ከአገር ውጭ የነበሩ የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች ወደ አገር ቤት እንዲገቡ ጥሪ የቀርበላቸው ለውጡ ይፋ በሆነ ማግስት ነበር። ጦር ያላቸው ከነነ ነፍጣቸው፣ የሌላቸውም አመራሮቻቸው በአየርና በየብስ ወደ አዲስ አበባ ሲገቡ አቀባበሉ፣ ጭፈራውና የደጋፊዎቻቸው ደስታ ልዩ ነበር። የሰው ጎርፍ እስኪፈስ ድረስ አዲስ አበባን ያጥለቀለቀ ትዕይንት መታየቱም አይዘነጋም።
አፈጣጠራቸውን ለራሳቸው ትተነው በአገር ውስጥ ሲንቀሳቀሱ ከቆዩት በተጨማሪ ከውጭ የገቡት ሲታከሉ ኦሮሚያ በተቀናቃኝ የፖለቲካ ድርጅቶች ብዛት ሰከረች። አፍታም ሳይቆይ ለውጡን ተከትለው የገቡት አክቲቪስቶች በተለይ ጃዋር የሚዲያ ማዕበል አስነሳ። በግል በርካታ ሚዲያ ባለቤት መሆኑ ብቻ ሳይሆን ” ራሱን በመንግስት ልክ ሰፍሮ ለውጡ ሳይጠና ይነቀንቀው ጀመር።
በጣምም ባይከርም ውስጥ ውስጡን የሚያያዘው የስልጣን ጉዳይ ሲለው በውይይት፣ ሲያሻ በሴራ እየተለወሰ ወራት ቆጠሩ። ወዲያው ግን አንድ ጉዳይ ተሰማ። “ጋዲሳ ሆገንሳ ኦሮሞ” የተሰኘ በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ህብረት ተመሰረተ። ስምምነቱ እውን መሆኑ ሲታወጅ በርካቶች ድጋፋቸውን ገለጹ። ስለ ስምምነቱ ዝርዝርና አተገባበር ብዙም ይፋ ሳይነገር አንድ ላይ ለመስራት መግባባታቸውን በፊርማ ሲያስረዱ ተጨበጨበ። ፍትጊያና ሁከት የሰለቻቸው አደነቁ። ይህ የሆነው ማክሰኞ መስከረም ፳ ቀን 2012 ወይም October 1, 2019) ነበር።

አቶ ለማና ጃዋር በጓሮ በር ምን ተስማሙ?
ብዙዎች የሳቱትና ትክክለኛው መረጃ ያላገኙበት ጉዳይ የሚጀምረው “ጋዲሳ ሆገንሳ ኦሮሞ” መመስረቱ እንጅ መጨንገፉ በስፋት እንዲነገር አለመፍለጉ ላይ ነው። ሲቋቋም ብዙ የተጮኸለት ይህ ህብረት ገና ዳዴ ሳይል የተቀጨበትን ምክንያት ግልጥልጥ ማድረግ ያልተፈልገው ሚዲያዎቹን የሚመሩትና አጀንዳ የሚሰፍሩላቸው በመረጃው ላይ ጥላቸዋን ስላጠሉበት ነበር።
ጉዳዩ ተጀምሮ እስኪያልቅ የነበሩ የተቀናቃኝ ድርጅት አመራር እንዳሉት ከሆነ አቶ ጃዋር መሐመድ አቶ ለማ መገርሳን በመያዝ የፈተሉት ሴራ ህብረቱን እንግዴ አድርጎታል። ለመሆኑ ዋናውና አንኳሩ የስምምነቱ ነጥቦች ማን ነበሩ?
