ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ በሶማሌ ክልል የጎዴን መስኖ ሲያስመርቁ ” በትንሹም በትልቁም ግጭት አያስፈልግም” ማለታቸውን ጠቅሶ ኦብነግ መግለጫ ማውጣቱን የጀርመን ድምጽ አቀናጅቶ ዜና አደረገው። “የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መልዕክት እና የኦብነግ መግለጫ” ሲል የሰላምን ጥሪ ከተቃውሞ ጋር አሳስሞ አቅርቧል።
“የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ከስልጣን ሊወርዱ ነው” በሚል ዜና ከጠላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ጋር በስራ ተገናኝተው የተነሱትን ፎቶ ተጠቅመው ዛሬ ዜና እንዳሰራጩት ሁሉ፣ የጀርመን ድምጽ ሁለት ከቶውንም የማይገናኙ ዜናዎችን አትሟል።
የጎዴ መስኖ ልማት በደርግ ስርዓት የተገነባ ቢሆንም ምክንያቱ ሳይሆን ኢህአዴግ እንዲፈርስ እንዳደረገው የሚታወቅ ነው። ይህ ሲሆን የኦጋዴን ነጻ አውጪ ተቃውሞ አላሰማም። የሶማሌ ህዝብ ከብቶቹንና ለራሱም ጭምር ውሃና ግጦሽ ፍለጋ ሲነከራተት እንደሚኖር እየታወቀ የጎዴ ማስኖ መገንባቱ ሰበር ዜና ሊሆን ሲገባው ተቃውሞ ማስነሳቱ፣ ወይም ለትችት መነሻ ሆኖ ዜና መሆኑ በርካቶችን አስገርሟል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ በምረቃው ላይ ተገኝተው ለተናገሩት የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦብነግ) ይህንን የጠቅላይ በ X ገጹ ባወጣው መግለጫ “ሰላም ስጦታ አይደለም – የመስዋዕትነት ውጤት እንጂ” ማለቱን የጀርመን ድምጽ ጽፏል። አክሎም በአካባቢው ሰላምን ለማስቀጠል ዋጋ የከፈሉ ያላቸው የቀድሞ ተዋጊዎቹን ማክበር እንደሚያስፈልግ መጠቆሙን አመልክቷል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መልዕክትን ተንተርሶ የኦብነግ መግለጫ የወጣው ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ በሶማሌ ክልል ባደረጉት ጉብኝት “ሙሉ ትኩረታችን ልማት ብቻ እንዲሆን አደራ ማለት እፈልጋለሁ” ማለታቸውን ተከትሎ እንደሆነ የጀርመን ድምጽ ዘግቧል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሶማሌ ክልል ሸበሌ ዞን የጎዴ መስኖ መሠረተ ልማትን ባለፈው አርብ ሲያስመርቁ “የሶማሌ ክልል ለአካባቢው ሕዝቦችም በረከት መሆን የሚችል ነው” በማለት የክልሉን ህዝብና አመራሩን አበረታተው ነበር።
በዚሁ ሥነ-ሥርዓት ላይ “በትንሹም በትልቁም ግጭት አያስፈልግም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “ኢትዮጵያ የጦርነት ሳይሆን የሰላም ምድር እንድትሆን በትብብር እንሥራ” ሲሉ መጠየቃቸውን ቃል በቃል ንግግራቸውን ጠቅሶ የዘገበው የጀርመን ድምጽ፣ ኦብነግ ኤርትራ መሽጎ መኖሩን የኩራት ያህል ቆጥሮለት እንደ ዜና ማመጣጠኛ አቅርቦታል። ዜናውን አንብበው የጠቆሙን ” የጎዴን የመስኖ ግድብ ዜና ለማደብዘዝና ለማራከስ መግለጫውን ተጠቅመውበታል” ሲሉ በሆነው ማዘናቸውን ተናግረዋል። በሁሉም ነገር ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለማጣጣል ታስቦ የተሰራው ዜና ቢያንስ የሶማሌ የክልሉ ህዝብ ለተሰራለት ስራ የሰጠውን ክብር ግንዛቤ ውስጥ ማግባት ይገባው እንደነበር አመልክተዋል።
የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦብነግ) ለዚህ በሰጠው ምላሽ ሰላም በመስዋዕትነት የሚገኝ መሆኑን በመጥቀስ፤ በአካባቢው ሰላም እንዲገኝ መስዕዋትነት ከፍለዋል ያላቸው የቀድሞ ተዋጊዎቹ እንዲከበሩ ጠይቋል። ድርጅቱ አስመራ ከትሞ ኢትዮጵያ ላይ ሴራ ሲገምድ ከመኖሩ ውጭ በኢህአዴግ ዘመን አንድም ቀበሌ ነጻ አውጥቶ እንደማያውቅ ድርጅቱን ጠንቀቀው የሚያውቁ ይናገራሉ።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ በሶማሌ ክልል ሸበሌ ዞን የጎዴ መስኖ መሠረተ-ልማት ግንባታን ትናንት ሲያስጀምሩ በክልሉ የሚለማው መሬት ማደጉን በዐወንታ አወድሰዋል። አያይዘውም የሰላም መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን “ሀብታም” ያሉት የሶማሌ ክልል መልማት የኢትዮጵያን ዕድገት የሚበይን ስለመሆኑም ጀርመን ድምጽ የኦጋዴን ነጻ አውጪ ድርጅት ቅሬታ ባጎላበት እጁ ጠቁሟል።
