መግቢያ
አብዛኛው የኢትዮጵያ ማህበረሰብ በግብርና ሥራ የሚተዳደር ሲሆን ግብርና ደግሞ የሀገሪቱ የጀርባ አጥንት ነው። የግብርና ሥራን ለማከናወን መሬት በጣም አስፈላጊና ዋናው ሲሆን በኢትዮጵያ ህገ-መንግስት መሰረት የገጠርም ሆነ የከተማ መሬት ባለቤትነት የመንግስትና የህዝብ እንደሆነ ተቀምጧል። የህዝብ ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ የመሬት ሀብት እያነሰ እንዲመጣ ያደረገው በመሆኑ የገጠር መሬትን ለማስተዳደርና ለመቆጣጠር እንዲያመች እራሱን የቻለ ህግ ማውጣት የግድ ይላል። የገጠር መሬትን በሚመለከት ከዚህ በፊት የተለያዩ ህጎች የወጡ ሲሆን ከሀገሪቱ አሁናዊ ሁኔታ በመነሳት ያለፉትን አዋጆች በመሻር በ2016 ዓ.ም አዲስ የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም አዋጅ በህዝብ በተወካዮች ምክር ቤት ፀድቆ በሥራ ላይ ውሏል፡፡ በዚህ ጽሁፍ በአዋጁ የተካተቱ መሰረታዊ ድንጋጌዎች በአጭሩ እንመለከታለን።
የገጠር መሬት ምንነት
የገጠር መሬት ማለት ከማዘጋጃ ቤት ክልል ውጪ ወይም አግባብ ባለው ህግ ከተማ ተብሎ ከሚሰየመው ውጪ ያለ ማንኛውም መሬት እንደሆነ በአዲሱ የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 1324/2016 አንቀፅ 2(1) ትርጓሜ ተሰጥቶታል፡፡
የገጠር መሬት የሚገኝበት ሁኔታ
በአዋጁ አንቀጽ 7 መሰረት በገጠር መሬት ላይ ያሉ የይዞታ አይነቶች የግል፣ የወል እና የመንግስት እንደሆኑ ተመልክቷል። በግብርና ሥራ እየተዳደረ ያለ ወይም ለመተዳደር የሚፈልግ ሰው የገጠር መሬት በነፃ የማግኘት መብት አለው። የገጠር መሬት ለማግኘት መሟላት ያሉባቸው ቅድመ ሁኔታዎች በአዋጁ ላይ የተቀመጡ ሲሆን የመጀመሪያው እድሜ ነው። በዚህ መሰረትም አንድ ሰው የገጠር መሬት ለማግኘት ዕድሜው 18 አመት መሆን አለበት፡፡ ነገር ግን በልዩ ሁኔታ 18 አመት ያልሞላው ልጅ እናትና አባቱ በግብርና ሥራ የሚተዳደሩ ሆነው የገጠር መሬት የሌላቸውና በህይወት የሌሉ ከሆነ የገጠር መሬት ሊያገኝ እንደሚችል በአዋጁ አንቀጽ 4(5) ላይ ተቀምጦ ይገኛል። በሁለተኛ ደረጃ የገጠር መሬት ጠያቂው በግብርና ሥራ የሚተዳደር ወይም ለመተዳደር የሚፈልግ መሆን አለበት። ከላይ ያየናቸው ሁለቱ መስፈርቶች የገጠር መሬት ለማግኘት ዋናዎቹና የግድ መሟላት ያለባቸው መስፈርቶች ናቸው። ሌላው ባልና ሚስቶች የጋራ የሆነ የገጠር መሬት የሌላቸው ከሆነ ወይም ከሁለቱ አንደኛው ብቻ የገጠር መሬት ካለው ሌላኛው ወገን የገጠር መሬት የማግኘት መብት እንዳለው በአዋጁ አንቀፅ 4(6) ተደንግጓል፡፡
