የትህነግ ጉዳይ እያደር እየከረረ ነው። በጦርነት እሳትና ጦርነቱን ተከትሎ በተፈጠሩ ቀውሶች እየተለበለበና በመቶ ሺህ የሚቆጠር ህይወት የገበረውን የትግራይ ህዝብ መሪ አድርጎ ራሱን የስየመው ትህነግ፣ ከጦርነቱ ማብቃት በሁዋላ አተካራ ውስጥ መግባቱ ይታወሳል። በመለስተኛ መነቃቀፍ የተጀመረው ልዩነት ጠንክሮ ትህነግ ለሁለት መከፈሉ ይፋ ከሆነ በሁዋላ የሚሰማው አምባጓሮ “ነገሩ ወዴት ወዴት እየሄደ ነው?” የሚያሰኝ ሆኗል።
ራሱን ” የትግራይ ታቦት”፣ የትግራይ ህዝብ ብቸኛ እጣ ፈንታ አድርጎ የሚያየው ትህነግ፣ አቶ ጌታቸው የሚመሩትን ትህነግ ” ከሃጂ፣ ባንዳ” አድርጎ በመሳል፣ ከስልጣን ለማስወገድ የህዝብ ድጋፍ መተየቁን ተከትሎ ነው አቶ ጌታቸው የሚመሩት ቡድን ” አማጺና ቂመኛ” ሲል ምላሽ የሰጠው።
” ከፌደራል መንግስት ስልጣን እንዲቸረው የሚለምን አማፂ እና ቂመኛ ቡድን ሌሎችን በባንዳነትና እና በክህደት ለመፈረጅ መድፈሩ አስደማሚ ነው” የሚል ሃረግ ያሰፈረበት በየአቶ ጌታቸው ረዳ ትህነግ መግለጫ ፣ ይህንኑ ቡድን የትግራይ ህዝብ እንዲታገለውና ለጊዚያዊ አስተዳደሩ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቋል።
በእነ ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል የሚመራው የትህነግ ማእከላዊ ኮሚቴ ታህሳስ 2/2017 ዓ.ም ላወጣው መግለጫ መልስ የሰጠው በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው የትህነግ ማዕከላዊ ኮሚቴ፣ ” በዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል የሚመራው ትህነግ ጊዚያዊ አስተዳደር ቃሉን አጥፏል፤ በአጭር ጊዜ ልኩን ለማስገባት በማካሂደው ትግል ህዝቡ ከጎኔ ይቁም የሚል የሚያስደምም መግለጫ ታህሳስ 2/2017 ዓ.ም በመገናኛ ብዙሃን አሰራጭቷል “በማለት የአቶ ጌታቸው ቡድን ባሰራጨው የጽሁፍ መግለጫ መልስ ለመስጠት ስላለነሳሳው ጉዳይ አንኳር ጉዳይ ይጠቅሳል።
” አማፂ እና ቂመኛ ቡድን ” ተብሎ የተገለፀው በደብረፅዮን ገ/ሚካኤል የሚመራው ትህነግ ” የፌደራል መንግስት የጊዚያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት በሁለት ሳምንት እንደሚነሳ ቀጠሮ ተሰጥቶኛል ” በማለት ቀደም ሲል የተሳሳተ መረጃ ይሰጥ እንደነበር ያስታወሰው መግለጫ፣ ይህ ሃሰት ሳያንሰው አሁን ደግሞ ” ጊዚያዊ አስተዳደሩን በአጭር ጊዜ መልክ ለማስያዝ ወሰኜ ቃል ገብቻለሁ፤ ተከተሉኝ የሚል አዲስ የክተት ጥሪ አቅርቧል” ሲል በአቶ ጌታቸው የሚመራው ትህነግ ገልጿል።
“የዚህ አማፂ እና ቂመኛ ቡድኑ አካሄድ ለህዝብ አዲስ አይፈለም ” ያለው መግለጫው ቡድኑ ከፌደራል መንግስት ጋር የሚነጋገረው እና የሚስማማው ሌላ፣ ለትግራይ ህዝብ የሚለው ደግሞ ሌላ እንደሆነ አስረድቷል።
