ባደጉት አገራት የነዋሪዎች መረጃ ሲወለዱ ጀምሮ በአንድ ቋት ውስጥ ስለሚገባ ማንነትን መቀያየር የሚያስችል ክፍተት የለም። መታወቂያ በጉቦ መውሰድ፣ ማምታታት ብሎ ነገር የለም። ከለውጡ በሁዋላ “ፋይዳ” የዲጂታል መታወቂያ መጀመር በኢትዮጵያም ተመሳሳይ ስርዓት ለመዘርጋት በሚል ነው።
የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም መረጃ እንደሚያሳየው እስካሁን አስር ሚሊዮን የሚተጉ ዜጎች መታወቂያውን ለመውሰድ ተመዝግበዋል። በአሰራሩ መሰረት የተመዘገቡት ቁጥር ሆነው መረጃ ቋት ውስጥ ገብተዋል። ከዚህ በሁዋላ ፕሮግራሙ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሲሆን አንድ ሰው ወይም አንዲት ሴት የትኛውም ክልልና ከተማ ቢሄድ ወይም ብትሄድ ከቋቱ የሚዘረገፈው መረጃ አንድ ነው። ስለዚህ አድራሽና ማምታታት፣ ስምን መቀየር፣ የትውልድ ዘመንን ማሳሳት አይሳካም።
የብሄራዊ ባንክ ለባንኮች ሁሉ ባሰራጨው ደብዳቤ፣ በአዲስ አበባ ከተማ ደንበኞች የባንክ ሂሳብ ለመክፈት የፋይዳ መታወቂያ ባለቤት መሆን ግዴታቸው ሆኗል። ትዕዛዙ የደረሳቸው ባንኮች በካርቶን መታወቂያ ወይም በማንኛውም ዓይነት መታወቂያ ሂሳብ መክፈት አይችሉም።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በአዲስ አበባ ከተማ ደንበኞች የባንክ አካውንት ለመክፈት “ፋይዳ” የተሰኘውን የዲጂታል መታወቂያ በግድ እንዲይዙ ያዘዘው ትዕዛዝ ተግባራዊ የሚሆነው ከታህሳስ ከ23/2017 ዓ.ም. ጀምሮ ነው።
ይህ አሰራር ከሁለት ዓመት በኋላ በመላ አገሪቱ የሚገኙ ደንበኞች የትኛውንም የባንክ አገልግሎት ለማግኘት የፋይዳ መታወቂያ እንዲይዙ ይገደዳሉ። ካልያዙ አገልግሎት ማግኘት አይችሉም። ይህ አሰራር ማናቸውንም የገንዘብ እንቅስቃሴና ዝውውር ህጋዊነት ለመከታተል ያስችላል።
ብሔራዊ ባንክ፤ የ“ፋይዳ” ዲጂታል መታወቂያ ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ በአስገዳጅነት ጥቅም ላይ እንዲውል ያዘዘው ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ሕዳር 17/2017 ዓ.ም. ለሁሉም ባንኮች በጻፈው ደብዳቤ ነው።
እያንዳንዱ ሰው የሚለይበት ባለ 12-አሃዝ ልዩ መለያ ቁጥር እንዲያገኝ የሚያስችለው የ“ፋይዳ” መታወቂያ፤ የነዋሪዎች የባዮሜትሪክ መረጃዎችን በመውሰድ ምዝገባ የሚደረግበት ስርዓት ነው። የጣት አሻራ፣ አይን አይሪስ ስካን እና የፊት ምስል ነዋሪዎች መታወቂያውን ለማግኘት የሚያቀርቧቸው የባዮማትሪክ መረጃዎች ናቸው።
እስካሁን ድረስም ከ10 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች ይህንን የዲጂታል መታወቂያ ለማግኘት እንደተመዘገቡ የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም መረጃ ያመለክታል። ይህ አስገዳጅ አሰራር በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ተግባራዊ መሆን የሚጀምረው በተለያየ ጊዜ እንደሆነም ባንኩ ገልጿል። የብሔራዊ ባንክ ደብዳቤ እንደሚያስረዳው አዲሱ አሰራር ተግባራዊ መሆን የሚጀምረው በአዲስ አበባ ከተማ ነው።
