የትግራይ ሰላማዊው ህዝብ አልታደለም። ቀደም ሲል በስሙ ድርጅት መስርተው፣ በስሙ ተደራጅተው፣ በስሙ ጫካ ገብተው፣ በስሙ ተኩሰው፣ በስሙ አገር መሪ የሆኑ ስልጣን በያዙበት ሃያ ሰባት ዓመታት የፈየዱለት ነገር የለም። ሕዝቡን ከሴፍቲ ኔት ተጠቃሚነት አላዳኑትም። መስኖ አልሰሩለትም። ገበሬውን ዘመናዊ ቴክኖሎጂ እንዲጠቀም አላደረጉትም። ለራሳቸው በአካባቢ ተቧድነው ሲዘርፉና ህዝቡን ከጎረቤቶች ጋር ሲያጋጩ ነው የኖሩት።
የአመራር ለውጥ ሲደረግ ወደ ትግራይ አፈግፍገው በጀመሩት ጦርነት የትግራይ ህዝብ እንዳይሆን ሆነ። የተሳሳተ ቅስቀሳ ቀስቅሰው፣ የመኖር ስጋት እንዲገባው አድርገው በማነሳሳት ማገዱት። ምንም ሳያተርፉ ህዝብ አስጨርሰው የሰላም ውል ከተፈራረሙ በሁዋላ፣ አሁን ደግሞ በጎበዝ አለቃ ተቧድነው በወርቅ ዘረፋ ላይ የተሰማሩ ጥቂት አይደሉም። በህገወጥ የወርቅ ዘረፋ ህዝብ የሚጠጣውን ውሃ፣ ቆፍሮ የሚዘራበትን ቀዬውን፣ ከብቶቹን በሚጨርስ ኬሚካል እያወደሙት ነው።
በዚሁ መልኩ የሚሰበስቡትን ወርቅ ወደ ኤርትራ እያጋዙ ሻዕቢያን እየቀለቡ ነው። የትግራይ ህዝብን ከማንኪያ ጀመሮ የዘረፈ፣ ልማት እያወደመ ላጋዘ፣ ወጣቶችን መርጦ ለጨፈጨፈ፣ የትግራይ ህዝብ ካልጠፋና ካላለቀ ሰላም አይታሰብም ለሚል አረመኔ ኢሳያስ ግብር እያስገቡ ነው።
ቢቢሲ “ከሁለት ዓመቱ ደም አፋሳሽ ጦርነት ማብቃት በኋላ በትግራይ ክልል ሕገወጥ የማዕድን ማውጣት ተግባር በስፋት እየተካሄደ መሆኑ በተደጋጋሚ እየተነገረ ነው” ሲል ያቀረበው ዘገባ ከስር ያንብቡ
በዚህ ሕገወጥ የማዕድን ማውጣት ሂደት በትግራይ ኃይሎች ውስጥ የሚገኙ ግለሰቦች፣ የፀጥታ ኃላፊዎች እንዲሁም በክልሉ አስተዳደር ውስጥ ያሉ ከፍተኛ ባለሥልጣናት እጃቸው እንዳለበት ነዋሪዎች እና በተለያዩ ደረጃ የሚገኙ ባለሥልጣናት ያምናሉ።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ በጉዳዩ ላይ ከዚህ ቀደም እንደተናገሩት ማዕድን ማውጣቱ ሂደት ሕገወጥ ከመሆኑ ባሻገር በተፈጥሮ ላይ የሚያስከትለው ጉዳት አሳሳቢ እደሆነ ጠቁመው ነበር።
በወርቅ ማውጣት ሥራው ወቅት ለአገልግሎት የሚውሉት አደገኛ ኬሚካሎች በተፈጥሮ፣ በሰው እና በእንስሳት ላይ ጉዳት እያደረሱ በመሆናቸው ሁኔታው እጅግ አሳሳቢ እንዲሆን አንዳደረጉት ነዋሪዎች ይናገራሉ።
ማዕድን ማውጣቱ በሚካሄድበት በሰሜናዊ ምዕራብ ትግራይ ዞን አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ጥናት ያደረጉ ባለሙያዎች ለሰው እና ለአካባቢ አደገኛ የሆኑ ኬሚካሎች “ከመጠን በላይ” ጥቅም ላይ እየዋሉ እንደሆነና “አያያዛቸውም” ሥርዓት እንደሌለው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በሰሜን ምዕራብ ትግራይ ክልል የሚገኙ እንደ አስገደ ፅምብላ፣ ዛና፣ አዲያቦና ፅምብላን ጨምሮ በቆላ ተምቤን እና በሐውዜን አካባቢዎች ሰፊ የወርቅ ቁፋሮ እንቅስቃሴዎች እየተካሄዱ ይገኛሉ።
