በሞገስ ዘውዱ ተሾመ ቦርከና አማርኛ ታህሳስ 28፣ 2017 ዓ ም

በዘመናዊ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ታሪክ ውስጥ አሻራቸው ጎልተው ከሚታዩት ግለሰቦች መካከል አቶ ጀዋር ሲራጅ መሀመድ በመጀመሪያ ረድፍ ላይ ይቀመጣሉ ቢባል ማጋነን አይሆንም። ገና በለጋ እድሜው የኦሮሞን ፖለቲካ የናጠ፣ አፍርሶ የገነባና እና የሚያጓጓውን የልጅነት ኑሮ ወደ ጎን ትቶ፣ ቄሮን በማነቃነቅ ከሌሎች ሀይሎች ጋር በመሆን አፋኙን የኢህአዴግ ስርአት ገዝግዟል። የመጣው ለውጥ ፍሬ አፍርቷል ወይ? በለውጡ መጨናገፍ ውስጥ የኦቦ ጀዋር ደርሻስ ምንድን ነው? አሁን ብቅ ያለው ለምንድን ነው? ከሌሎች የፖለቲካ ሀይሎች ጋር በምን መልኩ ይተባበራል? በአጠቃላይ ከእስር ቤት ግዞት በኋላ የምናየው ጀዋር ከቀድሞው ጀዋር በምን ይለያል? የአስተሳሰብ ወይስ የስትራቴጂ ለውጥ? የሚሉ ጥያቄዎች መነሳታቸው የሚጠበቅ ነው።
በዚህ ምጥን ጽሁፍ ከላይ የተዘረዘሩትን ሁሉንም ጥያቄዎች ለመመለስ አልሞክርም። ይልቁንም፣ አልጸጸትም/ Hin Gaabbu በተሰኘው የአቶ ጀዋር መጽሀፍ ላይ በማተኮር መሰረታዊ የሆኑ ጉዳዮችን በማንሳት ወፍበረር ዳሰሳን ማቅረብ ይሆናል። ይህን ግምገማ ለማቅረብ ያነሳሳኝ ዋናው መግፍኤ(driving factors) የኦቦ ጀዋር ወደ ትግል ሜዳ በይፋ መመለስ ትልቅ አንድምታ ስላለው፣ እንዲሁም በመጽሀፉ ውስጥ የተነሱት ጉዳዮች ከግለሰቡ በላይ በመሆናቸው ነው። በመሆኑም፣ የዚህ ዳሰሳ አድማስ የመጸሀፉ አስፈላጊነት፣ የግለሰቡ አስተዳደግ እና ፖለቲካዊ ፋይዳዎች፣ የታሪክ ትርክቶች፣ የኦቦ ጀዋር የፖለቲካ እይታዎች፣ በመጸሀፉ ውስጥ የተሰነዘሩት መፍትሄዎች እና መጪውን የፖለቲካ ጉዞን ይመለከታል።
ለአንባቢው ከወዲሁ መግለጽ የምፈልገው ከዚህ በፊት በአማርኛ የመጽሀፍ ዳሰሳ(Book Review) ሰርቼ ስለማላውቅ አንዳንድ የአቀራረብ መዛነፍ ቢኖር ይሄንኑ ተረድታችሁ ይዘቱ ላይ እንድታተኩሩ እጠይቃለሁ። በተጨማሪም፣ የአልጸጸትም/Hin Gaabbu መጽሀፍ ከርእሱ እና የፖለቲካ እየታችሁ ባሻገር በመሆን ብታነቡት ይመከራል።
- የመጽሀፉ አስፈላጊነት እና ጠንካራ ጎኖች
ከእያንዳንዱ መጸሀፍ የምንማረው አንድ ቁምነገር ይኖራል፣ በመጸሀፉ ውስጥ ከተካተቱት ነጥቦች ብቻ ሳይሆን ካልተገልጹትም ጭምር። ይሄንን ብሂል ከተከተልን የኦቦ ጀዋር መጽሀፍ በጥልቀት ከዘረዘራቸው በጥቂቱ፣ በከፊል ከዳሰሳቸው ጉዳዮች በመጠኑ፣ ጭራሽ ካልዳሰሳቸው ጉዳዮች ደግሞ በእጅጉ እንማር ይሆናል። ነገር ግን የመረዳታችን ስፋቱ እና ጥልቀቱ የሚወሰነው እንደየንባባችን ይወሰናል።
ኦቦ ጀዋር ከዋሉልን ትልቅ ውለታ መካከል የራሱን አስተዳደግ፣ የትግል ጉዞ እና አበርክቶ በመጽሀፍ መልክ ገና በወጣትነት እድሜው ማቅረቡ ነው። ይሄ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል ውስጥ የተለመደ አይደለም። ከአሁን ወዲህ በሰነድ የሰፈረውን እያመሳከሩ የደራሲውን እና ፖለቲከኛውን እያንዳንዱን እንቅስቃሴ ለመከታተል (ለክፉም ሆነ ለደግ) ያመቻል። ስለሆነም፣ ደራሲውን ለዚህ ትጋቱ እናመሰግናለን።