- ስምምነቱ ድርጅቶቹ በአንድ ምርጫ ጣቢያ እርስ በርስ እንዳይፎካከሩ
- የምርጫ ወርዳዎችን በውይይት ተከፋፍለው ህብረቱ ውስጥ የሌሉ ተወዳዳሪዎች ካሉ ለማሸነፍ፣ ካልሆነም በብቸኛነት ለመቅረብ
- ከምርጫው በሁዋላ ኦሮሚያን በመሪነት ከተቃዋሚዎች እንዲይዝ፣ ፌደራሉን ኦሮሞ ብልጽግና እንዲወከልበት፣ በተለይም አብይ አህመድ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆኑ ሙሉ ድጋፍ ለመስጠት ወዘተ የሚሉ አንኳር ጉዳዮች ነበሩበት።
በህብረቱ ውስጥ የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዴፓ/ ብልጽግና ኦሮሚያ)፣ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)፣ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ)፣ የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ግንባርና (ኦዴግ) ዋናዎቹ ተዋንያኖች ሲሆኑ ሌሎችም ይገኙበታል። ይህ ህብረት ውህደቱን ይፋ ለማድረግ በስካይ ላይት ሆቴል ዘርዝር የስምምነት ማዕቀፍ አዘጋጅቶ ለመፈራረምና ይህንኑ ዝርዝር ጉዳይ በሚዲያ በቀጥታ ስርጭት ለማወጅ ስብሰባ ሲደረግ የፓርቲው ሊቀመንበር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እንዲያውቁ አልተደርገም ነበር። እንግዲህ ክሽፈቱ የሚወለደው እዚህ ውስጥ ነው።
ዝርዝሩን ከጅምሩ እስከፍጻሜው ያጫወቱን የጠቀስናቸው የጉዳይ ባለቤት እንዳሉት የሁሉም ድርጅቶች ሊቃነ መናብርት ሲገኙ የብልጽግና ኦሮሚያ ሊቀመንበር ዶክተር አብይ ተዘለዋል። መዘለላቸው ብቻ ሳይሆን በእለቱ ሊታወጅ የነበረው የኦእሮሚያ ብልጽግና በገሃድ መፍረሱን አቶ ለማ እንዲያውጁና ጋዲሳ ሆገንሳ ኦሮሞ የተሰኘ ድርጅት ኦሮሚያን እንደሚመራ ለማስታወቅ ነበር። ይህን ስምምነት አቶ ጃዋር ከአቶ ለማ ጋር ፈጽመው እንዳበቁ፣ የሰሙ አንድ አስተባባሪ ጉዳዩን ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ቱስ ይላሉ።
እንደ ነገ ትያትሩ ተግባራዊ ሊሆን የሚዲያ ዝግጅት ተጠናቆ፣ መግለጫ ተዘጋጅቶ ነጋ አልነጋ ሲባል መረጃው የደረሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፣ በድርጅት የሚሰራውን ስራ እየሰሩ በተደጋጋሚ አቶ ለማን በስልክ ለማግነት ቢሞክሩ አልሆን ያላቸዋል። አቶ ለማ ስልክ አያነሱም። አይመልሱም። ነገሩ ጥብቅ ጉዳይ በመሆኑ አብይ አህመድ አቶ ለማ መኖሪያ ቤት ያመራሉ። እዛም ሲደርሱ ጠባቂዎቻቸው ” ማንም እንዳይገባ አዘዋል” በሚል ማሽ ይሰጣሉ። አሁን ነገሩ ፍንትው ያለላቸው አብይ ማምሻውን መመሪያ መስጠት ላለባቸው አካላት ሁሉ የሚፈለገውን አድርገው በበነጋው ስነ ስራዓቱ እየተካሄደ ባለበት ስካይ ላይት ሆቴል በድንገት ከተፍ አሉ።
እኚሁ የጉዳይ ባለቤት እንዳሉት ከሆነ ከፓርቲዎቹ ሊቃነ መናብርቶች ተርታ አቶ ለማ አብይ አህመድን ተክተው ተሰይመዋል። የራሳቸውን ዝግጅት አጠናቀው ድንገት ስብሰባው አዳራሽ ዘው ያሉት አብይ ድርጅታቸውን ወክለው ፊታቸውን እንዳኮማተሩ የቀረበላቸው ሰነድ ላይ ፈረሙ። መድረኩን የሚመሩት ሰውና ታዳሚዎች ሚስጥሩን ስለማያውቁ የጠቅላይ ሚኒስትሩን መድረስ እያወደሱ ሲዘላብዱ ድራማውን የሰሩት ወገኖች ግራ ተጋብተው ነበር። በዚህ ዓይነቱ የአይጥና የድመት ድራማ ከላይ የጠቀስነው ስምምነት ያለበት ሰንድ ተፈረመ። አብይ ፊርማቸውን ካኖሩ በሁዋላ የሁሉንም ድርሻ እንዲሰበሰብ አብረዋቸው ለመጡ አዘው ይዘው ውልቅ አሉ። ስብሰባው በዚያ ተበተነ።
