ፈረንሳይ ወታደራዊና የባህር ኃይል መልሶ ለማደረጃት ከኢትዮጵያ ጋር ውል ያሰረቸው ለውጡ ተከትሎ ነበር። በ2019 ፈረንሳይ የባህር በርዋን በግፍና በወቅቱ “መሪዎቿ” በነበሩ አካላት እንድታጣ ከተደረገችው ኢትዮጵያ ጋር ይህን ስምምነት ስታደርግ የዓለም ታላላቅ ሚዲያዎች ዜናውን በከፍተኛ ፍጥነት ተቀባበለውትም ነበር።
“ይህ ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቀው የመከላከያ ትብብር ስምምነት ማዕቀፍ የሚያካትተው…በተለይም የኢትዮጵያን የባህር ኃይሏን ዳግም ለማቋቋም የጀመረችውን እንቅስቃሴ ፈውረንሳይ እንድትረዳ መንገድ ከፍቷል።” ሲሉ ነበር ከጠቅላይ ሚኒስይትር አብይ ጎን ሆነው መግለጫ ሲሰጡ ይፋ ያደረጉት። ይህ የዛሬ አምስት ዓመት የታሰረው ውል ከትህነግ ጋር ተፈጥሮ በነበረው ጦርነት ሳቢያ ዓለም ሚዛኑንን ስቶ ኢትዮጵያ ላይ ሲረባበርብ ተግብራዊ እንዳይሆን እንቅፋት ሆኖ ነበር። በዚህም ሳቢያ የመርከብ ግዢው ለጊዜው እንዲቆም መደረጉ አይዘነጋም።
ስትራቴጂካዊ፣ ጂኦፖለቲካዊ የፀጥታ እና ኢኮኖሚያዊ ስጋቶች የተደቀኑባት ኢትዮጵያ፣ የባህር ሃይሏን ዳግም ለመገንባት ስራ መጀመሯን ይፋ ስታደርግ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ግንባር ቀደም የሚባል የአየር ኃይል እንደምትገነባ ተናግረው ነበር። አሁን ላይ በሚወጡ መረጃዎች ኢትዮጵያ በአፍሪካ በድሮን ብዛት አራተኛ መሆኗ ብቻ ሳይሆን ማምረትም መጀመሯ ነው። ከዚህም በላይ በቅርቡ ከቻይና የዓለም ዘመናዊ የሚባሉ ድሮኖች ባለቤት መሆኗም ተሰምቷል። ከፈረንሳይ ጋር በተደረገው ስምምነት 500 የሚደርሱ የባር ላይ የጦር መሃንዲሶችና አንድ ሺህ የሚጠጉ ከፈተኛ መኮንኖችን ለማብቃት ነበር። የኢትዮጵያ ጂኦፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እና በዓለም አቀፍ የየውሃ ህግ መሰረት የቀይ ባህርን ውሃ የመጠቀም መብቷን ተጠቅማ ጠንካራ የባህር ሃይል መገንባቷ ይፋ የሚሆንበት ጊዜ መቃረቡን ተከትሎ የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ለሁለተኛ ጊዜ አዲስ አበባ መገኘታቸው ጉዳዩን ከዜና በላይ አድርጎታል።

በይፋ አልተገለጸም እንጂ የጦር መርከብ ግዢውና ኢትዮጵያን ዘመናዊ የጦር መርከቦች ባለቤት በሚያደርገው ውል ዙሪያ ዳግም ስምምነት መደረጉን ኢትዮሪቪው ሰምታለች። በዚሁ መሰረት በቀደመው ስምምነት ኢትዮጵያ የጦር መርከብ ትረከባለች።
ኢማኑኤል ማክሮን ዝርዝር ውስጥ ባይገቡም ይህንኑ ጉዳይ አስታከው ” የባህር በር መኖር አስፈላጊነት ፤ ለወደፊት ያሉትን ነገሮች ማመቻቸት መቻል ትክክለኛ ጥያቄ ነው ” በማለት ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጋር በጉዳዩ ላይ መወያየታቸውንና እሳቸው ይህ እውን እንዲሆን አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።
በቅርቡ ከሶማሊ ላንድ ጋር የባህር በር ለማግኘት የመስማሚያ ሰነድ ሲፈረም “አቅጣጫ ማስቀየሪያ ነው” በሚል የደቦ ዘመቻ ሲያካሂዱ ለከረሙት መርዶ የሆነው የኢማኑኤል ማክሮን ንግግርና ጉብኝት የኢትዮጵያን ዳግም ወደ ቀይ ባህር መመለስ አይቀሬነት አመልካች ሆኗል። በዚህ ላይ የአንካራው ስምምነት ሲታከልበት የብልጽግናን መንግስት ህልም ያጎላዋል።
