ይህ የመጽሐፍ ዳሰሳ ሳይሆን የመጽሐፍን ውበት ማሳያ ነው።
“ዘበት እልፊቱ”
(ወለሎታት)
በሰለሞን ዴሬሳ
መጽሐፉ 54 ወለሎታትን የያዘ ነው።
የሰለሞን ዴሬሳ “ልጅነት” የተባለው የመጀመርያ መጽሐፉ እጄ ላይ ስለሌለ ላነበው ባልችልም ልጅነትን አሳትሞ 28 ዓመታት ካለፉ በኋላ የጻፈውን ይህንን “ዘበት እልፊቱ” የተባለውን መጽሐፉን ለማንበብ ዕድሉን ስላገኝው ደስ ብሎኛል። ከሶስት በላይ መጽሐፍ መጻፍ እንደማይፈልግ ተናግሮ የነበረው ሰለሞን ዴሬሳን ጋዜጠኛው ‘ለምን?’ ብሎ ምክንያቱን ሲጠይቀው ፈገግ አለና “ሶስት መጽሐፍ ይበቃል ከአንድ ሰው፣ እሱንም ደግ የሆነ ሰው ነው የሚያነበልህ” ብሎ መልስ ሰጥቶ ነበር። ለኔ ግን ዕድሉን አግኝቼ መጽሐፉን ማንበቤ የደግነት ስራ ሳይሆን እጅግ በጣም መታደል ነው።
ሰለሞን ዴሬሳ በስነጥበብ ሃያሲነቱና በጋዜጠኛነቱ ታዋቂ ከመሆኑም በላይ በጣም ድንቅ ባለቅኔ ነበር። እንደውም አንዴ የሆነ ቃለመጠይቅ ላይ ስብሃት ገ/እግዚአብሄር ሰለሞንን ከባለቅኔዎቹ William Shakespeare እና Lord Byron ጋር አወዳድሮ “ድንቅ ገጣሚ” ብሎ ጠርቶታል።
ስለ ግጥም ስናነሳ ሁሉም አንባቢ የራሱ የሆነ ምርጫ አለው። አንዳንድ አንባቢ ከባባድ ቃላት ካላየ ግጥሙ ግጥም አይመስለውም። አንዳንዱ ደሞ በቴክኒክ ስለሚያምን የአገጣጠም ቴክኒኩ በተለምዶ ከሚያውቀው ትንሽ ሸርተት ካለ ግጥሙ ግጥም አይመስለውም። ሌላው ደሞ በእያንዳንዱ ስንኝ ቅኔ ማሳደድ ደስ ይለዋል። የሁሉንም ምርጫ አከብራለሁ። ይህን አማርጦ የሚፈልጉትን የማንበብን ነጻነትም አልጋፋም። እኔ ግን ነፍሴ በጣም የምትሳበው ለስሜት የሚቀርብ፣ ፍስስ የሚል እና ልብ የሚኮረኩር ግጥም ላይ ነው። ቤት መታ አልመታ ብዙ ጉዳይ አይሰጠኝም። ቅርጹ ቢንሻፈፍ፣ ከተለምዶ ሸርተት ቢልም ምንም አይመስለኝም። ሳነበው የጸሃፊውን የልብ ትርታ ማዳመጥ ከቻልኩ በቃ ፍስሃዬ እዛ ላይ ነው። ሰለሞን ዴሬሳን ሳነበው ወዲያው ወደድኩት። መጽሐፉን አንብቤ ጨርሼ ቃለመጠይቆቹን ስሰማ ደሞ ስብዕናውና በዕውቀቱ ለሀገሩ ያበረከተው አስተዋጽዖ አስደመመኝ። ግልጽነቱ፣ ቀጥተኛነቱ፣ ተጫዋችነቱ፣ ለሀገሩና ለወገኑ ያለው ፍቅር እና በአጠቃላይ ራሱን የሆነ፣ በአቋሙ የጸና ሰው መሆኑን ስገነዘብ ግጥሞቹ ሌላ አይነት ከፍታ ላይ ደረሱብኝ።