ሌላው የመጽሀፉ ጠንካራ እና ምናልባትም ልዩ አቀራረብ ስለ ግል ህይወቱ በዝርዝር ያቀረበበት መንገድ ነው። በመጀመሪያው የመጽህፉ ክፍል እንደተቀመጠው፣ ፖለቲከኛውን ጀዋር ለአፍታ ረስተን ማህበራዊውን ግለሰብ እንድንተዋወቅ ይጋብዘናል። ይህ ክፍል ከድንቅ የማስታወስ ክህሎት በተጨማሪ ከፖለቲካው በፊት በኑሮው ላይ ያደረገውን ትግል ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል። ከፖለቲካ ትግል በፊት ከኑሮ ጋር ታግሎ ድል መንሳቱን ያሳየናል። እንደሚታወቀው ለስኬት ከደረሱት ስዎች ጀርባ የራሳቸው ትልቅ ጥረት፣ የቤተሰብ አስተዳደግ፣ የማህበረሰብ አሻራ(ቤተ-እምነቶችን ጨምሮ) እና የሌሎች ግለሰቦች ድምር አሻራ ይኖራል። በኦቦ ጀዋር የልጅነት ዘመንም ይሄንኑ እንመለከታለን። ለምሳሌ ዱሙጋ ሳለ ትምህርት ትቶ ወደ እርሻ ሲገባ መሬት የሰጠው የቅርብ ዘመድ ነው፣ አሰላ ትምህርቱን የተከታተለው እህቱ ጋር ተጠግቶ ሲሆን የውጪ የትምህርት እድል እንዲያገኝ የረዳው መምህር አበራ መሆኑን እንረዳለን። ይሄንን ከፍል ሳነብ የደራሲውን ሳይሆን የራሴን ታሪክ ዳግም እየኖርኩ (reliving) ሁሉ መሰለኝ። ምናልባትም ይሄ ሁኔታ የሌሎች አንባቢያን ታሪክም ይሆናል የሚል እምነት አለኝ።
ከሌሎች ክፍሎች ሲነጻጸር ይሄኛው ክፍል ከፍተኛ ግልጽነት በተሞላበት መልኩ የተጻፈ ነው። ለምሳሌ በገጽ 48 ላይ የሰፈረው እንዲህ ይላል: “ለካ እኔ ለመሳም የተጠመጠምኩባት ፍቅረኛዬ ሳትሆን እናቷ ነበረች“። ሌሎችም ተመሳሳይ የግል ገጠመኞች ሳይሸራረፉ ቀረበዋል። አስፈላጊነቱን በግሌ ባልረዳም፣ ዘርማንዘሮቹንም እስከ 7 ቤት በመዘርዘር ይጀምራል። በቅርቡ ይሄንን የአጻጻፍ ስልት ከመረጡት መካከል ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ በ ህብር ህይወቴ መጽሀፋቸው እና አቶ ብርሃኑ ባይህ በ ያለተጠበቀው ጉዙ መጽሀፋቸው ናቸው። ይሄ የግል ህይወታቸውን ከማይግልጹት ወይም ቢገልጹም መርጠው ከሚያቀርቡት ደራሲያን የተለየ አቀራረብ በመሆኑ ሊደነቅ ይገባዋል።
በአጭሩ፣ በትውልድ እና አስተዳደግ ከፍል ውስጥ የዱሙጋው ከርታታ፣ የአሰላው አፍላ ወጣት(ለመጀመሪያ ጊዜ የፍቅርን ወላፈን ያጣጣመው በዚህ ወቅት ነበር)፣ የአዳማው ነውጠኛ፣ የሲንጋፖሩ ታታሪ(ከአዛምድና እውነት ሀሰት ትምህርት ስርአት ሄዶ ከአዲስ አለም ጋር የተላተመና አምጾ አፋን ኦሮሞን ለኮሌጁ ያስተዋወቀ መሆኑን ልብ ይሏል)፣ የስታንፎድ እና ኮሎምቢያው የፖለቲካ ሳይንስ ተማሪ እና ተመራማሪ ይገኝበታል። ይሄ ደግሞ ለቀጣዩ የቄሮ ንቅናቄ አደራጅ እና ታጋይ፣ የፓርቲ ፖለቲካ ጀማሪ፣ የፖለቲካ ቆማሪ፣ ከባለ ባንክ እና ታንክ መሪ ጋር የተላተመው አብዮተኛ እና የቃሊቲ ግዞተኛ ጀዋርን የበለጠ እንድረዳ ተደርጎ ተቀንብቧል። ይሄም ሰውዬውን ከሞላጎዳል ምሉእ በሆነ መልኩ እንድንረዳው ያደርጋል።
በዚህ ከፍል ሁለት ውስንነቶች አስተውያለሁ። አንዳኛው (ቀጥሎ በዝርዝር እንድምንመለከተው) የታሪክ ትርክትን ያለቦታው እና በቂ ጥናት ማካተት ሲሆን ሁለተኛው እራሱን ለዚህ ስኬት ያበቃውን የብዝሀ-ቋንቋ ችሎታን በፖለቲካዊው ጀዋር ላይ ያለማየታችን ነው። የአማርኛ ቋንቋ ችሎታው ከልጅነቱ ጀምሮ በእጅጉ እንደጠቀመው እና የኦሮሚያ ክልል የትምህርት ስርአት ተማሪዎችን ለከፍተኛ ችግር እንደዳረገ በዚህ መልኩ ያስቀምጣል: “ብዙ ተማሪዎች ከታች ጀምረው አስረኛ ክፍል እስኪደርሱ ድረስ ከሁለት ቋንቋዎች አንዱን ብቻ እየተናገሩ ወይም እየተማሩ ነው የመጡት(…) ከታችኛው ክፍል ጀምሮ የተማሩት በአፋን ኦሮሞ ነው። አማርኛ ከአምስተኛ ክፍል ጀምሮ ሲሰጥ የቆየ ቢሆንም፣ የነበረው የመማር ማስተማር ሁኔታ የልጆቹን ችሎታ የሚያጠናክር አልነበረም”(ገጽ 11 ይመልከቱ)።
ይሄንን ትውልድ የመግደል ፖሊሲን በዚህ መልኩ የተቸው ማህበራዊው ጀዋር ከጥቂት አመታት በፊት አንዲት የወለጋ ልጅ ሁሉንም ትምህርት A አስመዝግባ አማርኛን F ስታገኝ የአቶ ጀዋር አጭር አስተያየት “እንኳን ተገላገልሽ!” የሚል ነበር። ይሄንን ተቃርኖ በተለዋዋጭ የትግል ስትራቴጂ ብቻ የምናልፍ ይሆን? ለእኔ አይመስለኝም። የህብረባህላዊ አንድነት መገንቢያ ዘዴዎች(integrating mechanisms) ውስጥ አንዱ እና ወሳኙ የቋንቋ ፖሊሲ በመሆኑ ፖለቲከኛው ወደፊት በሚኖረው ጉዙ ይሄንን ጉዳይ ትኩረት ይሰጠዋል የሚል እምነት አለኝ።