በተጨማሪም መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ማህበራዊ ተቋማት እና በገጠር ልማት የሚሰሩ የግል ባለሀብቶች የገጠር መሬት የማግኘት መብት እንዳላቸው በአዋጁ ላይ ተደንጓል፡፡ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሚባሉት ቢያንስ ሁለትና ከዚያ በላይ በሆኑ ሰዎች በፈቃደኝነት የሚመሰረቱ፣ የመንግስት አካል ያልሆኑ፣ ማንኛውንም የፖለቲካ ፓርቲ ያልወከሉ፣ ለትርፍ ያልተቋቋሙ ህጋዊ አላማን ለማሳካት አግባብ ባለው ህግ ስልጣን በተሰጠው አካል ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ሲሆኑ በአንፃሩ ማህበራዊ ተቋማት የማህበረሰብ አባላትን ችግር ለመፍታት በማህበረሰቡ ፈቃደኝነት ላይ ተመስርቶ የተቋቋሙ አደረጃጀቶች እንደሆኑ ከአዋጁ አንቀፅ 2(18) እና (20) መረዳት ይቻላል፡፡
ባለይዞታዎች በገጠር መሬታቸው ላይ ስለሚኖራቸው መብት
የይዞታ መብት
ለአርሶ አደሮች፣ ለአርብቶ አደሮች፣ ለከፊል አርብቶ አደሮች እና ለሀይማኖት ተቋማት በገጠር መሬት ላይ የተሰጣቸው መብት የይዞታ መብት ነው። በገጠር መሬት አዋጅ አንቀፅ 8 ላይ እንደተቀመጠው የገጠር መሬት የይዞታ መብት በመሬቱ መጠቀምን ጨምሮ የሚከተሉትን መብቶች ያካትታል፡፡
የማከራየት መብት
የገጠር መሬት ባለይዞታ የሆነ ሰው በመሬቱ ላይ ያለውን የመጠቀም መብት በህጉ ላይ ለተቀመጠው የጊዜ ገደብ ማከራየት ይችላል። የኪራይ ዘመኑን በተመለከተ መሬቱ የሚከራየው ለአመታዊ ሰብል ከሆነ ከ10 አመት ለቋሚ ተክል ከሆነ ደግሞ ከ30 አመት ሊበልጥ አይችልም፡፡ በዚህ አዋጅ የተቀመጠው የኪራይ ዘመን ከፈተኛው ወይም የኪራይ ዘመን ጣራው በመሆኑ ክልሎች ይህንን ገደብ ሳያልፉ በሚያወጧቸው ህጎች ላይ የኪራይ ዘመን ሊያስቀምጡ ይችላሉ። የገጠር መሬት ኪራይ ውል በጽሁፍ መደረግ ያለበትና ውሉም በክልል ስልጣን በተሰጠው ተቋም መረጋገጥና መመዝገብ እንዳለበት በአዋጁ አንቀጽ 9 ላይ በእሰገዳጅነት ተደንግጎ ይገኛል።
ይዞታን በስጦታ የማስተላለፍ መብት
የገጠር መሬት ባለይዞታ የሆነ ማንኛውም ሰው ይዞታውን በቤተሰብ ህጉ መሰረት የስጋ ዘመዱ ለሆነ እንዲሁም በይጦረኛል ስምምነት ውል ለገባለት ማንኛውም ሰው በስጦታ ማስተላለፍ እንደሚችል በአዋጁ አንቀፅ 11 በግልጽ ተደንግጎ ይገኛል። የመሬት ስጦታ ለቤተሰብ ብቻ ሳይሆን ከቤተሰብ አባል ውጭ ለሆነ ማንኛውም ሰው ሊሰጥ እንደሚችል መገንዘብ ይቻላል፡፡ ነገር ግን ከቤተሰብ ውጭ ስጦታ ሲሰጥ በስጦታ ሰጭውና ተቀባዩ መካከል የጡረታ ውል ስምምነት መኖር የግድ ይላል።