“የሶማሌ ክልል ለማደግ፣ ለመበልፀግ፣ ኢትዮጵያን ፣ ምሥራቅ አፍሪካን ለመመገብ የሚያስችል ሀብታም ክልል ነው። በትንሹም በትልቁም ግጭት አያስፈልግም፤ ተረጋግተን፣ ተወያይተን፣ በተደመረ መንፈስ የጀመርነውን የልማት ሥራ ማጠናከር ይኖርብናል” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
የጀርመን ድምጽ “ኦብነግ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ንግግር የሰጠው ምላሽ” የሚል ርዕስ ሰጥቶ አብይ አሕመድ “አትጣሉ፣ልማት ላይ አተኩሩ፣ ክልሉ አፍሪካን ይመግባል፣ የኢትዮጵያ ዕድገትም አመላካች ነው…” በማለታቸውን “ኦብነግ ምላሽ ሰጠ” ብሏል።
የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦብነግ) ይህንን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ንግግር አያይዞ በ X ባወጣው መግለጫ “ሰላም ስጦታ አይደለም – የመስዋዕትነት ውጤት እንጂ” ብሏል። አክሎም በአካባቢው ሰላምን ለማስቀጠል ዋጋ የከፈሉ ያላቸው የቀድሞ ተዋጊዎቹን ማክበር እንደሚገባ መጠቆሙን ያመለከተው ዜና የመስኖ ልማትና አስመራ ተቀምጦ በውጭ ኃይሎች ተልዕኮ አገር ሲያውክ የነበረው ኦብነግ ካሰማው ጩኸት ጋር ግንኙነቱ እንዳልገባቸው ዜናውን የጠቆሙን አመልክተዋል።
“የኦብነግ ተዋጊዎች ለበርካታ አሥርት ዓመታት የዘለቀውን ግጭት በማስቆም ረገድ ወሳኝ ሚና ቢኖራቸውም ባለፉት ለስድስት ዓመታት ግን ቸል ተብለዋል” ማለቱን የጀርመን ድምጽ ከመግለጫው ጠቅሶ ጽፏል። በዚህም ኦብነግ ብስጭቱ ስልጣን በመከለከሉ ሳቢያ መሆኑን ገልጿል።
ኦብነግ “ፍትሕ እስከ መቼ ቸል ሊባል ይችላል? በቸልተኝነት ላይ የተገነባው ሰላም ደካማ ነው በማለት ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጥ አሳስቧል” ያለው የጀርመን ድምጽ አያይዞ “ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ኢትዮጵያ የሰላም ምድር እንድትሆን ጥሪ አድርገዋል”በማለት ዜናውን ሁለት የማይገናኙ ጉዳዮችን አላትሟል። “ኢትዮጵያ ለማኝ ሳትሆን ረጂ እንድትሆን፣ የጭቅጭቅ የጦርነት ምድር ሳትሆን የሰላም ምድር እንድትሆን ሁላችን በተባበረ ክንድ፣ በተደመረ መንፈስ አብረን እንድንሠራ አደራ እላለሁ” ሲሉ አብይ አሕመድ መናገራቸውን ገልጿል።
የኦብነግ የአዲስ ዓመት መልዕክት ያለፈው የጎርጎረሳዊያን ዓመት በጠቅላላው ኢትዮጵያ ውስጥ ከነበረው ሁኔታ አንፃር በሶማሌ ክልል አንፃራዊ ሰላም ነበር ያሉት የኦብነግ ሊቀመንበር አብዱራሕማን ማሐዲ በክልሉ አሰቃቂ ግጭቶች፣ መፈናቀል፣ ውድመት እያደረሰ መሆኑን ከቀናት በፊት ባወጡት መልዕክት መግለጹን የጀርመን ድምጽ ከጎዴ የመስኖ ላማት ጎን ለጎን አስታውሷል።
ከራስ ገዝ ሶማሌላንድ አስተዳደር በኩል ያለው “ያልተፈቀደ ተሳትፎ እና ጣልቃ ገብነት” በሶማሌ ክልል ችግር ማስከተሉንም የኦብነግ መሪ መጥቀሳቸውን አመልክቷል። ኦብነግ ከግብጽ ጋር ግንኙነት ፈጥሮ እየሰራ መሆኑን ጀርመን ድምጽ አላነሳም። ድርጅቱ ሶማሌ ላንድ ላይ ጣቱን የቀሰረው ግብጽና የሃሰን ሼኽ መንግስት በሰጡት የቤት ስራ መሆኑን ጠቅሰው ሲቃወሙት እንደነበር አይዘነጋም።
ከሳምንት በፊት በሶማሊላንድ የፀጥታ ኃይሎች እና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ፖሊሶች መካከል ግጭት ተከስቶ እንደነበር ያረጋገጡት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው ጉዳዩ በዘላቂነት መፍትሔ እንዲያገኝ በሀገር ሽማግሌዎች እየታየ መሆኑን ትናንት አርብ በሰጡት መግለጫ ማመለከታቸውም የዜናው አካል ነው።
“የተከሰተ ግጭት እንደነበር በሚዲያዎች ላይ ያየነው ነገር ነበር። ይህንን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በአጎራባች ክልሎች ባሉ የሀገር ሽማግሌዎች ጉዳዩ የተያዘ ነው”።
የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጭ ግንባር (ኦብነግ) ሊቀመንበር ራስን በራስ የማስተዳደር እና የመወሰን መብትን ለማስከበር የሰላማዊ ትግል ጥሪ ያደረጉ ሲሆን ኤርትራ ውስጥ በድርጅቱ እና በኢትዮጵያ መንግስት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት አሁንም ሳይፈጸም በመቆየቱ “በመንግስት ቅንነት እና በዘላቂ ሰላም ላይ ትልቅ ጥርጣሬ ፈጥሯል” እንዳሉም የጀርመን ድምጽ አመልክቶ ዜናውን አስሯል።