ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ወደ አንካራ የተጉዙት በአዲሱ ኤር ባስ ነው። በጉዟቸው ይዘው የሄዱት ሚዲያን ጨምሮ በርካታ ባለስልጣናትን ነው። በቪዲዮ እንደታየው ውይይቱ ላይ አብይ አህመድ ብቻቸውን አለነበሩም። ይህ የሆነው በልማድ እንደሆነ አድርጎ ማሰብ የዋህነት እንደሆነ ዘግይተው አስተያየት የሰጡ እየገለጹ ነው።

የአሁን ፕሬዚዳንት ታዬ አቅጸስላሴ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እያሉ የጀመሩት ድርድር ሲቋጭ በዚህ መጠን ሰፊ ታዛቢዎች እንዲጓዙ መደረጉ ለታሪክም፣ ለምስክርነትም እንደሆነ የሚናገሩ ” ስምምነቱን አስመልክቶ ስጋት የለም” ባይ ናቸው።
ሁለቱን መሪዎች ያነጋገሩት እርዶጋንን የሰጡትን መግለጫ ቃል በቃል ጠቅሶ አልጀዚራ “ይሄ ታሪካዊ ስምምነት በዓለም ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ያላት ላንድ ሎክድ ሃገር /የባህር በር አልባ/ የሆነችውን ኢትዮጵያ አክሰስ ቱ ዘ ሲ/ የባህር በር ባለቤትነትን/ የሚያረጋግጥላት ነው ” ሲል ዘግቧል። ከዚህ አንጻር ምን ችግር ታይቷቸው እንደሆነ ማስረዳት የማይችሉ ቡድኖችና ወገኖች ” ኢትዮጵያ ተሸነፈች” ሲሉ ያማርራሉ። መንግስትን ቆዳውን እየገፈፉ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ የስድብ ዶፍ እያወረዱ ነው።
የህግ ባለሙያው አቶ አንዷለም ቡከቶ ገዳ ስምምነቱን አስመልክቶ “እናንተ ገብቷችሁ እኔ ያልገባኝ ነገር ካለ አስረዱኝ!” ሲሉ የሚከተለውን በፌስ ቡክ ገጻቸው ጽፈዋል። እንዲህ ይነበባል።
“በኤርዶጋን አስማሚነት ሶማሊያና ኢትዮጵያ ያደረጉትን ስምምነት አየሁት። ቀድሞ ከሶማሊላንድ ጋር በተደረገው ስምምነት ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ለ50 አመት የሚቆይ እራሷ የምታለማው የባህር በር በሊዝ ታገኛለች የሚል ነበር።አሁን የተደረገው ስምምነት ከዋናዋ ሶማሊያ በሊዝ እና በሌሎች አማራጮች የባህር በር የምትጠቀምበትን መንገድ ታገኛለች: ሶማሊያ የኢትዮጵያን የባህር በር አስተማማኝ እና ዘላቂ በሆነ መንገድ አክሰስ የማድረግ መብቷን ታከብራለች ለዚህም አስፈላጊውን ታደርጋለች የሚል ነው። ደም ካልተፋሰስን የባህር በር ምን ይሰራል ካልሆነ በቀር ይሄኛው ስምምነት ችግሩ ምንድነው!? እናንተ ገብቷችሁ እኔ ያልገባኝ ነገር ካለ አስረዱኝ! ”
ማት ብርያን የሚባሉት የአፍሪቃ ቀንድ ተንታኝ ለቪኦኤ ሲናገሩ ስምምነቱ ኢትዮጵያ ያሸነፈችበት ይመስላል ብለዋል። የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ጦር ከሶማሊያ እንዲወጣ ቢወሰን እንኳ ኢትዮጵያ ተግብራዊ ስለማታደርገው ከሽንፈት ይልቅ መቀበሉ እንደሚሻል መምረጣቸውንም ገልጸዋል። የህግ ባለሙያው ሶማሊያዊው ጉሌድ አህመድም ለቪኦኤ ሲናገሩ ሚዛኑ ወደ ኢትዮጵያ እንደሆነ አመልክተዋል።
