በኢትዮጵያ የተካሄደውን ለውጥ ተከትሎ የተግተለተለው አስመሳይ ለቁጥር የሚታክት ነበር። ድሮ ጀምሮ የግብጽ ባሪያ ለመሆን የማለው ሻዕቢያ ሳይቀር ቀፎውን ሰብሮ ከነመሪው አዲስ አበባን ውጠዋት ነበር። “ተራኪ ነን፣ ተንታኝ ነን፣ አክቲቪስት ነን፣ ‘ጋዜጠኞች ‘ ነን፣ ወዘተ ” ብለው የጎረፉት ሁሉ አዲስ አበባ “እንኳን ደህና መታችሁ” ብላ ሳትለይ ሰበሰበች።
ሕዝብ “እልል ብሎ” የተቀበለው ለውጥ እገሌ ከገሌ ሳይል ካግበሰበሳቸው መካከል፣ ችጋር ከበላቸው ዜጎች ላይ በጠራራ ጸሃይ ዘርፎ የኮበለለውን ሻለቃ ዳዊትን ጨምሮ ” በኢትዮጵያ ባንዲራ ቅበሩን” የሚሉ ሽርክቶችን ይገኙበታል። የቻለው ጠብ መንጃ ተሸክሞ፣ ያልቻለው ባዶ እጁን፣ በተለያዩ ማዕረጎች በአየር፣ በየብስ፣ በባህር ወዘተ ኢትዮጵያን ከሞሏት መካከል “ተኩላነታቸው” ወዲያው የታወቀባቸው ነበሩ። ውለውና አድረው ” ተኩላ ነን” ብለው በተግባራቸው የነገሩንም ነበሩ።
“ታስሬያለሁ፣ ተገርፌያለሁ፣ የለውጡ ሃዋርያን ነኝ” በማለት አሁን ደረስ “እኔ፣ እኔ” የሚጫወቱትን ጨምሮ ለውጡ ስር የሰደደ መዋቅር ስላልነበረው ጀግናና ” አረ ጎራው” አውራጁ ብዙ ነበር። ወቅቱ መንግስትን መንግስት የሚያሰኙት ካስማዎቹ በሙሉ በትህነግ ተነቃቅለው ወደ መቀለ በመዛወራቸው ሳቢያ የተፈጠረውን የአቅም ማነስ ችግር፣ ይህን ችግር ተንተርሰው የሰከሩ “የፖለቲካው” ውሪዎች ያለ ከልካይ አናፉ። ለውጡ እንዳይቆም በተከፈቱት በሮች ሁሉ ሴራና ሁከት ይሰበኩ ጀመር። ራሳቸውን መንግስትና የለውጥ ሃዋሪያ አድርገው ኢህአዴግ ያገሸበውን ትውልድ እንዳሻቸው ነዱት።
እየበሰበሰ በነበረው ኢህአዴግ ውስጥ ራሳቸውን ያደሱና ለውጥ እንዲመጣ (ዝም ተብሎ ‘እኔ’ በሚል ራስን በማግነን ከሚዘፈነው የስካርና የሚርቃና ማብራሪያ በመራቅ በቀጣይ ለውጡን እነማን እንደጸነሱት፣ አምስቱ የመጀመሪያ ተሰብሳቢዎችን ስብሰባና ረድፍ በቀጣይ እመለስበታለሁ) በራሳቸው ቆርጠው የውስጥ ትግል ያደረጉት የለውጡ የፊት መሪዎች በውስጥ የዘረጉትን መስመር ተከትለው ዕውቅና የተላበሱ፣ እነሱን ተከትለው የሚያሟሙቁ ጀሌዎቻቸውና በራሱ በለውጡ አራማጆች ውስጥ የነበረው የአሮጌው ስርዓት ቅሬትና ያልተቋረጠ ግንኙነት አገሪቱን አሳር አበላት።
በዚሁ የለውጡ ግለት ተንደርድረው ከመጡት መካከል ዶክተር ዮናስ ብሩና ሻለቃ ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ ለዛሬ መነሻዬ ናቸው። “የበረከት ስምዖን ሽንት” የሚባለው የዛው ዘመን የኮሙኒኬሽን ሚኒስትር ዳኤታ የነበረው የዛሬው “የወንበር ቁራኛ” (ማታ ማታ ተቀባብተው መርዝ እየረጩ በዩቲዩብ የሚሸቅሉትንና ስራ ጠል ዲጂታል ለማኞች ‘የወንበር ቁራኛ’ እንላቸዋለን )፣ ቦሎቄና ኮንትሮባንድ ወርቅ ንግድ ውስጥ የገባው የሰብአዊ መብት አቀንቃን፣ የዛሬ የሻዕቢያ አንደበቶች፣ ያሬድ ጥበቡ ወዘተ ስልጣን፣ ቤት፣ መኪና፣ መሬት … ወዘተ ጠይቀው ሲከለከሉ ብሄር ውስጥ መወሸቅ ለመምረጣቸው ከበቂ በላይ ዝርዝር ማስረጃ አለኝ።
