ጀዋርም ለውጥ ብሎ የመከረው መለስን በለማና በገዱ በመተካት ለውጥ ያለ አስመስሎ በማጭበርበር፣ ተረኛ ነኝ ያለው ኦሮሞ-መሩ ገዢ ቡድን እንደ ወያኔ ረግጦ እንዲገዛን የተመኘ ይመስላል። ከእስታንፎርድ የፖለቲካ ምሩቅ አይጠበቅም።
ከአንድነት ሰመረ – ነጻ አስተአየት
እኔን የወዘወዘኝ ገና የትምህርት ቤት ወረቅት አለን ብለን በመመጻደቅ ባለፉት 50 ዓመታት የማናውቅበትን እየቆሰቆስን በማበላሸት ራሳችን ያደኸየናትና የዓለም መሳቂያ ያደረግናት አገራችን ውድቀት ሲሆን፣ ያንኑ ያመጣነውን ውድቀት ፈጥነን በሕብረት እንዴት እንደምናስወግድ በመወያየትና ለአፈጻጸምም በመዘጋጀት ፈንታ በጀዋር ታሪክ ላይ መከራከሩ ግንዛቤ ቢያዳብርም ለእኔ ግን በሚሊዮን የሚቆጠር የሚሞት ወገን እያለን ክርክሩ ነፍስ ማዳኛ ዕድል የሚያባከን ነው።
ጀዋር በዚህ ምዕራፍ የኢሓዴግ መንግሥት የግራ ፓርቲ አምባገነን አገዛዝ እንደነበረ፣ ሕወሀት ደርግን በጠመንጃ አስወግዶ ለ27 ዓመት ሕዝብ አፍኖ ቢገዛም ውሎ አድሮ በአመፅ ከሥልጣን መባረሩንና ቆምሁለት ያለውን የትግራይ ሕዝብም ለባሰ እልቂትና ውድመት እንደዳረገው ያትታል። ከሕወሀት ውድቀት ያልተማረው ተረኛ ነኝ ባዩ አድሮ-ጥጃው ኦሕዴድም እንዲያውም ከአንድ ፓርቲ አምባገነንነት ወደ አንድ ግለስብ አባገነንነት ተሸጋግሮ፣ የመለስ ዜናዊ ሕወሀት እንዳደረገው፣ ለኦሮሞም ሕዝብ ታይቶ የማይታወቅ መፈናቀል፣ ስደት፣ ውድወትና ሞት እንዳተረፈለት ነግሮናል። ሁሉም የኖርነው ነው።
ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ ሆነና! ግልበጣ መሪ ነበርሁ ያለው የፖለቲካው ምሑር ጀዋር ከፍ ሲል እንደ ምርጡ አፍሪቃዊ ኔልሰን ማንዴላ ኢትዮጵያንም ለሀቀኛ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግር በማገዝ ባለታሪክ መሆን ይችል የነበረው ዕድል አምልጦት፣ ዝቅ ሲል ደግሞ ለዘመናት እቆረቆርለታለሁ የሚለውን የዛሬውን የኦሮሞን ውድመት ማገድ ይችል የነበረው የጁሐር ወርቃማ ዕድልም ባክኖ ቀረ። ለምን እንዲህ ሆነ? ምንድን ነው የዛሬ ኢትዮጵያውያን ልሂቃን የጎደለን ?
በኢትዮጵያ ሌጣ ዲግሪ ከባላገርነት፣ ከአገር ፍቅርና ከማስተዋል ጋር ካልተጣመረ፣ በምንም ደረጃ ይሁን፣ ችግር መፍቻ መሆኑ ቀርቶ ለባለዲግሪው መነገጃ፣ ዝቅ ሲልም ችግር ፈጣሪ ሆኗል። ዲግሪ ብቻውን አዕምሮ ቢያበለጽግ ኖሮ፣ ድሀና ምስኪን ሕዝብ መካከል ግብቶ በመግደልና በማጋደል ፈንታ፣ በሊቃውንት መድረክ ለዓለም ቤዛ የሚሆን አዲስ ዕውቀት በማፍለቅ የሣይንስን የምጥቀት አድማስ አስፍቶ ለኢትዮጵያና ለጥቁር ዘርም የሚያኮራ ገንቢ ምርምር ጌታ በመሆንና የዓለምን ሊቃውንት ዕውቅና በማግኘት የተናቀውን ጥቁር ዘር ማስከበር በተቻለ ነበር። በኢትዮጵያ ተማርን ባይ ችግር ፈጣሪዎች ሁሉ እንኳን በዓለም በመንደርም ደረጃ የሚጠራ በጎ ስም እንኳ የሌላቸው በትምሕርትም ሆነ በምርምር ምስኪኖች ናቸው።
ሌሎች አገሮች ወደ ማርስ ሲጓዙ እኛ ግን መተራረዱን አቁመን ለመብላትና በመሬት ላይ ከጥበበኛ አገሮች በታች መሆናችን እየቆጨንም፣ ቢያንስ እንደ ሰው ለመኖር እንኳ ማሰብ፣ ማቀድ፣ መተባበር፣ መደራጀትና ሙያተኞችን ማሠልጠንም አቅቶን፣ ዛሬም ከ 70 ዓመት የዩኒቬርሲቲ ስምሪት በኋላ፣ ዘመናዊ የኢኮኖሚ አመራር፣ ባቡር ዝርጋታ፣ መብራት ኃይል ግንባታ ፣ የኃይል ግድብ ሥራ፣ ማዕድን ማውጣትና ሌላም የቴክኖሎጂ ልማት ባለቤት መሆን ስንችል የፈረንጅ ሙያ ጥገኛ ሆነን ተኝተን፣ የዕድገት ቅደም ተከተል ማውጣት ፍጹም አቅቶን ከፈረንጅ ምፅዋት መላቀቅ ተስኖን የወሬውን ፖለቲካ በማተራመስ በግልና በቡድን እየነገድንበት በድህነት ተዋርደን መኖር የመረጥን ይመስላል። ለዚህም ነው አምባገነን ሥርዓት የሰፈነብን።
ለመሆኑ ጀዋር፣ የዝነኛው እስታንፎርዱ ዩኒቬርሲቲው የፖለቲካ ምሩቅ፣ የ2010 ዓ.ም. የመንግሥት ግልበጣ መሪ ተዋናይ ነበርሁ ካለ፣ የወያኔ-ኦነግ ክልላና ሕገ መንግሥቱ እንዲለወጡ ወይም እንዲሻሻሉ ጀዋር ያልመከረው ዲሞክራሲና የፌደራል ሥርዓት ከኢዲሞክራሲያዊና ክኢፌደራል ሥርዓት በታምር ይፈልቃሉ ብሎ ነው፣ ወይስ የአገር መሪነቱ በኦሮሞ እጅ ሲገባ በጭፍኑ፣ እንደ ብዙ ተማርን ባይ ጉዶች፣ የኦሮሞ አምባገነንነትን ለመደገፍ ነው፣ ወይስ እንደ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም፣ መለስ ዜናዊና ሌንጮ ለታ ለሆዱና ለማይዘልቅ ሥልጣን በማድላት የአገርና የወገን ፍቅር ስለሌለው ነው?
