ከግራና ከቀኝ የነበረው አውሎንፋስ ያስነሳው አዋራ ማብረድ የሚቻለው ሌላ አዋራ በማንሳት እንዳልነበር አሁን ላይ ተገልጧል። አሻራን ማኖር አዋራን ከማንሳት የሚለየው፣ አሻራ ተግባር ተኮር፣ ውጤት ተኮር በመሆኑ ነው። ይሄን መሪር ሀቅ ከቶም የሚክደው አይኖርም። ለዚህ እማኝ የሚሆነውም ኗሪው እንጂ አኗኗሪው አይደለም። ቀድሞ ከነበሩበት የወላለቀ መኖሪያ ቤት ተነስተው አሁን ያሉበትን ቤት ሲያወዳድሩት የሎተሪ እድል ያህል ነው ብለውታል። ለንፅፅሩ ከዚህ የበለጠ ገላጭ ቃል ሊገኝለት አይችልም።
ከሀዘን ድባብ ወጥተው በደስታ የተሞሉ የቀድሞ ካዛንቺስ ነዋሪዎች ዛሬ በሙሉ አፋቸው እየተናገሩት ያለው ሀቅ የትላንትን ፀፀት የሚሽር መሆኑን ልብ ይሏል።
“እንዲህ ዓይነት ቤትና ክብር በህይወቴ አያለሁ ብዬ አስቤም አላውቅም” ይላሉ ወይዘሮ ትርሃስ ተኪኤ። ከካዛንቺስ ተነስተው አሁን የገላንጉራ ነዋሪ ናቸው።

እኚህ እናት ካዛንቺስ ሊነሱ ነው በተባሉ ግዜ ሰማይ ምድሩ የተደፋባቸው መስሎ እንደታያቸው ለቀናት ተጨንቀው እንደነበርም አልሸሸጉም። ጩኸቱ የዋዛ አልነበረም። የበርካቶችን ጆሮ አግኝቶ ነበር። የብዙዎችን ትኩረትም ስቧል። በአንደበታቸው የሚተፉት ስለ መገንባት ሳይሆን ስለ መፍረስ ብቻ ነው። ወትሮም የፈረሰ ቤት አይፈርስም።
“ኢትዮጵያውያን የተሻለ ኑሮ ይገባቸዋል” የሚለውን እሳቤ በጥርጣሬ መነፅር የተመለከቱት ጥቂቶች አልነበሩም። ከዚህ እይታ ተነስተው የኮሪደር ልማቱ በሚያስደነግጥ ፍጥነት የአዲስ አበባን ገፅታ መቀየሩን እንኳ ለመቀበል ተቸግረው ነበር። አይኑን በፈቃዱ የጋረደ፣ ጆሮውንም አውቆ ለደፈነ የሚታይም ሆነ የሚሰማ ነገር አይኖርም።
“እልፍ ሲሉ እልፍ ይገኛል” እንዲሉ አበው ከቆሙበት ስፍራ ፈቀቅ ሲሉ የተሻለ ህይወት መኖሩን ይዘነጉትና ለዘመናት በቆሙበት ሆነው ይማረራሉ፣ አለፍ ሲሉም ተስፋን ሳይሆን ሞትን ብቻ ይመኟታል።

“በገላን የተሰጠኝን ቤት ሳይ ማመን አልቻልኩም” ይላሉ ወይዘሮ ትርሃስ። ማየት ማመን መሆኑን ሲገልፁ። በጆሯቸው የሰሙት ሽብር በአይናቸው ከተመለከቱት እውነታ ጋር ፍፁም ርቆ አገኙት። እድሉን “ሎተሪ” ከሚለው ሌላ ገላጭ ቃል አላገኙለትም። ለኚህ እናት ከካዛንቺዝ ውጪ ለኑሮ ሌላ ስፍራ ያለ አይመስላቸውም ነበር። እልፍ ሲሉ ያገኙት ቀዬ ግን መስፈርቱን ያሟላ፣ ደረጃውን የጠበቀ የመኖሪያ ቤት ብቻ አይደለም፣ ትምህርት ቤት፣ የጤና ጣቢያ፣ ወዘተ መሰረተ ልማቱ የተሟላለት አካባቢ መሆኑ ለኑሮ ምቹ እንደሆነ ይገልፃሉ።
የልማት መንደሩ ዜጎችን ወደ ምቹ እና የተሻለ ህይወት ያሻገረ ነው ሲባል ወሬ ለማሳመር ተብሎ የተነገረ አይደለም። እናቶች እንደመሰከሩት በቂ ምክንያት አለው። የገላን ጉራ የመኖሪያ እና የተቀናጀ የልማት መንደር 6500 ነዎሪዎችን የያዘ መኖሪያ መንደር ነው። 500 ለአቅመ ደካሞችን መመገብ የሚያስችል የምገባ ማዕከል፣ እንዲሁም ለ270 እናቶች የስራ እድል የፈጠረ የእንጀራ መጋገርያ ፋብሪካ አለው። መንደሩ ደረጃውን የጠበቀ የህጻናት መጫወቻ እና የህጻናት ማቆያ ይዟል። ለስፓርት አፍቃሪዎችም ሁለት የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች የያዘ ሲሆን አይን የሚስቡ አረንጓዴ ቦታዎችና መናፈሻዎችም ተገንብተዋል።
ይህን የተመለከቱ እናቶች እና አባቶች በደስታ እያነቡ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ክብርት ከንቲባዋን መርቀዋል።
የኮሪደር ልማት ከተማን ከማዘመን እና ለዜጎች ምቹ የሆነ አካባቢን ከመፍጠር ባሻገር ዘርፈ ብዙ ፋይዳ አለው። ኢንቨስትመንትን በመሳብ ለዜጎች የስራ እድል መፍጠሩን የገላን መንደር ትምህርት ሰጥቶ አልፏል። ጤናማ ያልነበረ መጨናነቅን በመቀነስ የተመቻቸ ዘና ያለና ቀልጣፋ ማበረሰብን መፍጠር መቻሉም ሌላ ትምህርት ነው።
የኮሪደር ልማቱ፣ የተወበችና የፀዳች የከተማን ከመፍጠር ባሻገር የዜጎችን የኑሮ እድገት አንድ ደረጃ ከፍ ያደረገ ተግባር ስለመሆኑ ዛሬ ላይ በኩራት ለመናገር በገላን መንደር ላይ ታይቷል።
(ምሥራቅ – ከወደካዛንቺስ)