- ጀዋር እና የታሪክ ትርክት
እንደ አንድ የፖለቲካ ሳይንስ ተማሪ እና ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰብ ኦቦ ጀዋር በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ላይ የራሱን አረዳድ መሰንዘር ይችላል፣ ይጠበቃልም። ጥያቄው የግል ትውስታ(Memoir) ቦታው ነው? ከሆነስ ለሚሰነዘሩት አወዛጋቢ ትርክቶች በቂ ጥናት እና ማስረጃ ቀርበዋል? የሚሉት ይገኙበታል። እንደኔ ምርጫ ቢሆን ጸሀፊው ይህንን ባያደርግ ጥሩ ነበር። ነገር ግን ይሄንን ማድረጉን ከመረጠ ትችቴን እንደሚከተለው አቀርባለሁ።
የጀዋር የፖለቲካ እሳቤን ከበየኑ ጉዳቾች ውስጥ ግለሰቡ በታሪክ ላይ ያለው ግንዛቤ አንዱ ነው። በዚህ መጽሀፍ ውስጥ ኦቦ ጀዋር ኢትዮጵያ የአጭር ዘመን እድሜ እንዳላት፣ በህዝቦች መካከል የነበረው ግንኙነትም የወረራ እና ጭቆና እንደሆነ፣ መፍትሄውም የብሄሮችን እራሳቸውን በራስ የማስተዳደር መብት በጽኑ አለት ላይ ማንበር እንደሆነ ያስቀምጣል። ስለተለያዩ ማህበረሰባዊ ግጭቶችም የራሱን ትንታኔ ያቀረበ ሲሆን በአመዛኙ የራሱ ትዝታ እና ከዚህ በፊት ያሰለቹ ትርክቶችን (historical narratives and mythology) መሰረት ያደረጉ ናቸው። እስቲ ጥቂት ማሳያዎችን አንስተን እንመልከት።
በክፍል 1 ገጽ 9-14 ላይ የቀረቡት የማህበረሰብ አሰፋፈር እና መስተጋብር፣ የታሪክ ክስተቶች እና የራሱ ቤተሰቦች የጭቆና ሰንሰለት ናቸው። የአማራ ማህበረሰብ ወደ አርሲ የሄደው ከአጼ ምንሊክ “ወረራ” በኋላ እንደሆነ እና ከሰላሌ ኦሮሞዎች ሰፈራ በፊት(የጸሀፊውን ን ቤተሰብ ጨምሮ) የአማራ እና ኦሮሞ ህዝብ ግንኙነት ልክ እንደ ዘይትና ውሃ እንደሆነ ያስቀምጣል (ገጽ 9-10 ይመልከቱ)። ይሄ በአንድ በኩል ምንም ማስረጃ ያልቀረበበት ሲሆን በሌላ መልኩ በረዥም የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ህዝብ በተለያየ መልኩ ማህበራዊ ግንኙነት ስለሚኖረው ዘይትና ውሃ ናቸው ብሎ መግለጽ ትልቅ ስህተት ይመስለኛል። አንድ ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰብ፣ ለዚያውም ወደ መሃል መንገድ እየተተጓዘ የሚመስል ፖለቲከኛ፣ እንዲህ ዐይነት ትርክት በመጽሀፍ መልክ አስቀምጦ ማለፍ ፖለቲካዊ አንድምታው ትልቅ ነው። ምናልባት የትርጉም ስህተት ከሆነ በሁለተኛው እትም ሊስተካከል ይችላል።
ከዚሁ የትርክት አረዳድ የሚቀዳው በገጽ 172 ላይ አማርኛ የስራ ቋንቋ ሲሆን አፋን ኦሮሞ በመንግስት ፖሊሲ ተከልክሏል የሚል ይገኛል። ይሄ ከፊል እውነት ከፊል የፖለቲካ ትርክት ነው። የማይካደው ነገር በመንግስት በኩል ለአፋን ኦሮሞ እና ሌሎችም አገር በቀል ቋንቋዎች የፖሊሲ ድጋፍ አልነበረም። ነገር ግን ቋንቋው እንዳያድግ በመንግስታዊ ፖሊሲ የተከለከለበት ዘመን አልነበረም( ለተጨማሪ ማስረጃ የአቶ ፋሲካ ሲደልል “የሻሞላው ትውልድ” መጽሀፍ ያንብቡ)።
የተሻለው አማራጭ ሁሉም ፖለቲከኛ የራሱን የታሪክ ትርክት በገባው ልክ እና በፈልገው መልኩ ከሚያቀርብ ወደፊት በገለልተኛ የታሪክ ምሁራን ቡድን እንዲጠና ማድረግ እና ውጤቱንም በሀቀኛ ብሄራዊ ምክክር በጋራ መገምገም ይሻላል። ካልሆነ ግን ታሪክ ሳይሆን የታሪክ ትርክት እያመረትን መዳከር ይሆናል። ማብቂያ የሌለው የትርክት ጦርነት!