የዚህ መጽሐፍ መግቢያ ላይ እንዲህ ብሎ ነበር።
“እያንዳንዱን ወለሎ ወረቀት ላይ ሳሰፍር፣ ጭረቱን እንደቡሄ ጅራፍ ከሚሰነጥቀው ንሸጣ የሚያልፍ አላማ ኖሮኝ አያውቅም፡፡ እዚህ ከተሰበሰቡት በቁጥር የማያንሱ ጠፍተው መቅረታቸው እጅግም የማያሳዝነኝ በዚሁ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም:: አልፎ አልፎ ሆዴን የምትበላኝ አንዲት በኤርትራ ነፃነት ማግስት የፃፍኳት ወለሎ ብቻ ናት’:: አንዳንድ ገጣሚ ወይንም ወለልቱ የፃፈውን በቃል ያስታውሳል፡፡ ገብረ ክርስቶስ ደስታ፤ ኮሌጅ ተማሪዎች በነበርን ዘመን ደግሞ ተገኘ የተሻወርቅ፤ እንዲህ ነበሩ፡፡ እኔ አላስታውስም፡፡ የየወለልቱው ምኞትና ተስፋ ይለያያል፡፡ የኔ ሀሌታ ምኞት፤ አንባቢን ከኔ ሃሳብ ለማቀራረብ ሳይሆን ከራሱ ወይንም ከራሷ ንሸጣ ጋር ለማቆራኘት ነው፡፡ የኔማ የተፃፈለት አለፈ፡፡ ኘሮፓጋንዳ ሲቃጣኝ ደግሞ ይህን መግቢያ ወደሚመስል አፃፃፍ እመጣለሁ፡፡ ተቀጥላ ምኞቴ ደግሞ፥ ወለሎው እንዲሰማ እንጂ፥ ከድንጋይ የታነፀ ትርጉም እንዲገኝለት አይደለም።” ገጽ 9
“ግጥም ሲዋጣ፥ ስንኝ ይገጥማል ቤት ይመታል፥ ዜማ ያነበንባል ፥ ቋንቋ ይፈነድቃል፡፡ ተረት ይተረታል፥ ታሪክ እልባት ያገኛል፡፡ ሙሾ ይወርዳል፥ ለፍቅር ግምጃ • ይገባል፡፡ ግጥምን የሚያረክሰው ያንዳንድ መስመሮች መበላሽት ሳይሆን፥ የሀሳብ ወይንም የስሜት ሀቅ ማጣት ወይንም ለገጣሚው ባይተዋር መሆን ነው፡፡
ወለሎ ሲዋጣ ፥ ሃሳብ በስሜት ይዋጥና፥ ባለጌ እንደወረወረው ርችት እልፍኝ መሃል ይፈነዳል፡፡ የወለሎ ዋና ውበቱ በቋፍ ያለ ሂደቱ መሆኑ ነው፡፡ ወለሎ ያነሳሳውን ሁናቴ ወይንም ታሪክ ወደ ጎን አድርጎ፥ የሁናቴውን፥ የታሪኩን፥ እንፋሎት ይከተላል፡፡ ወለሎ ሲከሽፍ፥ አመድ፡፡ ከምሱሩ እንደተበላሸ ፈንጂ፥ ቱሽ… ሽ…” ገጽ 10
“አሳጥሬም ቢሆን የምችለውን ያህል ማብራራት ከሞከርኩኝ በኋላ «ወለሎ የሚል ቃል ለምን ከኦሮምኛ ወደ አማርኛ ሰርጎ ገባ?» ብሎ የተንኰል ጥያቄ ለሚያጠብቅብኝ መልሴ ቀላል ነው፡፡ የዛሬ ሶስት ወር ተስፋዬ ገሠሠን አጅቤ ለቅሶ-ቤት ህጄ፥ ያገኘኋቸው አዛውንት መንዜ ኮሎኔል እንዳሉኝ፥ «ተንኰለኛ ወለጌ ስለሆንኩ ፥ _ ወለሎን ክልል አሳለፍሁ፡፡» ፈረንጅ ሃይኡን ከጃፓን ሲዋስ ፥ ደምቢዶሎ የራቀው አማርኛ ተናጋሪ፥ እንዲሁም ከጎንደር ዋሽንግተን የሚቀርበው ኦሮሚፋ ተናጋሪ፥ ኬክ ይብላ።” ገጽ 10-11