የገጠር መሬት ስጦታ ውሉ አካል ጉዳተኞችን እና እድሚያቸው ለአካለመጠን ያላደረሱ ልጆችን የሚጎዳ ከሆነ የስጦታ ውሉ በህግ ፊት ተቀባይነት አይኖረውም። በሌላ በኩል በሁኔታዎች ላይ የተመሰረተ የገጠር መሬት ስጦታ ውል የይፈረስልኝ ወይም የክስ አቤቱታ የሚቀርበው በውሉ ላይ የተቀመጠው ቅድመ ሁኔታ ከተጣሰበት ወይም መጣሱን ስጦታ ሰጭው ካወቀበት ጊዜ ጀምሮ በሚቆጠር የ2 አመት ጊዜ ውስጥ ሲሆን ይህ ጊዜ ካለፈ በኋላ የሚቀርብ ክስ ተቀባይነት አይኖረውም። የገጠር መሬት ስጦታ ውል በጽሁፍ ሆኖ ውሉ በክልል ስልጣን በተሰጠው ተቋም ቀርቦ ሊረጋገጥና ሊመዘገብ ይገባል።
የገጠር መሬትን በውርስ ማስተላለፍ መብት
የገጠር መሬት ባለይዞታ የሆነ ሰው ይዞታውን በፍትሐብሔር ህጉ የውርስ ድንጋጌዎች መሰረት በኑዛዜም ወይም ያለኑዛዜ በውርስ ለማንኛውም ሰው ማስተላለፍ እንደሚችል በአዋጁ አንቀፅ 12 ላይ ተደንግጓል፡፡
መሬትን ለጋራ አራሽ የመስጠት መብት
የገጠር መሬት ባለይዞታ የሆነ ሰው ይዞታውን ለጋራ አራሽ የመስጠት መብት ያለው ሲሆን ይህም በክልሎች በሚወጡ ህጎች በሚወሰን የጊዜ ገደብና የመሬት መጠን የሚፈፀም ሆኖ ውሉም በፅሁፍ መደረግና በክልል ስልጣን በተሰጠው ተቋም ቀርቦ መረጋገጥ እንዳለበት ከአዋጁ አንቀፅ 13 ተደንግጓል፡፡
ይዞታን ከባለሀብት ጋር በጋራ የማልማት መብት
በአዋጁ አንቀፅ 14 የመሬት ባለይዞታ የሆነ ሰው በመሬቱ ላይ ያለውን የመጠቀም መብት እንደ ካፒታል መዋጮ አድርጎ ከባለሀብት ጋር በሚገባው ውል መሰረት በጋራ ማልማት የሚችል ሲሆን በባለይዞታውና በባለሀብቱ መካከል የሚደረገው ውል በፅሁፍ ሆኖ በክልል ስልጣን ባለው አካል መረጋገጥና መመዝገብ አለበት፡፡
በይዞታ የመጠቀም መብትን ለብድር ዋስትና የማስያዝ መብት
ማንኛውም የገጠር መሬት ባለይዞታ የሆነ ሰው በየክልሉ በሚወጡ ህጎች መሰረት ለሚወሰን የጊዜ ገደብ እና የመሬት መጠን የመጠቀም መብቱን ለፋይናንስ ተቋማት በማስያዣነት ለብድር ዋስትና መስጠት እንደሚችል በአዋጁ አንቀፅ 15 ላይ የተመለከተ ሲሆን ባለይዞታው በይዞታው የመጠቀም መብቱን ሌላ ሰው ለሚበደረው ብድር ዋስትና ማስያዝ ይችላል። የፋይናንስ ተቋማት የሚሰጡት የብድር መጠን የተበዳሪውን ዕቅዶች ሊያሳካ የሚችል እንዲሆን የመሬቱን እምቅ አቅም ከፍተኛ ጣሪያ መሰረት ማድረግ የሚጠበቅባቸው ሲሆን የገጠር መሬት ለብድር ዋስትና በማሳያዝ የሚደረግ የብድር ውል በጽሁፍ ተደርጎ በክልል ስልጣን በተሰጠው የወረዳ፣ ልዩ ወረዳ እና ከተማ አስተዳደር ቀርቦ መረጋገጥ እና መመዝገብ እንዳለበት በአዋጁ ላይ በአስገዳጅነት ተቀምጧል።
