የምስራቅ ዕዝ ላይ በፉከራ የታገዘው የክህደት ጥቃት ከተፈጸመ በሁዋላ የትግራይን ሕዝብ እጅጉኑ የጎዳው ጦርነት ጠባሳው መታየት የጀመረው ጦርነቱ ካበቃ በሁዋላ ነው። አማራና አፋር ክልልም ቢሆኑ ጦርነቱ ለብልቧቸዋል። ትህነግ ሰራዊቱንና ድፍን የትግራይ ወጣቶችን ወደ አዲስ አበባ እየነዳ በመራው ጦርነት ከፉኛ የተጎዱት ሴቶች፣ ህጻናትና አረጋዊያን ናቸው። በተለይ ህጻናት ከትራውማ በተጨማሪ ለዓመታት ትምህርት ርቋቸው ድብርት ውስጥ እንደገቡ ማስንም አይክድም ወደፊት ሲረጋ ብዙ የሚያሙ ጉዳዮች ይፋ መሆናቸው አይቀርም።
ዩኒሴፍ ያነጋገረው የ13 ዓመት የትግራይ ታዳጊ፣ ” ትምህርት ቤት መሄድ ደስ ይላል ግን … ” ብሎ ዓይኑን ዕንባ ሞላው። ታዳጊው ከዚያ በሁዋላ ምን ብሎ ይሆን? ምን ይሁን ጭንቅላቱ ውስጥ ያለው? ምን ይሁን ተሸክሞ የሚያድገው? አፋር፣ አማራ፣ ኦሮ ሚያ፣ በተመሳሳይ ታዳጊዎች ምን ስሜት ይዘው እያደጉ ይሆን? ስንቶች በወገኖቻቸው ተፈረደባቸው? ይህን የሚያውቁ ያውቁታል። እውቅና የማይሰጡት በዩቲዩብ ትግል እንመራለን የሚሉት ከሰውነት የጎደሉት ብቻ ናቸው። የህጻናት ሞት በሚለጥፉበት የፌስ ቡክ ገጻቸው ጎን ለጎን ያለ አንዳች ሃፍረት የልጆቻቸውንና የሚስቶቻቸውን የልደት፣ የሰርግ፣ የሃኒሙን፣ የፒክኒክ፣ የበጋ ሽርሽር ወዘተ ፎቶ የሚለጥፉት ሞራል አልባዎች ናቸው። ለምነው ሊሞላቀቁ የሚፈልጉ እርመኞች ብቻ ናቸው ይህን ወነጀል ከመተወን በዘለለ ሌላ ሙያም ሆነ አሳብ የሌላቸው።
ትህነግ በወረራ ሲቆጣጠራቸው በነበሩ የአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የነበሩ 4ሺህ ትምህርት ቤቶች ወድደማቸውን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ማስታወቁ ማስታወስ ግድ ይላል። ቢሮው እንዳለው ከ1.8 ሚሊዮን በላይ ተማሪና አስተማሪዎች እንዲፈናቀሉ ተደርጎ ነበር። የወቅቱ አማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቅርበውት በነበረው ሪፖርት እንዳሉት የትምህርት ተቋማቱን መልሶ ለመገንባት ከፍተኛ ገንዘብ ያስፈልጋል። የሚገርመው አሉ የሚባሉት ወይም ተርፈዋል የተባሉት ከወደሙት የማይሻሉ መሆናቸው ነው። በክልሉ ካሉት ትምህርት ቤቶች ውስጥ 84 ከመቶ የሚሆኑት ከደረጃ በታች ስለሆኑ ለመማሪያ እንደማይሆኑ ይፋ ሲነገር በቁጭት መስራት ሲገባ የተረፉትንና የታደሱትን፣ አዲስ የተገነቡትን መልሶ ዱቄት የሚያደርግ ወነጀል አማራ ክልል መፈጸሙ መቼውንም የማይለቅ፣ አድሮ የሚጠዘጥዝ ሃዘን ነው።