ኢትዮጵያ በቀይ ባህርን ላይ ያላትን ፍላጎቷን አስመልክቶ በዝርዝር ውይይት መደረጉን ሁለቱ መሪዎች በጋራ ባደረጉት መግለጫ ለህዝብ ምስክሩ ፊት የገለጹት ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ፣ ውይይቱ እጅግ የተሳካ መሆኑን አንዳንድ ጉዳዮችን እየነካኩ አስረድተዋል።
” ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ እንዳነሳነው 130 ሚሊዮን ህዝብ ያላት ሀገር ፣ ኢኮኖሚዋ በፍጥነት እያደገ ያለ ሀገር ፣ ተጨማሪ የባህር በር አክስሰ የሚያስፈልጋት ሀገር በዓለም ህግ በሰላማዊ መንገድ ፣ በዴፕሎማሲያዊ መንገድ እንደ ፈረንሳይ ያሉ ወዳጅ ሀገራትን ተጠቅመን የምናገኝበት (የባህር ባር አክሰስ) መንገድ ላይ የእሳቸው ጠንካራ ድጋፍ እንዳይለየን የቀረበላቸውን ጥያቄ እሳቸውም በአክብሮት ተቀብለዋል ” በማለት አብይ አሕመድ ሕዝብ ይሰማ ዘንድ ተናግረዋል። ኢማኑኤል ማክሮን ላደረጉት ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል። መላው የኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት ከፈረንሳይ እና ከፕሬዚዳንት ማክሮን የሚጨበጥ ውጤት እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ በቅርቡ ኢትዮጵያ ያካሄደችውን ኢኮኖሚክ ሪፎርም ፈረንሳይ እና ቻይና ክትትል የሚያደርጉት እንደሆነ፣ ፕሮግራሙ እንዲሳካ ማክሮን ከፍተኛ ድጋፍ ለኢትዮጵያና ለሪፎርሙ እንዳዳረጉ ፤ የፈረንሳይ መንግሥት በቀጥታ ከሚያደርገው ድጋፍ በተጨማሪ በEU እና IMF አይተኬ ድጋፍ እንዳደረገ አመልክተዋል።
ፈረንሳይ በኢትዮጵያ ዋና ኢንቬስተር ሆና ሌሎች የአውሮፓ ሀገራትን በማስተባበር በወሳኝ ጉዳዮች ላይ አብሮ ለመስራት መግባባት ላይ መደረሱን አሳውቀዋል። ” ማክሮን የሚገቡትን ቃል በመፈጸም የሚታወቁ ናቸው ፤ በኢንቨስትመንት ረገድም አብሮ ለመስራት መግባባት ላይ ተደርሷል ” ሲል ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ተናግረዋል።
ፕሬዜዳንት ማክሮን በበኩላቸው ለኢትዮጵያ የባህር በር አክሰስ መኖር ላይ የተነሳው ጥያቄ ትክክለኛ እንደሆነ ዕምነታቸውን ይፋ አድርገዋል። ” ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር የገለጹት የባህር በር መኖር አስፈላጊነት ፤ ለወደፊት ያሉትን ነገሮች ማመቻቸት መቻል ትክክለኛ ጥያቄ ነው ” ያሉት ማክሮን ” ይህን አስመልክቶ ፈረንሳይ ባላት አቅም ልትጫወት የምትችለውን ሚና መወጣት ትፈልጋለች። ይሄ በምን ዓይነት መንገድ መሆን አለበት የሚለው በንግግር፣ በውይይት፣ ዓለም አቀፍ ህጎችን ባከበረ መልኩና ጎረቤት ሀገሮችን ባከበረ መልኩ መሰራት የሚችልበትን መንገድ ለኢትዮጵያና ለቀጠናው መሳካት እንዲችል ሚናችንን እንወጣለን ” ሲሉ ወዳጅነትን፣ ህግን፣ አካሄድን አጣቅሰው አቋማቸውን ይፋ አድርገዋል።
ፕሬዚዳንት ማክሮን አክለውም ” ከክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ላይ ተነጋግረናል ፤ በሰሜን ኢትዮጵያ ሰላም ማስፈን ይቻል ዘንድ ትልቅ እርምጃ መሆኑንና ለማሳካትም እየተሞከረ መሆኑን እንገነዘባለን ፈረንሳይ ከዚህ ጋር በተያያዘ ያሉ ነገሮችን ለመደገፍ ትፈልጋለች ፤ እርሻን ማበረታታ፣ የተጎዱ ሆስፒታሎችን መልሶ ማቋቋም ፤ ከሽግግር ፍትህ ጋር በተያያዘ ደግሞ የሚሰራውን ስራ የህግ የበላይነት የሚከበርበትን መንገድ ማየት እንፈልጋለን ለዚህ እናተ በምትጠይቁን መሰረት ከጎናችሁ ሆነን ሁል ጊዜ እንቀጥላለን ” ብለዋል።
