የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ድርጅት ኔቶ ዋና ጸሀፊ ማርክ ሩት የድርጅቱ አባላት በጦርነት እሳቤ ውስጥ መዘጋጀት እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል። ዋና ጸሃፊው የህብረቱ አባላት ልክ በጦርነት ውስጥ እንዳሉ በመቁጠር የጦር መሳሪያ ምርት እና የመከላከያ ወጪዎችን ሊያሳድጉ እንደሚገባ መክረዋል፡፡
ዜጎች ለዘላቂ የአውሮፓ ሰላም መስዕዋትነት መክፈል አለባቸው ያሉት ሩት ከጡረታ እና ከሌሎች ክፍያዎች ላይ በመቁረጥ መንግሥታት የመከላከያ በጀታቸውን እንዲያሳድጉ መተባበር እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል፡፡
በአማካኝ የአውሮፓ ሀገራት ከአጠቃላይ ገቢያቸው አንድ አራተኛ የሚሆነውን ለጡረታ፣ በጤና እና በማህበራዊ ዋስትና ሥርዓት ላይ ያውላሉ።
ኔቶ አባል ሀገራቱ የመከላከያ ወጪያቸውን ለማሳደግ በማህበራዊ አገልግሎት ላይ የሚያወጡትን ወጪ እንዲቀንሱ እየጠየቀ ይገኛል፡፡
ዋና ጸሀፊው አክለውም ከሩስያ በኩል እየመጣ ያለውን የጦርነት ስጋት አባላቱ በበቂ አልተደሩትም በሚል ወቅሰዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከሀገራቱ አጠቃላይ ሀገራዊ ምርት እድገት 2 በመቶ የሚዋጣው ገንዘብ የወታደራዊ ህብረቱን ጠንካራ ቁመና እና የአህጉሩን ሰላም ለማስጠበቅ በቂ አይደለም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የቀድሞ የኔዘርላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር የአሁኑ የኔቶ ዋና ጸሀፊ ወቅታዊ ሁኔታዎችን አስመልክቶ ባደረጉት ንግግር፤ “በጦርነት ውስጥ አይደለንም ግን ደግሞ በአካባቢያችንም ሰላም የለም” ብለዋል፡፡
በተጨማሪም “አሁን የምንገኝበት ሁኔታ ጥሩ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ከ2 በመቶ አመታዊ መዋጮ ጋር ተጣበቅን የምንቀጥል ከሆነ በአራት እና በአምስት ዓመታት ውስጥ ከሩሲያ እና በሌሎች የዓለም ክፍሎች ከሚከሰተው ከማንኛውም ሁኔታ ራሳችንን ለመከላከል በጣም ደካማ ልንሆን እንችላለን” ነው ያሉት፡፡
ዓለም እና እንደ አጠቃላይ አህጉሩ የሚገኝበት ሁኔታ የሚያዘናጋ አይደለም ያሉት ዋና ጸሀፊው በቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት ወቅት አባል ሀገራቱ ከነበረው ስጋት አንጻር አመታዊ ወጪያቸውን አሳድገው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ይህን ደግሞ አውሮፓ እና አሜሪካ በስጋትነት ከሳሏት ሩስያ ወታደራዊ በጀት አንጻር አወዳድረው ተመልክተውታል፡፡
ሞስኮ ከቀዝቃዝው ጦርነት ወዲህ ከፍተኛ የተባለውን ከአመታዊ በጀቷ ውስጥ አንድ ሶስተኛውን ለመከላከያዋ እንደበጀተች ይታወሳል በ2025 እና በቀጣዮቹ ዓመታት ደግሞ የዓመታዊ ጥቅል ምርት እድገቷን 7 እና 8 በመቶ ድረስ መከላከያዋ ላይ ለማዋል አቅዳለች አል ዐይን ዘግቧል፡፡