ቀደም ሲል በትህነግ ወረራ፣ አሁን ደግሞ በክልሉ በተነሳ ቅጥ ያጣ የጠብ መንጃ ትግል፣ ለቀናት፣ ለሳምንታት፣ ለወራት፣ ለዓመት ሳይሆን ለዓመታት ወደ ትምህርት ቤት እንዳይሄዱ የተፈረደባቸውን የአማራ ክልል ታዳጊዎችና ህጻናት “በለጋነታቸው ሞት የተፈረደባቸው ህጻናት” እያሉዋቸው ነው። ልጆቹ ብቻ ሳይሆኑ በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት የትምህርት ተቋማቱ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ወድመዋል። ተዘርፈዋል። ሁሉንም ወንጀል የሚፈጽመውና የፈጸመውን አካል በየአካባቢው ያለው ህዝብ ጠንቅቆ የሚያውቀውና እውነተኛ ምስክርነት የሚሰጥበት በመሆኑ የወን ጉዳይ ካልሆነ በቀር ወንጀሉ ክርክር የሚነሳበት አይደለም።
“ከኮቪድ ወቅት ጀመሮ ቢሰላ ህጻናቱ የተጎዱት ከሶስት ዓመት በላይ ሊዘልቅ ይችላል፤ ይህን ክፍተት ማን ይሞላዋል?” ሲሉ የሚጠይቁ በትግል ስምም ይሁን በሌላ ህጻናትን ወደ ትምህርት ቤት እንዳይሄዱ መከልከል ዓለም ዓቀፍ ወንጀል ነው።
ቀደም ሲል ገንዘብ ሳይቀር በማዋጣት አማጺዎችን ሲረዳ የነበረና እንግሊዝ አገር የሚኖር የደሴ ተወላጅ ” ለአጭር ጊዜ ድጋፍ አድርጌ ንስሃ ገብቼ አርፌ ተቀምጫለሁ” ይላል። እሱ በሚኖርበት አገርና በዙሪያው መላው አውሮፓ መማር ግዳጅ መሆኑን ጠቁሞ “አገሬ ውስጥ ህጽናት በገዛ ወገናቸው እንዳይማሩ ተፈረዶባቸዋል። ይህ ወንጀል ነው። በጋራ ልንቃወመው ይገባል” ሲል አስተያየቱን አቅርቧል። እኔ ልጆቼን ሰዓት ጠብቄ ወደ ትምህርት ቤት እየወሰድኩና እየመለስኩ፣ ምን በሉ፣ ምን ጠጡ፣ ምን ለበሱ እያልኩ ሳማርጥላቸው፣ ወገኖቼ በአገር ቤት፣ በትውልድ ቀያቸው ትምህርት እንዳይማሩ ተሳትፎ የማደርግ ከሆነ ከሰውነት ተራ ወጥቻለሁ ማለት ነው” በማለት በንፅጽር ቤተሰብ ያላቸው፣ በተለይም ልጆች ያላቸው እንዲያስቡ ጥሪ አቅርቧል።
ስለ ትግሉም ሆነ ስለጦርነቱ አስተያየት መስጠት ብዙም ፈቃደኛ ያልሆነው ይኸው አስተያየት ሰጪ፣ በርካታ የሚያውቃቸው በተለያዩ ዓለማት የሚኖሩ ልጆች ያላቸው ለምን ዝምታን እንደመረጡ ለመረዳት እንደሚከብደው ጠቅሶ “ለአማራ ልጆች ማን ይድረስላቸው። ቤት በመቀመጥ በሽተኛ እየሆኑ ነው። ይህ ከወንጀሎች ሁሉ የከፋው ነው ” በማለት ህዝብ ብሄርና ዘር ሳይለይ እንዲወያይበት ጠይቋል።
በኢትዮጵያ ላይ አንድ ቀን ሳያሰለሱ በዩቲዩብ መርዝ ከሚረጩት አክቲቪስት ነን ባዮች መካከል ” ማታ ማታ ላይቭ ሳስተላለፍ ልጆቼ እየሰሙ ተረበሹብኝ። ተጨነቁብኝ” በማለት ዲሲ ወስጥ ከአንድ ግለሰብ ምድር ቤት ተከራይቶ እንደነበር፣ ይህንንም አሜሪካ ሄዶ ማየትና መስማቱን የሚገልጸው የሎንደኑ ነዋሪ፣ “ይህ የአማራ ትግል መሪ ነኝ የሚለውና የሚታወቀው የዩቲዩብ አታጋይ እንዴት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህጻናት ጉዳይ ግድ ሳይለው ቀረ? ሚስቱስ እንዴት ስም አለችው?” ሲል ለአብነት አንድ ሰው አንስቶ ይጠይቃል።
