በስምጥ ሸለቆውና ዳርቻው ያለን ልብ እንበል
(ክፍል ሁለት)
ሁኔታው በኢትዮጵያ ውስጥ በማንኛውም ሰዓት ሊፈጠር ይችላል፤ በተለይ የስምጥ ሸለቆን ታከው የሚገኙ ከተሞች፤ ይህ መረጃ አስፈላጊ በመሆኑ ለሌሎችም ያካፍሉ፤ ያዳርሱ፡፡…
==የመሬት መንቀጥቀጥ በምስራቅ አፍሪካና በኢትዮጵያ==
አብዛኛውን ጊዜ ዶ/ር አታላይ አየለ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በጂዮ ፊዚክስ ስፔስ ሳይንስ አስትሮኖሚ ተቋም የመሬት መንቀጥቀጥ ባለሙያ የስጋት አስተያየታቸውን በሬድዮ ሲሰጡ እንሰማለን፤ እስኪ ለዛሬ ስጋታቸውን እንጋራ፡፡ ከክፍል አንድ የቀጠለ…
በምስራቅ አፍሪካ አካባቢ ለሚፈጠረው መሬት መንቀጥቀጥ መንስኤው ምንድን ነው? ካልን ከመሬት ከርስ በተለያየ መጠን እና ሁኔታ ወደላይ የሚወጣ ቅልጥ አለት አለ፡፡ ይህ የተለያየ መጠን ያለው ቅልጥ አለት ወደላይ ለመውጣት በሚያደርገው ግፊት የሚፈጠረው ውጥረት የመሬት መንቀጥቀጦችን ይፈጥራል፡፡ እሳተ ገሞራዎችም ይፈነዳሉ፡፡ በእንዲህ አይነት ሁኔታ ክስተቱ እየተደጋገመ ሲሄድ የመሬት ቅርፊተ አካል(Crust) እየተደረመሰና እየሳሳ በመሄድ ለስምጥ ሸለቆ መፈጠር ምክንያት ይሆናል፡፡ የቀይ ባህር፣ የኤደን ባህርሰላጤና የምስራቅ አፍሪካ ስምጥ ሸለቆዎች የዚህ አይነት ተፈጥሮ ሲኖራቸው የሚገናኙትም አፋር ውስጥ ነው፡፡ መገናኛ ቦታውም የአፋር ሦስትዮሽ መገናኛ (Triple Junction) የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ በሳይንሱ የቀይባህርና የኤደን ባህረሰላጤ ስምጥ ሸለቆዎች ከዛሬ 30 ሚልዮን ዓመት በፊት አልነበሩም ይባላል፡፡ የየመን ምዕራባዊ ክፍል እና የሰሜን ምስራቅ አፍሪካ ክፍል የገጠመ ነበር፡፡
በሀገራችን ኢትዮጵያ የመሬት መንቀጥቀጥ ሊያጠቃቸው ይችላሉ ተብለው የተለዩ አካባቢዎች አሉ ወይ? ብለን ብንጠይቅ አብዛኞቹ የሃገራችን ከተሞች አዲስ አበባን ጨምሮ ከስምጥ ሸለቆ የራቁ አይደሉም፡፡ ምናልባት በሃገራችን ምዕራባዊ ክፍል ባህርዳር፣ ጎንደር እና ወለጋ አካባቢ ደህና ይሆናል፡፡ እንዲሁም በምስራቃዊው የሃገራችን ክፍል ጎባና ሮቤ ሊድኑ ይችላሉ፡፡ ከነዚህ ውጪ ሌላው ከመሬት መንቀጥቀጥ እይታ ውጪ አይደለም፡፡ መቀሌን ብንወስድ የስምጥ ሸለቆ ጫፍ ላይ ትገኛለች፡፡ ወደታች ብንወርድ ወልድያ እና ደሴ ከስምጥ ሸለቆ ጫፍ አይርቁም፡፡ ድሬዳዋና ሃረር ያሉበት ሁኔታ ብዙም ባይርቅም የተሻለ ነው፡፡ ጥፋት ሊደርስ የሚችል የመሬት መንጥቀጥ ያለው