ተመራጩ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ዋይት ሐውስ በመመለሻቸው ዋዜማ፥ በመጀመሪያው የሥልጣን ቀናቸው በርካታ ትዕዛዞችን ለማስተላለፍ እንደሚያስተላልፉ ገልፀዋል።
በዋሺንግተን ዲሲ በሺዎች ለሚቆጠሩ ደጋፊዎቻቸው ንግግር ያደረጉት ትራምፕ፥ ቃለ መሐላ በፈፀሙ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ “በታሪካዊ ፍጥነት እና ጥንካሬ” እንደሚንቀሳቀሱ ተናግረዋል።
በሚቀጥሉት አራት ዓመታት ሊሠሯቸው ያሰቧቸውን ተግባራት ዘርዝረው ካበቁ በኋላ፤ ባለፈው ኅዳር ወር ዲሞክራቶችን በምርጫ በመርታታቸው ደስታቸውን ሲገልፁ ተስተውለዋል።
ሪፐብሊካኑ ፖለቲከኛ ያላቸውን ፕሬዚዳንታዊ ኃይል ተጠቅመው ስደተኞችን በገፍ ለማባረር፣ የተፈጥሮ ጥበቃ ላይ የሚያተኩሩ መመሪያዎችን ለመቀነስ እና የስብጥር (ዳይቨርሲቲ) ፕሮግራሞችን ለማስቆም ቃል ገብተዋል።
“ቅድሚያ የምንሰጠው ለአሜሪካ ነው። እሱ ደግሞ ነገ ይጀምራል” ሲሉ ለደጋፊዎቻቸው ተናግረዋል። አክለውም፥ “ነገ ቴሌቪዥን ስትመለከቱ እንደምትዝናኑ እርግጠኛ ነኝ” ብለዋል።
እንደ ቢቢሲ ዘገባ፥ ትራምፕ ከበዓለ ሲመታቸው በኋላ 200 ገደማ ትዕዛዞች ላይ ፊርማቸውን እንደሚያሰፍሩ ይጠበቃል። አንዳንዶቹ ትዕዛዞች እንደ ሕግ የሚቆጠሩ ሲሆኑ፤ ሌሎቹ ደግሞ ፕሬዚዳንታዊ መመሪያዎች ናቸው።
“እኔ ሥልጣን በያዝኩ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ የባይደን አስተዳደር ያስተላለፋቸው ትዕዛዞች ይሰረዛሉ” ብለዋል ትራምፕ።
አክለውም፥ የሰው ሰራሽ ክህሎትን ዕድገት የሚያፋጥን እንዲሁም ኢሎን መስክ የሚመራው ዶጅ የተባለው መሥሪያ ቤት እንዲቋቋም የሚወጣ ትዕዛዝ እንደሚፈርሙ አሳውቀዋል።
በአውሮፓውያኑ 1963 ስለተገደሉት ጆን ኤፍ ኬኔዲ መረጃዎችን እንደሚለቁ፤ ወታደራዊ ኃይሉን ‘አይረን ዶም’ እንዲሠራ እንደሚያዙ እንዲሁም ብዝሀነት፣ እኩልነት እና አካታችነት የሚባሉ ፖሊሲዎችን ከጦር ሠራዊቱ እንደሚያስወግዱም ቃል ገብተዋል።
ትራምፕ ለደጋፊዎቻቸው ባደረጉት ንግግር፥ ፆታ የቀየሩ (ትራንስጄንደር) ሰዎች በሴቶች ስፖርት እንዳይሳተፉ እንደሚያደርጉ እና የትምህርትን ሥልጣን ለአሜሪካ ግዛቶች አሳልፈው እንደሚሰጡ ተናግረዋል።
“እናንተን በጣም ደስተኛ የሚያደርጉ ብዙ ትዕዛዞች ማየታችሁ አይቀርም” ብለዋል።
የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ሥልጣን ሲጨብጡ በመጀመሪያ ቀናቸው ትዕዛዝ ማስተላለፋቸው የተለመደ ቢሆንም፤ ትራምፕ በቁጥር በርካታ ትዕዛዞችን ለማስተላለፍ ቃል ገብተዋል። አብዛኛዎቹም በፍርድ ቤት ሙግት እንደሚቀርብባቸው ይጠበቃል።
ትራምፕ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕጋዊ ወረቀት የሌላቸው ስደተኞችን ከአሜሪካ እንደሚያባርሩም ዝተዋል። ነገር ግን የስደት ተንታኞች የትራምፕ ዕቅድ ብዙ ሕጋዊ፣ የሎጂስቲክስ፣ የገንዘብ እንዲሁም የፖለቲካ አንድምታ እንዳለው ይናገራሉ።
Via Amir Emam