የኢሕአዴግ መንግሥት አምባገነን መሆኑን ጀዋር አስረግጦ ከነገረን፣ ክለላውና ሕገ መንግሥቱም የመጨቆኛ መሣሪያ መሆናቸው ግልጽ ሆኖ እያለ፣ በዚያው ጨቋኝ ሥርዓት ውስጥ ጥርሱን የነቀለ ሹም ለውጥ ብቻ ጀዋርን ያረካው ከሕወሐት የተሻለ አገዛዝ በኦህዴድ ዘመን ይመጣል ብሎ በማመን ነው? የኢትዮጵያ የጭቆና አገዛዝ ዋናው ምንጩ ሕገ መንግሥታዊው ሥርዓቱና ክለላው መሆኑን እየታወቀ፣ ለውጥ ናፋቂው ጀዋር የአምባገነኑ ሥርዓት መሪዎች የነበሩ አባላት የአመራር ለውጥ ብቻ በመርካት፣ ራሱም ባወገዘው አምባገነን አገዛዝ እየተረገጥን እንድንቀጥል መርጦልን ነው ?
የአምባገነንነት መደላድሉ ሕገ መንግሥትና የክለላው ሥርዓት
ለማንም አስተዋይ ኢትዮጵያዊ፣ ከ1983 ዓ.ም. ጀምሮ የአገዛዙ መሠረት የሕወሀት-ኦንግ ክለላና ሕገ መንግሥት ሆን ተብለው በሕወሀትና ኦነግ ጠባብና ራስ-ወዳድ አመራሮች የተቀየሱና ሕዝባችንን፣ ቆምንለት እያሉ ለዘመናት የነገዱበትን የትግሬና የኦርሞ ድሀ ወገናችንን ጭምር፣ ረግጦ ለመግዛትና አገር ዘርፎ ሀብት ለማካበት የታቀደ መሆኑ በኢሕአዴግ አገዛዝ ሕይወታችን በግልጽ ታይቷል። የተቀየሰልን የአገዛዝ ሥርዓት አምባገነንነት እንደሚያሰፍን ተማርሁ ያለ ሁሉ ይረዳዋል።
1ኛ/ ምርጫውን በማምታታት፣ ገዢው ፓርቲ ከ95 በመቶ በላይ የፓርላማ አባላት ወምበር ይዟል። ክልሎችንም ተቆጣጥሯል።
2ኛ/ መከላከያ፣ ፖሊስ፣ ሚሊሺና ደህንነት በገዢው ፓርቲ ቁጥጥር ሥር ውለዋል።
3ኛ/ ሕገ መንግሥቱ ኢዲሞክራሲያዊና ኢፊደራላዊ ሆኖ ተቀርጿል፦
1.1 ፓርላማው የፌደራል መንግሥቱ የበላይ አካል ነው ተብሎ ቢደነግም፣ የፓርላማ አባላት የገዢው ፓርቲ አባላት በመሆናቸው የሚታዘዙት በገዢው ፓርቲ መሪ በመሆኑ፣ ሕግ አስፈጻሚው ዘርፍ ዋናው የመንግሥት ኃያል ዘርፍ ሆኗል።
1.2 የፌደራል ሥርዓት አለ ተብሎ በአንቀጽ 52 የሥልጣን ክፍፍል ቢደነገግም፣ ሁሉም ክልሎች በገዢው ፓርቲ ስለሚተደዳደሩ፣ የገዢው ፓርቲ ፕሬዚደንትና ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የክልል ርዕሰ መስተዳድሮችንም ይሾማል፣ ይሽራል። በርዕሰ መስተዳድርም በኩል፣ ሌሎችን የክልል ባለሥልጣናት ሹመት ያጸድቃል፣ ይቆጣጠራል፣ ይበውዛል።
1.3 የፌደሬሽን ምክር ቤት ባመዛኙ የክልል ባለሥልጣናት ስብስብ በመሆኑ፣ በአንቀጽ 52 መሠረት የፌደራል ሥርዓት አለን ከተባለ፣ በማዕከላዊ መግሥት የሥልጣን ክልል ውስጥ ምክር ቤቱ ሊገባ አይገባም። ነገር ግን፣ ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምልምሎች ስብስብ ሕግ አስፈጻሚውን ዘርፍ፣ ሕግ አውጪውን ዘርፍና ሕግ ተርጓሚውን ዘርፍም የማዘዝ፣ የመምራትና የመቆጣጠር ሥልጣን በሕገ መንግሥቱ ስለተሰጠው፣ በክልልና በማዕከላዊ መንግሥት መካከል አለ የተባለው የሥልጣን ክፍፍል ይጠፋና የፌደራል ሥርዓት ራሳችንን በራሳችን ለማተለል የፈጠርነው ውሸት ሆኖ ይታያል። (አንቀጽ 62(1)፣ 62(8)፣ 62(9)፣ 84 ይታይ።) በዚህም በፌደሬሽን ምክር ቤት ሥልጣን መሣሪያነት፣ አንቀጾች 9(2)፣50(3)፣ 50(8)፣ 72(1)፣ 78(2)፣ 80(1) ይጣሳሉ። ብዙ የአገር ቤትም ሆነ የዳያስፖራ ሊቃውንትም፣ ሊቃውንት ከተባሉ፣ የኢትዮጵያ የዘር ፌደራል ሥርዓት አለ እያሉ የሌለውን የአገዛዝ ሥርዓት ሲገልጹት የፈጠርነው የፖለቲካ ድንቁርናና ሸፍጥ ያሳምማል።