ወደ ሁለቱ የዛሬ እንግዶቼ በየተራ ላምራ። ዶክተር ዮናስ “ነጻ” በነበሩበት ወቅት ሙያዊ ምክርና አስተያየት ሲሰጡ በመማሬ፣ በወንጀል ድርጊት ቀደም ሲል የሚነሱ ሰው ባለመሆናቸው ከሻለቃ ዳዊት ጋር አብሬ ባነሳቸውም፣ በፍጹም በማመሳሰል እንዳልሆነ ነጥብ ይያዝልኝ።
እናም ዶክተር ዮናስ ዛሬ በሙያቸው የሚሰጡትን ምክርና አስተያየት ወዲያ ጥለው ዛፍ ሲወድቅ፣ መንገድ ሲሰራ፣ የምገባ ፕሮግራም ሲካሄድ፣ ተማሪዎች በትምህርት ቤት ዳቦ ሲቆርሱ፣ ወይዘሮ ስርጉት ሰፈር ጭስ ሲጨስ ለትችት የሚሮጡ፣ በተፈለጉበት የሚገኙ የዩቲዩብ ” የወንበር ቁራኛዎች” ንግድ ማሞቂያ ሆነው ያረፉበትን ሚስጢር ምን ይሆን? ብለን ለጠየቅን መልሱ ይኸው። በነገራችን ላይ “ሃሰት ነው” ካሉ እንደ ፔፕሲ ማስታወቂያ “ተጨማሪ ይጠይቁ” የሚለውን የማስታወቂያ ዘፈን አዜምላቸዋለሁ።
ሰሞኑን አቶ ሲሳይ አጌና “በነገራችን ላይ ‘ጋዜጠኛ’ ማለት ስለማልወድ ነው ይቅርታ” የጠቅላይ ሚኒስትሩን የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ዲያቆን ዳንኤል ክብረትን ስም ሳይጠቅሱ የምንናውቀውን ዕውነት ነግረውናል። ጠያቂውን እያመሰገንኩ፣ እሳቸው “መንግስት ይሽኮረመማል” ላሉት፣ እኔ ” መንግስትን ምን ያሽኮረምመዋል?” የሚለውን ጥያቄ ለሳቸውና ለመንግስት በመተው የማውቀውን ከሰማሁት አዋህጄ ለማቅረብ ወደድኩ። ምን ይላኛል? የምን መሽኮርመም ነው።
“እኔ” አሉ ዶከተር ዮናስ ብሩ፣ ስለ ስለ ራሳቸው ሲያብራሩ። አዲስ አበባ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ዘንዳ ደርሰው አመጣጣቸውን ስልጣን፣ ለዚያውም የብሄራዊ ባንክ ገዢ ለመሆን የወሰኑበትን ምክንያት ሲያስረዱ። “እኔ” ብለው የትምህርት ዝግጁነት እንዳላቸው፣ የትምህርት ዝግጁነታቸው ኢኮኖሚስት መሆኑን፣ በዘርፉ በቂ ልምድ እንዳላቸው፣ በዓለም ዓቀፍ የገንዘብ ተቋም ውስጥ መስራታቸውን … በመዘርዘር የብሄራዊ ባንክ ገዢነት ስልጣኑ እንደሚገባቸው ጠይቀዋል። ዳንኤል ክብረት ስም መጥቀስ ሳይፈልጉ የትምህርት ዝግጅታቸውንና የስራ ልማዳቸውን ጠቅሰው ለሲሳይ አጌና ያወጉት ስለ ዶክተር ዮናስ ብሩ መሆኑን እንኳን ነገሩን በጥልቀት ለሚያውቅ፣ ዩቲዩብ ሰፈር ለሚዘዋወሩና የለፉበትን ወደውና ፈቅደው ለሚዘረፉ የዞረባቸው ዲያስፖራዎች ግልጥ ነው።