- መንገዶች ሁሉ ወደ ብሄር ያመራሉ!
ኦቦ ጀዋር ይሄን መጽሀፍ ሲጀምር የሚከተለውን ጸሎት ያደረገ ይመስለኛል። እሱም፣ “ያ ረቢ፣ በብሄር መንፈስ እንዳስጀመርከን በብሄር ቃልኪዳን አስጨረሰን”! ኦቦ ጀዋር ከብሄር ውጪ ሌላ የፖለቲካ ፍላጎት እና መገለጫ የሌለ እስኪመስለ ድረስ ከጀምሩ እስከፍጻሜው ስለ ብሄር ጭቆና፣ ትግል እና ድል አውርቶ ያበቃል። ስለሀይማኖት ባወራባቸው መድረኮች እንኳን ከብሄራዊ ጭቆና ጋር ያገናኘዋል። አልፎ አልፎ ስለሌላ ሀይሎች ሲያወሳ የአንድነት ሀይል ሆነ የሌሌች ብሄሮችን ተቃውሞ እና ቅሬታ በዋናነት ከአማራ ጋር ጨፍልቆ ያቀርባል። ለምሳሌ በኦሮሚያ ክልል ከኦሮምኛ ውጪ በአማርኛ ትምህርት ቤት መማር የፈለጉትን የክልሉ ነዋሪዎች ጥያቄ በሙሉ ለአማራ ይሰጣል(ገጽ 51፣ አንቀጽ 3 ይመልከቱ)። ስለ አስተደድር ስርአት በሚገልጽበት ክፍል (ገጽ 145 ይመልከቱ) የደርግንም ጨቋኝ መንግስት ለአማራ ገዢ መደብ በገደምዳሜ (implied meaning) የሰጠ ይመስላል። ምክንያቱም ያለፈውን ቀጥተኛ የምስለኔ በዝባዥ አገዛዝ እና የህወሃትን የእጅ አዙር አስተዳደር እያወዳደረ ስለሆነ። ይሄ ለክርክር ክፍት ቢሆንም ልክ እንደ ሌሌች ብሄርተኞች ሁሉ ደርግንም የኛ አልነበረም የማለት አባዜ ይታያል። ኦቦ ጀዋር በዚህ ጉዳይ ላይ ያለውን አቋም ለወደፊቱ ግልጽ ቢያደርገው ብዥታዎች እንዲጠራ ይረዳል የሚል ግምት አለኝ።
ሌላ ቦታ ላይ ደግሞ የሚድያ ትችት እና ተቃውሞ ሲቅርብበት፣ በዋናነት በተለያየ ጊዜ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ከለውጥ በኋላ የተጨፈጨፉትን ንጹሀንን አስመልክቶ፣ የአንበሳ ድርሻውን ለአማራ አንቂዎች እና ሚድያዎች ይሰጣል(ግጽ 164)። ይሄ የሚመነጨው ሁለንም ጉዳይ ከተገዳዳሪ ብሄር እና ብሄር አንጻር ብቻ ስለሚያይ ሊሆን ይችላል።
ይሄንን የብሄር ጸሎት እና ቃልኪዳን የበለጠ የሚያስረዳልን ስለ ሀረሪ እና ደሬዳዋ ከተማ ግጭት እና የሱን የሰላም ማስፈን ጥረቶች የዳሰሰበት ክፍል ነው። የሀረሪ ክልል ጉዳይ የኦሮሞ እና አደሬ፣ ከፍ ሲልም የሀረሪ፣ ኦሮሞ፣ ሶማሌ እና አፋር ጉዳይ እንደሆነ ያስረዳል (ግጽ 274 ይመልክቱ)። ይሄ ሁለት መሰረታዊ ችግሮች አሉት፣ አንዱ የጽንሰሀሳብ ሲሆን ሌላው የሀቅ መዛነፍ። ሲጀመር ከተማው የሚገባው እና በከተማው ጉዳይ የሚያገባው በስም የተጠቀሱት ብሄሮች ብቻ ነው የሚል አንድምታ አለው። ይሄ አንዱን የአገር ባለቤት (owners of ethnic homeland) እና አገር አልባ ነዋሪዎች መኖራቸው ትክክል እንደሆነ ያበረታታል። ይሄ ደግሞ በምንም መመዘኛ ትክክል ሊሆን አይችልም፣ ጉዳዮ ሁሉም የከልሉ ነዋሪዎች በመሆኑ። ሲቀጥል የሀረሪ ክልል ነዋሪዎች በታሪክም ሆነ በቁጥር የሌላውም ህዝብ ሀገር ነው። የድሬዳዋው ጉዳይ በአደባባይ የሚታወቅ የዘመናዊ አፓርታይድ ስርአት ይብቃ የሚል የእኩልነት እና ፍትህ ጥያቄንም የሚጨምር እንጂ የኦሮሞ እና ሶማሌ ንትርክ ብቻ ሆኖ አያውቅም። እንደ ኮንዶሚንየም እጣ 80-20(80% ለኦሮሞ እና ሶማሌ ቀሪውን 20% ድርሻ ለአገር አልባዎቹ ኢትዮጵያውያን የሚያከፋፍል ቀመር) በ21ኛው ክፍለዘመን መኖሩ ሳያንስ ይሄንኑ የሚያጠንክር የፖለቲካ እሳቤ ለማንበር የሚደረግ እሳቤ የሸውራራው የብሄር መንጽር እይታ ውጤት ነው።
ኦቦ ጀዋር ስለዜግነት ያነሱት ከእስር ቤት መልስ የኢትዮጵያ ፓስፖርት አግኝተው ቃለመሀላ ባደረጉበት ወቅት ብቻ ነው። እሱንም ያወሱት ከዜግነት መብት እና እኩልነት ጋር በተያየዘ ሳይሆን ከአገር አልባነት ስሜት ጋር አያይዘው ነው(ገጽ 405 ላይ የፎሮ ምስል ይመልከቱ)። በርግጥ በዚህ ጉዳይ ኦቦ ጀዋር ለብቻቻው የሚወቀሱበት አንዳችም ምክንያት የለም። መንገዶች ሁሉ ወደ ብሄር እንዲያመሩ ተደርጎ የተቀረጸ የፖለቲካ ማህበር እና ትውልድ ውጤት ናቸው። እኔ እስከማስታውሰው ድረስ ገና በጨቅላ እድሜያችን(የሁለተኛ ክፍል ተማሪ ሆኜ) መምህራኖችቻችን በሰልፍ ላይ የሚከተለውን ቃልኪዳን መሳይ ያዘምሩን ነበር:-