1.4 ሕገ መንግሥቱን የሚጥሱ ባለሥልጣናት የሚቀጡበትና ሲያስፈልግም ከሥልጣንና ከፖለቲካ የሚባረሩበት ሕግ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ስለሌለ፣ ሹማምንት ሲፈልጉ ሕገ መንግሥቱን ያከብራሉ፣ ሳይፈልጉ ይጥሳሉ።
1.5 ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ብቸኛው ባለሥልጣን ናቸው። ለምሣሌ፣ ከኤርትራ ጋር የተደረገው የእርቅ ሰንድ፣ ክሶማሊላንድ ጋር የተደረገው የወደብ ኪራይ ስምምነት ረቂቅ ሰነድ፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ በኩል ከውጭ የተገኘ የገንዘብ ስምምነት ሰነድ የመንግሥት የበላይ አካል ለተባለው ለፓርላማም እንኳ አልቀረቡም።
1.6 የሚኒስትሮች ም/ቤት አባላት አጠቃላይ አቅም ስለሌላቸው በሌላ ሥራ ከሚያገኙት የተሻለ መጠነኛ የጥቅም ፍርፋሪም ስለሚደርሳቸው፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ካልፈለጓቸው በማንኛውም ሰዓት ሊያባርሯቸው ስለሚችሉ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምንም ዓይነት ጥፋት ቢሠሩ የመተቸት ችሎታ የላቸውም። በመሪያቸው ሕልም ስለሚመሩም ባይኖሩም አያጎድሉም።
1.7 በአንቀጽ 47(1) መሠረት አዲስ አበባና ድሬዳዋ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፓብሊክ አባላት አይደሉም። ምናልባት የሪፐብሊኩ አባላት ባለመሆናቸውና በወቅቱ በኦሮሞ የብልፅግና ፓርቲ መሪና ጠቅላይ ሚኒስትር መልካም ፈቃድ ስለሚተዳደሩም፣ ይኸ ክልል የሚባል ኋላ-ቀር ልክፍት ከተጠናወተው የኦሮሞ ካድሬ ሁለቱም ከተሞች በኦሮሞ ክልል ይጠቃለሉ የሚል ቅዠት ይሰማል።
1.8 በአንቀጽ 47(1) የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አባላት የተባሉት ቢበዛ የ 9 ጎሣ ክልሎች፣ እያንዳንዳቸው በመረጡት አንድ ቋንቋና ባህል መሠረት ስለሚተዳደሩ፣ በውስጣቸው እስከ 75 ሥልጣን-የለሽ ጥገኛ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቢኖሩም፣ ሁሉም ሳይወዱ በግድ በክልሉ የቋንቋ ምርጫና ባህል በበታችነት በመገዛታችው፣ በአንቀጽ 8(1) “የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶች ናቸው።” የተባለው ድንጋጌ ለአብዛኛዎቹ ብሔር ብሔረሰቦች አልሠራም። በዚያ ላይ፣ በአንቀጽ 47 ሥር የሌሉ ክልል-የለሽ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሁሉ የሪፐብሊኩም አባል አይደሉም። ይኸ ክልል የሚባል ሰይጣን ለዛሬው ትርምስ አንዱ መንስዔ ነው።
