በአሜሪካ ባለፈው ሳምንት በተጀመረው አሰሳ ሰነድ አልባ ስደተኞች የሆኑ ስደተኞች በሙሉ በቁጥጥር ስር እንደሚውሉ ማዘዛቸውን የስደተኞች ጉዳይ ኃላፊው ቶም ሆማን ተናግረዋል።
ሰነድ አልባ ስደተኞች የሚባሉት የትኞቹ ናቸው? በሚል የጠየቅናቸው በአሜሪካ የሕግ ባለሙያ እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ፕሮፌሰር ሔኖክ ጋቢሳ የጥገኝነት ጉዳያቸው በየትኛውም የአሜሪካ መንግሥት ተቋም የማይታወቁትን መሆኑን ይናገራሉ።
“በመደበኛ ፍርድ ቤትም ይሁን የስደተኞችን ጉዳይ በሚመለከተው ፍርድ ቤት እየታየ ያለ ጉዳይ የሌላቸው ስደተኞች ሰነድ አልባ ስደተኞች በሚለው ውስጥ የሚካተቱ ናቸው።”
ዩኤስ ሲቲዝንሺፕ ኤንድ ኢሚግሬሽን ሰርቪስ (ሲአይኤስ) የሚባለው በአሜሪካ ለጥገኝነት ጥያቄ የሚያቀርቡ ሰዎችን ጉዳይ በመመልከት ፈቃድ የሚሰጠው እና የሚከለክለው ተቋም ጉዳያቸውን ያልያዘ ሰዎችም ሰነድ አልባ በሚለው ውስጥ ይገኙበታል።
ስለዚህም ፕሮፌሰር ሄኖክ “ከአሜሪካ መንግሥት ኤጀንሲዎች ጋር የሚያገናኛቸው ጉዳይ የሌላቸው ስደተኞች አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ናቸው” ይላሉ።
በፍርድ ቤት ከአሜሪካ እንዲወጡ ትዕዛዝ የተላለፈባቸው እና “እዚህም እዚያም እየተደበቁ የሚኖሩ” አልያም በፍርድ ቤት ቀጠሮ ያልሰጣቸው እንዲሁም ወደ ፍርድ ቤት ጉዳያቸውን የመውሰድ ዕድል የሌላቸው ሰዎችም ይህ የማባረሩ እርምጃ ይመለከታቸዋል።
በፍርድ ቤት ጉዳያቸው እንዲታይ ቀጠሮ በማስያዝ ወይም የቀጠሮ ቀን በመጠባበቅ ላይ ያሉት ግን አስጊ ሁኔታ ውስጥ እንዳልሆኑ በአሜሪካ የሕግ ባለሙያ እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ፕሮፌሰር ሔኖክ ያስረዳሉ።
የስደተኞችን ጉዳይ በፍርድ ቤት የሚከታተሉት ባለሙያው አሰሳ እና ጅምላ እስር እየተከናወነ መሆኑ ያስደነገጣቸው ኢትዮጵያውያን ስደተኞች “ሁሉም ሰው በፖሊስ ተይዞ ወደ አገር ቤት የሚወረወር መስሏቸው ፈርተው ነበር” ይላሉ።
ሆኖም ግን ይሄ እንደማይሆን ባለሙያው ያስረዳሉ። “ማንንም ሰው መንገድ ላይ አቁሞ መጠየቅ አይቻልም። ይሄ በቆዳ ቀለም ሰዎችን ዒላማ ማድረግ (racial profiling) ነው። ወንጀልም ነው” ሲሉ ያስረዳሉ።
አሰሳውን እና እስሩን እያካሄዱ ያሉት አካላት በአሁኑ ጊዜ እርምጃ እየወሰዱ ያሉት ሰነድ አልባ ስደተኞች ይገኙባቸዋል ተብለው ቀደም ሲል በተለዩ የሥራ ቦታዎች እና ማንነታቸው ተለይቶ በሚፈለጉት ላይ መሆኑን ሪፖርቶች ያመለክታሉ።
የትራምፕ ውሳኔዎች የስደተኞችን ሒደት ያጓትታል?
ትራምፕ የስደተኞችን ጉዳይ የሚከታተሉ የፍርድ ቤት ሠራተኞችን ማባረራቸውና በኃላፊነት የሾሟቸው ባለሥልጣኖችም በስደተኞች ጉዳይ እንደእሳቸው ዓይነት ተቋም ያላቸው መሆኑ ብዙዎችን ያሰጋ ነው።
ይህ ውሳኔ ጥገኝነት የመጠየቅ ሒደትን ሊያጓትት ይችላል? በሚል የተጠየቁት የሕግ ባለሙያ እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ፕሮፌሰር ሔኖክ እንደሚሉት፣ የስደተኞች ጉዳይን የሚከታተሉ ዳኞች እና ባለሙያዎች መባረራቸው የስደተኞች ፍርድ ቤት ላይ የሚወሰኑ ውሳኔዎችን ማስወገጃ መንገድ ነው። “ሒደቱ ይጓተታል። የስደተኞች ጉዳይ ፍርድ ቤት በጣም የሚጓተትም ይሆናል” ሲሉ ያስረዳሉ።
የስደተኞችን ጉዳይ የሚከታተሉ ፍርድ ቤቶች ሠራተኞች መባረር የፍርድ ቤቶች በሚመለከቷቸው ጉዳዮች የመጨናነቅ ሁኔታ እንዲፈጠር እና የፍርድ ቤት ቀጠሮዎች እስከ ዓመት እና ከዚያ በላይ እንዲዘገዩ እንደሚያደርግ ያክላሉ።
ሆኖም ግን ይህ ሁኔታ ስደተኞች ጉዳያቸውን በፍርድ ቤት የማቅረብ መብታቸውን በፍትሕ የመዳኘት መብታቸውን መንጠቅ እንደማይቻል ያስረዳሉ።
ስደተኞች ወደሌሎች ግዛቶች ‘መሸሽ’ ይችላሉ?
