የድርድርና የሰላም ዜና ሲሰሙ ተስፋቸው የሚለመልም እንዳለ ሁሉ፣ በብስጭት ጸጉራቸውን የሚነጩ፣ ደረታቸውን የሚደልቁና በቻሉት ሁሉ ውዝገት የሚያዘንቡ ጥቂት አይደሉም። የሚገርመው ዕርቅ ተስፋቸውን የሚያለመልምላቸውም፣ ሰላም በብስጭት ጨርቃቸውን የሚያስጥላቸውም ሁሉም “ኢትዮጵያዊ” መሆናቸው ነው።
የፋኖ አንድ ክንፍ የሰላም ንግግር መጀመሩን ተከትሎ ይፋ ከተደረገ በሁዋላ፣ ከየአቅጣጫው “ምንጮች” ሹክ እንዳሉዋቸው እየገለጹ ስጋና ደማቸውን ቀላቅለው የዜናው ባለቤት ለመምስል የሚሻኮቱም አሉ። ጠቅላይ ሚኒስትሩና አማራ ክልል የተሰየመው የሰላም ምክር ቤት ስም ባይጠሩም ድርድር ለማካሄድ የሚያስችል ጠብመንጃ ካነሱ ኃይሎች ጋር ንግግር ለመጀመር ሁኔታዎች እየተመቻቹ እንደሆነ በአደባባይ ማመልከታቸው አይዘነጋም።
በየአቅጣጫው ጭራና ቀንድ እየተበጀለት ዜናው ተዥጎርጉሮ ቢቀርብም፣ ሁሉም ዜናዎች ሲጨመቁ በአማራ ክልል ጠብ መንጃ አንስተው ጫካ ከገቡ የሚታወቁ ኃይሎች መካከል በእስክንድር ነጋ የሚመራው ክንፍ ወደ ውይይት የመንደርደሩ ጉዳይ ነው። ዜናው ከዚህ ውጭ የሚጨመርም የሚቀነስም ጉዳይ የለውም።
ለሰላም የተጀመረውን ቅድመ ንግግር “የፋኖና የዲፕሎማቶቹ ውይይት” የሚል ማዕረግ የሰጡ ውይይቱ አዎንታዊ ይዘት እንዳለው ጠቁመው በጎ ጅምር እንደሆነ ሲያመለክቱ፣ የጎጃም ፋኖ ደጋፊዎች እስክንድር “ ለምን ለመነጋገር ወሰነ” በሚል ብቻ ውግዘቱን እያወረዱበት ነው። ለነዚህ አካላት ቅድመ ንግግሩ፣ ውይይቱ፣ ወይም ጅማሮው ምን ምን አካቷል የሚለው ጉዳይ አጀንዳቸው አይደለም።
ከምንም በላይ ከጦርነት ወደ ሌላ ጦርነት እየተሸጋገረ የሚለበለበው ህዝብ፣ የሚጠፋው ህይወት የሚወድመ ንብረትና እየከሰመ ያለው ጥቅል የክልሉ ቁመና አይመለከታቸውም። ለምን ቢባል አንድም ባንዳነታቸው፣ ከዛም ሲዘል አልጠግብ ባይነታቸው ነው። ሌላም ሌላም ሊባል ይችላል።
እስከንድር ነጋ፣ እስር ቤት ሆኖ ምርጫ ሲወዳደር በዝረራ እንደሚያሸንፍ ያምን ነበር። በዝረራ ተሸነፈ። ወደቀ። ያሸነፉት ደግሞ በምርጫ ማጭበርበር ሊታሙ የማይችሉ በመሆናቸው ምንም መከራከሪያ አልቀረበም። ተመርጦ ስልጣን ለመያዝ ባልደራስን መስርቶ ሳይሳካ ሲቀር እስኬው ወየነ። ወይኖ ሻለቃ ዳዊት ወለደ ጊዮርጊስን የውጭ የፋኖ ኃላፊ አድርጎ መሰየሙን በይፋ አስታወቀ። ተጨበጨበ።
ጫካ ገብቶ አርበኛ፣ ፋኖ መሆኑን በገሃድ ያስታወቀው “ታላቁ እስክንድር” ልክ ያኔ ሲወይን እንዳደረገው በወዳጅና አድናቆዎቹ በኩል ወደ ድርድር ለመግባት ንግግር መጀመሩን ቀድሞ አላወጀም። ይሁን እንጂ “ እንደሰማነው፣ እንደተነገረን” በሚል ተቀጽላ መላምት የታጀበበት፣ ውስጡ መርዝ የተቋጠረበት፣ የሰላም ወሬ መሰማቱ የፈጠረባቸው ንዝረት እስኪታወቅ ድረስ ምኞታቸውን እያዳበሉ ዜናውን ያሰራጩት ባሉት መልክ የተድረገ ንግግር እንደሌለ፣ ነገር ግን ድርድር ሊኖር እንደሚችል እስክንድር አስታውቋል። ዜናውን ሳያጣሩ የሰሩትን መሰረት ሚዲያን ጨምሮ “ተከፋዮች” ሲል ወርፏቸዋል። “ፋክት ቼክ መሰረት ሚዲያ ላይ አይሰራም ወይ” ሲል ጠይቋል። በነገራችን ላይ ይህ ዜና በሚሯሯጥበት የማህበራዊ ሚዲያ አውድ ላይ የተሰጠውን የህዝብ አስተያየት መመልከት ጥሩ መረጃ እንደሚሰጥ ለመጠቆም እወዳለሁ።