ስለሆነም፣ በሕገ መንግሥቱ መሠረት፣ ኢትዮጵያ ቢበዛ የ 9 ጎሣዎች አገር ነች ማለት ይቻላል። ሕዝብ በፈለገበት ክፍለ ሀገር ሠርቶ በሰላም የኖረበትን የንጉሠ ነገሥቱን ጨቋኝ የተባለ ሥርዓት በጨቋኝነቱ የሚያስንቀው ይህ በእውነትም ጨቋኝና በዝባዥ ሥርዓት በመተካቱ የሚኩራሩና የሚፎክሩ፣ ተማርን የሚሉና የተቃዋሚ ፓርቲ መሪም ነን የሚሉና በባዶ ሜዳ የሚንጠራሩ፣ እንዲሁም በዳያስፖራም ያሉ የሚሸልሉ ብዙ ቆቅ ራሶች አሉ። የሞተው አምሳያቸው ዋለልኝ መኮንን ኢትዮጵያ የብሔር ብሔረ ሰቦች እሥር ቤት ናት ያለው እውነትነቱ በንጉሣዊ ሥርዓት ሳይሆን በዛሬው ግራ-ዘመም ጨቋኝ የጎሣ ሥርዓት ነው። ስለ ጭቆና ያደነቁሩን የነበሩት ወያኔና ኦነግ በየተራ የኢትዮጵያ ገዢ ሆነው እንዳየናቸው፣ ባገዛዝ ዘመናቸው እንኳን ለሌሎቻችን ለራሳቸውም ብሔር ያተረፉለት ውድቀት፣ ውርደትና ሞት ነው።
1.9 እንደ ቤኒሻንጉል ክልል ሕገ መንግሥት አንቀጽ 2 ዓይነት ድንጋጌ ያላቸው ክልሎች ደግሞ በውስጣቸው ለዘመናት የኖሩት፣ የክልል ባለቤት ናቸው ከተባሉት ጥቂት አናሳ ዘሮች እጅግ የሚበልጥ ቁጥር ቢኖራቸውም፣ በመግሥት ሙሉ ፈቃድ፣ የክልል ባለቤት አይደሉም ተብለው፣ ባገራቸው የፖለትካ ተሳትፎም ተከልክለው፣ በከፍተኛ ደረጃ ይፈናቀላሉ፣ ይገደላሉ። ይህም የሚደረገው ማንነታቸው እየተለየ ሲሆን፣ ተጨቋኝ ዜጎች
ለመብታቸው መከበር መታገል ተገድደዋል። አንቀጽ 2 ያለምንም እርምት ዛሬም አለ። ለዚህ ሁሉ ትርምስ መነሻው ሕዝብ ሳያማክሩ ኦንግ-ወያኔ የፈጠሩት ክለላ ነው።
1.10 አገር ለማስተባበሩ አንቀጽ 39 አይበጅም። ወላይታ፣ ጉራጌ፣ የጎንደሩ ስሜንና የሰሜን ወሎው ራያ ይህን አንቀጽና አንቀጽ 48 ን በመተማመን ያቀረቧቸው የወሰንና የክልል ጥያቄዎች ሁሉ ታፍነው ለዛሬው የአማራ ጦርነትም አንዱ ምክንያት ሆኗል። ለክልልና ለወሰን ጥያቄዎች መልስ እንዳይገኝ አገዛዙ ሲጀመር አውቀው ችግሩን የፈጠሩት ሕወሀትና ኦነግ፣ ዛሬም ተወካዮቻቸው በፌደሬሽን ም/ቤት ወሳኝ ድምጽ ያላቸው አባላት ስለሆኑ፣ እነዚህ ሁለቱ ጠባብ ቡድኖች በፈጠሩት ችግር ላይ ራሳቸውም ዳኛ ሆነው በመሰየማቸው፣ አንቀጽ 48 ምን ጊዜም ተፈጻሚ አልሆነም። የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈና አንዱ ውጤት የዛሬው የእርስ በእርስ ትርምስና እልቂት ነው።
1.11 በአንቀጽ 46(2) ክልል የሚዋቀረው በሕዝብ ፈቃድ መሆኑ ቢደነገግም፣ ያሉት 9 ክልሎች የተከለሉት በሕወሀትና ኦንግ መሪዎች ፈቃድ ብቻ እንጂ ራያና ስሜን ከትግሬ ጋር እንከለል፣ መተከል ከጎጃም ይገንጠል ብሎ የወሎ፣ የቤገምድርና ስሜን እንዲሁም የጎጃም ሕዝብ የፈቀደበት ሰነድ የለም። ዛሬም ከትግራይ ጋር የተከለልነው ያለፈቃዳችን ነው ብለው ደጋግመው ለዘመናት ስሜንና ራያ ሲያመለክቱ፣ ሕወሀቶች ከኦነግ ካድሬዎች ጋር ሲጀመር ጀምሮ ባበላሹት ክለላ ላይ ራሳቸው ዳኛ ሆነው በመሰየማቸው ፍትሐዊ ፍርድ ከፌደሬሽን ም/ቤት ማግኘት አልተቻለም። አባቱ ዳኛ ልጁ ቀማኛ ይሉታል ይኸ ነው ! ለወላይታና ጉራጌም የክልል ጥያቄ የተሰጣቸው መልስ ዱላና እሥራት ነው።
ይኸ ፀረ ሕዝብ የውሸት ሪፐብሊክ ሕገ መግሥትና ክለላው የአምባገነን ሥርዓት ዋናው መሠረት መሆኑ ገና በጧቱ አያሌ ወገኖቻችንን አግልሎ ብቻውን ሲያውጀው ግልጽ ነበር። በሕገ መንግሥቱ መሠረት፣ ሕግ አውጪውን ዘርፍ፣ ሕግ ተርጓሚውን ዘርፍ፣ ሕግ አስፈጻሚውን ዘርፍ፣ የታጠቀውን ኃይልና ክልሎችንም የሚቆጣጠር ገዢ ፓርቲ ያለምንም ሕጋዊ ገደብ መረን ተለቅቆ አምባገነን መሆኑ ግልጽ ከሆነ፣ አምባገነንነቱን ኦሕዴድም እንደሚወርስ ጀዋር እንዴት አጣው ?