እኔ አንባቢውን የምመክረው መጽሐፉን ከማንበባችሁ በፊት መጀመርያ ዮትዮብ ላይ ሰለሞን ዴሬሳ የሰጣቸውን ቃለመጠይቆች ብታዳምጡ ከግጥሞቹ በፊት ከስብዕናው ጋር ፍቅር እንደሚይዛችሁ አልጠራጠርም። ድንቅ ስብእናውን ስትረዱ ግጥሞቹ ከምን አይነት ልብ እንደፈለቁና ከምን አይነት ተሞክሮ እንደተጸነሱ ግልጽ ይሆንላችኋል። ከዚህ እይታዬ ስር ባለው Comment section የዩትዩቡን ሊንክ አስቀምጬላችኋለው። እኔ በግሌ ቃለመጠይቆቹን በሙሉ ሰምቼ ስጨርስ ይህንን ድንቅ ነፍስ መተዋወቄ ሕይወቴ ላይ የሆነ ነገር እንደተጨመረልኝ አይነት ስሜት ነው የተሰማኝ።
ከሰጠው ቃለመጠይቅ ውስጥ በጣም ያሳቀኝ ነገር:- ቢሮክራሲ ምን ያህል እንደሚጠላ ከተናገረ በኋላ የጥላቻውን ጥግ ለመግለጽ “ከሞትኩ በኋላ ምናልባት እዛ መንግስተሰማይ የሚባለው ቦታ ቢሮክራሲ ካለ፣ እነጴጥሮስን ወይ ጳውሎስን ማስፈቀድ፣ ማስፈረም ምናምን ካለብኝ በቃ ቦታው እደማይስማማኝ አውቃለሁ” ሲል በሳቅ ፈረስኩ።
ለቅምሻ ያህል ከመጽሐፉ ውስጥ ከወደድኳቸው ግጥሞች ጥቂቱን ላካፍላችሁ።
“ስጠብቅሽ ቀርተሽ”
በየማህሌቱ
በየመስጊዱ
በየኢሬፈቻው ጥላ
ስጠብቅሽ አንጀቴን ደቂቃው እየበላ ጠይም ነበርሽ የጠይም ማለቂያ
ጥርሶችሽ የንጣት መለኪያ
ማግባትሽን ከሰው ሰው ሰምቼ
ከ’ናት መወለዴን ጨርሼ ረስቼ
ከሰውነት ርቄ ጭሼ ተበትኜ
መልህቄን ለቅቄ በፅልመት ተውጬ፥
የፈላ ወርቅ ለጠበል ጠጣሁኝ
ክብደቴ ተሰምቷት መሬት እንድትውጠኝ
እንዳይነካሽ ርቄ የተጋትኩት ፍላት
ፓሪስ በረንዳ በተንጋለልኩበት
ገፍታኝ ቦታ ያዘች የሰሜኗ ወጣት
ነሀስ ቆዳዋ፥ ወርቅማ ፀጉሩዋ፥ ከወርቅ
የነጠሩ
አረንጓዴ አይኖቿ አነር የሚያስቀኑ
ሳቅና አረማመዷ ያንቺን የሚጠሩ
ፍቅሯ እንደ ድፍረቷ በይፋ የሚያቅራራ
ነቀለችሽ አንቺን በሽንጧ ገፍትራ፥
ተመልሶ እኔነቴ ከሷ ጋር ሊያቅራራ፤
ሃላፊ ናትና ፍቅርም እንደብሶት፥
ከኔ መለየቱ እየተናነቃት
እየተናነቀኝ የአይኖቿ እምነት ጥራት
ከንፈሮቿን፥ ባቷን፥ ፊቷን ዳሌዋን፥ ላስቀር ስመዘግብ
ሀዘኔ ተውጦ እሷ ባመጣችው ሰላም
እንኳን ልሞትልሽ፥ ላልመኝሽ ዳግም
ባቡር ይዟት ወጣ ከቆምኩበት ጣቢያ
እጆቼ ተራቁተው፥ ተራጥበን በእንባ
ተለያየን በእምነት፥ ተላቀቅን በሲቃ፥