የጠየቁትን ቦታ እንደማያገኙ፣ ነገር ግን በማስተማር ተግባር፣ በአማካሪ ቲም ትውልድና አገራቸውን መርዳት እንደሚችሉ የተነገራቸው ዶክተር ዮናስ፣ ተንደርድረው አሜሪካ ተመለሱና በገሃድ ከለውጡ ደጋፊነት ባቡር በብርሃን ፍጥነት ዱብ አሉ። ከለውጡ የደጋፊዎች ፉርጎ መውረዳቸውንም ማታ መታ ተኳኩለው መርዝ በሚረጩት ወሬኞች በኩል ይፋ አደረጉ። በታላላቅ ጉዳዮች ሙያዊ አስተያየት ሲሰጡ የሚታወቁት ዶከተር ዮናስ ራሳቸውን “የጥቃቅንና አነስተኛ ጉዳዮች አብራራው” አድርገው ሾሙ። በሌላ ቋንቋ ከፒኤችዲ የስራ ማዕረግ ወርደው የ “ጥጉ” መንደር አባል ሆኑ። የማናውቃቸው “ምን ነካብን” ብለን ምርመራ ጀመርን። ዛሬ ዳንኤል ክብረት ” መንግስታዊ መሽኮርመምን” አስቀድመው የነገሩን እውነት የኩርፊያቸው መነሻና መድረሻ መሆኑን ሰማን።
ዶክተር ዮናስ በሙያቸው ሲያስተምሩን፣ ሲተቹና ምክር ሲለግሱ “ኢትዮጵያ እንዲህ ዓይነትም ልጅ አላት” ብለን እንዳልመረቅን፣ እንዳላወደስን፣ እንዳልተመካን ወዘተ አሁን ላይ ሚስቶቻቸው እየሞሸሯቸውና ” ሸቅለህ ና” ብለው በሚልኳቸው የዩቲዩብ አበጋዞች የሚነዱ ሆነው አረፉት። እንደዛ የምንወዳቸው ምሁር፣ የተገኘውን፣ የተወራውን፣ የታሰበውን፣ የተሰማውን፣ ወደ ፊት ሊታሰብ የሚችለውን፣ በመላምት ሳይቀር ያለ አንዳች ዝግጅት የሚራገሙ … የዩቲዩብ ሳንቲም መልቀሚያ “ማሽን” ሆነው አረፉት። እባክዎትን ዶክተር የፖለቲካ አቋምዎ እንዳሻዎት ይሁን፣ ግን ቢያንስ ከ”ጥጉ” ሰፈ ይውጡና በምናውቅዎት ደረጃ ይተቹ፣ ይምከሩ፣ ይቃወሙ፣ …. አሜን!!
ሁለተኛው እንግዳዬ ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ ናቸው። ለዚህ ጽሁፍ እንደ መጀመሪያው እንግዳዬ ማዕረጉንና “አንቱታን” ስለከለከልኩ አንባቢያን ይቅርታ። ስለዚህ እኒያ የምናውቃቸው “ታሪካዊ” አባቱ እንዳሉት በሌጣ ስሙ ዳዊት እለዋለሁ።
ዳዊት በለውጡ ማግስት አዲስ አበባ ካግበሰበሰቻቸው መካከል አንዱና ዋናው የጥፋት ዘንዶ ነው። ዳዊት በደም የተጨማለቀ፣ ችግራ ካቃጠላቸው ዜጎች ጉሮሮ መንትፎ የኮበለለ፣ የኢትዮጵያን ምርጥ ጀነራሎች ባስፈጀውና ” ሆን ተብሎ እንዲከሽፍ ተደርጎ ተዘጋጀ” በተባለው መፈንቅለ መንግስት ሱዳን ሆኖ የተሳተፈና የመራ፣ እገሌ ከገሌ ሳይል መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የአደባባይ ፍርድ የሚመኙለት የባንዳዎች ቁንጮና፣ የባንዳ ሽንት ነው። እንግዲህ ይህ ሰው ነው አዲስ አበባ ተግበስብሶ ገብቶ ” የቤተመንግስት አማካሪ ልሁን” ብሎ ኢትዮጵያን ሊያሽመደምድ ክፍል ሁለት ዕቅዱን ከዘንዶው ጋር ይዞ ከች ያለው። “አይሆንም” የሚል መልስ እንኳን ሳያገኝ፣ ማንም ሳያስጠጋው፣ እንዲሁ ዘንዶውን ተሸክሞ እንደባተተብ ወደ ጌቶቹ የተመለሰው ዳዊት