በምዕራባዊ ዳርቻ ነው፡፡ አሁን በማደግ ላይ ያሉት ከተሞች አዳማ፣ ሻሸመኔ እና ሃዋሳ ስምጥ ሸለቆ ውሥጥ ናቸው፡፡ የሚገኙት በጣም አሳሳቢ በሚባል ቦታ ላይ ነው፡፡ የመሬት መንቀጥቀጥ እና እሳተ ገሞራ በጣም የተቆራኙ ናቸው፡፡ ነገር ግን ሊፈነዳ የሚችል እሳተ ገሞራን ክትትል ከተደረገበት አስቀድሞ ማወቅ ይቻላል፡፡ በአካባቢው አየር(ጋዝ) እና አመድ መሰል ብናኝ ቅንጣጦች የሚስተዋሉ ከሆነ እንደ ጥቆማ ሊወሰዱ ይችላሉ፡፡ በተጨማሪም የሚፈጠረውን ንዝረት በማጥናት ሊፈነዳ የሚችልበትን ወቅት መገምገም ይቻላል፡፡ ባይፈነዳ እንኳን ለጥንቃቄ ዝግጅት ይደረጋል፡፡ የመሬት መንቀጥቀጥን ከተመለከትን ባልታሰበ ሰዓት ሊፈጠር የሚችል እውነታ ነው፡፡ በመሆኑም መጠኑን ፣ ጊዜውን እና ቦታውን ለመተንበይ በጣም ከባድ ነው፡፡
መቸም ከጃፓኖች የመጠቀና ያደገ አገር የለም፡፡ በብዛት፣ በዓይነት እና በጥራት ድንቅ የሚባሉ ሳይንቲስቶች አሏቸው፡፡ የበርካታ ቴክኖሎጂዎች ባለቤትም ናቸው፡፡ ሆኖም ግን በ2011 ዓ.ም ወደ 2 ሺህ የሚደርሱ ዜጎቻቸውን በመሬት መንቀጥቀጥ ምክንያት በተፈጠረው የሱናሚ አደጋ አጥተዋል፡፡ ይህ ጉዳት የደረሰው መተንበይ ባለመቻላቸው ነው፡፡ ነገር ግን በየትኛውም አካባቢ የመሬት መንቀጥቀጥ ሊፈጠር እንደሚችል ስላወቁ የሚሰሩዋቸውን ፎቆች ደረጃቸውን የጠበቁ በማድረግ እና ህዝባቸውን በማስተማር ሊደርስ የሚችለውን መጠነ ሰፊ ጥፋት ይቀንሳሉ፡፡ ብዙውን ግዜ አደጋን ለመቋቋም መፍትሔው ህዝብን ማስተማር በመሆኑ ጃፓኖች ችግሩን ህዝባቸው እንዲያውቅ አድርገዋል፡፡ ከት/ቤት ጀምሮ እያንዳንዱ የጃፓን ህፃን የአካባቢውን ሁኔታ እንዲውቅ ይደረጋል፡፡ ይህን ሁሉ አድርገው እንኳን አደጋውን መተንበይ ሳይችሉ ቀርተው ብዙ ሰዎች ይሞታሉ፤ ይባስ ብሎ የ2011 መሬት መንቀጥቀጥ ሱናሚ በማስከተሉ፣ የሱናሚው ሞገድ ደግሞ የኒዮክለር ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎችን ማቀዝቀዣ ስላበላሸው ተደራራቢ የተፈጥሮ አደጋ ተፈጥሯል፡፡

ታዲያ ይህ ሁሉ ከሆነ ስለመሬት መንቀጥቀጥ ማጥናት ጥቅሙ ምንድን ነው? ብለን ልንጠይቅ እንችላለን፡፡ የዚህ ጥናት ዋና ጥቅሙ አደጋውን ማስቀረት እንደማይሆን የሚታወቅ ነው፡፡ ዋናው ነገር የት የት አካባቢ ሊከሰት እንደደሚችል፣በምን ያህል መጠን እና እንዴት እንደሚፈጠር መንስኤውን ለማወቅ ይረዳል፡፡ ይህ ሁኔታ ከታወቀ ደግሞ የጥንቃቄ ስራዎች እንዲሰሩ ያደርጋል፡፡ ይህንን ሁኔታ ለማየት ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን በሃይቲ እና በቺሊ የተፈጠረውን የመሬት መንቀጥቀጥ መመልከት ነው፡፡ የሃይቲው በሬክተር መጠን መለኪያ 7፣ የቺሊው ደግሞ 8.8 የተመዘገቡ ነበሩ፡፡ ቺሊዎች የመሬት መንቀጥቀጥ ሊያጠቃቸው እንደሚችል ቀድመው በጥናት ስላወቁ አቅማቸው በሚፈቅድላቸው የቴክኖሎጂ እና ኢኮኖሚ መጠን ጥንቃቄ ለማድረግ ሞክረዋል፡፡ ህንፃዎች፣ ድልድዮች እና መንገዶች ሲሰሩም ምን አይነት ደረጃ መጠቀም እንዳለባቸው ስላወቁ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል፡፡ የመሬት መንቀጥቀጥ ሊከሰት ይችላል ተብሎ የተለዩ ቦታዎች የሚኖሩ ሰዎችንም የጥንቃቄ መልዕክት በማሰራጭት ሰዎች አካባቢውን እንዲለቁ አድርገዋል፡፡ በተቃራኒው የሃይቲ መንግስት እና ህዝብ ግን ምንም አይነት ግንዛቤ ስላልነበራቸው በተፈጠረው አደጋ ምክንያት በችግር እስካሁን ተዘፍቀው በድንኳን ይኖራሉ፡፡ አደጋው በ2010፣ ከ220,000 በላይ ሰዎችን ጨርሶ ከ300,000 በላይ ሰዎችን ደግሞ አቁስሏል፤ ክስተቱ ሃገሪቱን አውድሟት ነው ያለፈው፡፡ ግንዛቤ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡ ማህበረሰቡ፣ መንግስት እና ባለሃብቶች ስለችግሩ ቀድመው ቢረዱና ቢያውቁ፣ ትምህርት ቢሰጣቸው ኖሮ እንደዚህ የከፋ አደጋ ጥሎ ባልሄደ ነበር፡፡
ወደ አገራችን ስንመለስ አሁን በአዲስ አበባ ውስጥ እየተገነቡ የሚገኙ ህንፃዎች ሊፈጠሩ የሚችሉ አደጋዎችን ከግምት ውስጥ ያስገቡ ናቸው ለማለት አያስደፍርም፡፡ ምክንያቱም አስገዳጅ ህግ ያለ አይመስልም፡፡ የትኞቹ ህንጻዎች ወይም ድልድዮች አደጋውን ይቋቋማሉ፣ አይቋቋሙም የሚለውን ችግሩ መጥቶ ሲታይ ካልሆነ በስተቀር ማወቅ አስቸጋሪ ነው፡፡ በከተማው ውሥጥ ብዙ ህንፃዎች ይገኛሉ፡፡ ትምህርት ቤቶች፣ የጋራ መኖሪያ ህንፃዎች እና ሌሎችም ህንፃዎች የኮለን ስፋታቸው እና እርዝመታቸው ሲታይ ንዝረት ቢመጣ ምን ይሆናል የሚለውን ስናስብ የሚያስፈራ ነው፡፡

በ1910 ዓ.ም ታንዛኒያ በሬክተር ስኬል 7.4 የተመዘገበ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ አጋጥሟት ነበር፡፡ በዚሁ ሳምንትም በታንዛኒያ በሬክተር ስኬል 5.7 ያስመዘገበው የመሬት መንቀጥቀጥ 17 ሰዎችን እንደገደለ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል፡፡ በ1990 በደቡብ ሱዳን 7.2፣ በ2006 በሞዛምቢክ እና