በርካታ ሰዎች የሚጠይቁት ኢትዮጵያ እንድተሸነፈች አድረገው የሚያቀርቡት ወገኖች ማስረጃዎችን አጣቅሰው የሽንፈቱን ነጥብ ማስጨበጥ አለመቻላቸውንና ጉዳዩን በአመክንዮ የመመልከት ፍልጎት ያጡበትን ምክንያት ነው።
ኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘቱና የጦር ቤዝ መመስረቷ በአውሮፕና በመካከለኛው ምስራቅ ፖለቲካ ላይ እጅግ ተደማጭ እንደሚያደርጋት፣ በዚህም ተደማጭነቷ በርካታ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንደምታገኝበት እየታወቀ ተቺዎቹ ጉዳዩ እንደ ባዕድ ለማየት የሞከሩበት አግባብም በሚያገናዝቡትና መረጃዎችን መመርመር በሚችሉት ዘንዳ ግርምት ፈጥሯል።
መንግስትን መጥላትና ብሄራዊ ጥቅምን መገዳደር ፍጹም የማይገናኙ ጉዳዮች እንደሆኑ በተደጋጋሚ የሚገልጹ፣ ለጊዜው በውል የታወቀ ጉዳይ ባይኖርም፣ “ከሶማሊ ላንድ ጋር የተደርገው ስምምነት ምንም ይሁን ምን፣ ዋናው ጉዳይ የባህር በር ባለቤት መሆን ከሆነ ግምገምው ስኬቱ ላይ እንጂ ሌላ ጉዳይ ላይ ሊሆን አይገባም” የሚል ምልከታ አላቸው።
የሶማሌላንድ የሃርጌሳ ወደብ አዛዥና ናዛዧ ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ ናት፤ የንግድ ጉዳይን ከኢመሬትስ ጋር ውል ገብቶ ማሳለጥ ይቻላል የሚሉ፣ ” በግፍ ተቆልፎብን፣ ባህር አልባ ሆነን፣ ስለ ባህር ጉዳይ ማንሳት ወንጀለኛ ያደረጋቸው ህዝብና አገር፣ ዛሬ ከወሬ አልፎ የባህር በር የሚያገኙበት የወራት ጊዜ እንደቀረ ሲነገረው እንዴት ተቃውሞ ይሰማል” በማለት ጥያቄያቸውን በሃዘን ይገልሳሉ። አያይዘውም “ምናችንን ነው የታመምነው” ሲሉ በዚህ ደረጃ በጠላት አስተሳሰብ የተዋቀረ ስነልቦና የተላበሱ ዜጎች መፈጠራቸውን ይጸየፉታል።
የሶማሊያ እና የኢትዮጵያ መሪዎች አንዳቸው ለሌላኛቸውን ሉዓላዊነት ፣ አንድነት ፣ነፃነት እና የግዛት አንድነት ለማክበር ቁርጠኝነታቸውን ገልጸው ባደረጉት ስምንት ሰዓት የፈጀ ውይይት የተስማሙባቸው አንኳር ነጥቦች
- በወዳጅነት እና በመከባበር መንፈስ ልዩነቶችን እና አከራካሪ ጉዳዮችን በመተው ፤ በመተጋገዝ ለጋራ ብልጽግና ለመስራት ተስማምተዋል።
- ሶማሊያ በአፍሪካ ህብረት ተልዕኮ ውስጥ የኢትዮጵያ ወታደሮች ለከፈሉት መስዋዕትነት እውቅና ሰጥታለች።
- ኢትዮጵያ የሶማሊያን የግዛት አንድነት ባከበረ ሁኔታ የባህር በር ተጠቃሚ መሆኗ / ወደ ባህር እና ‘ ከ ‘ ባህር / ሊያስገኝ የሚችለው ልዩ ልዩ ጥቅም ላይ ተማምነውበታል።
- ሁለቱንም ተጠቃሚ ባደረገ ሁኔታ የንግድ ውል ይታሰራል።
- ኢትዮጵያ አስተማማኝ፣ ደህንነቱ የተጠበቀና እና ቀጣይነት ያለው ዘላቂ የባህር በር መዳረሻ አክሰስ ቱ ዘ ሲ እንዲኖራት ስምምነት ላይ ተደርሷል ፤ ይህም በሉዓላዊ የሶማሊያ መንግሥት ስልጣን ስር የሚተገበር ነው።
ይህ ስምምነት አንኳሩ ሲሆን በየካቲት ዝርዝር ጉዳዩ ይፋ ይሆናል። ብዙዎችን ያላስማማውና ” እስኪ እኛ ያላግባን እናንተ የገባችሁ ካለ አስረዱን” ሲሉ እንዲማጸኑ ያደረጋቸው ይህ አንኳር ስምምነት ነው።