በእነዚህ አካባቢዎች የትግራይ ኃይሎች አባላት፣ የአካባቢው ወጣቶች እና ታዳጊዎች፣ ተፈናቃዮች፣ ቻይናውያን እንዲሁም ሌሎችም በወርቅ ማውጣቱ ተግባር ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙ ይነገራል።
‘የወላጆቼ ከብቶች አለቁ’
በፈጠራ ሥራዎቹ የሚታወቀው ወጣት ዕበ ለገሰ በላዕላይ አዲያቦ ወረዳ ምድረ-ፈላሲ ቀበሌ የሚኖሩ በእርሻ የሚተዳደሩ ወላጆቹ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ የነበሯቸው ከብቶች መሞታቸው ይናገራል።
የአካባቢው ማኅበረሰብ የሚተዳደረው በግብርና፣ በእንስሳት እርባታ እና በባሕላዊ መንገድ ወርቅ በማውጣት ሲሆን፣ አሁን በሕገወጥ መንገድ ኬሚካሎችን በመጠቀም ወርቅ ማውጣት በመስፋፋቱ የነዋሪዎች እና የእንስሶቻቸው ደኅንነት አደጋ ተጋርጦበታል።
“ወላጆቼ መጀመሪያ ከብቶቻቸው በምን ምክንያት እንደሚታመሙ አልገባቸውም፤ ነገር ግን ወደ 13 የሚሆኑት ሞተውባቸዋል። አሟሟታቸውም በስቃይ የተሞላ ነበር” ሲል ዕበ ለቢቢሲ ገልጿል።
እንስሳቱ የሞቱበት ምክንያት በምርመራ ባይረጋገጥም በአካባቢው የሚገኘውን “የተበከለ ውሃ” ከጠጡ በኋላ መሞታቸውን ነዋሪዎቹ ያምናሉ።
ወላጆቹ ለእርሻ የሚገለገሉባቸው በሬዎቻቸው በማለቃቸው በአማራጭነት “ግመሎችን ገዝተው ማረስ” እንደጀመሩ ይናገራል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በወንዞች አካባቢ ወርቅ የሚያጥቡ ግለሰቦች እጆቻቸው እንደተጎዱ መመልከታቸውን ማዕድን በሚወጣባቸው አካባቢዎች ጥናት ያካሄዱ ባለሙያዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
Copyright Zenawi A ማዕድን በሚወጣባቸው አካባቢ የሚገኙ ወንዞች እየተበከሉ እንደሆኑ ነዋሪዎች ይገልጻሉ

የዕበ ቤተሰቦች ‘እንዳ ጎሾ’ በሚባል ወንዝ አካባቢ ይኖራሉ። በዚህ ወንዝ ውስጥ ወርቅ የሚያጠቡ በርካታ በባህላዊ መንገድ ወርቅ የሚያወጡ ሰዎች ያሉ ሲሆን፣ በተጨማሪም ወንዙ ለሰዎች እና ለእንስሳት መጠጥነት እንደሚውል ነዋሪዎች ይናገራሉ።
ዕበ እንደሚያስታውሰው “ቀደም ሲል ወንዙ ጥርት ያለ ስለነበረ ጎንበስ ብለን የምንጠጣው ንጹህ ነበር። አሁን ግን ደፍርሷል፤ ሰዉ ግን ሙሉ በሙሉ ለመጠጥ ጭምር እየተጠቀመበት ነው።”
ለደኅንነታቸው ሲሉ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ ነዋሪ በበኩላቸው ከወንዙ ውሃ ጋር በተያያዘ “የእንስሳት ሞት መከሰት ሲጀምር በአካባቢው ለወርቅ ማዕድን ማውጣት እየዋሉ ያሉት ኬሚካሎች ያስከተሉት ችግር ሊሆን ይችላል ብለን እንገምታለን” ብለዋል።
በወርቅ ማውጣቱ ሂደት አፈሩን ከወርቅ ለመለየት ውሃ አስፈላጊ በመሆኑ፤ በቁፋሮው ላይ የተሰማሩ በርካታ ግለሰቦች እና ቡድኖች ወንዞች ባሉባቸው አካባቢዎች ሰፍረው ይህንን ተግባር ያከናውናሉ።
በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ወንዞች መካከል እንዳ ጎሾ የተባለውን ወንዝ ጨምሮ ከዓዲ ዳዕሮ እስከ መረብ ባለው ተፋሰስ ዙሪያ ወርቁ የሚያወጡት ግለሰቦች የወንዞቹን ውሃ እንደሚጠቀሙ ነዋሪዎች ይገልጻሉ።
እየተካሄደ ነው በሚባለው ሕገወጥ የወርቅ ቁፋሮ ላይ ከግለሰቦች እና ከቡድኖች በተጨማሪ የቁፋሮ ከባድ ተሽከርካሪዎች (ኤክስካቫተር) ያሰማሩ ባለሃብቶች እና ማኅበራትም ተሳታፊዎች መሆናቸውን ነዋሪዎች ይናገራሉ።
የመርዛማ ኬሚካሎች ሥርጭት
በቅርቡ በኬሚካል ኢንጂነሪንግ፣ በኬሚስትሪ እና በሌሎችም ዘርፎች የሰለጠኑ ባለሙያዎችን ያካተተ ቡድን የወርቅ ቁፋሮ በሚካሄድባቸው የሰሜን ምዕራብ የትግራይ አካባቢዎች የቅድመ ዳሰሳ ቅኝት አድርጓል።
በዚህም ቀደም ሲል በትግራይ ሰሜን ምዕራብ እና መካከለኛ ዞኖች ውስጥ በዝቅተኛ ደረጃ በባህላዊ መንገድ ይካሄድ የነበረው የወርቅ ማውጣት ሥራ አሁን በመካከለኛ እና በከፍተኛ ደረጃ ወደሚካሄድበት ደረጃ ከፍ ማለቱ ተጠቅሷል።
በባህላዊ ዘዴ ወርቅ በማውጣት የሚተዳደሩ ሰዎች በወንዞች አካባቢ ሰፍረው አፈሩን በወንዝ ውሃ በማጠብ ነበር ወርቁን የሚለዩት፤ ይህም ከ98 በመቶ በላይ ድርሻ ይይዝ እንደነበር ይነገራል።
አሁን ግን መልኩን ቀይሮ የወርቅ ቁፋሮው በከፍተኛ ደረጃ እየተካሄደ እንደሆነ የምርምር ቡድኑ መሪ እና በአክሱም ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ዮናስ ወልደማርያም ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“በከባድ ማሽኖች የታገዘ ወርቅ ማውጣት ሥራ እየተካሄደ ነው፤ ይህም ትላልቅ ተራራዎችን በመቆፈር ነው የሚከናወነው፤ ወርቅ አነፍናፊ በሚባሉ ማሽኖች እና በኤክስካቫተር በመታገዝ ነው ወርቅ ማውጣቱ እየተካሄደ ያለው” ሲል ያብራራል።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ሕገወጥ መሆኑን በተደጋጋሚ በሚገልጸው የወርቅ ቁፋሮ ላይ ተሠማርተው የሚገኙት ግለሰቦች እና ቡድኖች ወርቅ ለማጠብ የሚያገለግሉ ኬሚካሎችን “በስፋት” እየተጠቀሙ እንደሆነ ለመረዳት መቻሉን ይጠቅሳል።
የቅድመ ዳሰሳ ቅኝቱ በሰሜን ምዕራብ ዞን በሰየምቲ አዲያቦ ወረዳ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ የወርቅ ቁፋሮ የሚካሄድባቸው ቦታዎችን ሸፍኗል።
በታህታይ አዲያቦ፣ አስገደ ጽብላል እና ወርዒ የሚካሄዱ ሰፋፊ የወርቅ ማውጣት እንቅስቃሴዎች እንዳሉም ይነገራል።
