ኡጋንዳ በሰሜናዊ የሀገሪቱ ክፍል የብዙ ዜጎቿን ሕይወት የቀጠፈ ጦርነት በታሪኳ አሳልፋለች፡፡ ይህ ጦርነት የተካሄደው ጆሴፍ ኮኒ በሚባል ጦረኛ ግለሰብ ምክንያት ነበር፡፡ ይህ ግለሰብ የአካባቢውን ወጣቶች በተዋጊነት በመመልመል የዮቬሪ ሙሶቬኒ መንግሥትን ጦርነት በመግጠሙ የተነሳ ነበር ችግሩ የተፈጠረው፡፡
ባሕል፣ ወግ እና እሴት ሃብት ነው፡፡ ባሕል የአንድ ማኀበረሰብ የማንነት መገለጫ ነው፡፡ ባሕል ኀይል አለው፡፡ ባሕል አቅም አለው፡፡ ሰዎች በባሕላቸው ይደምቃሉ፤ በባሕላቸው ይዋባሉ፡፡ በዚህ ምክንያትም ሰዎች ባሕላቸውን ያከብራሉ፤ ይጠብቁታል፤ ይንከባከቡታልም፡፡
ስለ ባሕል ብዙ ማለት ቢቻልም በዚህ ጽሑፍ ግን ማንሳት የተፈለገው ሰዎች ባሕልን ይዳኙበታል የሚለውን ለማሳየት ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ ባሕል የጭንቅ ጊዜ መውጫ መንገድ በመኾንም ያገለግላል፡፡
ይህ ሊኾን የሚችለው ግን ለባሕል ተገቢውን ክብር ከሰጠነው ነው፡፡ ግርማ ሞገሱን ካላበስነው ነው፡፡ ከባሕሎች ውስጥ አንዱን ብቻ መዘን እንመልከት፡፡ ባሕላዊ የሽምግልና እርቅ ሥነ ሥርዓት፡-
የሰው ልጅ በኅብረት የሚኖር ነው፡፡ በማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ የፍላጎት መጣረስ ወይም ልዩነት ይኖራል፡፡ ለዚህ ደግሞ ሕዝቦች ሰላምን የሚያሰፍኑበት እና በጠበኞች መካከል እርቅ የሚያወርዱበት ባሕላዊ ልማዶች ያስፈልጋሉ፡፡ ከሀገራችን ወጣ ብለን አንድ አብነት እናንሳ፤ በሀገረ ኡጋንዳ አቾሊ ጎሳዎች ዘንድ የሚታወቀው ማቶ ኦፑት ባሕላዊ የእርቅ ሥነ ሥርዓት የብዙ ዓለማትን ቀልብ የሳበ የግጭት እና ጥላቻ ማስወገጃ ፍቱን መድኃኒት ነው፡፡
ኡጋንዳ በሰሜናዊ የሀገሪቱ ክፍል የብዙ ዜጎቿን ሕይወት የቀጠፈ ጦርነት በታሪኳ አሳልፋለች፡፡ ይህ ጦርነት የተካሄደው ጆሴፍ ኮኒ በሚባል ጦረኛ ግለሰብ ምክንያት ነበር፡፡ ይህ ግለሰብ የአካባቢውን ወጣቶች በተዋጊነት በመመልመል የዮቬሪ ሙሶቬኒ መንግሥትን ጦርነት በመግጠሙ የተነሳ ነበር ችግሩ የተፈጠረው፡፡
ኮኒ በርካታ ወጣቶችን በማገት በውጊያ አሰማርቷቸውም እንደነበር ይነገራል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ገና በዘጠኝ ዓመታቸው ከትምህርት ቤት ታግተው ተወስደው ለበርካታ ዓመታት በጦር ካንፖች እንዲኖሩ ከተደረገ በኋላ ለውጊያ ያሰማራቸዋል፡፡ በዚህ ግለሰብ አማካኝነት የተቋቋመው ቡድን የበርካታ ግለሰቦችን ሕይወት ቀጥፏል፡፡ በሴቶች ላይ ጾታዊ ጥቃት ፈጽሟል፤ ቤቶችን አቃጥሏል ፡፡