በአበዳሪና ተበዳሪ መካከል የሚደረገው ውል የሁለቱንም መብትና ግዴታ በግልፅ ማመልከት ያለበት ሲሆን የይዞታ መጠቀም መብት ለብድር ዋስትና የሚያዝበት ጊዜና የሁለቱ ዝርዝር መብትና ግዴታዎች ክልሎች በሚያወጧቸው ህጎች የሚወሰን ይሆናል፡፡ አበዳሪና ተበዳሪ የብድር መመለሻ ጊዜና ብድሩ በሙሉ ወይም በከፊል ባይመለስ አበዳሪ መሬቱን ሊይዝ የሚችልበትን የጊዜ ገደብ በግልጽ በውላቸው ላይ ማስቀመት ያለባቸው ሲሆን በዚህ ረገድ የሚቀመጠው የጊዜ ገደብ ከ10 አመት መብለጥ አይችልም፡፡ በዚህ መሰረትም ተዋዋይ ወገኖች በብድር ውላቸው ላይ የሚያስቀምጡት የጊዜ ገደብ 10 አመትና ከዛ በታች ይሆናል ማለት ነው። ሌላው በዚሁ አዋጅ አንቀጽ 15 ላይ እንደተቀመጠው ተበዳሪው በብድር ውላቸው ላይ በተቀመጠው ጊዜ ብድሩን ካልከፈለ አበዳሪው መሬቱን የመጠቀም፣ የማከራየት ወይም ለጋራ እርሻ የመስጠት መብት ያለው ሲሆን አበዳሪው በዋስትና የያዘውን መሬት በመጠቀም ካበደርው ገንዘብ በላይ ቢያገኝ ተበዳሪው ከተገኘው ገንዘብ ላይ ይሰጠኝ ወይም ይከፈለኝ በማለት ጥያቄ ሊያቀርብ አይችልም። በተመሳሳይ ሁኔታ አበዳሪው በዋስትና ከያዘው መሬት ላይ ካበደረው ገንዘብ በታች ጥቅም ቢያገኝ መሬቱን በውሉ ላይ ከተጠቀሰው ጊዜ ገደብ በላይ ለመያዝ ወይም የተበዳሪውን ሌላ ንብረት በመያዝ ለእዳው ማስፈፀሚያ ማድረግ እንደማይችል በአዋጁ ላይ ተደንግጎ ይገኛል።
በአበዳሪው እና በተበዳሪው መካከል በዋስትና ከተያዘው መሬት አጠቃቀም ጋር በተያያዘ አለመግባባት በመካከላቸው ቢፈጠር አለመግባባታቸውን ከፍርድ ቤት ውጭ በዕርቅ መጨረስ የሚችሉ ሲሆን በተመሳሳይ ሁኔታም ጉዳያቸውን ስልጣን ላለው ፍርድ ቤት አቅርበው ውሳኔ ማግኘት ይችላሉ።
ይዞታን የመለወጥ መብት
በአዋጁ አንቀፅ 16 መሰረት የገጠር መሬት ባለይዞታ የሆነ ሰው በአስተዳደር ወሰን ሳይገደብ ይዞታውን ከሌላ ባለይዞታ መሬት ጋር መለዋወጥ የሚችል ሲሆን በዚህ ረገድ የሚደረገው የይዞታ ልውውጥ ውል በፅሁፍ ሆኖ በክልል ስልጣን ባለው አካል መረጋገጥና መመዝገብ ይኖርበታል፡፡
በገጠር መሬት ይዞታ ላይ የተፈራን ንብረት በሽያጭ የማስተላለፍ መብት
የገጠር መሬት ባለይዞታ የሆኑ ሰዎች በመሬት ይዞታቸው ላይ በጉልበታቸው፣ በዕውቀታቸው ውይም በመፍጠር ችሎታቸው ያፈሯቸውን የማይንቀሳቀሱ ቋሚ ንብረታቸውን ማለትም ግንባታዎችን ወይም በመሬቱ ላይ ሙሉ ለሙሉ የለሙ ቋሚ ተክሎችን ባሉበት ሁኔታ የመሸጥ፣ የመለወጥ ወይም በሌላ በማናቸውም ህጋዊ መንገድ የማስተላለፍ መብት ያላቸው መሆኑን በአዋጁ አንቀፅ 17 ላይ ተደንግጎ ይገኛል። ከላይ በተቀመጠው አግባብ በይዞታው ላይ የተፈራውን ንብረት የገዛ ወይም በሌላ መንገድ ያገኘው ባለመብት የሆነ ሰው መብቱ ተፈጻሚ ሲሆን አብሮ የሚተላለፈው መሬት በክልሎች በሚወጣው ዝርዝር ህግ እና መስፈርት መሰረት ባለይዞታውን ከይዞታው በማያፈናቅል መልኩ በመሬቱ ላይ የተፈራውን ንብረት ለመጠቀም የሚያገለግል የመሬት ስፋት ብቻ መሆን ይኖርበታል።