ጃዋር መሐመድ ለበርካቶች ዕልቂት ፊት ተሰላፊ ወንጀለኛ ከሆኑት መካከል መሆኑን የማይዘነጉት እነዚህ ሚዲያዎች፣ ህልማቸው፣ የተቀጠሩበት ዓላማና ከላይ እንደተገለጸው የማይሞላው ከርሳቸውን እያሰቡ “የኦሮሞ ወጣት እንደገና ይከተለኛል ወይስ ጥሎኛል” የሚለውን ስሜት ለመለካት የጻፈውን መጻሃፍ ተቀባብለውታል። አልጸጸትም የሚለውን ትኩሳት መለኪያ መጽሃፍ አስተዋውቀዋል። ደረታቸው ላይ ለጥፈው ለማሻሻጥና፣ እሱንም አዲስ ለውጥ አዋላጅ ሊያደርጉት ተጋግጠዋል። በንጽሃን ደም መነገድ ስለተጠናወታቸው….
የርዕዮቱ ቴድሮስ ምንም ያህል በኢትዮጵያ ባንዲራ የተጀቦነ መርዘኛ የዘር ፖለቲካ አራማጅ ቢሆንም ጃዋርን ለሃጩን በማዝረክረክ አንድ ወግ ሰርቶ እነዚህኑ ጉዶች በልጧቸዋል። ቴድሮስ ጃዋር ለወያኔ ውድቀት ኦህዴዶች ለክተው የሰጡትን አደራ በአግባቡ በመወጣቱ ሳቢያ በጥላቻና ቂም አደባባይ አውጥቶ እንደ ቁርበት አነጠፈው። ጃዋር በሚቀልባቸው ሚዲያዎቹ ፊት ዘወትር እየቀረበ ሲተፋ ስለኖረ ቴዎድሮስን መቋቋም አቅቶት ሲዞርበት ላየ የመንደር ጩሎ ይመስል ነበር።
አዲስ አበባ በውድ በተገዛው ቤቱ “እኔ የዘመኑ ግራኝ መሃመድ ነኝ፣ ታላቅ ተጽዕኖ ፈጣሪ ነኝ፣ ሁለት መግስት አለ። አንዱ የአብይ ሌላው የኔ ነው … “ በሚል እየተመጻደቀ በርካቶችን ያስጨረሰውን ጃዋርን ያሞካሹ፣ ወደ ፋኖ ትግል ሊሰፉትና ሊያጠጋጉት የዳዳቸው መናኝ የሚዲያ ዳንኪረኞች፣ እስክንድር “ስለምን ዕርቅ አሰበ” በሚል ስድብ እያወረዱ ነው።
የአገራዊ ዕርቅ ኮሚሽንና በባህር ዳር የተቋቋመው የሰላም ኮሚሽን በተደጋጋሚ ከአማራ ታጣቂ ኃይሎች ጋር ንግግር መጀመሩን፣ ለደርድሩ መሳካት ይበጅ ዘንዳ ዋስትና እንዲሰጥ እንደሚያደርጉ ሲገልጹ እንደነበር ለሚያውቁ፣ ለሚያስታውሱና አንዳንድ የዲፕⶀማሲው ሰፈር ሰዎችም በጉዳዩ መካተታቸው የአደባባይ ሚስጢር ሆኖ ሳለ “ምንጮቼ፣ ወዳጆቼ” እየተባለ እንደ ዳንቴል ክር የሚተለተለው ዜና የሰላም ኮሚሽኑን የማሳጣት፣ አልፎ ሄዶ ሁሉንም ወደ ውይይቱ እንዳያመጣ የማሸማቀቂያ ኮተት ለማጀል ካልሆነ በስተቀር ሌላ ረብ የለውም።
በአማራ ክልል በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለመገንባት ከ100 ቢሊየን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሲያስታውቅ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህጻናት ድንቁርና ታውጆባቸው ቤታቸው ሲቀሩ፣ የማይደነግጡ ገና በጅምር ያለውን ጉዳይ ለመስበር ሩጫ መጀመራቸው በምን ያህል ሃዘንና ምሬት ሊገለጽ እንደሚችል የሚያውቀው ችግሩ ውስጥ ያለው ምስኪኑ ህዝብ ብቻ ነው።
