በአንድ አካባቢ ሁለትም፣ ሶስትም አደረጃጀት ቢኖርም የጎንደር ፋኖ፣ የጎጃም ፋኖ፣ የሽዋ ፋኖ፣ የደሴ፣ የኮምቦልቻ ወዘተ እንደሚባለው ሁሉ ” የወለጋ ክፍለ ሃገር ፋኖ” የሚለው አደረጃጀት ይፋ መሆኑን ተከትሎ ” ክፍለ ሃገር” የምትለዋ ተቀጥያ በተለይ ኦሮሚያ ላይ “ለምን ተፈለገች?” የሚል ጥያቄ በኦሮሞ ፖለቲከኞች ዘንዳ መነጋገሪያ ሆናለች። በተመሳሳይ አማራዎች በርከት በለው በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ክልል ሳይለይ ተመሳሳይ አደረጃጀት እየተፈጠረ መሆኑም እየተሰማ ነው። ይህ እንቅስቃሴ በሁሉም አገሪቱ ውስጥ በሰላም የሚኖሩ የአማራ ተወላጆችን ይጠቅማል? የሚለው ጉዳይ አድሮ የሚታይ ቢሆንም የሌሎች ክልሎች ምላሽ ባይታወቅም በኦሮሚያ ግን ከቶውንም እንደማይፈቀድ በይፋ እየተገለጸ ይገኛል።
አንድን ወገን እወክላለሁ የሚል የታጠቀ ኃይል፣ በአንድ በሚታወቅ፣ በህገ መንግስት ራሱን እንዲያስተዳድር ስልጣን በተሰጠው፣ የራሱ ወሰን፣ የአስተዳደር እርከንና ህግ ባለው ክልል ውስጥ ትጥቅ አንስቶ መንቀሳቀሱን በምንም መልኩ እንደማይቀበለው የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረንስ በተለይ ለኢትዮሪቪው የገለጸው በዚሁ እሳቤ ነው። አካሄዱ የጎንዮሽ ግጭት ሊያስነሳ እንደሚችልም ስጋቱን ከማስጠንቀቂያ ጋር አስተላልፏል።
የኦፌኮ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሱልጣን ቃሲም፣ ይህን ያሉት ራሱን ” የወለጋ ክፍለሃገር ፋኖ” በሚል ስያሜ በማስተዋወቅ በኦሮሚያ የትጥቅ ትግል ማድረጉን ይፋ ማድረጉን ተከትሎ ፓርቲያቸው ጉዳዩን በምን መልኩ እንደሚያየው ለተተየቁት ሲመልሱ ነው።
የወለጋ ክፍለሃገር ፋኖ መሪ ፋኖ ንጉሴ ሰሞኑን በይፋ እንዳስታወቁት እቅስቃሴው ከዚህ በፊትም የነበረ መሆኑንን አመልክተው አሁን ላይ በዕዝ ደረጃ መደራጀቱን አስታውቀዋል። ቀደም ሲል ራስን ለመከላከል በሚል የተጀመረው አደረጃጀት አሁን ላይ ወደ ዕዝ ደረጃ ማደጉን ያስታውቁት ፋኖ ንጉሴ ” በአማራ ክልል ካለው የፋኖ እንቅስቃሴ ጋር ግንኙነት አለን” ብለዋል።
የፋኖ ታጠቂዎች በምስራቅ ወለጋ አንገር ጉቲን አራት ወጣቶችን አግተው ሁለቱን ገደሉ፤ ግድያው የጠየቁት ገንዘብ ከተከፈለ በሁዋላ ነው
በኦሮሚያ በጃል ሰኚ የሚመራው ታጣቂ ኃይል ወደ ሰላም አማራጭ መመለሱን ተከትሎ፣ ይፋ የሆነው የወለጋ ክፍለሃገር ፋኖ አደረጃጀት በዚህ ስም ራሱን ባይጠራም ከኦነግ ሸኔ ጋር ተናቦና ህብረት ፈጥሮ ይሰራ እንደነበር በርካታ መረጃዎች ሲወጡ እንደነበር ይታወሳል።
እንዲህ መሰል መረጃዎች በሚወጡበት ወቅት ኢስመኮ ያወጣውን ሪፖርት አስመልክቶ ጃዋር መሐመድ ለቢቢሲ ” ተኩስ በማቆም ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጋር ንግግር መጀመር አለበት፤ በተጨማሪም የፋኖ ሚሊሻዎችን ከኦሮሚያ አስወጥቶ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው መመለስ አለባቸው ፣ አጠቃላይ ብሔራዊ የሰላም ሂደት ብቸኛው መፍትሄ በመሆኑ ይህን ለማሳካት አቅዶ መተግበር ያስፈልጋል” ማለቱ አይዘነጋም።
“ኦሮሚያ ውስጥ የሚሆነው ሁሉ በመናበብ የሚሰራ ላለመሆኑ ምን ማስረጃ ማቅረብ ይችላል”
ፋኖ ንጉሴ ከፋሲል የኔ ዓለም ጋር ባደረጉት ውይይት “መንግስት ሸኔ ስለሚል በተለምዶ ኦነግ ሸኔ እንላቸዋለን እንጂ ስማቸው ABO ወይም የኦሮሞ ነጻ አውጪ ጦር ነው” በማለት የስም ማስተካከያ ካደረጉ በሁውላ፣ ላለፉት አራት ዓመታት አማራን መንካት እንዳቆሙ አስታውቀዋል። ፋኖ በወለጋ ከተመሰረት መቆየቱንም ይፋ አድርገዋል።
አቶ ሱልጣን አሁን ላይ ይፋ ይነገር እንጂ ጉዳይ አዲስ እንዳልሆነ፣ ድርጅታቸው በተለያዩ ጊዜያት መግለጫ በማውጣት ማስጠንቀቂያ የሰጠበት ጉዳይ መሆኑን ያስታውሳሉ። አክለውም፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ‘በኦሮሚያና በቢኒሻንጉል ውስጥ ያሉ አማራዎች መታጠቅ አለባቸው’ ብለው በይፋ ሲናገሩና እንዲተገበር ሲያደርጉት ኦፌኮ ጉዳዩ አድሮ ችግር እንደሚያስነሳ ገልጾ መቃወሙን ይገልጻሉ።
“ታላቁ እስክንድር” በሚል ማዕረግ የሚጠራውና በአንድ ወገን ያለውን የፋኖ አደረጃጀት የሚመራው እስከንድር ነጋ፣ በውጭ አገር የአማራ ትግል አስተባባሪ ያላቸው ሻለቃ ዳዊት ወለደ ጊዮርጊስ፣ “ወለጋ የአማራ ዕርስት ነው” በሚል ትግሉ በገሃድ ወለጋንም የማስመለስ ትግል እንደሆነ መናገራቸው አይዘነጋም። ፋኖ ንጉሴ ይህን ጉዳይ ከፋሲል ጋር ሲወያዩ አልገለጹም፣ ፋሲልም አላነሳባቸውም።
ፋኖ ንጉሴ ትግሉ አማራውንም ሆነ ኦሮሞውን ነጻ የማውጣት እንደሆነ ጠቅሰው፣ በውስጣቸው ኦሮሞ የሆኑ አመራሮች መኖራቸውን አስታውቀዋል። በፋኖ ስም ኦሮሞን ላይ ያልተገባ ተግባር የሚፈጽሙ መኖራቸውንም አስታውቀዋል። ይህ አግባብ ባለመሆኑ እንደሚያወግዙ ገልጸዋል።
አቶ ሱልጣን የፋኖ አደረጃጀት የሚባል ትጥቅ ላይ የተመሰረተ እንቅስቃሴ ” አንድ በራሱ በህግ በተወሰነለት ድንበር ውስጥ በሚኖር ህዝብ ላይ ጦርነት ማወጅ ነው፤ በፍጹም ተቀባይነት የለውም”
የኦሮሞ ሕዝብ ትልቅ ቁጥር ያለው አንድ የኢትዮጵያ አካል መሆኑን አስታውሰው፣ ” አንድ የታጠቅ ኃይል በዚህ ህዝብ መካከል መንቀሳቀሱ ጣልቃ ገብነት ነው። የጎንዮሽ ግጭትም ሊያስከትል የሚችል አደገኛ አካሄድ ነው” ሲሉ ተቀባይነት የሌለውና በአስቸኳይ ሊታረም የሚገባው ጉዳይም መሆኑን አቶ ሱልጣን ያስረዳሉ።