ሌሎች መብቶች
የገጠር መሬት ይዞታ መብት ከላይ ከተገለፁት መብቶች በተጨማሪ ይዞታን ኩታ ገጠም ማድረግን፣ ይዞታን ማቀራረብን፣ የግል ይዞታን በኩታ ገጠም ማረስን የሚያጠቃልል መሆኑን ከአዋጁ መረዳት ይቻላል።
ከላይ ተገለፁት መብቶች በሙሉ የተሰጡት ለአርሶ አደሮች፣ ለአርብቶ አደሮች፣ ለከፊል አርብቶ አደሮች እና ለሀይማኖት ተቋማት ሲሆን በአንፃሩ በአዋጀ አንቀፅ 5(3) መሰረት መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በገጠር መሬት ላይ ያላቸው መብት የመጠቀም መብት ብቻ ሲሆን የማከራየት፣ ለጋራ እርሻ መስጠት፣ የማውረስ፣ በስጦታ የማስተላለፍ፣ ከባለሀብት ጋር በጋራ የማልማት፣ ለብድር ዋስትና የማስያዝ መብት የላቸውም። ነገር ግን ማህበራዊ ተቋማት ከመጠቀም መብት በተጨማሪ ይዞታቸውን ከማውረስ እና በስጦታ ከማስተላለፍ ውጭ ለባለይዞታዎች የተሰጡ ሁሉም መብቶች እንዳላቸው በአዋጁ አንቀፅ 5(4) ተመልክቷል፡፡ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ማህበራዊ ተቋማት የገጠር መሬት የሚያገኙት ክልሎች በሚያወጧቸው ህጎች መሰረት ሆኖ አላማቸውን ለማሳካት የሚውል መሆን እንዳለበት ጭምር በአዋጁ ተደንግጓል፡፡
በገጠር መሬት ላይ የሚነሱ ክርክሮች የሚፈቱበት አግባብ እና የይርጋ ጊዜ
ከገጠር መሬት ጋር በተያያዘ በደል ደርሶብኛል የሚል ወገን ጉዳዩን ከተከራካሪው ጋር በስምምነት ወይም ተከራካሪዎቹ እራሳቸው በሚመርጧቸው ሽማግሌዎች መፍታት የሚችሉበት ሁኔታ በገጠር መሬት አዋጁ አንቀፅ 40 ላይ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ በስምምነት መፍታት ያልፈለገ ወገን ደግሞ ስልጣን ላለው የክልል ፍርድ ቤት ክስ በማቅረብ ጉዳዩ እንዲፈታለት ማድረግ ይችላል። የአስተዳደር አካላት በገጠር መሬት ጉዳይን በተመለከተ በህግ በተሰጣቸው ተግባራት ላይ የሚነሱ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን ለማየት በልዩ ሁኔታ የተሰጣቸው ስልጣን እንደተጠበቀ ሆኖ ከገጠር መሬት ጋር ተያይዞ የሚነሱ አለመግባባቶች ከሽምግልናና ከፍርድ ቤት ውጭ በሌላ አካል መታየት አይችሉም።
ሌላው መነሳት ያለበት ጉዳይ ክስ የማቅረቢያ ጊዜ ወይም ይርጋ ነው። በገጠር መሬት አዋጅ አንቀጽ 64 ላይ እንደተቀመጠው ይዞታዬ ያለአግባብ በሌላ ሰው ተወስዶብኛል የሚል ሰው መብቱን መጠየቅ ከነበረበት ወይም ካወቀበት ጊዜ ጀምሮ በ15 (አስራ አምስት) ዓመታት ውስጥ ክስ ማቅረብ ካልቻለ መብቱ በይርጋ ይታገድበታል። በአንፃሩ የመንግስት ወይም የወል ይዞታን በህገ-ወጥ መንገድ የያዘ ማንኛውም ሰው የያዘውን ይዞታ እንዲለቅ ክስ ሲቀርብበት መሬቱን ለብዙ ጊዜ ይዤዋለሁ በማለት ይርጋን እንደመከላከያ ማቅረብ አይችልም።
