በ1520ዎቹ ፍራሲስኮ አልቫሬዝ የተሰኘ ካህን ከፖርቱጋል መልዕክት ለማድረስ መጥቶ ለስድስት ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ ተቀምጦ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ይናገራሉ። በዚሁ ወቅት የላሊበላን ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ለመጎብኘት ዕድል አግኝቶ እያንዳንዱን ሕንጻ ከገለጸ በኋላ በመደነቅ “ስለነዚህ ሕንጻዎች ከዚህ በላይ መጻፍ አልችልም፤ ምክንያቱም ከዚህ በላይ ብጽፍ አንባቢዎች የሚያምኑኝ አይመስለኝም፤ እስካሁን የጻፍኩትንም እውነት አይደለም ይሉኛል ብዬ እፈራለሁ፤ እኔ ግን በኃያሉ እግዚአብሔር እምላለሁ፣ የጻፍኩት ሁሉ እውነት ነው! እውነታው እንዲያውም ከዚህ ከጻፍኩትም እጅግ የበለጠ ነው፤ ውሸታም እንዳይሉኝ ግን ትቼዋለሁ” ብሏል።
ካህኑ በ16ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ይህን ሲያነሱ ስጋታቸው ገብቶኛል፤ እኔም በ21ኛው ክፍለ ዘመን ላሊበላ ላይ ከትሜ ተመሳሳይ ነገር ገጥሞኛል። የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት እንዲህ ናቸው ብሎ በበረታ ብዕሩ መግለጽ የሚችል ሰው ምንኛ የታደለ ነው። ኪነ ህንጻው ከዚህ ተጀምሮ እዛ አልቋልም ብሎ ማብራራት የሚቻለው ሰው ከወዴትስ ይገኛል?
በብዙ የሳይንስ እና የጥበብ ልህቀት ላይ ደርሰናል፤ ጨረቃን መርምረን ምድርንም አስሰን ጨርሰናል የሚሉት ነጮችም ከኔ እኩል በላሊበላ ሲደነቁም ተመለከትኩ። “በርግጥም ላሊበላ ግሩም ነው!” ከማለት ውጭ ሌላ የቃላት ጋጋታ ይገልጹት ዘንድ አቅም የላቸውም። ለአራተኛ ጊዜ የመጣሁት እኔ ለመጀመሪያ ጊዜ ለመጎብኘት ከመጡት እኩል አብሬ አጃኢብ ስል እራሴን አገኘዋለሁ።
ላሊበላን ሄደው ሲጎበኙ የተለያዩ ስሜቶች ይፈራረቃሉ። የመጀመሪያ ጊዜ ከሆነ “እንዴት እስከዛሬ ሳላየው ቀረሁ?” የሚል የቁጭት ስሜት አይቀሬ ነው። ከዚህ በፊት አይተውት ከሆነ ደግሞ እንደ እኔ “እንዴትስ ድጋሚ እያየሁት እንደ አዲስ ያስደንቀኛል?!” የሚል የመደመም ስሜት ወደ አእምሮ ያቃጭላል።
የኔ ብዕር ላሊበላን ለመግለጽ በእጅጉ ሰንፏል። ይልቁንም ስለ ሕንጻዎቹ ታሪክ በ15ኛው ክፍለ ዘመን አካባቢ የተጻፈው የገድለ ላሊበላን ገለጻ ልዋስ። የገድሉ ጸሐፊ የላሊበላን ቤተክርስቲያናት ሲያደንቅ እንዲህ ይላል፥ “በሰማይ ከዋክብት መቁጠርን የቻለ በላሊበላ እጅ የተሰራውን መናገር ይችላል፤ እናም ለማየት የሚፈልግ ካለ ይመልከት” ሲል አስቀምጦታል።
ላሊበላ በተለይ በገና በዓል በየዓመቱ ትሞሸራለች። ቤዛ ኩሉ ሥነ-ስርዓትም መድመቂያ ቦታው እዚሁ ነው። በተለይ በቅዱስ ላሊበላ የመጀመሪያው ምድብ ስራዎቹ ቤተ መድኃኔዓለም፣ ቤተ-ማርያም እና ቤተ-መስቀል ያሉበት ቅጥር ግቢ ውስጥ ዘንድሮ ጠጠር መጣያ አልነበረም።
በማለዳው ተነስቶ ከካሜራ ባለሙያ ባልደረባው ጋር ወደ ስፍራው ያቀናው የኢቲቪ ባልደረባ ዮሃንስ ፍሰሃ ቅጥር ግቢው በምዕመኑ፣ ካህናት፣ ዲያቆናት፣ ቱሪስቶች እና ጥሪ የተደረገላቸው ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች ተሞልቶ ነበር ይለናል። እልልታ እና ዝማሬ ከፍ ብሎ ይሰማል፤ በቤተ-መድኃኔዓለም እና በቤተ-ማርያም መካከል ካለው ጋራ በልብሰ ተክህኖ ያሸበረቁ ካህናት፥ ‘ቤዛ ኩሉ ዓለም ዮም ተወልደ’ እያሉ በዝማሜ ያንቆረቁሩታል። ምዕመኑም በእልልታ ይቀበላል። እንደምንም ጉልበቴን አሰባስቤ፣ ተጋፍቼ አንድ ከፍታ ላይ ደረስኩ። ከቤተ-ማርያም ቤተክርስቲያን ፊት ለፊት ራሴን አገኘሁት። አንዳች መንፈሴን የሚጠግን ስሜት ወደ ውስጤ ዘልቆ ገባ። ‘በጎል ሰከበ በአጽርቅት ተጠብለለ ቤዛ ኩሉ ዓለም ዮም ተወልደ መድኃኔዓለም’፥ “በበረት ተኛ፣ በጨርቅ ተጠቀለለ፤ የዓለም ቤዛ መድኃኔዓለም፣ ዛሬ ተወለደ”።
ኢትዮጵያ ውብ ሀገር ናት፤ ላሊበላ ደግሞ ኢትዮጵያን ማያ ድንቅ መስኮት!
በዮሃንስ ፍሰሃ ETV
TIPS
The Wars We Still Can Stop
Ethiopia: Israel Foreign Minister Says His Country Wants to Be Part of Ethiopia’s Success
A Nation Silenced: How the 1993 Referendum Stripped All Ethiopians of Their Sea
The 1976 TPLF Manifesto: TPLF’s “Republic of Greater Tigray”
Away from the global spotlight, Eritreans are trapped in a garrison state
Testimonials of a Sudanese Intelligence Officer on the Proxy war between Sudan and Ethiopia from 1970s to early 1990s
Ethiopia-Eritrea Tension: A Volatile History that Never Truly Ended – Could Assab Become Africa’s Crimea?
“As an outlier among the five tplf leaders, I wasn’t part of the armed struggle tradition”
Former Tigray fighters say no to war
Don’t Risk Your Future: The United States Cracks Down on Illegal Immigration
Counter-Video by EBC Challenges EBS Broadcast, Sparks Public Outcry Over Alleged Misinformation
Ethiopia and Eritrea Slide Closer to War amid Tigray Upheaval
Sea Outlet Serious and Unabated Agenda for Ethiopia: Retired Lieutenant General Yohannes
Israel’s Peace With Egypt Is Starting to Crack
Egyptian, Eritrean FMs reject involvement of non-bordering countries[Ethiopia] in Red Sea security
Ethiopia, Creditors Agree on $8.4 Billion Debt Restructuring