በደቡብ ኮሪያ ፣ ሙዋን በደረሰው አሰቃቂ የአውሮፕላን አደጋ አውሮፕላኑ ውስጥ ከነበሩት 181 ሰዎች 179 ሰዎች መሞታቸው መረጋገጡን ተዘገበ። በመላው አገሪቱ ሃዘን ታወጀ።
ንብረትነቱ የ ” ጄጁ አየር መንገድ ” በሆነው Boeing 737-800 የአውሮፕላን አደጋ ያጋጠመው ከታይላንድ ባንኮክ ወደ ደቡብ ኮሪያ ሙአን ዓለም ዓቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ለማረፍ ለማረፍ እየሞከረ ሳለ ተከስክሶ መሆኑ ተውቋል። ደቡብ ኮሪያ ዛሬ ሌሊት በአውሮፕላን አደጋ ህይወታቸውን ላጡ ሰዎች የሰባት ቀናት ብሔራዊ ሀዘን አውጃለች።
181 ሰዎችን ከታይላንድ ባንኮክ አሳፍሮ ደቡብ ኮሪያ የደረሰው አውሮፕላን ሙአን ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ለማረፍ ሲሞክር ተከስክሶ 179 ሰዎች ህይወታቸው ማለፉ የአገሪቱ ሚዲያዎች የሚመለከታቸውን ጠቅሰው በተከታታይ እየዘገቡ ነው። ከአደጋው ሁለት የአውሮፕላኑ ሰራተኞች በህይወት ተርፈው ወደ ህክምና ተቋም እንዲገቡ መደረጉን የሀገሪቱ መንግስት ገልጿል።
በአደጋው የደረሰውን ጉዳት ተከትሎ በታወጀው ሰባት ብሔራዊ የሐዘን ቀናት በሁሉም የመንግስት መስሪያ ቤቶች የሀገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብና የመንግስት ሰራተኞችም ጥቁር ሪባን እንዲያስሩ ትዕዛዝ ተላልፏል።
የጀጁ አየር መንገድ ንብረት የሆነ ቦይንግ 737-800 አውሮፕላን ለማረፍ ሲሞክር ከአውሮፕላን ማረፊያ አጥር ጋር ተጋጭቶ አደጋው መድረሱን አስቀድሞ ቢቢሲ ዘግቦ ነበር። በዚሁ ዘገባ የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አደጋውን አስመልክተው ይቅርታ መጠየቃቸው፣ ለተፈጠረውም አሳዛኝ ክስተትም ኃላፊነት እንደሚወስዱ ተመልክቷል።
የአውሮፕላኑ የበረራ መረጃ መመዝገቢያ ሳጥን (ብላክ ቦክስ) የተገኘ ሲሆን የአደጋውን መንስኤ መርምሮ ለማወቅ ጊዜ ይወስዳል ተብሏል።
ዘጋርዲያን የአደጋው መንስኤ እየተመረመረ ቢሆንም ባለስልጣናቱ አውሮፕላኑ ” ከወፍ ጋር ተጋጭቶ ነው ” ማለታቸውን ጠቁሟል። ከአደጋው ቀደም ብሎ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች አውሮፕላኑን የወፎች ጥቃት ስጋት እንዳለ ማሳወቃቸውም ተመልክቷል። ከአደጋው በህይወት ከተረፉ የበረራ አባላት መካከል እንደተሰማው ከአደጋው ቀደም ብሎ የወፎች ጥቃት እንደነበር መጠቆሙን ዘጋርዲያን ዘግቧል።