የወንጀል ተጠያቂነት
ሌላው በገጠር መሬት አዋጁ ላይ የተካተተው ጉዳይ የወንጀል ተጠያቂነት ሲሆን በአዋጁ አንቀጽ 62 እንደተቀመጠው የግል፣ የወል ወይም የመንግስት ይዞታን በህገ-ወጥ መንገድ የወረረ ማንኛውም ሰው ከ1(አንድ) ዓመት እስከ 5(አምስት) ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ወይም ከብር 30,000(ሰላሳ ሺ) እስከ ብር 100,000(መቶ ሺ) በሚደርስ መቀጮ ወይም በሁለቱም ሊቀጣ ይችላል። በግል፣ በወል ወይም በመንግስት ይዞታ ላይ ጉዳት ያደረሰ ሰው ደግሞ ከ3(ሶስት) አመት እስከ 7(ሰባት) አመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ወይም ከብር 50,000 (ሀምሳ ሺ) እስከ ብር 150,000(አንድ መቶ ሀምሳ ሺ) በሚደርስ መቀጮ ወይም በሁለቱም ሊቀጣ ይችላል። ማንኛውም ባልተፈቀደ ቦታ ላይ ማንኛውንም ግንባታ የሰራ ወይም እንዲሰራ የፈቀደ ሰው ክብር 25,000 (ሀያ አምስት ሺ) እስከ ብር 50,000(ሀምሳ ሺ) በሚደርስ መቀጮ ወይም ከ1(አንድ) ዓመት እስከ 3(ሶስት) አመት በሚደርስ እስራት ወይም በሁለቱም ይቀጣል። በተጨማሪም ከመሬት አጠቃቀም እቅድ ውጪ ይዞታውን ጥቅም ላይ ያዋለ ሰው ከብር 20,000 (ሀያ ሺ) እስከ ብር 50,000(ሀምሳ ሺ) በሚደርስ መቀጮ ወይም ከ1(አንድ) አመት እስከ 3(ሶስት) አመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ወይም በሁለቱም ይቀጣል፡፡
በሌላ በኩል ሀሰተኛ የመሬት ይዞታ ማስረጃ ያቀረበ ባለይዞታ እንዲሁም ማስረጃ የሰወረ ወይም የተሳሳተ ማስረጃ የሰጠ ባለሞያ ከ1(አንድ) ዓመት እስከ 3 (ሶስት) ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ወይም ከብር 10,000(አስር ሺ) እሰከ ብር 25,000(ሀያ አምስት ሺ) በሚደርስ መቀጮ ወይም በሁለቱም ሊቀጣ የሚችል ሲሆን ማንኛውም ሰው መሬት የገዛ ወይም የሸጠ እንደሆነ ከ1(አንድ) ዓመት እስከ 5(አምስት) ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ወይም ከብር 100,000(አንድ መቶ ሺ) እስከ ብር 200,000(ሁለት መቶ ሺ) በሚደርስ መቀጮ ወይም በሁለቱም ሊቀጣ እንደሚችል በአዋጁ ላይ ተደንግጎ ይገኛል። በንቃተ ህግ ትምህርትና ስልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ
የፍትህ ሚኒስቴር