መምህር: Ati Eenyu? (አንተ ማን ነህ?)
ተማሪዎች: Ani Oromoo dha(እኔ ኦሮሞ ነኝ)
መምህሩ: Biiyti tee hoo?(ሀገርህስ?)
ተማሪው: Oromiyaa!(ኦሮሚያ!)
የአቶ ጀዋርን ባላውቅም እኔ በ8 አመቴ ይሄ ሲደረግ አስታወሳለሁ። እንዲያውም አንድ ቀን ሰልፍ ላይ አገርህስ ስባል በደመነፍስ ኢትዮጵያ በማለቴ ግጥሙን አበላሽተሃል ተብዬ ኩርኩም ቀምሻለሁ። ኦህዴድ በአቅሟ ይሄንን ካደርገች የኦነግ ትርክት አሻራ ያረፈበት ትውልድ ስሜቱ ምን ይሆን? እዚህ ጋር ግልጽ መሆን ያለበት፣ ሰው ማንነቱን ኦሮሞ ወይም ሌላ ብሎ መግለጹ ትናንትም ሆነ ዛሬ ተገቢ ነው። እኔን ያስደነገጠኝ ሁለተኛው ስንኝ ነው፣ አገርህ አሮሚያ ተብሎ መሰበኩ!
ምናልባት እንዲህ ዐይነት ቅስቅሳ ከስንት ጊዜ በኋላ የሰማሁት በፋኖ ምልምል ወታደሮች ምረቃ ቪዲዮ ላይ ነው። እንዲህ ይላል፣ አሰልጣኙ እኮ አንተ ማነህ!? ብሎ ሲጠይቅ ምልምል ወታደሩም ድምጹን ከፍ አድርጎ እና ሶስቴ አጨብጭቦ “አማራ!” በማለት ይመልሳል። ይሄ ቢያንስ አላማውም የሚታወቅ የወታደራዊ ጥምቀት(indoctrination) በመሆኑ ለመረዳት አያዳግትም። ችግሩ ያለው ከወደፊት አገራዊ አንድነት አንጻር ሲታይ ሁሉም የራሱን አገር በኪሱ ይዞ እየዞረ የዜግነት መንፈስ እየደበዘዘ እና እየኮሰሰ መሄዱ ላይ ነው።
ወደ ያዝነው ጉዳይ ስንመለስ፣ በዚህ ሁኔታ ካደገ ህጻን ስለ ዜግነት ክብር እና ሀገር ፍቅር የተለየ ነገር አይጠበቅም።
የዜግነት መንፈስ(a sense of national identity) በሌለበት ስለ ዜግነት ክብር ለመዘመር የምንጥር አሳዛኝ ፍጡር ነን። የሀገር ፍቅር ስሜት የሚገነባውም ሆነ የሚፈርሰው መጀመሪያ በሰው ልጅ፣ በተለይ ታዳጊ ህጻናት፣ አዕምሮ ውስጥ ነው። በተቃርኖ የተሞላ የፖለቲካ ስርአት ባለቤቶች ከሚያደርጉን ነገሮች መካከል በጣም ልል የዜግነት እሳቤ (thin conception of citizenship) በህገመንግስት እና ፖለቲካዊ አሰራራችን ውስጥ ማቀፋችን ዋንኛው ነው።
የኦቦ ጀዋር የዜግነት እይታ አንድን እርከን፣ ለዚያውም መሰረቱን፣ ዘሎ ሌላኛው ላይ ማረፉ ነው። ይሄም ሲባል፣ የዜግነት ብያኔ የሚጀምረው ከህዝብ(peoplehood) ሲሆን አገረመንግስት (statehood) ቀጥሎ የሚመጣው ንብር(layer) ነው። ከዚህም የመነጨ ነው ጸሀፊው በተደጋጋጊ አገረመንግስቱ(the state) ላይ ብቻ የሚያተኩረው። ለኦቦ ጀዋር ኢትዮጵያ የብሄሮች ስብስብ ስትሆን፣ የራሷ የሆነ ውስጣዊ ማንነት(inherent identity) የላትም። የሚኖረው ልል የፓስፖርት ማንነትም ብሄራዊ (national identity) ሳይሆን ከብሄር ስብስቦች የሚቀዳ የፖለቲካ እና የህግ ስምምነት(derivative identity) ብቻ ይሆናል። ለዚህም ነው በኢትዮጵያ ምድር ብሄራዊ ጥቅም እና የብሄር ጥቅም ቦታ ተቀያይረው የተገኙት። ይሄ ስሁት አመልካከት፣ መዋቅር እና አሰራር ካልተስተካከለ በስተቀር ኢትዮጵያዊ ማንነት ከስቶ እና ገርጥጦ ከጥቂት ጊዜ በኋላ እንደ ታሪክ ልናወራው እንችላለን።
ኦቦ ጀዋርም ከብሄር ውጪ መደራጀት አማራጭ የሌለው አማራጭ ነበር በማለት በመጽሀፉ ገጽ 410 ላይ ይሞግታል። ሌላ የትግል አማራጭ እንዳይኖር ያደረገው ታሪካዊ በደል እና ጭቆና ብቻ ሳይሆን ገበያው የሚፈልገው እሱ ስለሆነ ነው። ከኦሮሞ ብሄር ማህበራዊ መሰረት ወጥቶ የዜግነት ፖለቲካን ማራመድ እንደ ነውር(taboo) የሚታይበት ዘመን ላይ በመገኘቱ ነው። ገበያ-ተኮር ከሆኑ ነግሮች ውስጥ ፖለቲካ አንዱ ነው። ይሄ የቤቱ አወቃቀር ችግር(flawed by design) ነው።