ለአብነትም በምሥራቅ ጎጃም ዞን ከ400 በላይ ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን የሚያውቀው ዘመነ ካሴ ይህን ሲሰማ ተንደርድሮ ወደ ሰላም እንዳይመጣ፣ የቃላት እክሮባት እየሰራ እስክንድርን ያወግዛል። የጠዋት አፉን በስድብ ያሟሻል። የሚገርመው አማራን የሚያክል ትልቅ ህዝብ፣ እንደ መካን፣ ልጆች እንደሌሉት ሆኖ በእንዲህ ያለ ኩታራ እድል ፈንታው እንዲወሰን ባንዶች እንዲፈርዱበት መደረጉ ነው።
እዚህ ላይ እስክንድርም ሆነ ሌሎች ጽድቅ ናቸው ለማለት ሳይሆን ወደ ዕርቅ ለመምጣት ማሰባቸው በራሱ የተለየ ስሜት እንደሚፈጥር ለማመላከትና ሊበረታታ የሚገባው እንደሆነ ለማሳየት ብቻ ነው። አማራ ክልል፣ መንግስት፣ ፋኖ ወዘተ ውስጥ እንደየደረጃቸው ለጥፋቱ ኃላፊነት እንደሚወስዱ ላፍታም አልስተውም። አሁን ግን ቀዳሚው ሰላም በመሆኑ አልፈዋለሁ።
ጉዳዩን የያዙት ወገኖች አስቀድመው እንዳሉት ከተለያዩ የፋኖ ክንፎች ጋር ንግግር ተጀመሯል። የተጀመረው ንግግር ድርድር የሚባለውን ዋና ጉዳይ የማመቻቸት ነው። እነዚህ ወገኖች ከወራት በፊት እንዳሉት ይህ ድርድር ዛሬ ላይ የተደረሰው በብዙ ውጣ ውረድ ነው። ይቀጥላል። ሌሎችም በይፋ እንደ እስክንድር ይህንኑ ያደርጋሉ።
በአማራ ክልል ከመንግሥት ጋር ውጊያ ላይ ያለው የፋኖ ኃይል በአንድ ዕዝ ሥር አለመሆኑ መንግሥት ከኃይሉ ጋር ለሚደረግ “ንግግርም ሆነ ድርድር አመቺ እንዳልሆነ የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ታህሳስ 11 ቀን 2023 ለቢቢሲ ተናግረው እንደነበር ማስታወስ ዛሬ “ምንጮች” ሹክ እንዳሏቸው ገልጸው አሮጌውን ዜና እንደ አዲስ እያናፈሱት እንደሆነ ለመረዳት ይረዳል።
ነሃሴ 2 ቀን 2024 ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ከሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ኃይሎች ጋር መንግሥት ተከታታይ የሆነ ንግግር እያደረገ መሆኑን ማስታውቃቸው አይዘነጋም። በተለያዩ ሰላም የሚያስደነግጣቸው ኃይሎች አማካይነት ለማጣጣል ቢሞከርም ግማሹ ኦነግ ሸኔ እርቅ ቅውርዶ ገብቷል። በቀጣይም ስራው ቀጥሏል። ይህ እርምጃ ምንም ይሁን ምን በበጎ የሚነሳ እንጂ የሚተች ሊሆን ባልተገባ ነበር። እንኳን በሺህ የሚቆጠሩ አንድ እንኳን ጠብመንጃ ይዞ ጫካ የነበረ ወደ ሰላም መመለሱ አስደሳች …