ትህነግ ከተወገደ በኋላ ከሁሉም ቀድሞ አዲስ አበባ የደረሰው ዳዊት “ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሻግራችኋለሁ ብለዋል፤ መልካም ነው ያሻግሩን፤ ግን እንዴት እንደምንሻገር ሮድማፕ ያስፈልገናል” በማለት እኔ ላሻግራችሁ ብሎ ለምዕራባውያን ሊሸጠን በመርዝ የተለወሰውን ዕቅዱን የተፋው አስታዋሽ እንኳን ባለማግኘቱ ነው። ዕቅዱን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ለማቅረብ አዲስ አበባ ለአንድ ወር ደጅ ሲጠና ቢቆየም በስውር አጀንዳው መነሻነት “ወግድ” ተባለ። ትንሽ ቆይቶ አምርሮ የሚጠላቸው አቶ ካሣ ከበደ በኢትዮጵያ መንግሥት ጥሪ አገር ቤት ገብተው በቀጣይ መደረግ የሚገባውን ከልምዳቸው አካፍለው በክብር መሸኘታቸው አንጨረጭሮት አሜሪካ እንደገባ በገሃድ በኢትዮጵያ ላይ ዘመቻውን አወጀ። የሽግግር መንግስት አለ። ቀጥሎ “የአማራ ተቆርቋሪ” ሆኖ እሳቱን ከሻዕቢያ ጋር ሆኖ ለኮሰ። ይህን ሌባ፣ በደም የተጨማለቀና ከረሃብተኞች የዘረፈ፣ የኢትዮጵያን ምርጥ ጀነራሎች ያስፈጀ እሪያ አማራ ሕዝብ ላይ ተሳፈረ።

ገቢ ካገኙ ለአፍታም ማሰብ የሚባል ነገር የላፈጠረባቸው የዩቲዩብ ነጋዴዎች ዳዊትን ከነደም ካባው የቸዋው ህዝብ መሪ አድርገው አነገሱት። አንዴ ግብስ፣ አንዴ ኤርትራ እየተወራጨ ኢትዮጵያን ለማፍረስ አማራና ኦሮሞ መካከል እልቂት እንዲነሳ ሲሰብክ የነበረው ዳዊት ብዙም ሳይቆይ በሌብነት ተያዘ። በአማራ ሕዝብ ደም ዶላር የሚያፍሰው ዳዊት ነበር እንግዲህ ኢትዮጵያን ሊመራ አዲስ አበባ የገባው። ዳንዔል ክብረት ” መንግስት ይሽኮረመማል” ብለው ያለፉት ዕውነት ይህ ነው።
ጎልጉል ይህንኑ ወስላታ አስመልክቶ “ለግንዛቤ” ሲል ባቀርበው ጽሁፍ ውስጥ ይህን ወስደናል።የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ አገዛዝ በደርግ በተወገደ ጊዜ በትምህርት ውጭ አገር የነበረው ዳዊት ወልደጊዮርጊስ በራሱ አንደበት ሲናገር እንደተሰማው (የፒኤችዲ) ትምህርቱን አቋርጦ ወደ አገር ቤት መጣ። እርሱ እንደሚለው ትግሉን ለመቀላቀል ቢሆንም ዋናው ዓላማ ግን በደርግ ውስጥ በመግባት ለምዕራባዊ ኃይሎች ለመሰለል እንደሆነ የበኋላ ሥራው ይናገራል። እርሱ እራሱም ቢሆን ይህንን የሁለት ቢላዋ ጨዋታ ሊያስተባብል አይችልም። እንዲያውም በአንዳንድ ቃለመጠይቆች ሞቅ ሲለው እየዘላበደ እምነቱን ሰጥቷል።
ደርግ ውስጥ በመግባት የስለላ ተግባሩን የቀጠለው ዳዊት፤ በወቅቱ ደርግን አሳልፎ ለመስጠት የሚያስችል አመቺ ሁኔታ ባለመኖሩና ወቅቱ የጎላ አገር ወዳድነት የሚንጸባረቅበት፣ እንደ ዛሬ የጎጥ አስተሳሰብ የነገሰበት ባለመሆኑ ደርግን የተቀላቀለበትን ዋና የማፍረስ ተግባሩን አዘገየው። በቀጣይም ወታደርነቱን ሳይገፋበት የኤርትራ አስተዳዳሪ፣ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ወዘተ የተለያዩ ሥልጣን ላይ ከቆየ በኋላ ኢትዮጵያን ለምዕራባውያን በሯን ወለል አድርጋ እንድትከፍት የሚያደርጋት ሤራ ዋና ጠንሳሽ ሆነ። ይህንኑ እንዲያመቻች “ወታደሩ” ዳዊት የዕርዳታ ማስተባበሪያና ማቋቋሚያ ዋና ኮሚሽነር ተደረገ።