የፖለቲካ እይታው ከዚህ የሚቀዳ ከሆነ ኦቦ ጀዋር እንደመፍትሄ የሚያቀርቡት መንገድ ተገማች ይሆናል። ይሄም፣ የፖለቲካችን ብልሽት ማከሚያ ፍቱን የልሂቃን ድርድር ሆኖ ይቀርባል።
- የልሂቃን ድርድር እንደ አልፋ እና ኦሜጋ?
ኦቦ ጀዋር ከመታሰሩ በፊትም ሆነ ከዚያ በኋላ በነበረው ዘመን በወጥነት ካራመደው አቋም ውስጥ የልሂቃን ድርድር እንደ ፖለቲካዊ መፍትሄ አንዱ ነው። ለመሆኑ የልሂቃን ድርድር በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ምን ማለት ነው? የሚለው ወሳኝ ጉዳይ ነው። የልሂቃን ድርድር በጽንሰሀሳብ ደረጃ ሲታይ በተለያዩ የፖለቲካ ሀይሎች መካከል ምክክር እና የስልጣን መጋራት ድርድርን ይመለከታል። በተለይ ከግጭት መለስ ባሉ የተከፋፈሉ የፖለቲካ ማህበረሰብ ውስጥ ችግሩ ወደ ህዝብ ከመውረዱ በፊት ፖለቲካዊ ችግሮች በልሂቃን መካከል በሚደረግ የሰጥቶ መቀበል ባህል እንዲፈታ ማድረግን ያካትታል።
የልሂቃን ድርድር ሀገርን ለማስተዳድር እና ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት ሳይሆን የፖለቲካ ልዩነቶች ወደ ግጭት እንዳያመሩ እንዲሁም መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት ምቹ መደላድል ለመፍጠር ነው። በማክሮ ኢኮኖሚ ቋንቋ automatic stablizer ተብሎ የሚታወቀው ፖሊሲ የልሂቃን ድርድር ጊዚያዊ መፍትሄነትን የበለጠ ይገልጻል። ከፍተኛ ቀውስ ለማስወገድ ወይም ከቀውሱ በኋላ ለማገገም የሚረዳ አንዱ የመፍትሄ አማራጭ ነው።
ይሄ በኢትዮጵያ ሁኔታ የብሄር ተወካዮች ተሰብስበው የድርሻቸውን የሚያነሱበት(the politics of sharing the national cake) ነው። ችግሩ የዜጎች ስላልሆነ በመፍትሄውም ላይ ዜጋ አይመለከተውም። ምናልባት የብሄር አለቆች ከፈቀዱ ወይንም ዜጎች በርትተው ተደራጅተው ከወጡ እንደ አንድ ሀይል (block) ሊመጡ ይችሉ ይሆናል። ነገር ግን አላማው እና አሰራሩ ለዜጎች የታለመ አይደለም። የዜጎች ስብስብ ለመወከል ቢሞክር ምላሹ የሚሆነው “በእኛ ድግስ ላይ ምን ትሰራላችሁ?” ነው።
ይሄም ይሁን ቢባል እንኳን የልሂቃን ድርድርን እንደ ዘላቂ መፍትሄ(የሀገር ማስተዳደሪያ ፍልስፍና) አድርጎ ማቅረብ ከላይ ስለ ዜጎች ከተገለጸለው በተጨማሪ ሁለት መዘዝ አለው። የመጀመሪያው አገር በልሂቃን እገታ ስር ለዘላለም እንድትዳክር ያደርጋል። ኬኩን የቀመሱ የብሄር ልሂቃኖች ምንም እርምጃ ለመውሰድ እንሱን ማማከር ግዴታ እንድሆነ ይፈልጋሉ። ምንም ዐይነት ነገር፣ ሹመት እና ቅጣትን ጨምሮ፣ በብሄር መንጽር ብቻ እንዲታይ ያደርግና አገርን እጅ ከወች ያስራል። ሁለተኛው መዘዝ ደግሞ ልሂቃኖች ሳይስማሙ ቢቀር እና አንዱ ፓርቲ አብላጫ ድምጽ ካላገኘ አገር ያለ አስተዳዳሪ ትቀራለች። የዴሞክራሲ ባህል ባደገበት እና ጠንካራ ተቋማት ባሉበት አገር የመንግስት ክፍተት መቋቋም ይችሉ ይሆናል(ለምሳሌ ቤልጅየም ያለመንግስት ከአመት በላይ ቆይታለች)። እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገር ላይ ግን ሁኔታው በቀጥታ ወደ ግጭት ነው የሚያመራው፣ ለዚያውም የብሄር መልክ ይዞ።
በመሆኑም፣ የኦቦ ጀዋር የልሂቃን ድርድር ሀሳብ (ገጽ 418-419 ይመልከቱ) በጊዜያዊነት የሚወሰድ የኮሶ መድሀኒት ቢሆንም የዘላቂ መፍትሄ አካል ወይም አልፋ እና ኦሜጋ ሊሆን አይችለም። ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያ የሶስት አውራ ብሄሮች ሃላፊነቱ የተገደበ የግል ንብረት እንዳልሆነች አጽንኦት መስጠት ያስፈልጋል። በሁሉም፣ ለሁሉም የሆነች ኢትዮጵያን ለመገንባት በጋራ መስራት ግዜ የማይሰጠው የቤት ስራችን ነው።