በአካባቢው 7.0 ሬክተር ስኬል የተመዘገበ አደጋ ነበር፡፡ ይህ እንግዲህ ባለፉት መቶ ዓመታት የተከሰተ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ወደ ኋላ ከሄድን የመሳሪያው ቴክኖሎጂ ሳይመጣ የተከሰቱ የእግዜር ቁጣ ተብለው የተመዘገቡ ብዙ ክስተቶች ነበሩ፡፡ ታሪኮቹን በቤተክርስቲያን ድርሳናት ማግኘት ይቻላል፡፡
ያደጉ አገሮች ግንባታውን እንደአካባቢው ሁኔታ ሊፈጠር የሚችለውን አደጋ እንዲቋቋም አድርገው ይሰራሉ፡፡ ሁኔታውን ስለሚያውቁት ይዘጋጃሉ፡፡ እንደኛ እያደጉ ባሉ ደሃ ሃገራት በአደጋው ዙሪያ የግንዛቤ እጥረት ስለሚኖር እና አደጋውን ሊቋቋም የሚችል ግንባታ ስለማይደረግ ክስተቱ ቢፈጠር ባለማወቅ እና ባለመዘጋጀት ብቻ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት መገመት አይከብድም፡፡
በሀገራችን ዘመናዊ ትምህርት ከ100 አመታት በላይ ታሪክ አስቆጥሯል፡፡ ስለዚህ በሎጂክ እና በሳይንስ ማመን አለብን፡፡ አብዛኛው ከተሞቻችን የተመሰረቱት ስምጥ ሸለቆን ተከትለው ነው፡፡ እነዚህ ከተሞች አዲስ አበባን ጨምሮ በስምጥ ሸለቆ ዳርቻዎች መሆናቸው በጥንት ቢታወቅ ኖሮ ለዋና ከተማነት ተመራጭ አይሆኑም ነበር፡፡
ብዙ ኢኮኖሚ የሚፈስበት ግንባታ በደንብ መጠናት አለበት፡፡ በተለይ መሠረቱ የሚወጣበትን ቦታ በጥልቀት መመርመር በሚያስችል መሳሪያ በመታገዝ ቅድመ ጥናት መደረግ አለበት፡፡ አንድ ከተማ ከመከተሙ በፊት መምረጥ ይቻላል፡፡ የኋላ ታሪኮችን ስናይ አንድ ከተማ ታስቦበት አይቆረቆርም፡፡ በ1906 በኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆ ውስጥ ተፈጥሮ በመሳሪያ የተመዘገበው ትልቁ የመሬት መንቀጥቀጥ በሬክተር ስኬል 6.8 ሲሆን በወቅቱ በነበረው መረጃ አዳሚ ቱሉ የተባለችው ከተማ አካባቢ እንደተነሳ ይነገራል፡፡ ከዛ በኋላ በተደረገውም ምርምር ከወደ ምስራቃዊ ፕላቶ አካባቢ እንደተነሳ ያሳያል፡፡ በዚህ የመሬት መንቀጥቀጥ ምክንያት ከአዳሚ ቱሉ የተነሳው ንዝረት የእንጦጦ ማርያም ቤተክርስቲያንን ደውል ማንም ሳይነካው እንዲደውል አድርጓል፡፡ ከዚህ መረዳት የምንችለው እንዲህ ዓይነት ክስተት የመፈጠር እድሉ መኖሩን ነው፡፡ ከአዲስ አበባ ቅርብ ርቀት ላይ 6.8 በሬክተር ስኬል የመሬት መንቀጥቀጥ ተነስቷል፡፡
በክፍል ሦሥት ምን ዓይነት የጥንቃቄ እርምጃዎችን እንውሰድ የሚለውን እንመለከታለን፡፡
(2016 ላይ የተጻፈ) by Muluken Asrat fb (Muler)