የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የነዋሪውን የቤት ጥያቄ ለመመለስ የተለያዩ አማራጮችን ታሳቢ በማድረግ እየሰራ ይገኛል፡- ዘሪሁን አምደማሪያም (ኢ/ር)
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የነዋሪውን የቤት ጥያቄ ለመመለስ የተለያዩ አማራጮችን ታሳቢ በማድረግ እየሰራ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግስት እና የግል አጋርነት ጽ/ቤት ኃላፊ ዘሪሁን አምደማሪያም (ኢ/ር) ገለጹ፡፡
ኃላፊው ዘሪሁን አምደማሪያም (ኢ/ር) ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የነዋሪውን የቤት ጥያቄ ለመመለስ 4 የተለያዩ አማራጮችን አስቀምጦ እየሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡
እነዚህ የቤት ልማት አማራጮች በመንግስት በጀት ፤ በመንግስት እና በግሉ ዘርፍ አጋርነት፤ የ20/80 እና 40/60 እንዲሁም በግሉ ዘርፉ የሚገነቡ የቤት ግንባታ ፕሮግራሞች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በካዛንችስ የመልሶ ማልማት ፕሮግራም የሚለማው የመኖሪያ ቤት በመንግስት እና በግል አጋርነት የሚለማ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በመልሶ ማልማት ፕሮግራሙ መንግስት በራሱ በቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ለኦቪድ ኮንትራት ተሰጥተው የሚያሰራቸው 1 ሺ ቤቶች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
በተጨማሪም በግል አልሚዎች የሚሰሩ ቤቶች መኖራቸውን የጠቀሱት ኃላፊው በሚቀጥሉት 18 ወራት በካዛንችስ መልሶ ማልማት በጥቅሉ ወደ 20 ሺ ቤቶች እንደሚገነቡ ተናግረዋል፡፡
በካዛንችሱ መልሶ ማልማት ፕሮጀክት የመንግስት ድርሻ ማደጉን ገልጸው 65 በመቶ የግሉ ዘርፍ እንዲሁም 35 በመቶ የመንግሰት ድርሻ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በዚህም ለህብረተሰቡ የሚቀርበው የቤት ቁጥርም ከፍ ያለ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡
ሁሉም የቤት ፕሮግራሞች ታሳቢ የሚያደርጉት የቤት አቅርቦቱን ማስፋት ነው ያሉት ኃላፊው መንግስት ባለው ድርሻ የመግዛት እና የመከራየት አቅምን ከግምት በማስገባት መዝግቦ የያዛቸውን የቤት ፈላጊዎች ተደራሽ የሚያደርግበት ሁኔታ እንደሚፈጥር አብራርተዋል፡፡
በአጠቃላይ መንግስት በተለያዩ የቤት ልማት ፕሮግራሞቹ የቤት አማራጮችን ማስፋት ላይ እንደሚያተኩር ያብራሩት ኃላፊው አቅርቦቱ ከሰፋ በሁሉም አቅርቦቶች ቤት የማግኘት እድሎች እንደሚኖሩ አውስተዋል፡፡
በዚህም እየቆጠቡ ያሉ ነዋሪዎች የተለያዩ የቤት አማራጮች እንደሚከፈቱላቸው አስረድተዋል፡፡
መንግሰት ከራሱ ድርሻ ላይ በተለያየ ሁኔታ እየቆጠቡ ያሉ ነዋሪዎችን የፕሮግራሞቹ እና የአቅርቦቶቹ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሁኔታዎችን ያመቻቻል ብለዋል፡፡
በዚህም በኪራይ ለሚሳተፉ በኪራይ የመግዛት አቅም ላላቸው ደግሞ በግዢ ያቀርባልም ብለዋል፡፡
በመሆኑም የቤት አቅርቦት ፕሮግራሞቹ የቤት ተመዝጋቢዎችን ታሳቢ ያደረጉ ናቸው ብለዋል፡፡
በ፣ሆኑም ተመዝጋዎችም የአሁኑን ወቅታዊ ሁኔታ ታሳቢ ያደረገ እና ወቅቱን የሚመጥን ቁጠባ ማድረግ እዳለባቸውና ቁጠባቸውን አጠናክረው መቀጠል እንደሚኖርባቸው አስረድተዋል፡፡
AMN