በትምህርት ቤቶች ላይ በመግባት በርካታ ተማሪዎችን እረሽነዋል፡፡ ይህ ጦርነት ብዙ ዓመታትን አልፎ የብዙዎችን ሕይወት ከቀጠፈ በኋላ በዮሪ ሙሶቬኒ መንግሥት አሸናፊነት ተጠናቀቀ፡፡ ከዚህ ጦርነት መጠናቀቅ በኋላ በጆሴፍ ኮኒ መሪነት የተዋቀሩት ወጣቶች ችግር ላይ ወደቁ፡፡
ያገቱት፣ የገደሉት እና የደፈሩት ማኅበረሰብ መካከል ላይ መቀላቀል ካለፈው ጦርነት በላይ ፈተና ኾነባቸው፡፡ በጦርነቱ ወቅት የራሳቸውን የጎሳ አባላት ሳይቀር ግፍ ፈጽመውበታል፡፡ የሠሩት ሥራ በቂም በቀልነት እንዲጠባበቁ አድርጓቸዋል ፡፡
ይህንን ችግር የሚፈታው ብቸኛው መፍትሔ ማቶ ኦፑት የተሰኘው በአቾሊ ጎሳዎች ዘንድ የሚታወቀው ባሕላዊ የእርቅ ሥነ-ሥርዓት ነበር፡፡ በዚህ ደም አፋሳሽ ጦርነት ላይ የተሳተፉ ወጣቶች ወደ ነበረ ሕይወታችን መመለስ እንፈልጋለን እና ይቅር በሉን ሲሉ ለአቾሊ ጎሳ ማኅበረሰብ መልዕክት በመላክ ተማጸኑ፡፡
ማቶ ኦፑት አውቀው በዓላማ ሳያውቁ በስህተት ወደ ጥፋት ቡድኑ ተቀላቅለው የነበሩ ወጣቶችን ለመመለስ ተስፋ ሰጣቸው፡፡
ለመኾኑ ማቶ ኦፑት ምንድ ነው? እንዴትስ ይከወናል? ማቶ ኦፑት የይቅርታ መንገድ ነው፡፡ ማቶ ኦፑት ቂምን ይሽራል፤ በቀልን ያስቀራል፤ ቁስልንም ይፈውሳል እና በማኅበረሰቡ ዘንድ ፍቱን መድኃኒት ነው፡፡
የቀደመ ግንኙነትን ወደ ነበረበት በመመለስ የሚታወቅ ነው፡፡ ደም አፋሳሽ ጦርነት እና ጥፋት ሲከሰት በኡጋንዳዊያን ዘንድ ማቶ ኦፑት ተግባራዊ ይደረጋል፡፡ የጎሳው መሪዎች በጋራ ኾነው የማቶ ኦፑት ሂደቱን ያስፈጽማሉ፡፡
ዋና ዓላማውም በተፈጠረው ጥፋት ሰዎች በጸጸት እና በቂም በቀልነት ስሜት እንዳይኖሩ ከመጥፎ ጠባሳ ተላቀው ሰላማዊ ኑሮን እንዲጀምሩ ማስቻል ነው፡፡
ኦፑት የዛፍ አይነት ነው፡፡ የዚህ ዛፍ ፉሬ ጣፋጭ ሻይ ለማዘጋጀትም ያገለግላል፡፡ በአቾሊ ጎሳዎች ዘንድ ከዚህ ዛፍ ፍሬ የሚዘጋጀው ሻይ የሰላም፣ የአብሮነት እና የፍቅር ተምሳሌት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ የእርቅ ሥነ-ሥርዓት በሚፈጸምበት ጊዜ የአቾሊ ጎሳዎች የሚጠጡትም ከዚህ ዛፍ የተዘጋጀውን ሻይ ነው፡፡ በማቶ ኦፑት ልማድ በግ ይታረድ እና ደሙን ከኦፑት ሻይ ጋር ይቀላቅሉ እና ይጠጡታል፡፡ ይህንን ማድረጋቸው ተፈጥሮ የነበረው ጥላቻ ታጥቦ እንደተወገደ ተደርጎ ይቆጠራል፡፡
ኦፑት ዕውነትን የማወቂያ ዋነኛ መንገድ ተደርጎም ይወሰዳል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በደል የፈጸሙ ሰዎች የፈጸሙትን ጥፋት አንድም ሳያስቀሩ እንዲናዘዙ የማቶ ኦፑት ልማድ ስለ ሚያስገድድ ነው፡፡ ማቶ ኦፑት ራሱን የቻለ ባሕላዊ ክዋኔ አለው፡፡
