“ኢትዮጵያዊ ነን” የሚሉ ሚዲያዎች፣ ስለ ኢትዮጵያ በተለያዩ ቋንቋዎች እንዲዘግቡ በውጭ አገራት በተቋቋሙ ሚዲያዎች የሚሰሩ አብዛኞቹ በሰበርና፣ በደማቅ ዜና “ኢትዮጵያ ከአውሶም ተሰናበተች። በጃንዋሪ የኢትዮጵያ ሰራዊት ከሶማሊያ ለቆ ይወጣል” ደጋግመው ሲዘግቡ ነበር። ዝምታን የመረጡት የኢትዮጵያ መሪዎች ከአንካራው ስምምንት በሁዋላ የሶማሊያ ባለስልጣናትን ጩኸት መና አድርገውት ኢትዮጵያ በሶማሊያ ጦር እንድታዋጣ ስምምነት መደረሱ ተሰምቷል። “ተባረረች” ሲሉ ሰበር ዜና ያከታተሉ ግን ዜናውን ዝም ብለው አልፈውታል።

ብሉምበርግ “በሶማሊያ እና ኢትዮጵያ መካከል ያለው ውዝግብ በአንካራ ስምምነት መፈታቱን ተከትሎ ሶማሊያ የኢትዮጵያ ወታደሮችን በአውሶም ለማካተት እያሰበች ነው” ያለው የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሐመድ ወደ ሶማሊያ አቅንተው ሞቃዲሾ መድረሳቸውን ይፋ ሲያደርግ ነው።
ዴይሊይ ሶማሊያ ከብሉምበርግም ሆነ ሮይተርስ ቀድም ዜናውን ኢትዮጵያ በ AUSSOM ተልዕኮ ሰራዊት እንድታዋጣ የሶማሊያ መንግስት እንደወሰነ ይፋ አድርጓል።
የሶማሊያ መንግስት ኢትዮጵያ በ AUSSOM ተልዕኮ ሰራዊት እንድታዋጣ የወሰነ ሲሆን የምታዋጣው የሰራዊት ቁጥር የሁለቱ ሃገራት መሪዎች ቀጣይ January 10, 2024 በአካል ተገናኝተው በስምምነት የሚቋጩት እንደሚሆን ይጠበቃል።
ዛሬ ይፋ እንደሆነው የመከላከያ ሚኒስትሯ አይሻ መሐመድ የመሩት ልዑክ ወደ ሶማሊያ ያቀኑት ከአቻቸው ጋርና ከሚመለከታቸው ጋር ለመምከር ነው።
ብሉምበርግ ጉዳዩን አስመልክቶ የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታን ጠቅሶ ይህንኑ አረጋግጧል። ሚኒስትሯ ወደ ሶማሊያ ያቀኑት የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል በአዲሱ የአፍሪካ ኅብረት የሶማሊያ ድጋፍ እና ማረጋጋት ተልዕኮ (አውሶም) የሚኖራቸውን ተሳትፎ አስመልክቶ ይወያያሉ። ብሉምበርግ አያይዞ “በሶማሊያ እና ኢትዮጵያ መካከል ያለው ውዝግብ በአንካራ ስምምነት መፈታቱን ተከትሎ ሶማሊያ የኢትዮጵያ ወታደሮችን በአውሶም ለማካተት እያሰበች ነው” ሲሉ ሚኒስትሩ መናገራቸውን አስታውቋል።
ብሉምበርግ እርግጠኛ ሆኖ ኢትዮጵያ ጦር እንደምታሰማራና ሶማሊያ አቋሟን መቀየሯን በሰፊ ዘገባው ገልጿል። ይህ ከመሆኑ በፊት አማራጭ ያጡት የግብጽ ፕሬዚዳንት አልሲሲ የሶማሌያና ኢትዮጵያን ስምምነት አድናቂ አፈጻጸሙን በአጽንዎ የሚከታተሉና ስምምነቱ ቀጣናውን ስለማ እንደሚያደርግ ጠቅሰው መግለጫ ሰጥተው ነበር።
የሶማሊያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሕመድ ፊቂ “በሶማሊያና በኢትዮጵያ መካከል ያለው አለመግባባት ተፈትቷል” ማለታቸውን ቢቢሲ ሶማሊኛን ጠቅሶ አማርኛው ዘግቧል።
ዘገባው አክሎም “የአፍሪካ ኅብረት የሶማሊያ የሽግግር ተልዕኮ (አትሚስ) የሚተካው የሶማሊያ ድጋፍ እና ማረጋጋት ተልዕኮ (አውሶም) ውስጥ የኢትዮጵያን ወታደሮች ማካተት እንደማትሻ ሶማሊያ የጠቆመች ሲሆን፣ ሁለቱ አገራት የሻከረ ግንኙነታቸውን በአንካራ ስምምንት ካደሱ በኋላ ውጥረቱ የረገበ ይመስላል።” ሲል የግምቱን ድምዳሜ አስፍሯል።
“አስቀድመን የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከሶማሊያም ሆነ ከአዲሱ ተልዕኮ ውጭ አይሆንም ብለን ሽንጣችንን ገትረን የተሟገትነው በመሪያችን የዲፕሎማሲ ጥበብና በሰራዊታችን ብቃት ስለምንተማመን ነው።” ሲል ፕሮፌሰር ጌትነት አልማው “ጋት” በሚባለው የግል ሚዲያው በዜናው መደሰቱን ጠቅሶ ገልጿል።