የግልበጣ መሪው ጀዋር በ 2010 ዓ.ም. የተመኘው የሥርዓት ለውጥ
በእንስሳት ማጎሪያ ዓይነት ክለላና በጨቋኝ ሕገ መንግሥት ላይ የተመሠረተ መንግሥታዊ ሥርዓት አገር ማተራመሱን ተገንዝቦ መንግሥት ግልበጣ ለቀየሰው ጀዋር የአገዛዝ ሥርዓቱ አስከፊነት ግልጽ ሆኖ ሳለ፣ ይህን የጸረ ሕዝብ ሥርዓት መሠረት ጀዋር ደግፎ በለማ መሪነትና በገዱ አጃቢነት አመራር ለውጥ እንዲደረግ መምከሩ የጀዋርን የፖለቲካ ብቃት፣ ታማኒነትና ዲሞክራሲያዊነት አጠያያቂ ያደርገዋል። የኢሕአፓው የ1966 ዓ.ም. “ጉልቻ ቢቀያየር ወጥ አይጣፍጥም።” ከዚያ ዘመን ይልቅ ጀዋር ላለመው የአገዛዝ ሥርዓት ይመጥናል። የኢሕአዴግን መንግሥታዊ ሥርዓት አምባገነንነት በገልጽ ለ 27 ዓመት ከኖርንበት በኋላ፣ ሹሞ በመቀየር ሊስተካከል እንደማይችል አለመረዳት የጀዋርን የሕገ መንግሥት ዕውቀትና የዲሞክራሲያዊ ፖለቲካ ግንዛቤ ደረጃ እንዲሁም ለአገርና ለሕዝብ ዘላቂ ደህንነት ያለውን አቋም ይጠቁማል።
ሕገ መንግሥቱን መሠረት አድርጎ፣ መከላከያን፣ ፖሊስንና ደህንነትን በገዢው ፕርቲ ጎሣ ቡድን የበላይነት የሚቆጣጠር የገዢ ፕርቲ መሪ፣ የሕዝብ ስምምነት ያላገኙ ክልሎችን በጦር መሣሪያ የሚቆጣጠር መሪ፣ ፍርድ ቤት በነፃ የለቀቀውን ዜጋ ከፍርድ ቤት በር ላይ እንደገና ወደ እሥር ቤት አፍሶ የሚወረውር ሥርዓት መሪ፣ የፌደራል መንግሥትን ሶስት ዘርፎች በቀጥታና በፌደሬሽን ም/ቤትም በኩል የሚቆጣጠር መሪ፣ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ወቃሽ ከሳሽ ስለሌለ እንደማይጠየቅና ከሥልጣንና ከፖለቲካም እንደማይሰናበት ተገንዝቦ ማንንም የማይፈራ መሪ፣ አምባገነን ለመሆን ሁኔታዎች ሁሉ በሥርዓቱ የተመቻቹለት መሆኑን ጀዋር አልተረዳሁም ብሎ የግለሰቦች ለውጥ ብቻ ይበቃል ማለቱን ለማመን አይቻልም።
የመለስ-ሌንጮ አምባገነን ሥርዓተ መንግሥት ለብልፅግናም ሙሉ ለሙሉ እንደሚተርፍ፣ እንኳን የእስታንፎርድ የፖለቲካ ምሩቅና አስተዋይ መሀይምም መገመት ይችላል። መለስ ዜናዊና ሌንጮ ለታ የፈለጉት አገርና ሕዝብ ለማስተዳደርና ለማበልጸግ ሳይሆን፣ ቆምንለት ያሉትንም የራሳቸውን መንደር ሕዝብም ግጠውና ረግጠው ለመግዛትና ለመዝረፍ ስለነበረ ይኸው ባለፉት 33 ዓመታት ተሳክቶላቸው አገር እያተራመሱ ኢትዮጵያንም ለውርደት፣ ውድመትና ግንጠላ ዳርገው የግል ጥቅምና ሥልጣን ብቻ ሲያሳድዱ ባደኸዩአት አገራችን ዛሬም እየተነገደ ነው። የመንግሥት ፍንቀላ መሪ ነበርሁ የሚለው ጀዋር አከላለሉንና ሕገ መንግሥቱን የሚደግፈው ይህን ሁሉ ጉድ እያወቀ የኢትዮጵያን የፍዳ አገዛዝ ለማራዘም ነው።
መለስ ዜናዊ ብቸኛው ኃያልና ፈላጭ ቆራጭ የሆነው ሕገ መንግሥቱ ስለፈቀደለትና ሊለውጠውም ሲችል ለአምባገነን አገዝዝ በመመቸቱ ረግጦ ሊገዛበት ስለፈለገና ስለገዛበት ሲሆን፣ ተማርን የሚሉት ጠባቦችና ግብረ-በሎች፣ ተንበርካኪዎችና እንደ ብአዴን፣ ደህዴንና ኦሕዴድ ያሉ የገዢው ፓርቲ አጨብጫቢዎች የገዢው ፓርቲ ምስኪን ጥገኞች ስለሆኑ ሆዳቸው ይሙላ እንጂ የአገር ውድቀትና ውርደት ስለማይታያቸው፣ መለስ ዜናዊም ከሰማይ በታች የሚፈራው አንድም አካል ስላልነበረ፣ የፈለገውን ሲሾም፣ ያልፈለገውን ሲሽር፣ ሲያባርርና ሲያስር ኖሮ ድህነት፣ ትርምስና ዕልቂት አውርሶን ሄደ።
ጀዋርም ለውጥ ብሎ የመከረው መለስን በለማና በገዱ በመተካት ለውጥ ያለ አስመስሎ በማጭበርበር፣ ተረኛ ነኝ ያለው ኦሮሞ-መሩ ገዢ ቡድን እንደ ወያኔ ረግጦ እንዲገዛን የተመኘ ይመስላል። ከእስታንፎርድ የፖለቲካ ምሩቅ አይጠበቅም።
ብሔርተኛው ጀዋር አማራን በብሔርተኛነትና በአሐዳዊነት ናፋቂነት መፈረጅ
ከልቡ ከሆነ፣ ጀዋር የግልና የቡድን ጥቅም ማሳደዱ ለማንም እንደማይበጅ ያመለከተው የሚወደስ ነው። አማራን በተመለከተ ግን የሰጠው የአማራ አሐዳዊ ሥርዓት ናፋቂነትና ዛሬ ለትርምስ፣ ለጦርነትና ለሞት ያበቃንን የብሔር ብሔረሰብ ሥርዓትም አማራ ደገፈ ማለቱ፣ ምናልባት አሻግሮ ሳያይ ዘሎ ገደል የገባውን የዋለልኝ መኮንንን ግልብ
አስተያየትና የመሰሎቹን ጅል አመለካከት ለትልቁ የአማራ ሕዝብ በማጋባት፣ ወቀሳው የተለመደው ጭፍን ፀረ-አማራ ቅጥፈትና ከሕገ አራዊት ወጥተን እንደ ሰው እንድንኖር ያደረጉትን የአድዋ ድል አባትና የዘመናዊት ኢትዮጵያ ፈር ቀዳጅ አባ ዳኘውን በመካድ የሚነዛው ፀረ-ምኒልክ ቅጥፈት ቅጣይ ነው። የአባየን ለእማየ ሆነ እኮ !
