የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለስራ ስምሪት እና ለትምህርት ዕድል ዜጎችን ወደ ተለያዩ ሀገራት ለመላክ ውክልና እንደሰጠ ተደርጎ በማህበራዊ ትስስር ገጾች የተሰራጨው መረጃ ሐሰተኛ መሆኑን የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኦቢኤን/ ‘OBN Cyber Media’, Fact check’ አረጋግጧል::

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ ተቋማት የተጻፉ በማስመሰል ሀሰተኛ የውክልና ደብዳቤዎች በማዘጋጆት የተለያዩ አገልግሎቶችን እንሰጣለን የሚሉ ኣካላት እየተበራከቱ መጥተዋል።
ከዚህም ባለፈ ሰዎች የልዩ ዕጣ ወይም ሎተሪ ባለዕድል እንደሆኑ በማስመሰል የማጭበርበር ተግባራት ይፈጸማሉ።
ከነዚህም መካከል ”ካናዳና አሜሪካን ጨምሮ ወደ ተለያዩ አገራት እንልካለን ለዚህም ሕጋዊ ውክልና አለን” የሚሉ አካላት የማጭበርበር ድርጊት ይጠቀሳል።
ለዚህም ማሳያ የሚሆነው የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት አምባሳደር ታዬ አጽቀ ስላሴ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት ነሐሴ 14 ቀን 2016 ዓ.ም እንደፈረሙበት ተደርጎ እየተሰራጨ ያለው ሀሰተኛ የውክልና ደብዳቤ ይገኝበታል።

ደብዳቤው ለውጭ ሀገር የስራ ስምረት፣ የትምህርት ዕድል፣ ለፓስፖርት፣ ለቪዛ አገልግሎት ካርድና ለመመዝገቢያ ክፍያ ውክልና የተሰጠ በማስመሰል በሀሰት የተዘጋጀ ነው።
ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤቱ ከዚህ ቀደም በሚኒስቴሩ ስም ተመሳሳይ ሀሰተኛ መረጃዎች ይሰራጩ እንደበር ገልጾ መረጃዎቹ የተሳሳቱ መሆናቸውን ለኦቢኤን/‘OBN Cyber Media’, Fact check’ አረጋግጧል።
ማህበረሰቡ መረጃዎቹ ሐሰተኛ መሆናቸውን ተገንዝቦ በእንደዚህ አይነት የማጭበርበር ድርጊቶች እንዳይታለልና እራሱን ከአጭበርባሪዎች እንዲጠብቅ ጥሪ አቅርቧል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስም የሚወጡ የተሳሳቱ መረጃዎችን አስመልክቶ ተቋሙ በቀጣይ ዝርዝር ማብራሪያዎችን እንደሚሰጥ አስታውቋል።
የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ሕዳር 14 ቀን 2017 ዓ.ም የስራ ስምሪትን አስመልክቶ ባወጣው መረጃ በውጭ ሀገር ስራ ስምሪቱ ወደ አውሮፓና አሜሪካ ዜጎችን ለሥራ ለማሰማራት ለየትኛውም አካል ውክልና አለመስጠቱን መግለጹ የሚታወስ ነው።
ካናዳን ጨምሮ በተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት ለሥራ ዜጎችን እንልካለን፤ ለዚህም ከሚመለከታቸው አካላት ፍቃድ አግኝተናል በሚል በተለያዩ የማህበራዊ ትስስር ገጾች ህገ-ወጥ ማስታወቂያዎችን በማሰራጨት ህብረተሰቡን ላላስፈላጊ ወጪና እንግልት እየዳረጉ መሆኑን ሚኒስቴሩ አመልክቷል።
ለሥራ ዜጎችን እንልካለን በማለት የማጭበርበር ድርጊት የሚፈጽሙ አካላትን የሕግ ተጠያቂ ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝም አስታውቋል።
ዜጎች የሁለትዮሽ ስምምነት በተፈረመባቸው መዳረሻ ሀገራት የሥራ ዕድል ለማግኘት (lmis.gov.et) የተሰኘውን ማስፈንጠሪያ በመጠቀም የኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ስርዓት ላይ በመመዝገብ ደህንነቱ የተረጋገጠ የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ ሚኒስቴሩ አመልክቷል።

Via OBN