“ የፈረሙት ሁለቱ አገራት ናቸው፣ እኛ ሶማሊላንድ ነን”
በአንካራው ስምምነት ዙሪያ የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት አብዲራህማን ሞሐመድ አብዱላሂ (ኢሮ) ዋዳኒ ፓርቲ ቃል አቀባይ ሞሐመድ ፋራህ አብዲ የሶማሌላንድ መንግሥትን አቋም ለቢቢሲ ሶማሊኛ ተናግረዋል።
ቃል አቀባዩ ፤ ” የፈረሙት ሁለቱ አገራት ናቸው፣ እኛ ሶማሊላንድ ነን። ሁለቱ ወንድማማች አገራት የራሳቸውን ስምምነት ነው የተፈራረሙት። እነሱ ተነጋግረው ከስምምነት ላይ መድረሳቸው የተለመደ ነገር ነው። እኛን የሚመለከት አይደለም ” ብለዋል።
በተጨማሪ ቀደም ሲል በሶማሊላንድ ሥልጣን ላይ የነበረው መንግሥት ከኢትዮጵያ ጋር የተፈራረመው የመግባቢያ ሰነድ (MoU) ያለበትን ሁኔታን በተመለከተ ተናግራዋል።
ሞሐመድ ፋራህ ፥ ” ገና ሥልጣን መረከባችን ነው፤ ከኢትዮጵያ ጋር የተደረገውን ስምምነት አልተመለከትነውም። ነገር ግን የምናየው ይሆናል፤ አይተነው የሶማሊላንድን ጥቅም የሚያስጠብቅ ከሆነ እንሠራበታለን፤ ካልሆነ ግን የሚቀር ይሆናል። ስለዚህ ምን እንሚሆን ለማወቅ መጠበቅ አለብን፣ ከዚያ በኋላ ውሳኔ ይሰጥበታል ” ብለዋል።
በዚህ የሞሐመድ ፋራህ መግለጫ መሰረት ከሶማሊላንድ ጋር ስለሚኖረው ቀጣይ ጉዳይ ምንም የተሰጠ ፍንጭ የለም። ይልቁኑም ሃርጌሳ ወደብ ላይ ኢትዮጵያ ቢሮ ከፍታ በይፋ ስራ መጀመሯን ከቀናት በፊት አስታውቃለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሰብ ላይ ሻዕቢያ በማንገራገሩ ወደ ሶማሊላንድ ካመሩ በሁዋላ ጅቡቲ የታጁረን ወደብ እንደምትሰጥ በይፋ አስታውቃለች። ሶማሊያም አሁን ስምምነቷን ገልጻለች። ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም የሚበጀው እንዲፈጸም የተኬደበት አግባብ ኢትዮጵያን ከዕስር ካላቀቀ ምን ተፈልጎ ይህ ሁሉ ውግዘት እንደሚወርድ ለመረዳት ያስቸግራል። እንደ ኢትዮጵያዊ እንዲህ ያለውን በገዛ አገር ላይ የሚሰነዘነዘር ዘመቻ ከማሳፈርም በላይ አንገት የሚያስደፋ ነው።
አሁን የፈሉትን ብንተዋቸው፣ በስም የሚታወቁቱ ህዳሴ መጨጡን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልክ ደውለው ድርድሩ ላይ ጣልቃ በመግባት ግድቡ እንዲሸጥ መመሪያ ሰጡ፣ ግብጽ ሄደው ተፈራረሙ ወዘተ የሚሉ ዘገባዎችን ሲያሰሙን የነበሩትን ” የህዳሴ ግድብ አልተሸተም እኮ። ለምን ትዋሻላችሁ?” የሚል ባለመኖሩ “ለዛሬ ለፍልፎ ማደር” ሙያ ሆኗል። አሁንም የሶማሊያው ስምምነት ተመሳሳይ እንደሚሆን ይጠበቃል።
ተመድ የአንካራው ስምምነት በቀጣናው ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት ለማምጣት የሚያስችል መልካም እርምጃ መሆኑን ገለጸ።
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት እና ተቋማት የአንካራው ስምምነት በቀጣናው ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት ለማምጣት የሚያስችል መልካም እርምጃ መሆኑን አስታውቀዋል።
በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እና መረጋጋት ለማስፈን ለሚደረገው ጥረት ድጋፋቸውን እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በተርኪዬ አደራዳሪነት ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የደረሱበትን ስምምነት አድንቋል።
የተቋሙ ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪች በወዳጅነት እና በመከባባር መንፈስ የተደረገው ውይይት መልካም ጅማሮ እንደሆነ ገልጸዋል።
በቀጣይ የሚካሄደው የቴክኒካል ውይይት የተሻለ ውጤት ይዞ እንደሚመጣ እምነቴ ነው ብለዋል።
ተርኪዬ ሀገራቱ ስምምነት ላይ እንዲደረስ ለተወጣችው ሚና ያደነቁት ቃል አቀባዩ፤ ተመድ የውይይት ሂደቱን በየትኛውም መንገድ ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን አመልክተዋል።
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በቱርኪዬ አደራዳሪነት ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የደረሱበትን ስምምነት አድንቃለች።
የሀገሪቷ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስምምነቱ ተግባቦት እና ውይይትን ለማጠናከር የሚያስችል ትልቅ እርምጃ መሆኑን ገልጾ፤ በአፍሪካ ቀንድ መረጋጋት እና ገንቢ ትብብር ለመፍጠር አስተዋጽኦ ያደርጋል ብሏል።
ውይይቱ በቀጣናው እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰላም እና ልማትን ለማረጋገጥ የተወሰደ በጎ እርምጃ መሆኑንና ስምምነቱ ሁለቱ ሀገራት የጋራ ጥቆሞቻቸውን ባከበረ መልኩ እንዲለሙና እንዲበለጽጉ በር እንደሚከፍት አመልክቷል።
ሚኒስቴሩ ተርኪዬ ለአንካራው ስምምነት ለተወጣችው የአደራዳሪነት ሚና አድናቆቷን ገልጿል።
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከኢትዮጵያና ሶማሊያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ትብብር ለማጠናከር እንደምትሻ የገለጸች ሲሆን በቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን በቁርጠኝነት እንደምትሠራም አስታውቃለች።
በተያያዘም የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአንካራ ስምምነት ለአፍሪካ ቀንድ ሕዝብ መረጋጋትን ለማምጣት የሚያስችል ትክክለኛ እርምጃ ነው ሲል ገልጿል።
በቀጣይም ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ውይይታቸውን በመተማመን የአጋርነት መንፈስ እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርቧል።