በእነ ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ ከሳሽነት የተጀመረው ክስ በዕርቅ እንዲፈታ ፍርድ ቤት አማራጭ ማቅረቡ ተሰማ። ኢትዮሪቪው እንደሰማችው ፍርድ ቤቱ “በዕርቅ ሞክሩ ” በሚል ያቀረበውን አማራጭ ከሳሽ የእነ ኃይሌ ወገን ወዲያው ችሎቱ ላይ ተቀብሏል። ከኦሎምፒክ ኮሚቴ ወገን የቆሙት ጠበቆች በመርህ ደረጃ መቀበላቸውን፣ ነገር ግን ፕሬዚዳንቱ አሁን አገር ውስጥ ስለሌሉ ሲመለሱ መክረው ውሳኔያቸውን እንደሚያሳውቁ ገልጸዋል። በስተመጨረሻ እንደተሰማው የእርቅ ምክረ አሳቡን መቀበላቸውን ለኢትዮሪቪው የደረሰ መረጃ ያመልክታል።
የዕርቅ ምክረ አሳብ መቅረቡን ተከትሎ መነጋገሪያ የሆነው ከሳሾች በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ላይ ያሰራጩት ተቃውሞና መግለጫ ግለሰቦች ላይ የተነጣጠረ የስም ማጥፋት ጉዳይ ዕርቁ ላይ ዕንቅፋት ይሆናል የሚል ስጋት መፍጠሩ ነው። ያለ በቂ መረጃና ጥናት ለሚዲያና ለማህበራዊ አውዶች የተሰራጩ ሪፖርቶች በግል የኦሊምፒክ ኮሚቴ አባላትን ስም ማጉደፉ ዕርቁን ላይ ሳናካ እንደሚሆን የሚገልጹ ቢኖሩም የእነ ኃይሌ ወገን ቅድመ ሁኔታ እንዳስቀመጠም የሚናገሩም አሉ።
የእነ ኃይሌ ወገን የሆኑ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ሙሉ በሙሉ ራሱን እንዲያፈርስ ከተስማማ ዕርቅ እንደሚቀበሉ ቅድም ሁኔታ ማስቀመጣቸውን ይገልጻሉ። ከኦሊምፒክ ኮሚቴ ወገን የሆኑ ደግሞ ቅድመ ሁኔታ የሚባል ነገር ጭራሽ እንደሌለና የእርቅ አካሄዱ ከሁለቱም ወገኖች በሚወከሉ ሽማግሌዎች አማካይነት ሁለቱም የሚያቀርቡትን አቅርበው እንደሚካሄድ ይገልጻሉ። የህግ ባለሙያዎች ደግሞ “ቅድመ ሁኔታ የሚባል ነገር አልተደመጠም። ፈጠራ ነው” ሲሉ ትዝብታቸውን ያቀርባሉ።
የእነ ኃይሌን አካሄድ የሚደግፉ መንግስታዊም ሆኑ የግል ኤፍ ኤም ጣቢያዎች፣ ፍርድ ቤት ጉዳዩ በዕርቅ እንዲቋጭ ያቀረበርውን ምክረ አሳብ ብዙም ጆሮ እንዳልሰጡት፣ ክሱ መቅረቡን ሲዘግቡ በነበረበት ክብደትና “ሰበር” ዜና ደረጃም ባይሆን፣ እንደ ጥቆማ መረጃውን ለማሰራጨት ተነሳሽነት እንዳላሳዩ የኢትዮሪቬው ምልከታ ገምግሟል።
ከሳሽ ወገኖችን በተከታታይ በማነጋገር መረጃ የሚያሰራጨው ሃትሪክ ስፖርት ጉዳዩ በሽምግልና እንዲያልቅ ፍርድ ቤት አሳብ ማቅረቡን ጠቅሶ መረጃ ሰጥቷል። በመረጃው ማን ምን እንዳለና ዕርቁን አስመልክቶ ከሳሽ ወገንችን፣ ወይም ጠበቆቻቸውን አነጋግሮ ያለው ነገር የለም። ቅድመ ሁኔታ ስለሚባለው ጉዳይም ምንም አላለም።
ከሁለቱም ወገን መረጃ ያላቸው እየቀነጫጨቡ ከሚሰጡት አስተያየት በመነሳት ኢትዮሪቪው እንዳጣራቸው በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴም ሆነ በአመራሮቹ ላይ በግል የተላለፉ እገዳዎችና ማናቸውም ገደቦች ሙሉ በሙሉ መነሳታቱ ተረጋግጧል። ይህ ከሆነ በሁዋላ ነው ፍርድ ቤቱ በስምምነት ጉዳዩን እንዲቋጩ ምክር ተኮር አቅጣጫ ያመላከተው። ዜናውን እግር በእግር እየተከታተሉ ሲያቀርቡ የነበሩ ዕግዱ እንድተነሳ ገልጸው የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ቀደም ሲል የዕግዱን ዜና ላበሰሯቸው አላስታወቋቸውም። በእግዱ ሳቢያ የኦሊምፒክ አትሌቶች የሽልማት ገንዘብ ሳይሰጥ መቆየቱ በተሸላሚዎች ዘንዳ ቅሬታ እንዳስነሳ መገለጹ አይዘነጋም።
ቀደም ሲል ክሱ የሚዘልቅና የሚያዋጣ እንዳልሆነ ባለሙያዎች አስተያየት ማሰጠታቸንም የሚታወስ ነው። ፍርድ ቤቱ ባለጉዳዮች ነገራቸውን በዕርቅ እንዲጨርሱ ያቀረበውን አማራጭም ውሎ አድሮ የክስ ሂደቱ በተጀመረው አግባብ ሊቋጭ እንደማይችል፣ ክሱ ደረጃውን ጠብቆ ወደ ዓለም ዓቀፍ መድረክ ማምራቱ እንደማይቀር ግንዛቤ በመወሰዱ እንደሆነ እነዚሁ ወገኖች ያስረዳሉ።
ጉዳዩን አስመልክቶ ያነጋገርናቸውና ስማቸው ለጊዜው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ስራ አስፈሳሚ፣ ” እርቅ ጥሩ ነው። በእርቅ መጨረስ ክፋት የለውም። ብዙ የተበላሹ ጉዳዮች አሉ። ተቃውሞና ቅሬታን መግለጽ፣ በህግ አግባብ የተጓደለን ነገር መጠየቅ፣ አሰራርን መተቸት አግባብ ቢሆንም የግለሰቦች ስም በስማ በለው እንዲቆሽሽ ተደርጓል። ይህን ያደረጉት አካላት በሚዲያ ወጥተው ማረሚያ በመስጠት ያሳሳቱን ህዝብና ተበዳዮችን ይቅርታ ማለት አለባቸው” ብለዋል።
ግለሰቦች እየተጠቀሱ በተሰራጩ መረጃዎች እንደተባለው ክሱ ላይ በማስረጃ የቀረበ ጉዳይ ስለመኖሩ ወደፊት የፍርድ ቤት የፍርድ አፈጻጸም ሪፖርት በይፋ የሚገለጽ እንደሆነ አመልክተው፣ ባልተጨበጠና ባልተጣራ መረጃ በተካሄደው የስም ማጥፋት ዘመቻ የደረሰው ጉዳት ቀላል እንዳልሆነ ተናግረዋል። እንዲህ ያሉ አካሄዶች ሊለመዱ እንደማይገባ ጠቅሰው ” ስህተት፣ በደል፣ የህግ መተላለፍ፣ ብክነትና ሙስና ካለ በጅምላ የግለሰቦች ስም ሳይጎድፍ መጠየቅ ይቻል ነበር” ሲሉ በሆነው ሁሉ ማዘናቸውንም አመልክተዋል።
“ስም ሲያጠፉ ያሰቡበት አይመስለኝም። እንደው ዝም ብለው በውርጅብኙ ተደናግጠው ይበተናሉ የሚል ሂሳብ ሰርተው ነው። የሚፈራ ስብስብም መስሏቸው ሊሆን ይችላል። ያ ሳይሆን ቀርቷል። አሁን ችግሩ ዕርቅ ሲከናወን ሳይታሰብበት የተረጨው አሉባልታ ያስከተለው ስብራት እንዴት ይጠገን የሚለው ነው” ያሉን እኚሁ ሰው፣ ” ይህን ሲመሩና ሲያስተባብሩ የነበሩት በግል ይህን የማድረግ ድፍረት አይኖራቸውም። ከደፈሩም ታማኝነታቸውን እስከወዲያኛው ያጣሉ። ስለዚህ ዕርቁ እንዴት ሊሳካ እንደሚችል አሁን ላይ ለመረዳት ይከብደኛል” ብለዋል። ጉዳዩ የሞራል፣ የቤተሰብ፣ የክብርም የዕምነትም እንደሆነ አመልክተዋል።
“እነ ኃይሌ ወይም ከሳሾች እርስዎ እንዳሉት በአደባባይ ማስተባበያ ወይም ማረሚያ የማይሰጡ ከሆነ ምን ይከተላል?” በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ “አለመስማማታችንን፣ ያልተስማማነው በምን መነሻ እንደሆነ፣ የሚያስረዳ የሽማግሌዎች ሪፖርት ለፍርድ ቤት ይቀርባል። ከዛ ተከታዩ የክስ ሂደት ይቀጥላል” ሲሉ መልሰዋል። በእሳቸው ዕምነት ጉዳዩ በስምምነት ቢያልቅ እንደሚወዱ፣ በዚህም እውነተኛ ዕርቅ በማውረድ ለሌሎች አርአያ መሆን እንደሚቻልም አመልክተዋል። ተድበስብሶ በሚከናወን ሽምግልና ግን ዕርቅ ሊያወርድ እንደማይችል አስታውቀዋል።
ሌላ ያነጋገርናቸው የህግ ባለሙያ ” ብዙ ነገር ተበላሽቷል። የፓሪስ ኦሊምፒክ ውጤት ያበሳጨውን ህዝብ በዛው ስሜት ውስጥ ሆኖ የቀረቡለት ዜናዎችና ትንታኔዎች ጉዳት አድረሰዋል። ይህን ጠግኖ ወደ ዕርቅ መመለስ ቀላል አይሆንም። ድፍረት ይጠይቃል። የዝና፣ የክብርና ታማኘትን ወዘተ ጉዳዮችን ስለሚነካ ስህተት በተሰሩባቸው አግባቦች ልክ ማስተባበያ ለማቅረብ የከሳሽ ወገን ፈቃደኛ ይሆናል ተብሎ ስለማይታሰብ ከሽማግሌዎች ብዙ ይጠበቃል” ብለዋል።
“ስማችን ጠፍቷል” በሚሉ ተከሳሾችና “ማስተባበያ ከሰጠን ዝናችን ይበላሻል፣ ተአማኝነታችን ይቀንሳል፣ ክብራችን ይጎድላል” ብለው በሚሰጉ ከሳሾች መካከል ያለውን ልዩነት ማቀራረብ አስቸጋሪ ከሆነ፣ በጠበቆቻቸው አማካይነት አስታራቂ መግለጫ በመስጠት ነገሩን አላዝቦ መጨረስ እንደሚቻል ያነጋገርናቸው የህግ ባለሙያ መክረዋል።
“ስለዚህ” አሉ የህግ ባለሙያው፣ ” ስለዚህ ቴክኒካል አካሄዶችን ተጠቅሞ ዕርቅ በማውረድ መገላገሉ አቋራጭ መንገድ ነው። ህዝብም ቢያወራው ለቀናት ነው ይረሳል” ሲሉ የህግ ባለሙያው አመላካች አሳብም አቅርበዋል። ይህ የሚሆነው ትልቁን ስዕል ማየት ሲቻል እንደሆነ አውስተው ሁሉም ወገኖች ትዕግስትንና ብልሃትን በመምረጥ፣ ከተራ የማህበራዊ ሚዲያ ውዳሴና ከሚዲያ ገበያ ራሳቸውን በማግለል ሊመክሩና ሊዘክሩ እንደሚገባ አመልክተዋል። ከምንም በላይ ስፖርቱ ከገባበት ቅርቃር ሊወጣ የሚችልበት ዋና ጉዳይ ላይ ሊያተኩሩ እንደሚገባ ጥቆማ ሰጥተዋል።
ቀደም ባሉ ሪፖርቶቻችን የህግ ባለሙያዎች የኦሊምፒክ ምርጫን አስመልክቶ የአገር ውስጥ ፍርድ ቤቶች ብይን የመስጠት መብት እንደሌላቸው፣ የአገር ውስጥ የማህበራት ማደራጃ ህግ ሳይሆን ለኦሊምፒክ ኮሚቴ ተልኮ የጸደቀው የብሄራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው ህግ ገዢ እንደሆነ የዓለም ዓቀፍ ተሞክሮ በማጣቀስ ማስታወቃቸው አይዘነጋም። ምርጫን አስመልክቶ ቅሬታ ካለ በሃያ ቀን ውስጥ ሎዛን ለሚገኘው ህጋዊ የግልግል ፍርድ ቤት ብቻ ማቀረብ እንደሚቻል ጠቅሰው ምክር ለግሰው እነደነበር ይታወሳል።
ህጋዊ አካሄዱ እየታወቀ ምርጫው ከተደረገ ዓመት በላይ ተቆይቶ ኦሊምፒክ ሊጀመር ሲል የተነሳው ትርምስ በውድድሩ ወቅት ሯጮችን ለስነ ልቦና ቀውስ መዳረጉን በስፍራው የነበሩ ታዛቢዎች ከውድድሩ በሁዋላ መናገራቸው አይዘነጋም። ኦሊምፒክ ኮሚቴው “ጊዜውን ጨርሷል” በሚል እንዲፈርስ የተጀመረው እንቅስቃሴ በሻለቃ ኃይሌ መሪነት ከኦሊምፒክ በሁዋላ ወይም አስቀድሞ ምርጫው እንደተደረገ ሊሆን እንደሚገባው ኢትዮሪቪው አቋሟን ማስታወቋም አይዘነጋም።
ውድድር ላይ ያሉ አትሌቶችን ከመደገፍና የአሸናፊነት ሞገስ ከማላበስ በተቃራኒው የውድድር መዳረሻን ቀንን ጠብቆ የተነሳውና ዝግጅት የተደረገበት ትርምስ የተመረጠበትን ወቅት ከብሄራዊ አጅንዳ ጋር አይይዘው አስተያየት የሰጡም ጥቂት አልነበሩም። ስፖርተኞች ለዚያውም በዓለም ዓቀፍ ደረጃ አገር የሚወክሉ የስነ ልቦና ግንባታ እንጂ ረብሻ እንደማያስፈልጋቸው ጠንቅቀው በሚያውቁ ልምድ ያላቸው ወገኖች ይህ መፈጸሙ አሁን ድረስ “ዋናው ምክንያቱ ምንድን ነው” በሚል ግራ የተጋቡ ጥቂት አይደሉም። ውድድር ሲጀመር ትርምስ መፍጠርና ተናቦ ዘመቻ መክፈት ያስፈለገበትን ምክንያት በተደጋጋሚ ከከሳሾች ጋር ጥያቄና መልስ የሚያደርጉ ሚዲያዎች የዘለሉት ጉዳይ መሆኑ “ዋናው አጀንዳ ምንድን ነው” የሚለውን ጥያቄ ያጎላዋል። ይህ ሲባል ሌብነት፣ አድልዎ፣ የህግ ጥሰት፣ ማናቸውም ያልተገቡ አሰራሮች በዝምታ ይታለፉ ሳይሆን፣ ተወዳዳሪዎችን በስነ ልቦና የሚያሽመደመድ ትርምስ የተፈጠረበት ወቅት ቀና ልቦና ላላቸው ሁሉ አግባብ ባለመሆኑ ነው።
አሁን ድረስ ይህን ጥያቄ የሚጠይቁ እንደሚሉት እነ ኃይሌ የፓሪስ ኦሊምፒክ ውድድር ሊጀመር ሳምንት ሲቀረው ይህን የተቀነባበረ ዘመቻ ለመክፈት የመረጡበት ዋና ምክንያት ለእውነትና በትክክል ለስፖርቱ ተቆርቋሪ ከሆኑ ወገኖች ምላሽ ሊያፈላልጉ ይገባል። ያቺ ወሳኝ የኢትዮጵያ ባንዲራ ከፍ የሚልበት ወቅት ታስቦና ተደራጅቶ በተከፈተ ዘመቻ አትሌቶቹ በስነልቦና እንዲጎዱ አድርጓል? ምን ጫና አስከትሏል? የሚለውን ጉዳይ ከስነ አዕምሮ ባለሙያዎች እና ከራሳቸው ከአትሌቶች መረጃ በመሰብሰብ ለወደፊቱ እንዳይደገም ሃቁ ገሃድ ሊወጣ እንደሚገባ የሚጠይቁና የሚያሳስቡ ኢትዮሪቪውን ይህን ጠይቀዋል።
ተከሳሾች የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቲ እንደተቋም፣ ፕሬዝዳንቱ ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ፣ ዐቃቤ ነዋይዋ ዶ/ር ኤደን አሸናፊ፣ ዋና ፀሐፊው አቶ ዳዊት አስፋው እና ምክትል ፀሐፊው አቶ ገዛኸኝ ወልዴ ሲሆኑ፣ ከሳሾቹ በፈቃደኛነት የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንትነትን “በቃኝ” ያለው ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ አሁን ከአትሌቲክስ ስራ አስፈጻሚነት የወጣው አትሌት ገዛኸኝ አበራ፣ የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢያሱ፣ እና ከኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ጽኃፊነታቸው የተነሱት የኢትዮጵያ ቴኒስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ታምራት በቀለ መሆናቸው ቀደም ሲል ክስ መመስረቱን ሲያውጁ የነበሩ ሚዲያዎች ጠበቆቻቸውን ጠቅሰው ማስታወቃቸው አይዘነጋም።