ይቀጥላሉ ምስክሩ ሚስጥሩን የምያውቁት አቶ ለማ፣ ጃዋር መሐመድ፣ አብይ አሕመድና ይህን ያካፈሉን ሰው ናቸው። በሁዋላ ላይ ነገሩ ከገባቸው በቀር ፈራሚዎቹ ድርጅቶ ራሳቸው መን እንደሆነ አይውቁም። አቶ ለማ ክልሉን የሚመራው ፓርቲያቸው በይፋ እንደሟሟ ወይም እንደከሰመ አውጀው መዋቅሩን ጋዲሳ ሆገንሳ ኦሮሞ እንደሚረከበው ሲገልጹ በመላው ኦሮሚያ የሚከናወን ቀጣይ ስራ ነበር። አብይ አሕመድ ማምሻውን ይህን አምክነው ነበር ስካይ ላይት የተገኙት።
ፕሮፌሰር መረራ የሚመሩት ኦፌኮ ህብረቱ መክሸፉ ሲገባው ኦነግን “አብረን ምርጫውን አንሳተፍ። እርስ በርስ አንወዳደርም። ካሸነፍን አንድ ላይ የጥምር መንግስት እንመሰርታለን” የሚል አሳብ ይዞ ሄደ። ኦነግ እርስ በርስ መወዳደሩ እንደሚሻል ገልጾ የኦፌኮን ጥያቄ ውድቅ አደረገ። መቸረጫ ላይም ለውጡ ሲመጣ ከ200 በላይ ቢሮ ከፍቶ ሲሰራ የነበረውን ኦፌኮን አቶ ጃዋር ተቀላቀለውና ድርጅቱ የማያውቀውን ነዳጅ ነሰነሰባቸው። በር በገፍ ሰጠና አጣደፋቸው። ምርጫ ሳይወዳደሩ ቀሩ። ብልጽግና ብቻውን ኦሮሚያን ተረከበ።
በመርህ ደረጃ ስምምነት ከተደረሰ በሁዋላ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱ ቦታ ለአብይ አሕመድ እንዲሆን የተደርገው ስምምነት ጃዋርን አልተመቸውም ነበር። “ሁለት መንግስት አለዖ አንዱ አብይ ሌላኛው እኔ የመመራው ነው” በማለት አራት ኪሎን ሲያስብ የነበረው ጃዋር አቶ ለማን ገንጥሎ ያሰበው ውጥን በዚህ መልኩ ተነነ። የማይጸጸተው ጃዋር ይህን ህብረት ባያፈርሰው ኖሮ ኦሮሚያ ላይ ዛሬ ድረስ ጦርነት፣ መተላለቅ፣ መፈናቀል ወዘተ ባልኖረ ነበር።
ታሪኩን ያጫወቱን አሳቡ ባይሳክም ተሞክሮ ቢሆን ኖሮ ኦሮሚያ ላይም ሆነ አገሪቱ ላይ ምን ሊያስከትል እንደችል ማሰብ ብቻ ነበስን እንደሚያርድ ገልጸዋል። የኦሮሚያ መዋቅር ፈርሷል ብሎ ምንም አዲስ መዋቅር ሳይዘረጋ ማወጅ በጤኛ አዕምሮ ከቶውንም የሚታሰብ እንዳልሆነ ሲናገሩ አሁን ድረስ ስጋቱ እንዳልለቀቃቸው በመግለጽ ነው።
ሁሉም አልፎ እነ ጃዋር እስር ቤት በገቡበት ወቅትም እስር ቤት ውስጥ የተጀመረና የከሸፈ ሴራ እንዳለ እኚሁ ሰው ያውቃሉ። እስር ቤት የነበሩ የትህነግ አመራሮች ከእነ ጃዋር ጋር መሲጥረዋል። እዛ እያሉ ህብረት በሚፈጥሩበት አግባብ ተነጋግረው ኦፌኮ አሳቡን አልተቀበልም። ለወደፊቱ ዝርዝር የሚቀርብ ቢሆንም ትህነግ ዳግም በጦርነት መንግስት ሲሆን በሚቋቋመው መንግስት ውስጥ ብልጽግና እንደማይካተት ጠቅሶ ያቀርበውን ሰነድ ጃዋር ተቀብሏል። ሌሎችም የተቀበሉ እስረኞች አሉ። ኦፌኮ ግን ብልጽግና በማይወከልበት ማናቸውም እንቅስቃሴ ውስጥ እንደማይሳተፍ በያዘው አቋም እንደ ድርጅት አሳቡ ውድቅ ሆኗል። ትህነግም ደብረ ሲና ደርሶ ዳግም እንዳይመለስ ተደርጎ ተመልሷል።
እስር ቤት እንዴት ነበር ሰነድና መረጃ የሚቀያየሩት? ስብሰባ የሚያካሂዱት? ወዘተ ዝርዝር እናቀርባለን።