ኢማኑኤል ማክሮን በቱርክ ከሶማሊያው ፕሬዚዳንት ጋር የተደረገውን ንግግርና የሰላም ስምምነት አድነቀዋል። ቱርክንም አመስግነዋል። “ስለ ባህር በር መኖር አስፈላጊነት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ያነሱት ትክክለኛ ጥያቄ ነው ፤ ፈረንሳይ ባላት አቅም ልትጫወት የምትችለውን ሚና ታመቻቻለች” ሲሉ በንግግር ፣ በውይይት ፣ ዓለም አቀፍ ህግ ባከበረና ጎረቤት ሀገሮች ባከበረ መልኩ መል ዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
” ከኢኮኖሚ ጋር በተያያዘ ተነጋግረናል። በ2019 በመጣሁበት ጊዜ ያንን ታላቅ የኢኮኖሚ ሪፎርም ከመንግሥቶት ጋር በተያያዘ 100 ሚሊዮን ዩሮ በAFD አማካኝነት እንዲሁም የተለያዩ ቴክኒካል ድጋፎችንም መጨመር ችለናል። በአሁን ጊዜ ደግሞ ያለንን ሁሉ ነገር እንደምናደስ ለዚህም በ25 ሚሊዮን ዩሮ በጀት ድጋፍ ለማድረግ ነው። ” ሲሉ ተናግረዋል።
” ከኤሌክትሪክ ኔትዎርክ ጋር በተያያዘ የፈረንሳይ ድርጅቶች መግባት የሚችሉበት አጋጣሚ ይኖራል በዚህ ከአውሮፓ ህብረት ፈንድ ጋር እንዲሁም አውሮፓ ካሉ ባንኮች ጋር በመሆን 80 ሚሊዮን ዩሮ ይቀርባል ” ብለዋል።
” ከዕዳ ጋር በተያያዘ ከG20 ጋር የሚያያዘውን ከቻይና ጋር የሚሰራ ስራ ይኖራል። ይህ ለተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የሚቀርብ ነው። ባለፈው ፓሪስ ባዘጋጀነው ዝግጅት ተጨባጭ ነገር ተገኝቷል። ይህም እርሶ እያደረጉት ባሉት የሪፎርም ስራ ሲሆን 3 ቢሊዮን ዩሮ የምናመቻች ይሆናል እናተንም በሙሉ መደገፍ እንፈልጋለን ፤ መመቻቸት ስላሉባቸው ጉዳዮች ከIMF ጋር እንነጋገራለን ” ብለዋል።
” የፈረንሳይ ድርጅቶች ይበልጥ ተሳታፊ እንዲሆኑ (በኢንቨስትመንት) ፍላጎት አለን ” ሲሉ ገልጸዋል። ማክሮን በኢትዮጵያ ቆይታቸው ሀገራቸው ትልቁን ድጋፍ አድርጋበታለች የተባለውን የብሔራዊ ቤተመንግሥት እድሳት ስራን ተመልክተዋል።
ፈረንሳይ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት እድሳት ስራዎችን በግንባር ቀደምትነት በፋይናንስና ቴክኒክ ረገድ እየደገፈች ሲሆን ስራው 50% መሰራት እንደተቻለ ተነገሯል። በመግለጫው ወቅት ባይነሳም አካባቢው ላይ ባለው ጦርነት ሳቢያ ዕድሳቱን በሚፈልገው ፍጥነት ሰርቶ ማጠናቀቅ እንዳልተቻለ በስፍራው ያሉ አስተዳደሮች በተደጋጋሚ መናገራቸው ይታውሳል። አሁን ላይ ግን ስራው በፍጥነት እየተከናወነ እንደሆነ ይታወቃል።
ቅዳሜ’ለት በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደረጉት የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን፣ ኢትዮጵያ የዕዳ ሽግሽግ እንዲደረግላትና ይህም በቀጣይ ሳምንታት መፍትሄ ሊያገኝ እንደሚገባ ድጋፋቸውን ሰጥተዋል።
ፕሬዝዳንት ማክሮን፣ ኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በማድረጓ፣ አበዳሪዎች የአገሪቱን የሦስት ቢሊዮን ዩሮ ብድር የማሸጋሸግ ሂደት “በቀጣይ ሳምንታት” ውስጥ የማጠናቀቅ ሃሳብ እንዳላቸው ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ከዓለማቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይ ኤም ኤፍ) ጋር እያካሄደች ያለችውን ንግግር ፈረንሳይ እንደምትደግፍም ፕሬዝዳንት ማክሮን አስታውቀዋል