አሰሳና የጅምላ እስር ከተካሄደባቸው ግዛቶች አንዱ በሆነው ቺካጎ ከንቲባ የሆኑት ብራንደን ጆንሰን ሰዎች የታሰሩት በስደተኞች ጉዳይ ተቋም እንጂ በቺካጎ ፖሊስ እንዳልሆነ ገልጸው፣ ሰዎች መብታቸውን እንዲያውቁም አስታውሰዋል።
ወታደራዊ አገልግሎት የሰጡ ሰዎችን ጨምሮ ሰነድ አልባ ነዋሪዎች እና ዜጎች በአሰሳው መያዛቸውን የገለጹት የኔዋርክ ከንቲባ ራስ ባራካ በበኩላቸው “ሰዎች በሕገ ወጥ መንገድ ሲሸበሩ ኔዋርክ ዝም ብላ አታይም” ብለዋል።
አንዳንድ የአሜሪካ ግዛቶች ስደተኞች የፌደራል መንግሥትን አሰሳ እና የጅምላ እስርን በመሸሽ እነሱ ጋር ከለላ እንደሚያገኙ አስታውቀዋል።
የሕግ ባለሙያ እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ፕሮፌሰር ሔኖክ እንደሚሉት፣ የፌደራል መንግሥት “የተወሰነ ሥልጣን ነው ያለው። ከአንድ ግዛት ግለሰቦችን የመውሰድ መብት የለውም”።
የግዛቶች ሉዓላዊነት የተጠበቀ እንደሆነ በመጥቀስ፣ የፌደራል መንግሥትን ድጎማ አንፈልግም ብለው ከለላ የሚሰጡ ግዛቶች (sanctuary states) በአሜሪካ ይገኛሉ።
“አንድ ስደተኛ ከአንድ ግዛት ወደ ሌላው ሲሄድ የግዛት መታወቂያ ብቻ ሳይሆን የፌደራል መታወቂያ መያዝ ያስልጋል የሚል ሕግ ወጥቷል። ስለዚህ ከአንድ ግዛት ወደ ሌላው ሲሄዱ ችግር ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ። ሆኖም ግን ከለላ በሚሰጡ ግዛቶች መኖር ይችላሉ” ሲሉ አብራርተዋል።
በእነዚህ ግዛቶች መኖር ቢቻልም የስደተኞችን ጉዳይ የሚመለከተው የፌደራል መንግሥት ስለሆነ ግዛቶች “በስደተኞች ጥያቄ ጉዳይ መፍትሔ መስጠት” እንደማይችሉ ባለሙያው ያስረዳሉ።
እነዚህ ግዛቶች ሠራተኛ በመፈለግ፣ በሰብአዊነት ተቆርቁረው አልያም ከፌደራል መንግሥት ጋር ባላቸው የፖለቲካ ልዩነት ለስደተኞች ከለላ ሊሰጡ ይችላሉ።
የትራምፕ አሜሪካ ለስደተኞች ምን ትመስላለች?
የትራምፕ ዳግም ወደ ሥልጣን መመለስን ተከትሎ በአሜሪካ ውስጥ ያሉ ያልተመዘገቡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ስደተኞች በአሁኑ ጊዜ ጭንቅ ውስጥ ገብተዋል።
ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ስደተኞችን በወንጀለኝነት እና በሕብረተሰቡ ውስጥ ፍርሃትን በሚፈጥር ሁኔታ በመፈረጅ የሚያደርጓቸው ንግግሮች፤ ለዘመናት የዘለቀውን የአሜሪካንን ጥገኝነት ጤኣቂዎች ተቀባይነት ዝና የሚቀይር ነው።
ይህ በቀጣይ አራት የትራምፕ የሥልጣን ዘመን የሚቀጥከው ስደተኞችን የማሻደድ እርምጃ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይመስላል።
ፕሮፌሰር ሄኖክም “በጣም እርግጠኛነት የጎደለው እና አስፈሪ ይሆናል” ሲሉ ቀጣዩን የትራምፕ አራት የሥልጣን ዓመታትን ይገልጻሉ።
ሆኖም ግን ተስፋ እንደማይቆርጡ እና የሚለወጡ ነገሮች እንሚኖሩ “በአገሩ [አሜሪካ] እተማመናለሁ” ሲሉም ሊኖር የሚችለውን ተስፋ ይጠቅሳሉ።
“ፕሬዝዳንት ትራምፕ ዛሬ አይደለም የመጡት። ከሥልጣን ሲወርዱ የአገሪቱ ዴሞክራሲ ቀጥሏል። አሜሪካ የ250 ዓመት ልምድ ያካበተች ነች። ዛሬ ላይ ተነስቶ የሚቀየር የለም” ይላሉ።
ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ቀናት አርብ 538፣ ቅዳሜ 593 እና እሑድ 286 ሰዎች በጅምላ ተይዘዋል።
በጆ ባይደን የአራት ዓመታት አስተዳደር ዘመን ከአሜሪካ ተባረው ወደ አገራቸው የተመለሱ 1.5 ሚሊዮን ስደተኞች ናቸው።
ዘገባው ከቢቢሲ የተወሰደ ነው