ይህም በሰው ሰራሽ ምክንያት የደረሰብን ችጋር አጉልቶ በዓለምአቀፍ መድረክ እንዲሰማ በማስደረግ በዕርዳታ ሰበብ ለምዕራቡ ዓለም በሯን ጥርቅም አድርጋ የዘጋችው ኢትዮጵያ በግድ እንድትከፍት ጫና ተደረገባት። “እምቢ” ብትል በዓለም ዓቀፉ መድረክ ክስ እንዲቀርብባት የሚያስደርግ እንደሚሆን በተሠራው ሥራ ውስጥ የዳዊት ሚና የጎላ ነበር። ከውጭ የሚመጡትን “የዕርዳታ ሰዎች” የሚያነጋግር ወደ ውጭ አገራት በመሄድ የሚወያይ፣ የሚዋዋል … ተደርጎ የተሾመው ዳዊት ወልደጊዮርጊስ ሆነ። ራሱ በተለያዩ መድረኮች እንደተናገረው አየርላንዳዊውን ቦልጊዶፍን እና “We are the World” የዘፋኞች ቡድን እንዲመጣ በማስደረግ ትልቅ ድርሻ አለው።
በዳዊት ወልደጊዮርጊስ አጼ ዮሃንሳዊ ምሪት ምዕራባውያን ሰተት ብለው አዲስ አበባ ገቡ። ኢትዮጵያ ተበረበረች፤ ትህነግ እስካፍንጫው ታጠቀ፤ የዕርዳታ እህል እየሸጠ ጦር መሣሪያ እንዲገዛ ዕድሉ ተከፈተለት፤ እነ ቦብ ጊልዶፍ “አናውቅም” ቢሉም በድራማው ዋና ተዋናይ ሆኑ፤ የድራማው ዳይሬክተር ዳዊት ወልደጊዮርጊስ ነበር። ሁሉም ሲጠናቀቅ ዳዊት ከችጋር ሰላባዎች ጉሮሮ 300ሺ የአሜሪካ ዶላር ዘርፎ ወደ “እናት አገሩ” አሜሪካ ኮበለለ። እዚያም ሆኖ የኮ/ሎ መንግሥቱን ስም በሚያጠለሽ መልኩ እርሱ የሌለበት ይመስል “የደም ዕንባ” የሚል መጽሃፍ አሳተመ፤ በእንግሊዝኛ ተተርጉሞ ለምዕራባውያን የፖሮፓጋንዳ ፍጆታ እንዲውል ተደረገ። ዳዊት በዓላማና በትዕዛዝ ሁሉንም ይፈጽም ስለነበር ልክ እንደ ዛሬው ያኔም የትህነግ ህጻናትን በጦርነት የመማገድ ወንጀል ዝም ተባለ።
ኮ/ል ጎሹ ወልዴ ሳንቲም ሳያጎድሉ፤ የውሎ አበላቸውንና የመመለሻ ቲኬታቸውን ወደ አገርቤት በመመለስ አሜሪካ በስደት ለመኖር ሲወስኑ (በወቅቱ ቪኦኤ ላይ ቀርበው ተናግረዋል) ዳዊት ወልደጊዮርጊስ ግን 300ሺህ ዶላሩን ከረሃብተኛ ሕዝብ ጉሮሮ ላይ ዘርፎ የተንደላቀቀ ኑሮውን በአሜሪካ ጀመረ። ለቀጣይ የሤራ ፖለቲካም ራሱን አዘጋጀ። እርም የሌላቸው የአገራችን ሚዲያዎች ከዚህ ወስላታና ወንጀለኛ ጋር አብረው ይሰራሉ። አይናቸውን በቸው አጥበው የምናውቀውን ዳዊት ዳግም እንደ አዲስ ጻድቅ አድረገው ሊያዋልዱልን ይለፋሉ።
በግንቦት ወር 1980ዓም ወታደራዊ መኮንኖች መፈንቅለ መንግሥት ሲያቅዱ የውጭውን ሤራ ሲመራ የነበረው ዳዊት ራሱ እንደነበር በተደጋጋሚ ሲናገር የነበረው ሃቅ ነው። እስከ ሱዳን ድረስ በመምጣት ከሻዕቢያ፣ ከትህነግና ከኦነግ መሰል ድርጅቶች ጋር ተደራድሮ፣ ሰነዶችን ፈርሞ የሄደው ራሱ እንደሆነ በአንደበቱ መስክሯል። ይህ መፈንቅለ መንግሥት እንዲከሽፍ ካስደረጉትና ኮ/ሎ መንግሥቱ በዕልህ ተነሳስተው