ተመራጩ የአሜሪካን ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2024 «የዓመቱ ሰው» ተባሉ። ትራምፕን በዓመቱ ሰውነት የመረጠው ታይም መጽሔት ነው። ዶናልድ ትራምፕን ለሁለተኛ ጊዜ ነው ታይም መጽሔት ይህን ስፍራ ያገኙት። ቀደም ሲል በ2018 ዓ.ም. ከሁለት ዓመታት በፊት በተካሄደው ምርጫ ማሸነፋቸውን ተከትሊ በተመሳሳይ «የዓመቱ ሰው» ተብለዋል።
ታይም መጽሔት «የዓለም በጣም ኃያል ሰው» ያላቸው የ78 ዓመቱ ትራምፕ ዳግም ወደ ሥልጣን የመጡበትን መንገድም በአሜሪካ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ብሎታል። ታይም መጽሔት ሰማያዊ ሱፍ ሙሉ ልብስ ከቀይ ክራቫት ጋር መለያቸው ነው ያላቸው ዶናድል ትራምፕ፤ የመጀመሪያ የሥልጣን ዘመናቸው በጎርጎሪዮሳዊው 2020 ዓ.ም. የተካሄደውን የምርጫ ውጤት ለመቀልበስ ካፒቶል ላይ በተሞከረው ጥቃት ሳቢያ በውርደት መጠናቀቁን አስታውሷል።
ይህን ጨምሮ የተለያዩ ክሶች የቀረቡባቸው ትራምፕ ለእጩ ፕሬዝደንትነት እንደሚቀርቡ መግለጻቸውን ተከትሎ ፍርድ ቤት ሲመላለሱ መክረማቸውን፣ ሆኖም በወንጀል መከሰሳቸው በምርጫው ድል ከማስመዝገብ እንዳላገዳቸውም አንስቷል። ትራምፕ ለድል ስኬታቸው የሕዝቡን መሠረታዊ ቅሬታዎች መጠቀማቸውን፤ ከታይም መጽሔት ጋር በነበራቸው ቃለመጠይቅ ገልጸዋል።
የታይም ዋና አዘጋጅ ሳም ጃኮብስ ስለውሳኔው ለአሜሪካው ኤንቢሲ መገናኛ ብዙሃን ሲገልጽ «በጥሩም ሆነ በመጥፎ ትራምፕ በ2024 በዜና ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድረዋል» ነው ያለው። ባለፈው ኅዳር በአሜሪካ በተካሄደው ምርጫ ዶናልድ ትራምፕ የዴሞክራቲክ እጩ ካማላ ሃሪስን በማሸነፍ 47ኛው የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሆነው ተመርጠዋል።
ለዓመቱ ሰው ምርጫም፤ ተፎካካሪያቸው ዴሞክራቷ ካማ ሃሪስን ጨምሮ፤ የሜክሲኮ ፕሬዝዳንት ክላውዲያ ሺንባም፣ እስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እና የሟቹ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ አሌክሲ ናቫልኒ ባለቤት ሩሲያዊቷ የኢኮኖሚ ባለሙያ ዩሊያ ናቫልኒ እጩዎች ነበሩ።
DW