- የሰውዬው ቀጣይ የፖለቲካ ጉዞ ምን ይሆን?
ለዚህ ጥያቄ አጭሩ መልስ ቀጣይ ፌርማታውን ማንም አያውቅም የሚል ይሆናል። ነገር ግን ፖለቲካ በመሰረቱ በትንበያ የተሞላ ስለሆነ፣ በኦቦ ጀዋር ያለፉት 10 አመታት የፖለቲካ አካሄድ እና ከቃሊቲ ግዞት ወዲህ የተመለከትናቸው ምልክቶች ላይ በመመስረት ጥቂት ግምቶችን ለማስቀመጥ እሞክራለሁ። በሌላ አነጋገር፣ የሰውዬው የቅርብ ጊዜ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ የሚያመላክተን የአስተሳሰብ ወይስ የስትራቴጂ ለውጥ?
ምንም ብዥታ የሌለው ከቃሊቲ ግዞት በፊት የነበረው እና ከዚያ ወዲያ የምናየው ጀዋር ይለያያሉ። የበፊቱ ጀዋር ችኩል፣ ውጤት ተኮር፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ባህልን በቅጡ ያላጤነ፣ የፖለቲካ ባላንጣዎቹን አብዝቶ የሚንቅ፣ እራሱን እንደ ተገዳዳሪ መንግስት የሚያይ እና የህዝብን ጊዜያዊ የድጋፍ እና ተቃውሞ ስሜት ከሚገባው በላይ ለጥጦ የሚረዳ ፖለቲከኛ ይመስላል። በተቃራኒው ሲታይ፣ ዳግመኛ ጀዋር የኢትዮጵያን ፖለቲካ የበለጠ የተረዳ(more pragmatist)፣ ባንክ፣ ታንክ እና የተጠረነፈ ህዝብ ያልያዘ በኢትዮጵያ ምድር ፖለቲካውን በቀላሉ መዘወር እንደማይችል የተረዳ፣ ከሌሎች ሀይሎች ጋር መስራት ግዴታ እንደሆነ የገባው፣ ፖለቲካ ገበያ እንደሚያስፈለገው ጠንቅቆ የገባው እና በፖለቲካ ረገድ የመጣንበት መንገድ አውዳሚ መሆኑን በተግባር ያያ ይመስላል።
ከላይ የተዘዘሩትን ማሳያዎች ኦቦ ጀዋር ከዚህ በፊት ካደረጋቸው ቃለምልልሶች፣ ከጽሞና ጊዜ ዝምታው፣ ከሰላም ሰባኪነት ዘመቻው እና የዲፕሎማሲ ስራ፣ ሰሞኑን ወደ ሜዳው በሙሉ ጉልበት ሲመለስ የማንነት ድንበር ዘለል ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ማተኮሩ እና ህገመንግስታዊ ስርዓቱ በሂደት መሻሻል እንደሚገባው፣ የማንነት ፖለቲካ እና ብሄራዊ አንድነትን ለማስታረቅ እሴታዊ አርበኝነት(progressive patriotism) የመሀል መንገድ እንደሆነ ካስረዳበት መጣጥፍ መረዳት ይቻላል።
የነኚህን ድምር ውጤት ብንመለከት የሚሰጠን ምስል ቢኖር ጀዋር በፖለቲካ አስተሳሰብ በጥቂቱ እና በስትራቴጂ ረገድ በእጅጉ መለወጡን ነው። አንዳንድ ሰዎች ጀዋር ኢትዮጵያኒስት ሆነ ሲሉ ይደመጣሉ። ይሄ ትልቅ ስህተት ነው። ይሄም በዋናነት የሚመነጨው ከስሁት የኢትዮጵያኒስት/ እንድነት ፖለቲካ አረዳድ ነው። “አገረ፟ መንግስቱን እናድን” ማለት ከብሄር ፖለቲካ መውጣት ጋር አንዳች ግንኙነት የለውም። ኢትዮጵያ የህልውና አደጋ ገጥሞታል ማለትም እንዲሁ በኢትዮጵያኒዝም ፖለቲካ መጠመቅን አያመላክትም። ኦቦ ጀዋር ሆነ ከፋኖ ታጋይ አገርን ከመፍረስ እናድን ሲሉ ከስትራቴጂ አንጻር ኢትዮጵያ ብትቆይልን (the state) ለምናራምደው ፖለቲካ ይጠቅመናል እያሉ እንጂ የብሄር ፖለቲካን እንጸየፍ ማለታቸው አይደለም። የኢትዮጵያዊነት ፖለቲካ ማለት በየትኛውም የብሄር ቅርጫት ውስጥ ሳይገቡ እና የኢትዮጵያ አንድነትን እንደ ርዕዮተ ዓለም ማራመድ ማለት ነው። አገረ መንግስት እና የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለምን ደባልቆ መመልከት ስሁት ብቻ ሳይሆን ዋጋም ያስከፍላል። አሁን ባለው ሁኔታ ኢትዮጵያዊ ጎራ ውስጥ ያሉ ጠንካራ ድርጅቶች የሌሉ ሲሆን (ገዢ ፓርቲን ጨምሮ) የኢትዮጵያዊነት ፖለቲካ በዋናነት ያለው በግለሰቦች አዕምሮ እና ልብ ውስጥ ነው። በመሆኑም ኦቦ ጀዋር ኢትዮጵያኒስት አይደለም፣ ብሎም አያውቅ!
