የሰው ልጅ ከምድር አልፎ የተለያዩ የህዋ ምርምሮችን ማከናወን ከጀመረ በርካታ አመታት ተቆጥረዋል፡፡ በዚህም እግሩን ጨረቃ ላይ በማሳረፍ ታሪክ መስራት ችሏል፡፡
ከዚያም አልፎ በማርስ፣ በፀሐይና በሌሎች ፕላኔቶች ላይ የሚያደርጋቸው ምርምሮች ዛሬም እንደቀጠሉ ናቸው፡፡
ሰሞኑን ከወደናሳ የተማው ዜናም የዚህ ማሳያ ነው፡፡ መረጃዎች እንደጠቆሙት፣ የናሳ መንኮራኩር ከመቼውም ጊዜ በላይ ለፀሐይ የቀረበ ጉዞ በማድረግ ታሪክ ሰርታለች፡፡
ነገሩ እንዲህ ነው፤
በፀሐይ ዙሪያ ለዓመታት ምርምር ሲያደርጉ የቆዩት የናሳ ተመራማሪዎች በቅርቡ “ከፀሐይ ጀርባ ያለው ሀይል ምድነው”፤ የሚለውን ምስጢር ለመረዳት አንድ ተልዕኮ ወስደው ምርምራቸውን ይጀምራሉ፡፡ በዚህም አንዲት መንኮራኩር አዘጋጅተው ወደስፍራው ለመላክ ይወስናሉ፡፡
ነገር ግን ይህ በቀላሉ የሚከናወን አይደለም፡፡ ምክንያቱም አካባቢው ማንኛውንም ነገር በሰከንዶች ሽርፍራፊ ወደፈሳሽ የመቀየር አቅም አለውና፡፡
ሆኖም ተመራማሪዎቹ ተስፋ ሳይቆርጡ ይህንን ሙቀት ለመቋቋም ያስችላል ያሉትን ዘዴ በመጠቀም ስራቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ከ12 ቀናት በፊት መንኮራኩሯን ወደስፍራው ይልካሉ፡፡
መንኮራኩሯም በፀሐይ የውጭ ምህዋር በኩል በማድረግ ወደፀሐይ በመጠጋት ከፍተኛ ሙቀት እና ጨረር ባለበት ስፍራ በማለፍ ታሪክ ሰርታለች፡፡
መንኮራኩሯ ይህንን ታሪካዊ ጉዞ የጀመረችው ከ12 ቀናት በፊት ሲሆን በትናንትው እለት ተልዕኮን በአግባቡ በመፈጸም መልዕክት መላክ መቻሏም ተነግሯል፡፡
ይህ ጉዞ ስለፀሐይ ከዚህ በፊት ከሚታወቁ ሚስጢሮች ሁሉ የበለጠ መረጃ ለማግኘት ትልቅ እድል እንደሚፈጥር ሳይንስቲስቶቹ ተስፋ አድርገዋል፡፡
ናሳ በፀሐይ ዙሪያ የሚያደርገውን ምርምር የጀመረው እአአ ነሐሴ 12 ቀን 2018 ሲሆን በነዚህ ጊዜያትም የተለያዩ ጥረቶችን አድርጓል፡፡
የናሳ የሳይንስ ዘርፍ ዳይሬክተር ዶክተር ኒኮላስ ፎክስ እንደተናገሩት የሰው ልጅ ለምዕተ አመታት ስለፀሐይ ሲያጠና ኖሯል፡፡ ነገር ግን በፀሐይ ምህዋር ዙሪያ ምን እንዳለ በተጨባጭ ለማየት አልቻለም፡፡
በመሆኑም አሁን በፀሐይ ምህዋር ዙሪያ ለመዞር የሚደረግው ጥረት ስለፀሐይ ከዚህ በፊት ከምናውቀው ሁሉ አዲስ ነገር ለማወቅ ትልቅ እድል የሚሰጥ ነው፡፡ ስለዚህ ፀሐይን በአግባቡ ለመረዳት በምህዋሯ ውስጥ ማለፍ ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው ነው፡፡
ይህ የፀሐይን ምህዋር የማጥናት እንቅስቃሴ ከተጀመረበት 2018 ጀምሮ 21 ጊዜ በአጠገቧ ለማለፍ የተቻለ ቢሆንም እንደአሁኑ በቅርብ ርቀት ላይ በምህዋሯ ውስጥ ለማለፍ የተሞከረበት ጊዜ የለም፡፡
በዚህ ጉዞ ከተሳካ ከፀሐይ 6 ነጥብ 2 ሚሊየን ኪሎሜትር ርቀት ላይ ማለፍ ይቻላል፡፡ ይህም ሩቅ ሊመስል ይችላል፡፡
