ሰሞኑን በአፋር ክልል በፈንታሌ ተራራ እየተከሰተ ያለው የመሬት መንቀጥቀጥ ንዝረቱ አዲስ አበባ ከተማ ድረስ ቢሰማም የከፋ ጉዳት ያደርሳል ተብሎ እንደማይጠበቅ በኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት የጂኦዴሲ እና ጂኦዳይናሚክስ መሪ ስራ አስፈፃሚ ናትናኤል አገኘሁ ገለጹ።
የመሬት መንቀጥቀጥ ምንም የማይተነበይ ወይም ተገማች ያልሆነ፣ በዋናነትም በተፈጥሮ ውስጣዊ ኃይል ምክንያት የሚፈጠር ክስተት መሆኑንም ነው አቶ ናትናኤል በተለይ ለኢቢሲ ዶት ስትሪም የገለፁት።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦፊዚክስና ስፔስ ሳይንስ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ዶ/ር ኤሊያስ ሌዊ እና በተቋሙ የዘርፉ ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር አታላይ አየለ በበኩላቸው፥ የኤደን ባህረ ሰላጤ፤ የምስራቅ አፍሪካ እና የቀይ ባህር ስምጥ ሸለቆዎች በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ዓመታት ሲያደርጉት የነበረ መፈላቀቅ አሁንም የቀጠለ ተፈጥሯዊ ክስተት በመሆኑ የመሬት መንቀጥቀጥ እንዲከሰት ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል።

ከአፋር አንስቶ በሀዋሳ፣ አርባ ምንጭ፣ ኤርትራ እስከ ቀይ ባሕር ያለው መስመር የታላቁ ስምጥ ሸለቆ መገኛ በመሆኑ በፈንታሌ አካባቢ እየተከሰተ ላለው የመሬት መንቀጥቀጥ አንዱ ምክንያት ነው ብለዋል።
የፈንታሌ የእሳተ ገሞራ ተራራ ቅልጥ አለት እስከ ዶፋን ድረስ 30 ኪሎ ሜትር ውስጥ ለውስጥ መሄዱን፤ የአካባቢው መሬት እስከ 33 ሴንቲ ሜትር በፊት ከነበረበት ወደ ላይ ከፍ ማለቱን ከሳተላይት የተገኘው መረጃ ያመለክታል ብለዋል።
የፈንታሌ ተራራ እስከ 13 ሴንቲ ሜትር ወደ ላይ መወጠሩን፤ ውጥረቱ ከላይ ያለውን ድንጋይ እንዲሰባበር ማድረጉን፤ ይህም ደካማ ቦታዎች ላይ መንሸራተትን መፍጠሩን፤ ድንጋይ ከድንጋይ ሲጋጭ የሚፈጠረው ንዝረትም ሞገዱ ተጎዞ ሰሞኑን እስከ አዲስ አበባ እየተሰማ መሆኑንም የተናገሩት።
ሰሞኑን በሬክተር ስኬል እስከ 5 የሚደርስ የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱን የተናገሩት ባለሙያዎቹ፤ ይህም በየቀኑ በተለያየ መጠን፣ በተደጋጋሚ እየተመዘገበ መሆኑን ተናግረዋል።
የመሬት መንቀጥቀጡ ለመሬት፣ ለትምህርት ቤቶች፣ ለመኖሪያ ቤቶች፣ ለአንዳንድ ሕንጻዎች እና የአስፋልት መንገዶች መሰንጠቅ ምክንያት መሆኑን አንስተው፤ ክስተቱ የማንቂያ ደወል ነው ብለዋል።
ክስተቱ በፈንታሌ እሳተ ገሞራ አካባቢ ባሉ ነዋሪዎች ዘንድ ድንጋጤ መፍጠሩን ገልጸው፤ መጠኑ እየጨመረ ከሄደ በህብረተሰቡ ዘንድ የሚፈጠረውን ስጋት ለመቀነስ ተገቢ ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
የፈንታሌ አካባቢ ኢትዮጵያን ከጅቡቲ የሚያገናኘው መንገድና የባቡር መስመር የሚያልፉበት መሆኑን ጠቅሰው፤ ክስተቱን እንደማንቂያ ደወል በመውሰድ መንግሥት እንዲሁም የዘርፉ ምሁራንና ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሊሰጡት ይገባል ብለዋል።
የመሬት መንቀጥቀጥ እንዳይከሰት ማድረግ ባይቻልም አደጋው ቢፈጠር የሚያስከትለውን ጉዳት መቀነስ ይቻላል ያሉት ባለሙያዎቹ፤ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ለህዝብ ወቅታዊ መረጃ ተደራሽ ለማድረግ በቅንጅት መስራት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።
በላሉ ኢታላ ETV