ለዓመታት ድረሱልን ብሎ ጮሆ መልስ በማጣት ሕልውናውን ማስከበር መሞከሩ አማራም ብሔርተኛነት ደጋፊ ነው ማለት ሌላ ቅጥፈት ነው። አማራ ለተሻለች ኢትዮጵያ ለውጥ አስፈላጊ መሆኑን በማመን ባለፉት አያሌ ዘመናት ደሙን እያፈሰሰና አጥንቱን እየከሰከሰላት የለውጥ መሪ እንጂ ዳር ቆሞ ለጨቋኝና ለወራሪ አጨብጫቢ ሆኖ አያውቅም። ከቆየ ሰፊ ታሪካችን መጥቀሱ ይቆይና፣ በ1953 ዓ.ም. እና በ1966 ዓ.ም. ንቅናቄዎች፣ በ2010 ዓ.ም. ጭምር ማን ነበር መሪው ?
ምናልባት “ Constitutional Monarchy “ ይኑረን የሚል አስተያየት ከአንዳንድ አማሮች ቢሰነዘርም፣ ንጉሣዊው ቤተሰብ እኮ የመጣው ቢያንስ ከሀዲያ፣ ክሸዋ ኦሮሞ፣ ከትግሬ፣ ከጉራጌና ከአማራም ጭምር ስለሆነ፣ ብዙ ጠባቦች እንደሚሉት፣ የአማራ ንጉሣዊ ሥርዓት ሊባል አይችልም። የግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሤ አያት ደጃዝማች ወልደ ሚካኤል ጉዲሣ፣ ከዚያም በፊት ከሀዲያ ባላባት ተወልደው አፄ ዘርዐ ያዕቆብን አግብተው ኢትዮጵያን ለ40 ዓመት የገዙትንና ልጆቻቸውን የልጅ ልጆቻቸውን ኢትዮጵያን ያስገዙትን ንግሥት መጥቀሱ ንጉሣዊው ሥርዓት የአማራ ብቻ አለመሆኑን ያሳያል።
በንጉሣዊ ሥርዓት አማራ ብቻውን ኢትዮጵያን አስተዳድሮ እንደማያውቅ፣ የቅርቡ ታላላቅ የአገር አለኝታዎች እነ ፊታውራሪ ሀብተ ጊዎርጊስን፣ ራስ ጎበናንና ደጃች ባልቻን፣ በቅርብ ካየናቸውም መካከል ጀኔራል ሙሉጌታ ቡሊን፣ ልጅ ይልማ ደረሣንና ጀኔራል ጃገማ ኬሎን የመሳሰሉትን ጅግና አባቶች መጥቀስ ይቻላል። በዚህ ላይ፣ ንጉሣዊው ሥርዓትም ከአሐዳዊነት ይልቅ ከዛሬው አገዛዝ የተሻለ ለፌደራል ሥርዓት የሚቀርብ ነበር። ለምሣሌ፣ አባ ጅፋር፣ እንደሌሎቹ አውራጃ ገዢዎች፣ ለንጉሠ ነግሥቱ ግብር ይክፈሉ እንጂ፣ የባሪያ ንግድ ከማካሄድ በንጉሠ ነገሥቱ ከመከልከላቸውና አገር አስተዳደሩ ላይ የፍትሕ ማስፈን ግዴታ ከመኖሩ ውጭ በውስጥ የግዛት አስተዳደራቸው ማንም አይገባም ነበር።
በ1983 ዓ.ም. ሕወሀትና ኦነግ በመለስና ሌንጮ መሪነት ኢትዮጵያን እንደፈለጉት ከልለው ሲከፋፈሉና ፌደራልነትም ሆነ ዲሞክራሲያዊነት የሌለበት ሕገ መንግሥት ሲያውጁ፣ አማራ ከሴራው መገለሉን ጀዋር አያውቅም ማለት አይቻልም። የጎሣ ከፋፋይ ክለላና የአገዛዝ ሕገ መንግሥት ማወጁ ላይ አማራ ተሳትፎ፣ የቤገምድርና ስሜኑን ስሜንና የወሎውን ራያን ለትግሬ የሚሰጥ፣ ደሙን አፍስሶ አጥንቱን ከስክሶ ያመጣትን ኤርትራን የሚያስገነጥልና፣ 74 የኢትዮጵያ ወንድም ጎሣዎች ቢበዛ በዘጠኝ ጎሣዎች እየተረገጡ ተገዢ እንዲሆኑ የሚስማማ፣ እያንዳንዱ ክልል በአንድ ጎሣ ፈላጭ ቆራጭነት እንዲገዛና ሌላውን ጎሣ ከክልሉ የማባረር ሥልጣንም እንዲኖረው የሚደነግግ ጨቋኝ ክለላና ሕገ መንግሥት የሚደግፍ አማራ አልነበረም። ከመለስ-ሌንጮ የአገዛዝ መሥራች ጉባዔም የተገለለው የጭቆና ሥርዓቱን እንደማይደግፍ እነ መለስ በማወቃቸው ነው። በዚህ ላይ፣ የፌደሬሽን ም/ቤት የክልል ባለሥልጣናት ስብስብ ሆኖ ሳለ ማዕከላዊ መንግሥትን የመቆጣጠር፣ የመምራትና የማዘዝ ሥልጣን በሕገ መንግሥቱ ተሰጥቶት የፌደራል ሥርዓት የሥልጣን ክፍፍል መርህ እንዲናድና ለመለስና ሌንጮ ጭቋኝ ሥርዓት በመንበርከክ ለጭፍን አሐዳዊ ጎሣ-መር አገዛዝ አጨብጫቢም አልሆነም።
ከ 420 ገጽ በላይ ባለው መጽሐፉ፣ ጀዋር ለዛሬው አምባገነንነት፣ ጦርነት፣ እልቂት፣ ሞት፣ መፈናቀልና ስደት ባበቃን የመለስ-ሌንጮ አከላለልና ሕገ መንፍግሥቱ ላይ አንድም ትችት በቀጥታ አልሰነዘረም። የዛሬው የክልል ወሰን ግብግብ፣ የአንድ ጎሣ ቡድን አስከፊ አገዛዝ፣ ከጎረቤት አገራት ጋር ያለው መናከስ፣ የኤርትራ መገንጠልና ወደብ የለሽ መሆን፣ አገር አቀፉ የእርስ በእርስ የወሰን ጦርነት፣ ጎሣ እየለዩ የማፈናቀልና የመግደል አስከፊ የሰብአዊ መብት ረገጣ መሠረቱ ይኸው ሕገ መንግሥትና አከላለሉ መሆናቸውን የስታንፎርዱ የፖለቲካ ምሩቁ ጀዋር አያውቅም፣ አልተረዳም ማለትም አይቻልም።
በኦሮሞው የታሪክ ሊቅ በፕሮፊሶር መሐመድ ሐሰን ነጥሮ የተተረከውን የኦሮሞን አውዳሚ ወረራዎች እልቂትና አስከፊውን የሞጋሣ ሥርዓት የማንነት መብት ጭፍለቃ ደብቆ፣ የአማራን የአገር ግንባታ ትግል አስከፊነት ደጋግሞ ጀዋር ያነሳል። የት አገር ነው በግብዣና በፈንጠዝያ አገር የተገነባው ? የቅርቡን የ19ኛ ክፍለ ዘመን የጣሊያን፣ የፈረንሳይ፣ የጃፓን፣ የጀርመንና የአሜሪካንን የአገር ግንባታ ጦርነት ጀዋር አያውቅም ? አገር መገንባትና መምራት ከባድ መሆኑን አለመረዳት፣ “ከበሮ በሰው እጅ ያምር፣ ሲይዙት ያደናግር” እንደተባለው ያለፉት 6 ዓመታት ጭፍን፣ ጨካኝና ጨቋኝ የ21ኛ ክፍለ ዘመን የኦሮሞ መር የውርደትና የውድቀት አገዛዝ ደጉን የኦሮሞ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን ታሪካዊ መልካም ስምና ዝናም ያጎደፈና አንገት ያስደፋ የጭካኔና የውድመት አገዛዝ ዘመን ጀዋር አላስተዋለም ?