ሚስቱ እሱን ጎትጉታው ከተመሳሳይ ተግባሩ እንዳረቀችው አስታውሶ፣ ሚስቶች ማታ ምታ እየወጡ ጦርነትና ትርምስ የሚያውጁትን ባሎቻቸው ላይ ጫና እንዲፈጥሩ ጠይቋል። ህጻናትን ወደ ትምህርት ቤት እንዲሄዱ በሚክለክሉ አካላት ላይ እከሌ ከከሌ ሳይባል ዘመቻ እንዲጀመር ሁሉም ወገን ድምጽ ሊያሰማ እንደሚገባ አመልክቷል።
የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የሚመለከታቸውን ኃላፊ አነጋግሮ በሚልዮን ለሚቆጠሩት ህጻናት ሁሉም ዜጋ ሊያብላቸው እንደሚገባ የሚያሳስብ መረጃ አቅርቧል። መረጃውን ከስር እንዳለ አትመነዋል።
በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ኾነዋል፡፡ ተማሪዎቹ ከትምህርት ገበታ ውጭ የኾኑ ለቀናት፣ ለሳምንታት እና ለወራት ብቻ አይደለም ለዓመታት ኾኗል እንጂ፡፡
በልጆቻቸው ተስፋ ያደረጉ ወላጆች የተስፋቸውን ፍሬ በዘመኑ እንዳይበሉ እንቅፋት ኾኗል፡፡ ነገን ለማሳመር ተስፋ የሰነቁ ልጆች ያለ በደላቸው ከዕድሜያቸው ላይ ተሠርቀዋል፡፡
ከእኩዮቻቸው ጋር እንዳይወዳደሩ ኾነዋል፡፡ ከትምህርት ርቀው በቁዘማ እንዲኖሩ ተገድደዋል፡፡
ሕጻናት የመማር መብታቸውን ተነፍገዋል፡፡ በትምህርት ቤቶቻቸው እንዳይንቀሳቀሱ ገደብ ተጥሎባቸዋል፡፡ መምህራን ሠርተው እንዳይኖሩ ተደርገዋል፡፡
እናስተምራለን ባሉ መገፋት ደርሶባቸዋል፡፡ ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት የሚልኩ ወላጆች የግድያ ዛቻ ደርሶባቸዋል፡፡
ከአሚኮ ወቅታዊ ጋር ቆይታ ያደረጉት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) የመማር መብት መጣስ ከሕጻናት መብት ጥሰት ጋር ይያያዛል ነው የሚሉት፡፡
የነገዋን ኢትዮጵያን ለማሳመር የዛሬው ትውልድ ላይ መሥራት ግድ ይለናል፤ ዛሬ የሚገነባው ትውልድ የነገውን የኢትዮጵያ ገጽታ የሚያንጸባርቅ ነው ይላሉ፡፡
በአማራ ክልል የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ሕጻናት ወደ ትምህርት ቤት እንዳይሄዱ አድርጓል፡፡ በ2017 የትምህርት ዘመን ሰባት ሚሊዮን ተማሪዎችን እናስተምራለን ብለን አቅደን አፈጻጸማችን ዝቅተኛ ነው ይላሉ፡፡
ለትምህርት ዘመኑ ከወረሐ ነሐሴ/2016 ዓ.ም ጀምሮ ተማሪዎች እንዲመዘገቡ ጥረት ቢደረግም በሚፈለገው ልክ አልኾነም ነው የሚሉት፡፡ በጸጥታው ምክንያት ተማሪዎች ከትምህርት ርቀዋል፡፡
ትምህርት ቤቶችም ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ከትምህርት ገበታ ርቀው የቆዩ ተማሪዎች ወደ ትምህርት እንዲመጡ ጥረት እያደረግን ነው ብለዋል፡፡
በዘመናት መካከል፣ በተለያዩ ሀገራት እና ፖለቲከኞች የፖለቲካ ልዩነት ይኖራል የሚሉት ኀላፊዋ ትምህርትን ግን ለፖለቲካ መጠቀሚያ ማድረግ እና ትውልድን መጉዳት የተገባ አይደለም ነው የሚሉት፡፡
በግጭቱ ምክንያት ተማሪዎች እና መምህራን በሥነ ልቦና ተጎድተዋል ነው ያሉት፡፡ ዕድሜያቸው ባክኗልም ብለዋል፡፡