በአጠቃላይ “የማዕድን ማውጣት ሂደት ከተለመደው ባህላዊ አሠራር ወደ መካከለኛ እና ከፍተኛ ደረጃ ሲሸጋገር ኬሚካሎችን መጠቀሙ የማይቀር ነው። በአካባቢው መርዛማ ኬሚካሎች ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው፤ አንዳንዶቹ ሜርኩሪ፣ ሌሎች ደግሞ ሳይናይድ እየተጠቀሙ ናቸው” በማለት አደገኛ ኬሚካሎች ጥቅም ላይ መዋላቸውን ማረጋገጥ እንደተቻለ ተመራማሪው ያስረዳሉ።
የእነዚህ በወርቅ ማዕድን ማጣራቱ ሂደት ላይ ጥቅም ላይ እየዋሉ መሆናቸው የሚነገርላቸው አደገኛ ኬሚካሎች ምን ያህል ለአገልግሎት መዋላቸውን እና እያደረሱት ያለውን ጉዳት ለማወቅ ተጨማሪ ጥናት እንደሚፈልግ ባለሙያዎቹ ተናግረዋል።
በወርቅ ማዕድን ማጣራት ሂደት ውስጥ የተለያዩ ዓይነት ኬሚካሎች ጥቅም ላይ የሚውሉ ሲሆን፣ ኬሚካሎቹ በተፈጥሮ አካባቢ፣ በሰዎች እና በእንስሳት ላይ ቀላል የማይባል ጉዳት እንደሚያደርሱ ባለሙያዎች እነ ነዋሪዎች ይናገራሉ።
ሜርኩሪ
የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚለው ከፍተኛ የጤና ጉዳቶችን ከሚያስከትሉ አስር ኬሚካሎች ወይም ንጥረ ነገሮች አንዱ የሆነው ሜርኩሪ፣ አደገኛ ኬሚካል በመሆኑ መሬት ላይ ከፈሰሰ ሊወገድ ወይም ሊጠፋ አይችልም።
ይህ ኬሚካል በወርቅ ማጣራት እና በሌሎችም የማዕድን ማውጣት ሥራ ላይ የሚውል ሲሆን፣ ጥቅም ላይ ከዋለ በኋላ በአግባቡ ካልተወገደ ሊተን እና ሊቀልጥ ስለሚችል ተጽእኖው አደገኛ ነው።
በአብዛኛው የዚህ ኬሚካል ተጋላጭነት የሚከሰተው ወደ ሳንባ በሚሳብበት ጊዜ ነው። በተጨማሪም ዓሳ ወደሚገኝባቸው ወንዞች እና ሌሎች የውሃ አካላት በሚገባ ጊዜ ምግብን እና የመጠጥ ውሃ ሊበክል ይችላል።
አንድ ሰው ለሜርኩሪ ተጋልጦ ከሆነ ለማረጋገጥ የደም፣ የሽንት እና የፀጉር ምርመራ ይካሄዳል።
ኬሚካሉ በሰው ላይ በነርቭ ሥርዓት፣ በልብ፣ በአንጎል፣ በኩላሊትን እና በሌሎችም የአካል ክፍሎች ላይ ጉዳትን በማስከተል የተለያዩ የጤና መቃወሶችን እንደሚያስከትል የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያመለክታል።
ሴቶች እና ህጻናት በማዕድን ቁፋሮ ስለሚሰማሩ ለኬሚካሉ የበለጠ ተጋላጭ መሆናቸውን የዓለም ሥራ ድርጅት የሚገልጽ ሲሆን፣ ሜርኩሪ በተለይ በነፍሰጡር ሴቶች ላይ ተደራራቢ ውጤት አለው።
ኬሚካሉ በእናት ጤና ላይ ከሚያስከትለው ጉዳት ባሻገር በፅንስ ጤናማ የአእምሮ ዕድገት ላይ ዘላቂ እክልን ሊያስከትል ይችላል።
በህጻናት ላይ ደግሞ የአካል እና የአእምሮ ዕድገታቸው፣ የትኩረት አቅማቸው፣ የቋንቋ እና የማየት ችሎታቸው እንዲሁም የመገንዘብ አቅማቸው እንዲዳከም ያደርጋል።
