የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ሽመልስ አብዲሳ እና የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ከፍተኛ አመራር የነበሩት ጃል ሰኚ ነጋሳ ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ የሰላም ስምምነት ተፈራረሙ። ጃል ሰኚ ነጋሳ መንግሥት ያቀረበላቸውን የሰላም ጥሪ በመቀበል ነው ከአቶ ሽመልስ አብዲሳ ጋር የሰላም ስምምነቱን የፈረሙት፡፡
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ወቅት፣ የሰላም ጥሪውን ተቀብለው ለስምምነት የመጡትን አመስግነዋል።
“ከጦረኞች በላይ ጦርነትን የሚያባብሱት ስለጦርነት የማያውቁ ናቸው” ያሉት ፊልድ ማርሻሉ፣ “እኔ ካለኝ ልምድ አንፃር ጦርነት ጎጂ በመሆኑ የሰላምን መንገድ መርጣችሁ በመምጣታችሁ ልትመሰገኑ ይገባል” ብለዋል። ይህ አይነቱ ተግባር በሌሎች አካባቢዎችም ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ በመገለጽ ጥሪ አሰምተዋል።
አቶ ሽመልስ በበኩላቸው የኦሮሞ ሕዝብ በባህሉ መሰረት “ሰላም ይውረድ ብሎ ያቀረበውን ጥሪ ተቀብላችሁ በመምጣታችሁ በክልሉ መንግሥት ስም አመሠግናለሁ” ብለዋል። መከላከያ ሠራዊቱ ለሰላም ስምምነቱ ላበረከተው አስተዋፅኦም አቶ ሽመልስ አመሥግነዋል፡፡
የፖለቲካ ልዩነት ያለና ተፈጥሯዊ መሆኑን ያወሱት ጃል ሰኚ ነጋሳ፣ “እኛም ያለንን የፖለቲካ ልዩነት በጠመንጃ ከመፍታት በሰለጠነ መንገድ በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት ወስነን ነው ስምምነቱን የመረጥነው” ብለዋል። ስምምነቱ ለኦሮሞ ሕዝብ ትልቅ እፎይታን እንደሚሰጥም በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል መንግሥት እና በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት መካከል የተፈረመው የሰላም ስምምነት በኦሮሞ ሕዝብ የፖለቲካ ትግል ታሪክ ውስጥ ታላቁ ምዕራፍ መሆኑን አቶ ሽመስል በግል ማህበራዊ ገጻቸው አመልክተዋል።
አቶ ሽመልስ፣ የለውጡ መንግሥት የሰላም እጦት እና ለሕዝብ ስቃይ ምንጭ የሆነውን የፖለቲካ ልዩነት በሰላማዊ ውይይት ለመፍታት በማይናወጥ ቁርጠኝነት ሲንቀሳቀስ እንደነበር አስታውሰዋል።
የኦሮሞ ልሂቃን፣ አባገዳዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ሀደ ሲንቄዎች እና የኦሮሚያ ሰላም ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች ሁሉ፣ በተለይም ደግሞ ሰፊው የኦሮሞ ሕዝብ ልዩነቶች በሰላማዊ መንገድ መፍትሔ እንዲያገኙ በተደጋጋሚ ሲጠይቁ እንደነበርም ጠቅሰዋል።
ይህንኑ መሠረት በማድረግ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊትም የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ለሰላማዊ ውይይት ላለው ቁርጠኝነት እውቅና በመስጠት እና የባለድርሻ አካላትን የሰላም ጥሪንም በመቀበል ሕዝቡ የገባበት ስቃይ እንዲያበቃ ተቋርጦ የነበረውን የሰላም ውይይት ዳግም በመጀመር በዛሬው ዕለት ታሪካዊ ስምምነት ላይ ተደርሷል ብለዋል።
አቶ አደም ፋራህ
ባለፉት አመታት በሀገራችን የትኛውም የፖለቲካ ልዩነት በንግግር እንጂ በአፈሙዝ እንደማይፈታ በተደጋጋሚ ታይቷል – አቶ አደም ፋራህ
ኦቢኤን ሣይበር ሚዲያ ህዳር 22፣2017- ባለፉት አመታት በሀገራችን የትኛውም የፖለቲካ ልዩነት በንግግር እንጂ በአፈሙዝ እንደማይፈታ በተደጋጋሚ ታይቷል ሲሉ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ገለጹ።
አቶ አደም በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትና በኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ክንፍ ከፍተኛ አመራር ጃል ሰኚ ነጋሳ መካከል በዛሬው እለት የተፈረመው የሰላም ስምምነት እጅግ ሊበረታታ የሚገባውና እንደ ሀገር ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ለምናደርገው ጥረት ከፍተኛ አስተዋኦ የሚያበረክት ነው ብለዋል።
እንደ ብልፅግና ፓርቲ ሰላም ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ተገንዝበን እራሳችንን ለንግግር፣ ለድርድር እና ለትብብር ክፍት አድርገናል ሲሉም በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል።
ህብረተሰባችን በተደጋጋሚ የሚያቀርባቸው የህግ የበላይነት መከበር ጥያቄዎች በምሉዕነት እንዲመለሱ ለማድረግም የተጀመሩ ተስፋ ሰጪ ጥረቶችን ይበልጥ አጠናክሮ መሄድ እንደሚገባ እናምናለን ብለዋል።
ባለፉት አመታት በሀገራችን የትኛውም የፖለቲካ ልዩነት በንግግር እንጂ በአፈሙዝ ኃይል በዘላቂነት ሊፈታ እንደማይችል በተደጋጋሚ ታይቷል ሲሉም ገልጸዋል።
በመሆኑም በየትኛውም የሀገራችን ክፍል የሚገኙ ታጣቂዎች አሁንም ቢሆን የተሻለው አማራጭ ሰላማዊ መንገድ መሆኑን ተገንዝበው በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ ምርጫቸው እስካደረጉ ድረስ እንደ ብልፅግና ፓርቲ የሚጠበቅብንን ድርሻ ለመወጣት ሁሌም ዝግጁ መሆናችንንም ጭምር በዚህ አጋጣሚ ለመግለፅ እወዳለሁ ብለዋል።