“ዜናው ይፋ መሆኑን ተከትሎ በኦሮሚያ አማራዎች በሚኖሩበት ቦታ ሁሉ ህዝብ በጥርጣሬ እንዲመለከት እያደረገ ነው። መሰል አደረጃጀቶች ከወከጋም አልፎ በተለያዩ አካባቢዎች እንዳሉም መረጃዎች አሉ” ሲሉ የኦፌኮ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አስታውቀዋል።
አካሄዱ ተዋልዶና ተከባብሮ በፍቅር የሚኖረውን ህዝብ ለማጋጨት ካልሆነ በቀር ሌላ አንዳችም ውጤት እንደማያመታ ትኩረት ሰጥተው የተናገሩት አቶ ሱልጣን፣” በኦሮሚያ ውስጥም ሆነ በአጎራባች ክልሎች በሰላም መኖር የሚቻለው ህዝብን ከህዝብ በሚያጋጭ አደረጃጀት ሳይሆን፣ በመከባበርና በመስማማት ብቻ ነው” ሲሉ ውጤቱን በማየት ዕርምት እንዲደረግ መክረዋል።
“ሕዝብን ከሕዝብ ማጋጨት የጽንፈኞች ተግባር ነው” በማለት የኮነኑት አቶ ሱልጣን፣ “የግዛት ይገባናል ጥያቄ ካለ በህግና በህገ መንግስቱ አግባብ መጠየቅ ይበጃል። ሌሎችም ተመሳሳይ ጥያቄ ሊኖራቸው ይችላል” ብለዋል።
ህጋዊ ያልሆኑ ታጣቂዎች ለሰላማዊ ዜጎች ፈተና መሆናቸው በርካታ አብነት የሚቀርብበት ጉዳይ በመሆኑ ድርጅታቸው ቀደም ሲልም፣ ዛሬም ሆነ ነገ የትጥቅ ትግልን እንደማይደግፍም እግረ መንገዳቸውን አስታውሰዋል።
አቶ ሱልጣን ደጋግመው ያነሱት ” ወለጋ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ተመሳሳይ እንቅስቃሴ እንዳለ ይሰማል” የሚለውን ጉዳይ ነው። እንቅስቃሴው ከፖለቲካው በላይ የድህንነት ስጋት መሆኑን እንደሆነ ይገልጻሉ። በኦሮሚያ በስፋት ተቀላቅለውና ተዋልደው ለሚኖሩ የአማራ ተወላጆችም እረፍት የሚነሳ አደገኛ አካሄድ መሆኑን በመጠቀስ ለሰማዊ ዜጎች ሲባል አሁን ደግመው እንዲያስቡ ጥሪ ያቀርባሉ።
በኦሮሚያ ማንም ከማንም ሳይለይ በእኩልነት ለረዥም ዓመታት መኖራቸውን፣ አሁንም እየኖሩ እንደሆነ ያመልከቱት አቶ ሱልጣን፣ መንግስት የፖለቲኪአ ምህዳሩን ማጥበቡ አንዱና ትልቁ የአገሪቱ ችግር ቢሆንም ህዝብን ሰላም የሚነሳ፣ የሚያጋጭና የሚያጫርስ የትግል ስልት አግባብ እንዳልሆነ ገልጸዋል።
የፋኖ ኃይል ጫካ ካለው የኦነግ ሰራዊት ጋር አብረው እየሰሩ እንደሆነ መስማታቸውን ተጠይቀው ” እሱ የሁለቱ ጉዳይ ነው። እናን አይመለከትም” ብለዋል። ይህ ስለመሆኑ የኦነግ ሰዎች ማረጋገጫ ባልሰጡበት አግባብ ዘርዝር ጉዳይ መናገር እንደማይቻልም ገልጸዋል። በሳቸው ዕምነት አሁን የተጀመረው አካሄድ ግን ምንም ይሁን ምን ግጭት ከማስፋት የዘለለ ውጤት ሰላማያመጣ ወደ ውይይት ማምራቱ ሁሉንም ተጠቃሚ ያደርጋል ባይ ናቸው። መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት ለንግግር በሩን መክፈትም እንዳለበት አሳስበዋል።
በቴሌግራም ይከተሉን https://t.me/+f_kxmaPjD-9jYTdk