በቀጣይ ኦቦ ጀዋርን የምናየው ከግራ ወደ መሃል እየተጠጋ የሚሄድ(የብሄር ፖለቲካ አስተሳሰብን ሳይለቅ) ይሆናል። ይሄም በተግባር ሲገለጽ የተለያዩ የብሄር ፓርቲዎች አንድ ግንባር ወይም የትብብር ማዕቀፍ የሚፈጥሩበት፣ ይሄንን ለማሳለጥ የምርጫ ስርዐት የሚከልስበት(proportional electoral system)፣ ሁሉም ቡድን በፈለገው መልኩ እንዲደራጅ ሁኔታዎች የሚሻሻሉበት፣ ህገመንግስቱ ቢሻሻል በዋናነት የፌደራል አወቃቀሩ የብሄር መልኩን ሳይለቅ፣ ፓርሊያመንተሪ ስርዐተ መንግስት የሚቆይበት እና የልሂቃን ድርድርን ተከትሎ የህዳጣን መብት የሚጠበቅበት እንዲሆን መስራት እና ስልጣን ላይ ያለውን መንግስት በጋራ መታገልን ያካትታል። ከዚህ ውጪ የኦቦ ጀዋርን እንቅስቃሴ ለጥጦ መረዳት ለደጋፊዎቹ ቶሎ መራገም፣ ለተቺዎቹ ቶሎ ማድነቅን ያስከትላል። ቀሪውን አብረን የምናይ ይሆናል።
እንደ መውጫ
በዚህ ምጥን ጽሁፍ የኦቦ ጀዋር የፖለቲካ መንገድን በወፍ በረር ለማስቃኘት ተሞክሯል። እንደዚያም ሆኖ ትኩረት የተደረገው በጥቂት ጉዳዮች ላይ ብቻ ነው። እኔ ከዚህ በላይ ባሉ ነጥቦች ላይ ስላተኮርኩ ሌሎቻችሁ ደግሞ የራስችሁን ዳሰሳ በቀሪው ጭብጦች ላይ እንድታደርጉ እጋብዛለሁ። የዚህ መጣጥፍ አላማም ውይይት እና ምሁራዊ ክርክሮችን ለመቆስቆስ በመሆኑ በርካታ ሶዎች በእነዚህና መሰል ጉዳዮች ዙሪያ ሙግት እንደሚገጥሙ ይጠበቃል። እኔ ከላይ የሰነዘርኳቸው እንዳንድ ትችቶች እና ምልከታዎች ተገቢ ናቸው ብዬ አምናለሁ። ስለሆነም፣ በዚህ ጽሁፍ ውስጥ የተለዩት ወሳኝ ነጥቦች ትኩረት እንዲሚያገኙ ምኞቴ ነው። በእኔ በኩል በሀሳብ ታጥቄ ፍጩቱን በጉጉት እጠባበቃለሁ።
የአልጸጸትም/Hin Gaabbu መጽሀፍ ደራሲ የሆነው ኦቦ ጀዋር መሀመድም ይሄንን የግል ህይወቱን፣ የትግል ጉዙውን እና የፖለቲካ እምነቱን የሚያትት መጽሀፍ ሰንዶ እነሆ በረከት በማለቱ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከሀሜት፣ ዛቻ እና አጉል ፍራቻ ወጥቶ ወደ ሀሳብ ሜዳ እንዲመለስ ለማድረግ የበኩሉን ጥረት በማድረጉ ሊመሰገን ይገባል። ይሄንን መጽሀፍ ማንም መጪው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ይገደኛል የሚል ለአቅመ ንባብ እና ፖለቲካ የደረሰ ሰው ሁሉ ቢያነብ ብዙ ያተርፋል። መልካም ንባብ!
ፖለቲካችንን ከአፈሙዝ አውጥተን ወደ አፈቀላጤ እንመልስ!
በቴሌግራም ይከተሉን https://t.me/+f_kxmaPjD-9jYTdk