ከቆሰለ ልቤ፥ በሷ ስሰናበት
ማእበሉን ቋጥኙን፥ ተመስገን እያልኩት
ለጋስ አካላቷን ከልቤ እንዳቀፍኩት
ለኖርማንዲ ባህር ድፊት ሰገድኩለት -ገጽ 56-57
“ፈውሱ“
ደማችን ካልባሌ ሽሮ ጓጉሎ
የማይሞቀን እሳት እንዲያው ተንበልብሎ
አልወርድ አለ ጠበሉ፥ እንደይፈውሰን ረግቶ አልረካ አለ ጥማችን ከጨጨብሳ ከብዶ፥
የተስያት ፀሐይ ተዳክማ ልትጋለጥ
አስር ብንወራጭ ከውርጩ ላናመልጥ -ገጽ 38
“ክቡር ኢትዮጵያውያን”
በኢትዮጵያ ባልጎ መታየቱ
ሳይሆን ቂንጥር ማስቆረጡ
ህፃኗን ልጅ እንደ ቆዳ መስፋቱ
መባለጉ
አፍ ሞልቶ «ቂንጥርን» መጥራቱ”- ገጽ 60
“ድብቅ ስም”
አንዳትረግሚኝ አልነገርኩሽ ስሜን
አታውቂ የናቴን አልሰማሽ ያባቴን
ጠይቂኝ አጥብቀሽ ስንገናኝ ሲመሽ
አለዚያ ከንቱ ነው ከፍለሽ ማስጠንቆልሽ”- ገጽ 77
********************************************
“አንዳፍታ”
እውንና እውቀት ከሆኑ አንዳፍታ
ውበትና ሞት ሃላፊ እንደ ሽታ፥
ከምስጢር ጓሮ ጉድጓድ ቆፍሩላት
ፍቅርን አግዘናል መስከን ትመልሳት”- ገጽ 55
********************************************
“ዘበት እልፊቱ”
ሳይበተኑ አይቆጠሩ ከዋክብት
ቀዝቅዘው ሳይረጉ አእላፋ ኣለማት
ስፋት
ከርዝመት
ከጥልቀት
ሊነጠል ገና ሳይፈራገጥ፥
አንጋፋ ጎህ ሳይቀድ
ኑሮ ባለመኖር ሳይሸበር
አለመሆን በሁኔታ ሳይታሰር
ቡችላ ጊዜ ኣይኖቿን ሳትከፍት
ከዘመናት አራስነት በፊት
ነበር ያፈቀርኩሽ፥
ካድማስ አልነበረ አድማስ
ስተኰስ ፈጥኜ ከጨረር
አለመሆን ማህፀን የግዜ ፍሬ ሆነሽ
ነበር ያፈቀርኩሽ፥
ሳንተዋወቅ ተነፋፍቀን
ልንፋለግ ከምኞት ተፀንሰን
ስንቱን አጋንንት ባ’ብዶ አሳብደን
ነበር ያፈቀርኩሽ፥
የትም ብልከሰከስ፥
እኔነቴን በቁመናሽ ላውቀው
ቅርፄን በቅርፅሽ ልተምነው
መልኬን በመልክሽ ልለየው
ስቀሰቀስ ያየሁትን እንዳልረሳው፥
ናፍቆትሽ ከሀሳብ ፈጥኖ
ናፍቆቴ ከስልቅ ሲቃ ቀጥኖ
ብትነጠፊ በየሜዳው
እኔኑ ፍለጋ ነው፥
ትንፋሽሽ ሲዳስሰኝ
አይገመት ርቀትን አቋርጦ
ጊዜን ነጥሎ አሳጥሮ አጥፎ
ነበር ብቻ ሳይሆን ይሆናል፥ ነው፥ ፍቅርሽ ሳልጠራጠር አፍቅሬ ሁሌም የማፈቅርሽ፡፡
ካማልክት መሻፈድ ተረግዘን
ላንዳፍታ ተቀራርበን
ቁጥር-አለፍ ብርሃነ-ዘመናት ለይተውን
ዘለኣለማት አልፈው፥ ተረስተው፥ ዳግም ልንገናኝ