በሥርዓቱም መሠረት የዘመኑ የሀገሪቱ ባለሥልጣናት እና የጎሳው መሪዎች በተገኙበት የማቶ ኦፑትን ክዋኔ መሠረት አድርገው ወደ ማኅበረሰቡ በዕርቅ፣ በሽምግልና እና በይቅርታ እንዲቀላቀሉ ተደረገ፡፡ ከዚያ ቀን ጀምሮ በማቶ ኦፑት ልማድ መሠረት ቂም ይሽራል፣ ለመገዳደል ቀንን መጠበቅ ከዚህ በኋላ ያበቃል፡፡
ኡጋንዳዊያን በሰሜኑ ክፍል የነበረው እልቂት ከተፈጸመ በኋላ ወደነበሩበት የእርስ በእርስ ግንኙነት መመለስ የቻሉት በማቶ ኦፑት ድንቅ ባሕላዊ የዕርቅ ሥነ ሥርዓት አማካኝነት ነው፡፡ ዛሬ በሰሜን ኡጋንዳ የሰላም አየር ይነፍሳል፡፡ ምስጢሩ ደግሞ ለባሕላቸው ልዩ ትርጉም ሰጥተው በመተግበራቸው ነው፡፡
በኢትዮጵያስ በርካታ ማቶ ኦፑትን መሰል ሀገር በቀል ባሕሎች ምን እየሠሩ ይኾን?
በአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ የባሕል እሴቶች ልማት ባለሙያ ደርበው ጥላሁን ባሕላዊ የእርቅ ሽምግልና ከባሕል እሴቶች ውስጥ የሚመደቡ ናቸው ይላሉ፡፡ ሰላምን፣ መቻቻልን እና እርቅን በማምጣት ረገድ ሚናቸው ከፍተኛ ነው ባይ ናቸው፡፡
በኢትዮጵያ በርካታ ባሕላዊ የዕርቅ ሥነ ሥርዓቶች አሉ፡፡ ዘወልድ በሰሜን ወሎ እና ራያ፣ አበጋር በከሚሴ፣ ወፍ ለገስ በሰሜን ሸዋ እና በሌሎችም አካባቢ በርካታ ባሕላዊ የሽምግልና ሥነ ሥርዓቶች እንዳሉ ይጠቅሳሉ፡፡
እነዚህ ባሕሎች በየአካባቢያቸው ተደማጭ እና ቅቡልነት ያላቸው ስለመኾናቸውም ያነሳሉ፡፡ ይሁን እና ይላሉ ባለሙያው በጥናት የተረጋገጠ ባይኾንም የዘመኑ ትውልድ ለሽምግልና እና ለሽማግሌዎች ክብር እና ትኩረት በመስጠት በኩል እያነሰ የመጣ ይመስላል ነው ያሉት፡፡
ሽምግልና ድንበር የለውም ነገር ግን የኛ ሀገር የሽምግልና ሥነ ሥርዓቶች ብዙውን ጊዜ ከሰፈር እና ከአካባቢ የወጡ አይደሉም፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት በአቅም የጎለበቱ መኾን ነበረባቸው፡፡
ይህ የኾነው በመንግሥት ተቋማት በኩል የሚደረግላቸው ድጋፍ አናሳ ከመኾኑ የመጣ እንደኾነም ጠቁመዋል፡፡ ባለሙያው እንዳሉትም የኢትዮጵያ ባሕላዊ የሽምግልና ሥርዓቶች ሰላምን በማስፈን በኩል ድርሻቸው ከፍተኛ ቢኾንም ይህን ማድረግ ግን ይቀራቸዋል ይላሉ፡፡ በሰላም እጦት ውስጥ ላለችው ኢትዮጵያም መላ ቢዘይድ መልካም እንደኾነም አስገንዝበዋል።
ቀደም ብለን ያነሳነው የኡጋንዳ የባሕል ሽምግልና ሥነ ሥርዓትም ይህን በተግባር አሳይቷል፡፡ እኛም ’’ኢትዮጵያዊ ለዛ ያለው ማቶ ኦፑት ቢኖረን መልካም ነው’’ የኛ የኾኑት ባሕላዊ መልኮቻችን በዚህ ወቅት ለሰላም ሊረባረቡ ይገባል፡፡
Via አሚኮ