ተማሪ ብሩክ ግርማ ይበላል። የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ነው። ትውልዱና እድገቱ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሀድያ ዞን ሆሳዕና ከተማ ውስጥ ነው።
ይህ ታዳጊ ከመዋዕለ ህጻናት ጀምሮ ለፈጠራ ስራዎች ዝንባሌ እንደነበረው ይናገራል። በአካባቢው ያገኘውን የተለያዩ ቁሳቁሶችን በመጠቀም የፈጠራ ስራዎችን እየሰራ መቆየቱን ያስታውሳል። እናም ከልጅነቱ ጀምሮ በሮኬቶች እና በስነ ፈለክ ጥናት ፍቅር መውደቁን ነው ታዳጊው የሚገልፀው።
ተማሪ ብሩክ ግርማ በዋቸሞ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ11ኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን ከሀድያ ቴሌቪዥን ጋር ባደረገው ቆይታ በአሁኑ ወቅት የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ባዳረጉለት ድጋፍ የተለያዩ ቁሳቁሶችን በመጠቀም ሮኬት፣ድሮና ድማሚትን መስራቱን ገልጿል
በአሁኑ ወቅት የተለያዩ ሀገራት የመጨረሻ ደረጃ ቴክኖሎጂ ተጠቅመው የሚሰሩትን ወታደራዊ መሳሪያዎችን ማለትም ሮኬት፣ ድሮንና ድማሚትን ተማሪ ብሩክ ግርማ በትምህርት ቤት ሰርቶ የተሳካ ሙከራ አድርጓል።

ተማሪው የሰራው ሮኬት 1-3 ኪሎ ሜትር ድረስ የመወንጨፍ አቅም ያለው ሲሆን፤ ሌላው ድሮን ጠላትን መምታት የሚችል ሲሆን ደማሚት /Dynamite/ ደግሞ ከፎቅ ጀምሮ የተለያዩ ነገሮችን ማፋንዳት እንደሚችል ተናግሯል።
እንደ ተማሪ ብሩክ ገለጻ፤ እነዚህ የፈጠራ ስራዎች የራሳቸው የሆነ መቆጣጠሪያ ስርዓት ያለቸው ናቸው።
ከትምህርቱ ጎን ለጎን የፈጠራ ሥራውን የሚሰራው ተማሪ ብሩክ
የተለያዩ ድጋፍ ቢያገኝ የተሻሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን እንደሚሰራና ከራሱ አልፎ ለሌሎች ተማሪዎች የሥራ እድል ለመፍጠር እንደሚሰራ አብራርቷል።
ታዳጊ ተማሪው አድጎ በፈጠራ ስራዎች ህልሙን እውን ለማድረግ ሁሌም እንደሚሰራ ነው የተናገረው።
ተማሪ ብሩክ እየሰራ ያለው የፈጠራ ሥራዎች የሚደነቁ መሆናቸውን የገለፁት የትምህርት ቤቱ የፈጠራ ስራ አስተባባሪ መምህር ራመቶ ኃ/የሱስ ወደፊት በርካታ የፈጣሪ ስራዎችን መስራት እንደሚችል ተናግረዋል።
እንደዚህ አይነት ታዳጊዎች በትምህርት ቤት ውስጥ የፈጠራ አቅማቸውን እንዲጠቀሙበት ድጋፍ እንደሚደረግላቸውም ገልጸዋል።
እንደ መምህር ራመቶ ገለጻ፤ በቴክኖሎጂ ክህሎት ያዳበረ ተሰጥኦ ያላቸውን ወጣቶችን እና ሌሎች ግለሰቦችን በምክር፣ በገንዘብና በቁሳቁስ መደገፍና
ማበረታታት ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ይጠበቃል።
Wolaita communication