በእስክንድር የሚመራው የፋኖ አንድ አካል አቅሙና ያለው ኃይል ለጊዜው ባይታወቅም፣ ቀደም ሲል ከቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የአሁኑ ፕሬዚዳንት አቅጽስላሴ ጋር መነጋገሩን ሰምተው ተቃውሞ ያዘነቡ፣ አሁን ቃል በቃል እስክንድር ባይናገረውም የሰላም ጅማሮ መኖሩን አያነጋግርም። “ምንጮችና ዲፕⶀማቶች ሹክ አሉን” በሚል ማስፈራሪያ በማከል ለማሰራጨት የተሞከረው ሌሎችን እግር ተወርች አስሮ ደም መፋሰሱ እንዲቀጥል ካለ የቅጥረኛነት እሳቤ የሚመነጭ እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም።
ሌላው የድርድርና የስምምነት ዜና አንገሽግሾት አደባባይ የወጣው የባንዶች ሰብሳቢና የሻዕቢያ ጉዳይ አስፈጻሚ አንዳርጋቸው ጽጌ ነው። ድርድሩ በተሰማ ቅጽበት ከወዳጁ ጋር በአንከር ሚዲያ የፈተፈተውን የስጋት ትንተና “አንብቡልኝ አድምጡልኝ” ብሎ በፌስ ቡክ ለጥፏል።እነማንን እንደሆነ ባይታወቅም “ውድ ወገኖች” ይልና ይጀምራል። ሲቀጥልም ” ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ ውስጥ ከተለያዩ አቅጣጫዎችና በተለያዩ መንገዶች እየተከሰቱ ያሉ አዳዲስ የፖለቲካ ሁኔታዎች አሉ። የፋኖ እንቅስቃሴ እነዚህን ሁኔታዎች በአግባቡ ሊያጠናቸውና በአግባቡ ሊስተናግዳቸው ይገባል። ይህን ወሳኝ ስራ ለመስራት አስፈላጊ ከሆኑ መሳሪያዎች መሃል ዋናው የተሳለጠና በስነስርአት የሚመራ ድርጅታዊ አቅም መፍጠር ነው።” ይለናል።
አንዲ ያክልና “አንድ ወጥ የሆነ፣ የፋኖ እንቅስቃሴዎችን አስተባባሮ የሚመራ ፖለቲካዊና ወታደራዊ አካል በሌለበት ሁኔታ የተለያዩ የፋኖ አደረጃጀቶች በተጠናል ከየትኛውም በሚገባ ከተደራጀ አካል ጋር የሚፈጥሩት ግንኙነት ፋኖን እና የአማራ ህዝብ ትግልን በከፍተኛ ደረጃ የሚጎዳ ይሆናል”ይላል።
“አማራ የሚባል ህዝብ የለም” ሲል የነበረውና በራሱ ጽሁፉ ያተመበትን ጉዳይ የረሳው አንዲ ሻዕቢያ እንዳንደረደረው ተወርውሮ ያረፈው “የለም” ያለው አማራ ላይ ነበር። ሁሉንም ረስቶ ” በቅርቡ በእስክንደር ነጋ የሚመራው የአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት ከአሜሪካና ከአወሮፓ መንግስታተ እንዲሁም ከኢጋድና ከአፍሪካ ህብረት ተውካዮች ጋር በሸዋ የፋኖ ነጻ ቀጠና ያደረጉት ውይይት እንዲሁም ሌሎች በሃገራችን ውስጥ ያሉ አካላት ከተለያዩ የፋኖ ሃይሎች ጋር በመቀራረብ ለመስራት በመፈለግ እያደረጉ ያለው ግንኙነት የአማራ ፋኖ በአንድ ወጥ የተማከለ ወታደራዊና ፖለቲካዊ አመራር ባልተደራጀበት ሁኔታ የሚደረግ በመሆኑ በአማራ የህልወና ትግል ላይ ከፍተኛ አደጋ ሊያስከትል ይችላል።” ሲል ለአማራ ተቆርቋሪ መስሎ ለሻዕቢያ ህልውና ሲባል የሰላም ጅማሮው እንዲጨናገፍ መርዙን ይረጫል።
ሰውየው ሕዝብ እንዲያልቅ ካለው ፍላጎት በመነሳት ስምምነት መጀመሩን እያወገዘ፣ “ውድ ወገኖች ከፋኖ እንቅሳቅሴ ጋር በአመራርነት በአባልነትና በደጋፊነት የሚሳተፉ የምታውቋቸው ግለሰቦች ሁሉ ይህን ቃለመጠይቅ እንዲያደምጡት በማድረግ በማጋራት ተባበሩ” ሲል የተፋውን የጥፋት መርዝ ዜጎች እንዲያስራጩለት ተማጽኗል።