የጀዋር ያልተለመድ ዲሞክራትነትና የአገር ግንባታ ሕልም
ሥልጣን በበላይነት ይዞ አፍኖ መግዛት እንዳላዋጣ፣ መገንጠሉም ብዙ ዕርቀት እንዳላስሄደ ጀዋርም ነግሮናል። የአምባገነን አገዛዝ አፈና አመጽ በመቀስቀስ የአገዛዝ ዕድሜ እንድሚያሳጥርም ጀዋር ጠቅሶ እኩልነትን ከተፋጠነ ልማት ጋር አጣምሮ ሊያስኬድ የሚችል የፖለቲካ ሥርዓት መመሥረት እንደሚገባ አመልክቷል። ከልቡ ከሆነ፣ ለአሜሪካና እስታንፎርዱ ግርፉ ጥሩ ጅማሮ ነው። ከሌሎች ዲሞክራት ኢትዮጵያውያን ጋር ያለምንም ሴራ ወደ ተግባር ቢገባ ይበልጥ ሊታመን ይችላል።
ዛሬ የሚያስፈልገን ከብሔር ልክፍትና ከጨነገፈው ሕገ መንግሥትና ክለላ ወጥተን አገር የጋራ፣ ሃይማኖት የግል ያሉትን አስተዋይ አባቶች በመከተል፣ ኢትዮጵያን በእኩልነትና በመከባበር በጋራ መገንባት የሚያስችል፣ በደጉ ሕዝብባችን ስም ከሚነግዱ ራስ-ወዳድና ሆዳም ካድሬዎች ማወናበድ የጸዳ ሀቀኛ ፌደራልና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት ነው። ለም አገርና ሰፊ የማዕድን ሀብት ከጀግና ሕዝብ ጋር እያለን፣ በሕዝብ ስም እየማሉና እየተገዘቱ ከሚዘርፉን፣ ከሚገድሉንና
ከሚያወድሙን ሁሉ በትብብር ታግለን ነፃ ወጥተን ፌደራላዊት ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን በጋራ መሥርተን በራሳችን ወገኖች የክፋት አገዛዝ ደህይተን ለፈረንጅ የስንዴ ምፅዋት ተዳርገን ከሰው በታች መሆንን አፋጥነን ማስወገድ አለብን።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ሙሉ ተሳትፎ ያለበት የሽግግር ሥርዓት አደራጅተን እንደ 1982-1986 ዓ.ም. የማንዴላዋ ደቡብ አፍሪቃ የሁሉንም ኢትዮጵያውያን ሰላም፣ አንድነትና ወንድማማችነት የሚገነባና ለጋራ ፈጣን ዕድገት የሚያመቻች ዲሞክራሲያዊ ፌደራል ሥርዓት ብንመሠርት፣ ባለፉት 50 ዓመታት የተጣባንን ውርደት፣ ዕልቂት፣ ሞት፣ መፈናቀልና ስደት የሚገላግል ይሆናል። እንኳን እንደ እኛ የተዛመደ፣ የተቀላቀለና ለዘመናት አብሮ በሰላም የኖረና ዛሬም እንኳ ካድሬና ደንቆሮ አመራር ሆን ብሎ እያጋደለን ቢሆንም ሰላም የሚመርጠው ሕዝባችን ቀርቶ፣ የደቡብ አፍሪቃ አፓርታይድ ሥርዓት ለዘመናት ያጋደላቸውና ከመቶ ዓመት በላይ ሲተራረዱ የኖሩትም የደቡብ አፍሪቃ ጥቁሮችና ነጮችም በ1986 ዓ.ም. ዲሞክራሲያዊት ፌደራል ደቡብ አፍሪቃን በሕብረት በአንድ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ መሥርተው ዛሬ በሰላም እየኖሩ ነው።
ታዲያ ደቡብ አፍሪቃ ለዚህ የበቃችው እንደ ኔልሰን ማንዴላ ያለ በሳል፣ አገር ወዳድ፣ አርቆ አሳቢና አዋቂ መሪ ከ27 ዓመት የእሥር ቤት ኑሮ ወጥቶ፣ ዘረኛነትን ከጠሉና ለአገርና ለወገን አርቆ አሳቢ ከሆኑት ፕሬዚደንት ደክለርክ ጋር ተጣምሮ፣ ከሁሉም ፓርቲዎችና አርበኞች ጋር በመወያየትና በመመካከር ለጋራ ዘላቂ ሕልውናና አገራዊ ደህንነትና ዕድገት ታሪክ መሥራት ስለቻሉ ነው። ኢትዮጵያ ግን፣ ባለፉት 50 ዓመታት የገዟት መሪዎች፣ እንደ ኔልሰን ማንዴላ ለዲሞክራሲና ለታሪካዊ የጋራ ሰላምና ዕድገት በመቆም ፈንታ፣ ሁሉም ቆምንለት ያሉትንም ሕዝብ እንኳ ከድተው ለግል ጥቅምና ሥልጣን በመገዛታቸው፣ ቆመንላቸዋል ያሏቸውን የራሳቸውን ጎሣዎችና ሌሎችን ኢትዮጵያውያንንም ከማፋጀት፣ ከማጋደል፣ አገር ከመዝረፍ፣ የተገነባውን ከማፍረስና አገር ከማስገንጠል ውጭ ሲሠሩ እምብዛም አልታዩም።
ያለፉትን 50 ዓመታት የሰቆቃ ሕይወት ሁላችን ያየነውና የቀመስነው ስለሆነና መቀጠል ስለሌለበት፣ በጠባቦች የተጫነብንን የትውልድ እርግማን የሆነ የአምባገነን ሕገ መንግሥት አርመን፣ ኋላ-ቀሩን የክፍፍልና አጋዳይ ክለላን ወርውረን፣ ለሁላችንም የምትሆን እውነተኛ ፌደራላዊት ዲሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ እንድንመሠርት በጋራ መቆም አለብን። የመጣው ሁሉ አምባገነን ዘርና ሃይማኖት ሳይለይ ለሚረግጠውና ለሚበዘብዘው ህዝባችን ክልብ ከተቆረቆርን ከጎሣ ፖለቲካ መርዝ ፀድተን፣ እንደ 1980ዎቹ እንደ ነ እነ ኔልሰን ማንዴላና 26ቱ የወቅቱ የነፃነት ታጋይ ፓርቲዎች፣ ሁሉንም ያቀፈ የሽግግር የጦርና ፓርቲ መሪዎች ጉባዔ አደራጅተን ወሳኝ የሽግግር ስብሰባዎችን በየተራ በጉባዔው መሪ አባላት በመምራት የሥልጣን ጋኔሉን አሸንፈን፣ እንደ ደቡብ አፍሪቃ፣ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ማዋለድ አለብን።
ዝግጅት ክፍሉ – ከቦርከና ገጽ ተወስዶ ከአንባቢ የተላከ
ኢትዮሪቪውን ይርዱ ያግዙ