” ከፌደራል መንግስት ስልጣን እንዲቸረው የሚለምን አማፂ እና ቂመኛ ቡድን ሌሎችን በባንዳነትና እና በክህደት ለመፈረጅ መድፈሩ አስደማሚ ነው ” ሲል በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው ህወሓት ገልጿል።
” አማፂ እና ቂመኛ ቡድኑ የትግራይን ህዝብ ከፌደራል መንግስት የሚያጋጭ አቅጣጫ እየተከተለ መሆኑ ያወጣው መግለጫ አመላካች ነው ” ሲል መግለጫው ቡድኑ የያዘውን አቋም ዘርዝሮ ኮንኗል። ጨዋታ እየቀያየረ እንደሚያምታታም አመልክቷል።
ቲክቫህ የተረጎመው መግለጫ እንደሚያስረዳው የደብረጽዮን ቡድን “ህዝቡ በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ላይ እንዲያምፅ የሚቻለውን ሁሉ እያደረገ ነው” በሚል ከሷል። ከፌደራል መንግስት በድብቅ ” የውጭ ሽምጋይ ሳያስፈልገን ጉዳያችን ብቻችን መጨረስ እንችላለን ” በማለት ስልጣን እንደሚለመንም አብራርቷል።
” ቡድኑ ከስልጣን ውጪ የትግራይ ህዝብ ጉዳይ እንደ ጉዳዩ የማይቆጥር ራስ ወዳድ ነው” ሲል አቶ ጌታቸው የሚመሩት ትህነግ አብጠልጥሎታል። አያይዞም ” ለስልጣን ሲል ተፈናቃዮች ወደ ቄያቸው እንዳይመለሱ የመከልከል እና የማደናቀፍ ስራውን ቀጥሎበታል ፣ ዴሞብላይዜሽን (DDR) እንዲደናቀፍ ሴራዎች እየሸረበ ነው ” ሲል በድብቅ እየሆነ ያለውን አጋልጧል።
” አማፂ እና ቂመኛ ቡድኑ ቃሉ እና ተግባሩ ለየቅል ናቸው ፤ የህዝብ ችግር እና መከራ እንዳይፈታ በማወሳሰብ እንደ ምክንያት ተጠቅሞ ህዝብን እና መንግስት በማቃቃር በአመፅ ስልጣን ላይ ለመቆየት ሙጥኝ ያለ ፀረ ህዝብ ነው ” ሲል ፈርጆታል።
የትግራይ ህዝብ ጊዚያዊ አስተዳደሩ የተሰጡት አስተዳደራዊ ፣ ፓለቲካዊ ተልእኮዎች በተሰጠው ጊዜ አጠናቅቆ በህዝብ የተመረጠ መደበኛ መንግስት እንዲኖር የሚደረገው ትግል በመደገፍ ” አማፂ እና ቂመኛ ” ሲል የጠራውን የነ ደብረጽዮን (ዶ/ር) ቢድን ” የሚያካሂደውን አፍራሽ ተግባር በፅኑ እንዲቃወመውና እንዲያመክነው ጥሪውን አቅርቧል።
ከትላትና በስቲያ በደብረፅዮን ገ/ሚካኤል የሚመራው የትህነግ ማእከላዊ ኮሚቴ ፤ በምክትል ሊቀመንበር ጌታቸው ረዳ የሚመራውን ትህነግ ” በትግራይ ህዝብ ብሄራዊ ክህደት የፈፀመ ቡድን ” ሲል መፈረጁ ይታወሳል።
አቶ ጌታቸው ረዳ እንዲሁም ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል በተገኙበት ከቀናት በፊት በአዲስ አበባ ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ የመሩት ውይይት ቢደረግም ወደ መቐለ ከተመለሱ በኃላ ጠንከር ባሉ መግለጫዎች አንድ ሁለት እየተባባሉ ነው።