ልጆችን ከትምህርት ቤት ማስቀረት ሚሳኤል ከመወርወር ያልተናነሰ ጥቃት ነው፤ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመለሱ ሁሉም ሊያግዝ ይገባዋል ነው የሚሉት፡፡
እታገላለሁ የሚሉ አካላትም የሚታገሉት ለሕዝብ ከኾነ ሕጻናትን ያለ ሐጥያታቸው ጨለማ ውስጥ እንዲኖሩ መፍረድ የለባቸውም ነው ያሉት፡፡ በሕጻናት ሕይዎት ላይ መቀለድ የተገባ አይደለም ብለዋል፡፡
ሕጻናትን ከትምህርት ቤት አስቀርቶ መታገል ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የማይመጥን የትግል ስልት መኾኑንም አንስተዋል፡፡ የትምህርት ተቋማትን ከመዝጋት እና ተማሪዎች እንዳይማሩ ከማድረግ የበለጠ ጥፋት የለም ነው ያሉት፡፡
የትኛውም አካል ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዳይመለሱ የሚያደርገውን አካሄድ በቃህ ሊለው ይገባልም ብለዋል፡፡
“ሕዝቡ ልጆቼ እንዳይማሩ የሚከለክል ሁሉ ጠላቴ ነው ሊል ይገባል” ነው ያሉት፡፡ ሕዝቡ በትምህርት ጉዳይ የሚመጣበትን በቃህ ሊለው ይገባል፤ ትምህርት ቤቶችን መጠበቅም አለበት ብለዋል፡፡
አንዳንድ አካባቢዎች ላይ እንሞታለን እንጂ ድጋሜ ልጆቻችን ከትምህርት ገበታ ውጭ አይኾኑም እያሉ መኾናቸውንም አንስተዋል፡፡ ሁሉም ኅብረተሰብ በዚህ ልክ በቃችሁ ሊል ይገባል ነው ያሉት፡፡
ተማሪዎችን እናስተምር ያሉ መምህራን ችግር እንደደረሰባቸውም አንስተዋል፡፡ መምህር ራሱን እንደሻማ እያበራ ለሌሎች ሕይዎት የሚኖር ነው ብለዋል፡፡
ኅብረተሰቡ መምህራንን መጠበቅ እንደሚገባውም አመላክተዋል፡፡ ያለፈው ዓመት ይበቃል ዘንድሮ ተማሪዎች ሳይማሩ እንዲከርሙ መፍቀድ አይገባም ነው ያሉት፡፡
በትምህርት ላይ የሚደርስ ጉዳት በትውልድ ላይ ክፍተት የሚፈጥር መኾኑንም አንስተዋል፡፡ የትምህርት ስብራት የትውልድ ሥብራትን ይፈጥራል፤ ሁሉም ሊያወግዘው ይገባል፤ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችም ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ የኾኑበትን መንገድ በቃ ሊሉ ይገባል ነው ያሉት፡፡
ታጣቂ ኀይሎች መጠለያ ያደረጓቸው በርካታ ትምህርት ቤቶች መኖራቸውንም አስታውቀዋል፡፡ የትኛውም አካል በቃችሁ ብሎ ሊነሳ ይገባል ብለዋል፡፡
የሰበዓዊ መብት ተሟጋቾች በለሆሳስ ከመጻፍ ባለፈ በአደባባይ ወጥተው ማውገዝ አለባቸው ነው ያሉት፡፡ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታ ለመመለስ የሚያደርገውን ጥረት ሁሉም ማገዝ እንደሚገባውም አሳስበዋል፡፡ ትምህርትን መደገፍ ትውልድን መደገፍ፣ የነገዋን ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ መሥራት መኾኑንም አመላክተዋል፡፡