ስለ ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎች – በአቶ ዮዳሔ አርዓያሥላሴ ይህን ብለው ነበር። ኢዜአ እንዳለው በትግበራ ላይ የሚገኘው የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ስያሜ ነው – ፋይዳ። የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ፕሮግራም ፅህፈት ቤት አስተባባሪ አቶ ዮዳሔ አርዓያሥላሴ “ፋይዳ የሚለው ቃል በፅህፈት ቤቱ የተመረጠው ለዕለት ከዕለት አጠቃቅም ገላጭና ምቹ በመሆኑ ነው” ይላሉ።
የ’ፋይዳ’ ዲጂታል መታወቂያ በሁሉም የሀገሪቷ ቋንቋዎች ወጥ በሆነ ስም እንደሚጠራም እንዲሁ።
‘ፋይዳ’ በዲጂታል ዓለም ውስጥ የሚኖረው ሀገራዊ ፋይዳ ዘርፈ ብዙ እንደሆነ ያነሱት አቶ ዮዳሔ፤ መታወቅ ለግለሰቡም፣ ለማህበረሰቡም እንዲሁም ለተቋማት አገልግሎት ወሳኝ ፋይዳ እንዳለው ይገልጻሉ።
በባዮሜትሪክ መረጃዎች ወጥ በሆነ ማንነት መታወቅ፤ መተማመን በመፍጠር አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመገንባትም ጉልህ አንድምታ እንዳለው ያነሳሉ።
በዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ የዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅም ሁነኛ ፋይዳ ይኖረዋል ነው ያሉት።
‘ፋይዳ’ ለሀገሬው ዜጋም ሆነ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚኖሩ የውጭ ዜጎች ያለምንም የማንነት ልዩነት የሚሰጥ በመሆኑ፣ አቃፊና አካታች የመታወቂያ መንገድ ስለመሆኑ ይጠቅሳሉ።
በወንጀል መከላከል ረገድ የሚኖረው ፋይዳ ወሳኝ መሆኑን በመጥቀስ፣ ለአብነትም በፍትሕ ተቋማት ዘንድ የማጭበርበር ድርጊትን በመቀነስ ቀልጣፋናና ትክክለኛ የፍትህ አገልግሎት ለመዘርጋት ያስችላል።
ፅህፈት ቤቱ መሰረታዊ ከሆኑ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ጋር በመፈራረም የማስተሳሰር ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢትዮቴሌኮም፣ ባንኮችና መንግስታዊ አገልግሎት ሰጭ ተቋማትን ለአብነት ጠቅሰዋል።
የተቋማት አገልግሎት ጋር መተሳሰር ደግሞ የፋይዳ መታወቂያ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ማሳያ መሆኑን ያነሳሉ።
‘ፋይዳ’ ዲጂታል መታወቂያ በመሆኑ የታተመ ካርድ ወይም ወረቀት መያዝ ግዴታ አለመሆኑን በማንሳት አንድ ሰው ያለምንም ክፍያ ተመዝግቦ ባለ12 አሃዝ ቁጥሮች መለያ ከተላከለት የፋይዳ ባለቤት ነው ይላሉ።
ነገር ግን በወረቀት ወይም በካርድ መልክ መታወቂያውን መያዝ የሚፈልግ ሰው፣ ከበይነ መረብ አውርዶ በግሉም ይሁን አትመው በሚሰጡ አካላት በኩል የአገልግሎት ክፍያ ከፍሎ መያዝ እንደሚችል ገልጸዋል።
የተላኩለት ቁጥሮች የጠፋበት ሰው ደግሞ በ*9779# በመደወል ቁጥሮችን ማግኘት እንደሚችል ተናግረዋል።
በብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ አዋጅ ‘ፋይዳ’ መታወቂያ መመዝገብ ግዴታ ባይኖረውም ተቋማት ግን ለአገልግሎታቸው የዲጂታል መታወቂያን እንደ ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጥ ይችላሉ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቅርቡ የፋይዳን መታወቂያ ለአገልግሎት አሰጣጥ እንደ ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጡን አስታውሰው፤ ይህን ተከትሎም ከተማ አቀፍ የፋይዳ ምዝገባ ዘመቻ መጀመሩን ገልጸዋል።
በመሆኑም ዜጎች ከተለያዩ ተቋማት አገልግሎት ላለመስተጓጎል ለዲጂታል መታወቂያ እንዲመዘገቡ ጥሪ አቅርበዋል።