ጄኔራሎቹን ገድለው የጦሩ ሞራል እንዲላሽቅ፤ በቀጣይም ትህነግ (ወያኔ) ወደ አዲስ አበባ የሚያደርገው ጉዞ የጽጌረዳ ምንጣፍ የተነጠፈበት እንዲሆን በማስደረግ የዳዊት የውጪ ሚና እጅግ የጎላ ነው። መፈንቅለ መንግሥቱም ከሽፎ የቀረው ዓላማው መንግሥቱን ፈንቅሎ ነጻነት ለሕዝብ ለማምጣት ሳይሆን ኤርትራን ለማስገንጠልና ኢትዮጵያን ለምዕራባውያን አሻንጉሊትና ተላላኪ ለሆነው ትህነግ አሳልፎ ለመስጠት ነበር።
ትህነግ ከተወገደ በኋላ ከማንኛውም ፖለቲከኛ በመቅደም አዲስ አበባ ድረስ በመምጣት የሽግግር መንግሥት ምሥረታን ሃሳብ በይፋ ያቀረበው ዳዊት ወልደጊዮርጊስ ነበር። “ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሻግራችኋለሁ ብለዋል፤ መልካም ነው ያሻግሩን፤ ግን እንዴት እንደምንሻገር ሮድማፕ ያስፈልገናል” በማለት እኔ ላሻግራችሁ ብሎ ለምዕራባውያን ሊሸጠን ሲያስማማን የነበረው ዳዊት ነበር። ዕቅዱን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ለማቅረብ አዲስ አበባ ለአንድ ወር ደጅ ሲጠና በስውር አጀንዳው መነሻነት “ወግድ” ተባለ። ትንሽ ቆይቶ አምርሮ የሚጠላቸው አቶ ካሣ ከበደ በኢትዮጵያ መንግሥት ጥሪ አገር ቤት ገብተው በቀጣይ መደረግ የሚገባውን ከልምዳቸው አካፍለው በክብር መሸኘታቸው አንጨረጭሮት አሜሪካ እንደገባ በገሃድ በኢትዮጵያ ላይ ዘመቻውን አወጀ።
ትህነግ በኢትዮጵያ በየቦታው የቀበረውን ጊዜውን ጠብቆ የሚፈነዳ የብሔር (የዘውግ) ቦምብ ምን እንደሆነ እያወቀ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ የመሸጋገሪያ ዕቅድ ብሎ ያቀረበው አንዱ ሃሳብ “በብሔር ላይ የተመሠረቱ ድርጅቶችን በሙሉ በኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይሠሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአዋጅ ማገድ አለባቸው” የሚል ነበር። ይህንን ረቂቅ በየዋህነት የተቀበሉ የዛሬ ሦስት ዓመት ጀምረው “የሽግግር ሮድማፕ (ፎኖተካርታ)” እያሉ ዳዊታዊ ዝማሬ ሲያሰሙ ሰኔ 15 ቀን በተደረገው ምርጫ የሕዝቡን ምላሽ አግኝተዋል።
አሁን ባለችው ኢትዮጵያ፣ መንግስት ህገመንግስቱን ቀዶ ቢጥል ምን ሊከሰት እንደሚችል የሚያውቀው ዳዊት፣ ይህ አገራቸውን የሚወዱና የዘር ፖለቲካ የሰላቻቸው ዜጎች ጥያቄ የሆነውን የህገመንግስት ማሻሻል ሂደት እንደ ተራ ጉዳይ በአንድ ጀንበር የሚፈጸም አድርጎ ያቀርበው አገሪቱን ለማፍረስ ካለው ዕቅድ እንደሆነ ጥርጥር የለውም። ይህን ለማረጋገጥ ክልሎችን መጠየቅ በቂ ነው።
በቀጣይ የአምስቱን ሰዎች ታሪክ እመለስበታለሁ
በሞገስ በጸጋ – ይህ ጽሁፍ የጸሃፊው አሳብ ብቻ ነው። አስተያየት ላላቸው ክፍት ነው