ተመራማሪው ዶክተር ዮናስ ወልደማርያም እንሚሉት አሁን በወርቅ ማዕድን አውጪዎች ጥቅም ላይ እየዋለ ስላለው የሜርኩሪ ሕብረተሰቡ የሚያውቀው ነገር የለም። ኬሚካሉ ከሚያስከትለው ከባድ ጉዳት አንጻር ስለአጠቃቀሙ እና ሊወሰዱ ስለሚገቡ ጥንቃቄዎች መመሪያ መቀመጥ እንዳለበት ያሳስባሉ።
“አሁን ያለው ሁኔታ ተጠቅሞ መጣልን ነው። የአጠቃቀም ቁጥጥር እና ደንብ የለም። ኬሚካሎቹ ወርቅ ማግኘት በሚያስችል መንገድ ጥቅም ላይ እየዋሉ ስለሆነ መጠኑ አደገኛ በሚባል ደረጃ ላይ ደርሷል” ይላሉ።
አክለውም ኬሚካሎቹ ወደ መተንፈሻ አካላት ከገቡ ገዳይ መሆናቸውን እና ወደ አፈር እና ወደ ውሃ አካላት ውስጥ ከገቡ ከአዝርዕቶች እና ከዓሳ ጋር ተቀላቅለው በምግብ መልክ ወደ ሰው አካል ሊገቡ እና ጉዳት ሊያደርሱ ይችላሉ።

ሳይናይድ
ሳይናይድ በወርቅ ማውጣት ሥራ ላይ በብዛት ጥቅም ላይ የሚውል ኬሚካል ሲሆን፣ ያለአግባብ ጥቅም ላይ ሲውል በሰው እና በአካባቢ ጤና ላይ ጎጂ ተጽእኖ ይኖረዋል።
የማዕድን ማውጣት ሠራተኞች የዚህ ኬሚካል ቀጥተኛ ተጽእኖ ሰለባዎች ሲሆኑ፣ ኬሚካሉ የውሃ እና የእርሻ አካባቢዎችን የመበከል አቅሙ ከፍተኛ ነው።
ሳይናይድ በመተንፈሻ አካል በኩል፣ በኬሚካሉ በተበከሉ ምግቦች እና ውሃ አማካይነት፣ ከቆዳ ጋር በሚኖር ንክኪ ለምሳሌ ለሳይናይድ በተጋለጠ መሬት ላይ በባዶ እግር መራመድ ጉዳት ያደርሳል።
የዓለም ጤና ድርጅት ኬሚካሉ ከባድ የራስ ምታት [ኤፒለፕሲ ስትሮክ]፣ የነርቭ ህመም፣ የልብ እና የአእምሮ፣ የአጥንት ችግር እንዲሁም የመተንፈስ ችግሮችን፣ ሲከፋ ደግሞ ወደሞት ሊያደርስ እንደሚችል ያስገነዝባል።
በትግራይ እየተካሄደ ባለው ሕገወጥ የወርቅ ቁፋሮ ጥቅም ላይ በሚውሉት ኬሚካሎች ምክንያት ምልክቶችን የሚያሳዩ ሰዎች እንዳጋጠማቸው የሚናገሩት ዶክተር ዮናስ፣ “ገዳይ ከሚባሉ እና ተጽዕኗቸው ከትውልድ ወደ ትውልድ ከሚተላለፍ ኬሚካሎች መካከል አንዱ ሳይናይድ” ነው ይላሉ።
በከፍተኛ መጠን ማዕድን የሚያወጡት አካላት እነዚህን ኬሚካሎች ተጠቅመው የሚወገደውን ፈሳሽ ወደ ሌሎች ተፋሰሶች ይቀላቀላል። “ኬሚካሎቹ ወደ ወንዙ ሲገቡ በባህላዊ መንገድ የሚወርቅ የሚያወጡት ላይ ጉዳት ያደርሳል” በማለት ጉዳቱ ሰፊ አካባቢን እንደሚሸፍን ገልጸዋል።
በማዕድን ማውጣት ሂደት ጥቅም ላይ የሚውሉ አደገኛ ኬሚካሎች የሚያደርሱትን ጉዳት ለመቀነስ አገራት ለሰዎች፣ ለእንስሳት እና ለአካባቢ ደኅንነት ጎጂ የሆኑ ኬሚካሎች ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ከማገድ በተጨማሪ ዓለም አቀፍ ስምምነትን ፈርመዋል።
ኢትዮጵያም በአውሮፓውያኑ 2013 ‘የሚናማታ ስምምነት’ የተባለውን ስምምነት ከፈረሙ አገራት መካከል አንዷ ናት። ይህ ስምምነት ሜርኩሪ እና ሳይናይድ በማንኛውም የማዕድን መውጣት ሥራ ላይ ጥቅም ላይ እንዳይውል የሚያግድ ነው።