ሆኖም እኛ የምንገኘው ከፀሐይ 152 ሚሊየን ኪሎሜትር ርቀት ላይ መሆናችንን ስንገዘነዘብ አሁን የምንሄድበት ቦታ ምን ያህል ለፀሐይ በቅርብ ርቀት ላይ እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ለምሳሌ በመሬትና በፀሐይ መካከል ያለው ርቀት አንድ ሜትር ቢሆን አሁን መንኮራኩሯ የምትደርስበት ርቀት 4 ሴንቲ ሜትር ርቀት ላይ ይሆናል ማለት ነው፡፡
አሁን መንኮራኩሯ የምትሄድበት ርቀት 1400 ዲሴ የሙቀት መጠን ይኖረዋል፡፡ ይህ ደግሞ የሚሄደውን ማንኛውንም የኤሌክትሮኒክስ መሳርያ ማቅለጥ የሚችል ነው፡፡
በመሆኑም ይህንን ለመከላከል የተላኩት የኤሌክትሮኒክስ መሳርያዎች 11 ነጥብ 5 ሴንቲ ሜትር ውፍረት ባለው የካርበን ንጥረነገር እንዲሸፈን ተደርጓል፡፡ ከዚህም ባሻገር በፍጥነት እንዲጓዝ መደረጉም ሙቀቱን ለመቀነስ አንድ አማራጭ ነው ተብሏል፡፡
በዚህ መሰረት የሰው ልጅ እስካሁን ከሰራቸው ተንቀሳቃሽ ነገሮች ይህ መንኮራኩር በዚህ ስፍራ ሲጓዝ ይበልጥ ፍጥነት አለው፡፡
በሰዓትም 430 ሺህ ኪሎሜትር እንዲጓዝ ተደርጓል፡፡ ይህ ማለት ከ30 ሰከንድ ባነሰ ጊዜ ከለንደን ኒውዮርክ መድረስ ይችላል ማለት ነው፡፡ ይህ ፍጥነት እውን ሊሆን የቻለው በአካባቢው ካለው የስበት ሀይል ጋር ተዳምሮ የተገኘ ነው፡፡
ለመሆኑ ፀሐይን መቅረብ ይህ ሁሉ ጥረት ለምን አስፈለገ?
ሳይንቲስቶች እንደሚሉት በፀሐይ የውጭኛው ክፍል ማለፍ የረጅም ጊዜ ሚስጢሮችን ለመፍታት የሚያስችል ነው፡፡ ለምሳሌ የፀሐይ ሙቀት በዚህ ደረጃ ከፍተኛ የሆነበት ምክንያት እስካሁን ሊታወቅ አልቻለም፡፡
በመሆኑም ይህንን ምስጢር መረዳት ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው ነው፡፡
በዌልስ የሥነ ከዋክብት ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ጄኒፈር ሚላርድ እንደሚሉት የፀሐይ የውስጠኛው ገጽ የሙቀት መጠን 6000 ዲ.ሴ ሙቀት አለው፡፡
ሆኖም የፀሐይ የውጭኛው ገጽ በሚሊየን ሴንቲግሬድ ሙቀት ሊኖረው ይችላል፡፡ ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ ለሚለው እስካሁን ምክንያት ማወቅ አልተቻለም፡፡
በዚህ የተነሳ ተልዕኮው የፀሐይ ሚስጢር ለመረዳት ትልቅ መፍትሄ ያመጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከፀሐይ ማግኔቲክ ሃይል የሚፈነጥቁ ቅንጣቶች ከመሬት የማግኔቲክ ሃይል ጋር ሲላተሙ ሰማዩ በከፍተኛ ብርሃን ይሞላል፡፡
ይህ ምን ያስከትላል የሚለውም እስካሁን አልታወቀም፡፡ በመሆም ስለፀሐይ መረዳት ለቀጣይ የሰው ልጅ የአኗኗር ስልት መሰረታዊ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል፡፡
የፀሐይ ኃይልን መረዳት፣ እንቅስቃሴዋን ማወቅ፣ የከባቢዋን የአየር ሁኔታ መገንዘብ፤ የፀሐይ ንፋስን ሁኔታ መረዳት ለእለት ተዕለት ህይወታችን እጅግ ወሳኝ መሆኑን ዶክተር ሚላንድ ይናገራሉ፡፡
በዚህ የተነሳ ተመራማሪዎች ያሰቡት ተሳክቶላቸው የዘንድሮን የገና በዓል በአዲስ ግኝት አድምቀዋል፡፡
Via Gazett plus