የማታልፊ ፍቅሬ፥ ፍቅርሽ የማይርቀኝ”- ገጽ 48-49
********************************************
“አንቺን”
አንቺን ላየ አንድ እድሜ ላይበቃ
ያቃጠለኝ ጥማት ባረቄ ላይረካ
ፋኖ ልምታሽ ፋኖ ማታ
ልጣበቅሽ እስክነቃ- ገጽ 35
********************************************
“ገናናው በረሃ” (ለፀጋዬ ገብረ እግዚ)
ያ ሁሉ አፍላነት ለዘለአለም መስሎን
ከጠይም ጉንትቶ ጦፊጦ ጨው ልሰን
ጆርጊስን አራዳ ምን አመጣው ብለን፥
ኤይድስ አልገባ ገና ሃያን አላሟላን
ከማህሌቱ በስተ-ምስራቅ ደፍረን ተሸራሙጠን
እቼቼ ገዳሜ በታንጎ ተለዝቦ
አለሌነት ከረመጥ ፍሞ ጐልቶ
ሲረገድ ተመሽቶ ሲረገድ ተነግቶ፥
ልጅነትና አረቄን በቁርባን አጋብተን
እከበሮው እምብርት ጋደም ብለን ቃዥተን
እያላበን ውበቷ ቁልቁል ታይቶን፥
በቀላ ውጋጋን ድንጉጥ አስደንሰን
ለሉሲፈር ጭፍሮች አልቂት አስፈትፍተን
አፍላ ነበርንና ሸርሙጠን ወስውሰን
ስልጡን ነበርንና ጦቢያት አድባራትን ገፍተን
ከእምሆቴፕ ከሆመር ያማልክት ስም ተውሰን
መልከ-መልካም ጠንቋይ ዳፍንት አስገልጠን
ላፍላነት ቅዳሴ ጧፍ ሆነን ቀልጠን፥
ከልዝቡ ሽገር ሰማይ ምህረትን እንደሚሻ
እጣን ጪሶ ሲዝለገለግ እንጦጦ መርገጫ
እንኳን የገጠማት አልታየችን እሷ
በንቶን ጭነት ተጐትተን ወርደን
ለምድራ’ለም ተስለን
አይናችንን ሳናሽ እነ‑ፀጉን ቀብረን
ህያው ነበርንና
ዘለአለማዊ ልኡላን ሆነን ነግሰን
ያ ሁሉ አልፎ ባእድ መንገድ ቀረን-ገጽ 41-42
*****************
“ላይበቁ ለደቦው”
ፎቅ በፎቅ ደረቡ
መርቸዲዝ ተንጋለሉ
በቄሳሩ መዲና ናጠጡ ሸለሉ
ሰርቀው እንዳልከበሩ
ገርፈው እንዳልበሉ
አሰቃይተው ያመለጡ ሁሉ
ተደባለቁን በየሰርጉ
በየስደት ቤቱ
ለሙሾው በየቀብሩ
አልቅሰው ሊያላቅሱን
አብረውን ሊጨፍሩ
ተፅእኖ ሆነና ያለፈን መወደስ
ወኔ ጠፋና ከህሊና ለመዋቀስ
ንፅህና ደብቦ፥ እውነት እንዳይካስ
መርሳት ልማድ ሆኖ አይከፉት – ክፋት ሲደርስ
እንዳልጋጡን ሁሉ አብረውን ሲበሉ
የተበሉትም ብር ብለው ጨፈሩ – ገጽ 24
********************************************
“ደርሶ”
መብነን አምሮኝ ከሁነት ተላቅቄ
መዋቅር ነኝና በትንፋሽ ደቅቄ
ስፍራ ላልይዝ ደርሶ መንፏቀቄ – ገጽ 40
ትግስት ሳሙኤል