ከእነ ሻለቃ ኃይሌ ጋር አብረው ከሳሽ የነበሩት የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታው አምባሳደር መስፍን ቸርነት፣ ” መንግስትን ከሳሽ አስመስሎ ያቀርብና በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በጣልቃ ገብነት አሉታዊ ክስ ያስነሳል” በሚል ከከሳሽነት ሊስት እንዲቀነሱ መደረጉን የከሳሽ ወገን ደጋፊዎች ቢገልጹም፣ ኢትዮሪቪው ባላት መረጃ ” አርፈው ይቀመጡ” በሚል መንግስት በሰጣቸው ማስጠንቀቂያ ሳቢያ ራሳቸውን ከከሳሽነት እንዳገለሉ ጠቁመን ነበር።
በሌላ ዜና ባለቀ ሰዓት ከአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ውክልናውን ሰርዞ ወደ ኦሮሚያ ያመራው ስለሺ ስህን ባሸነፈበት ምርጫ የተከበሩ አቶ ዱቤ ጅሎን ወክለው ድምጻቸውን ለገብረእግዚአብሄር እንዲሰጡ ከተደረጉት ሶስት ተወካዮች መካከል የአንዱ ድምጽ ውድቅ መደረጉ ታውቋል። ይህም የሆነው አንድ ድምጽ ሰጪ የምርጫው ድምጽ መስጫ ፎርም ላይ የራይት ምልክት ማድረግ ሲገባው ኤክስ በማድረጉ ነው። በዚህ ሳቢያ ገብሬ አንድ ድምጽ ሊያጣ ችሏል። ገብሬ ለስለሺ “እንኳን ደስ አለህ ” ብሎ ስልክ እንደደወለለት በሸገር ስፖርት ላይ ተናግሯል።
ዱቤ ጅሎን ለይስሙላ ወክለው ገብረእግዚአብሄርን ለማስመረጥ የተሰራው ሂሳብ ስሌቱ ለጥቂትም ቢሆን የተበላሸው በዚህ መነሻ እንደሆነ እማኞች ገልጸዋል። ስለሺ 11፣ ገብረእግዚአብሄር /አንድ ድምጽ ተሰርዞበት/ 9 ድምጽ አግኝተው የተጠናቀቀውን ምርጫ የተከታተሉ እንዳሉት ስለሺ ” ከፈለጉ ይምረጡኝ፣ ካልፍለጉ ይጣሉኝ” በሚል ምንም ዓይነት ክፍያ እንዳልፈጸመ አመልክተዋል። ይሁን እንጂ በሌሎች ወገኖች ድምጽ የመግዛት ስራ ይሰራ ስለነበር ያንን ለማክሸፍ ስለሺ የሚያሸንፍበትን ድምጽ እንዲያገኝ አስፈላጊውን ሁሉ ያደረጉ ወገኖች መኖራቸውን እነዚሁ ወገኖች አስታውቀዋል። ኃይሌ ገብረእግዚአብሄር ወይም ዱቤ ጅሎ ቢመረጡ የሚል አስተያየት ከምርጫው አስቀድሞ መስጠቱን የጠቆሙ፣ ለምን ስለሺን ሊያነሳ እንዳልፈለገ ግልጽ እንዳልሆነላቸው ተናግረዋል። ምን አልባትም ይህ አካሄድ ስለሺ በሌሎች ወገኖች እንዲደገፍ ምክንያት ሳይሆን እንዳልቀረ ግምታቸውን ሰጥተዋል። ድፋማው ያልተገለጸለት ዱቤ ” የወከለኝ አዲስ አበባ እንዴት ድምጽ ይከለክለኛል” ሲል ከምርጫው በሁዋላ ሃዘን እንደተሰማው ገልጿል። ዱቤ ዜሮ ድምጽ ነበር ያገኘው። ምትጫው ሳይደረግ ቀደም ብሎ ኃይሌን የሰጠውን አስተያየት በጤናማ አስተያየትነቱ የወሰዱም አሉ።
በቲሌግራም ይከተሉን / https://t.me/+f_kxmaPjD-9jYTdk