ኢትዮጵያ ወታደሮቿን ወደ ሶማሊያ ካስገባችና ህይወት መክፈል ከጀመረች 17 ዓመታት ሆኗታል። በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር በሚገኘው የሰላም አስከባሪ ኃይል ኢትዮጵያ ሶስት ሺህ የሚጠጋ፣ በሁለቱ አገራት ስምምነት ደግሞ አምስት ሺህ የሚልቅ ኃይል ማስፈሯ በተለያዩ ጊዜያት መገለጹ ይታወሳል። አንዳንዶች ቁጥሩን ከዚህም ከፍ ያደርጉታል።
የጦር ኃይሎች አዛዥ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የሶማሊያን 60 ከበመቶ በላይ የኢትዮጵያ መከላከያ እንደሚጠብቅና፣ የሶማሊያ ህዝብ በኢትዮጵያ መከላከያ ላይ ሙሉ እምነት እንዳለው በመግለጽ ሶማሊያ ባትፈልግም ከብሄራዊ ጥቅምና ስጋት አንጻር ጦሩ ለቆ እንደማይወጣ ፍንጭ መስጠታቸው ይታወሳል።
ፊልድ ማርሻሉ ይህን ሲሉ በስም ጠርተው የተለያዩ ክልሎች የኢትዮጵያ ወታደሮች እንዲወጡ እንደማይፈልጉ፣ ይህንንም በገሃድ ማቅረባቸውን ጠቁመው ነበር። ከአንካራው ስምምነት በፊት ሶስቱ ትልልቅ ክልሎች ከሞቃዲሾ መንግስት ጋር በይፋ መለየታቸውን እስከማወጅ መድረሳቸውም አይዘነጋም።
የሶማሊያ ፕሬዚዳንት የአንካራውን ስምምነት ከፈረሙ በሁዋላ ኤርትራ ሄደው ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጋር በቅርቡ መክረው ነበር። ሚኒስትሮቻቸውን ወደ ኢትዮጵያን ግብጽ ልከው የተለያዩ መግለጫዎች ሲሰጡ ነበር። ኤርትራና ግብጽም ኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባህር ለመመለስ የምታደርገውን ጥረት እንደሚያወግዙና በይፋ መናገራቸው የሚታወስ ነው።
ከአንካራው ስምምነት በሁዋላ ” መንግስት ተሸነፈ፣ ኢትዮጵያ ተዋረደች” ወዘተ ሲሉ የነበሩ ይህን ዜና አልፈውታል። ቢቢሲ የመከላከያ ሚኒስትሯን ጉብኘት ተከትሎ ሶማሊያ አሳቧን መቀየሯን ድምዳሜ ላይ ደርሶ ዘግቧል።
የተመራው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ልዑክ በሞቃዲሾ ቆይታው፦
- በኢትዮጵያና በሶማሊያ መሪዎች በአንካራ የተፈረመው “የሁለቱን ሃገራት ብሄራዊ ጥቅም አስጠብቆ ችግሮችን በውይይትና በንግግር የመፍታት ሥምምነት – Ankara declaration” በሁለቱ ሃገራት መካከል ያለውን ሽኩቻ በማስወገድ ይልቁንም መከባበርና መተማመን ለማስፈኑ ሁነኛ ማሳያ መሆኑን ያስገነዝባል፣
- አትሚስን በተካው የአፍሪካ ሕብረት ባሰማራው አዲሱ የአፍሪካ ሕብረት የሰላም ማስፈንና ድጋፍ ተልዕኮ በሶማሊያ (AUSSOM) ውስጥ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ድርሻና ተልዕኮ ዙሪያ በጥልቀትና በስፋት በመወያየት ለሁለቱ ሃገራት መሪዎች ግብዓት ያዘጋጃል (የመጨረሻ ውሳኔ በቀጣይ January 10, 2025 የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) እና የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ ሞሐመድ በ CAADP — Comprehensive Africa Agriculture Development Programme ስብሰባ ኡጋንዳ ላይ ሲገናኙ እንደሚወስኑ ይጠበቃል፣
- በሁለቱ እህትማማች ሃገራት የደህንነትና መረጃ ልውውጥ (በዋነኝነትም ወታደራዊ መረጃ ዙሪያ)፣ በድንበር አካባቢ የሚከናዎኑ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርንና ኮንትሮባንድ ንግድን በመከላከል፣ የጋራ ወታደራዊ ስልጠናና አቅም ግንባታ ዙሪያ እንዲሁም በሌሎች የሁለትዮሽ፣ ቀጠናዊና አሕጉራዊ ጉዳዮች ዙሪያ እንዲመካከሩ ይጠበቃል። ሲል ጋት ሚዲያ አመልክቷል።
ይህ እስከተጻፈ ድረስ ከመንግስት ወገን ይፋዊ መግለጫ አልተሰጠም።