑን ተናገኦ ተለየ። እነ አቶ ዳውድ ዋና ወራሽ መሆናቸውን ቢያስታውቁም የተከፈለው አካል የያዘውን ይዞ ወጣ። አቅማቸውን ወደ ሃረርጌ ወረድ ብሎ ማየትና በዛ ባለው አንሳራዊ ሰላም መለካት ይቻላል።
እንግዲህ የኦነግ ወርቃማ ታሪክ መከፋፈል፣ ከመከፋፈል ውስጥ ደግሞ ሌላ ስንጣቂ እየሆኑ መራባት ከሆነ እነ ጃልመሮና ጃል ሰኚ ቢለያዩ ምኑ ይገርማል? ጃል ሰኚም የያዙትን ይዘው፣ ጃል መሮም የያዙትን ይዘው ቢለያዩ አንዱ ሌላውን ” ኦነግ አይደለህም” ብሎ ሚኖሶታ ሆኖ ፈቃጅና ነሺ እንዴት ሊሆን ይችላል? መስንተቅ የድርጅቱ ወግ አይደለም እንኳን ቢባል፣ የጠበንጃ ትግል በምርጫ ቦርድ የሚታወቅ ሰርተፊኬት ስለሌለው በምን ማስረጃ ነው አንዱን አቅፎ ሌላውን መግፋት አግባብ የሚሆነው? ለመሆኑ የተከፈሉትን ወገኖች አቅም በአመራር፣ በኦፊሴር፣ በአዋጊ መኮንንና በሌሎች መመዘኛዎች የትኛው ወገን ነው መዝኖ ደረጃ ሊሰጥ የሚቻለው?
እስከምናውቀው ድረስ ጃል ሰኚ ከጃል መሮ በላይ ቁልፍ ሰዎችን ይዘዋል። አዋጊ ኦፊሰሮችና የበላይ አመራሮች ሙሉ በሙሉ ማለት እስከሚቻል ድረስ ከጃል ሰኚ ጋር ናቸው። ይህን እውነት በቅርቡ በሚለቀቅ ዘጋቢ ፊልም ላይ የምናየው ይሆናል። በነገራችን ላይ ከጃል መሮ ጋር ከቀሩት ውስጥ በሰላም ለመግባት ንግግር የጀመሩም አሉ። ይህም በቅርቡ ጸሃይ የሚወጣ ሃቅ ስለሆነ ” የጨረቃ ስምምነት ቁጥር ሁለት” ለማለት ከወዲሁ ተዘጋጁ።
ግድያ ፣ ዘረፋ፣ መፈናቀል፣ ልጆቹ ትምህርት መማር አቅቷቸው፣ ኪሊኒክና ጤና ጣቢያ ተዘግቶበት ህዝብ ተማሯል። ዛሬ የመሳይም ሆነ የሌሎች ጩኸት ለሚስቶቻቸውና ለሚቀልቧቸው ካልሆነ በስተቀር ሰሚ የለውም። ጎንደር ምስክር ናት። ዛሬ ጎንደር ኮሽ የሚል ነገር የለም። ይህ ይቀጥላል። ልብ ያላቸው ተደራጅተው ብልጽግና ውስጥ የተሰገሰጉትን የቀደመው መንፈስ ተሸካሚዎች በካርድ ለመዘረር ከወዲሁ ቢዘጋጁ አገር ጥሩ ልምምድም ትለማመድ ነበር። ቀይ ባር ላይ መንሳፈፊያዋ ቀንም ይቀርብ ነበር።