የትግራይ ታጣቂ ኃይል መሪዎች የጌታቸው ረዳን አስተዳደር ይፍረስ አሉ፤ “የውጭ ኃይል ” ባሏቸው ላይ እርምጃ የመውሰድ አቅም አንዳላቸው አወጁ
ለአምስት ቀን በዝግ መምከራቸውን በመጠቆም መግለጫቸውን ያሰራጩ አካላት እንዳሉት፣ በትግራይ ያሉትን ታጣቂ ኃይሎች የሚመሩት የቀድሞ የትግራይ ተወላጅ ከፍተኛ መኮንኖች በአቶ ጌታቸው የሚመራውን የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር እንዲፈርስ ወስነዋል።
ይኸው በትግርኛ የተሰራጨውና ቢቢሲ ተርጉሞ ለዜና ያበቃው የቀድሞ መኮንኖች መግለጫ ዶክተር ደብረጽዮን የሚመሩትን የትህነግ አንድ ቡድን በይፋ የሚደግፍ ነው።
የጦር መኮንኖቹ ውሳኔ ጦርነት በሁሉም አቅጣጫ የከፋ ቀውስ ውስጥ የከተታትን ትግራይ ወዴት እንደሚያመራት ይህ ነው ብለው ለጊዜው የሚናገሩ ባይኖሩም፣ ዜናው በርካቶችን እንዳስጨነቀ ከየአቅጣቻው የሚሰሙ መረጃዎች ያስረዳሉ።
የትግራይ ክልል ታጣቂዎችን የሚመሩት የቀድሞ ከፍተኛ መኮንኖች ” የእነ ደብረጽዮን / ትህነግ የትግራይን ጊዜያዊ አስተዳደር ለማሻሻል ያሳለፈው ውሳኔ በአስቸኳይ ተግባራዊ እንዲሆን ” አዘዋል። ” ሠራዊቱን ወክለው በጊዜያዊ አስተዳደሩ የካቢኔ አባላት የሆኑትን ግለሰቦች በመገምገም እምነት የሚጣልባቸው ያልሆኑትን በሌሎች እንዲተኩ ወስነናል ” ሲሉም አስታውቀዋል።
በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት የፌደራል መንግስት በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ ውክልና እንደሚኖረውና መሪውም የሚወሰነው በጠቅላይ ሚኒስትሩ በመሆኑ የታጣቂዎቹ አመራሮች ያወጡትን መግለጫና ፖለቲካዊ ውሳኔ አስመልክቶ ከመንግስት ወገን ለጊዜው የተባለ ነገር የለም። አቶ ጌታቸው የሚመሩት አስተዳደርም ይህ እስከታተመ ድረስ በተመሳሳይ ምንም ሲል አልተደመጠም።
በትግራይ ክልል ያሉ የበላይ ወታደራዊ ኃይል አመራሮች እንደሆኑ የገለጹ መኮንኖች ዛሬ መግለጫ ሲሰጡ የአቶ ጌታቸውን አስተዳደር “የተዳከመ” በማለት ዘልፈውታል። አስከትለውም ጊዜያዊ አስተዳደሩ ተነስቶ በሌላ እንዲዋቀር መወሰናቸውንም አስታውቀዋል።
” የጊዜያዊ አስተዳደሩ እንደ አዲስ እንዲዋቀር ውሳኔ አሳልፈናል ” ያለው መግለጫቸው ሠራዊቱን ወክለው በጊዜያዊ አስተዳደሩ የካቢኔ አባላት የተካተቱ ግለሰቦች በመገምገም እምነት የሚጣልባቸው በሌሎች እንዲተኩ መወሰኑን ገልጸዋል። እነዚህ አካላትም የራሳቸው ተከታይና ታጣቂ፣ እንዲሁም ደጋፊ የህብረተሰብ ክፍል ስላላቸው ወደ ተግባር ሲገባ አስጊ ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል ስጋት የገባቸው እየወተወቱ ነው።
በአሁኑ ወቅት በትግራይ ውስጥ ያለው ችግር ፖለቲካዊ መፍትሄ የሚሻ እንደሆነ መኮንኖቹ ገልጸዋል። አያይዘውም ” ማንኛውም ነገር ከትግራይ ሠራዊት አቅም በላይ አይደለም ይህንን ሰበብ በማድረግ የሚደረግ ጣልቃ ገብነትን አንቀበልም ” ሲሉም በስም ባይጠቅሱም የፊደራል መንግስቱን ነካክተዋል።
የፖለቲካ መፍትሄ ያሉትን በይፋ በዝርዝር ባያቀርቡም፣ በትግራይ ውስጥ ያሉ የታጣቁ ኃይሎች ከአቅማቸው በላይ የሆነ ነገር እንደሌለ አመልክተው ክልሉን ለቀው እንዲወጡ ጠይቀዋል። ይህን ሲሉ መከላከያን ይሁን፣ በወልቃይት ጠገዴ ያለውን ሚሊሻ ይሁን የሻዕቢያ ወራሪ ኃይል በግልጽ አላስታወቁም።
” በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት የተቋቋመው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ኃላፊነቱን በአግባቡ አልተወጣም የሌሎች መጠቀሚያ ሆኗል ” የሚል ክስም አቅርበዋል። “ሌሎች” ያሎዋቸውን አልዘረዘሩም።
” በጊዜያዊ አስተዳደሩ ቁልፍ ሥልጣን የነበራቸው አመራር እና አባላት ከተሰጣቸው ተልዕኮ ውጪ የሕዝብን ጥቅም ወደ ጎን በመተው ክህደት በመፈጸም የውጭ ኃይል መሣሪያ ሆነዋል” ብሏል። መኮንኖቹ “የውጭ ኃይል” ያሉዋቸውን በስም አልጠሩም።
በሕዝብ ጥቅም ላይ ስለደረሰው ጉዳትም ሆነ ” የውጭ ኃይል ” ያሉት አካል ማንነትን በተመለከተ በግልጽ የተናገሩት ነገር ባይኖርም ዶክተር ደብረጽዮን በተመሳሳይ አቶ ጊታቸው የሚመሩትን ቡድን “ከሃዲ፣ የትግራይን ጥቅም አሳልፎ የሰጠ፣ ” ወዘተ በማለት ሲያወግዙ ከነበረው ጋር ተመሳሳይ ሆኗል። ይህም መኮንኖቹ ከጀርባ ሆነው ድጋፍ ያደርጉ እንደነበር ሲገለጽ የነበረውን በገሃድ ያረጋገጠ ሆኗል።
እነዚህ ራሳቸውን ከአገር መከላከያ የለዩ የቀድሞ ከፈተኛ መኮንኖች በመግለጫቸው ጊዜያዊ አስተዳደሩ ደጋግመው ተችተዋል። ” የስልጣን ዘመኑን ለማራዘም እየሞከረ ነው ” ሲሉም ከሰውታል። ይህን ባሉበት አግባብ ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ለተካሄደው (በእነ ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል ቡድን) የትህነግ 14ኛ ጉባኤ እውቅና በመስጠት በጉባኤው ውሳኔ መሠረት የጊዜያዊ አስተዳደር የአመራሮች ለውጥ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል። “ጊዜያዊ አስተዳደሩን በሠራዊቱ ላይ የሚካሄደውን የስም ማጥፋት ዘመቻን መከላከል አልቻለም ” በሚል በክህደት ወንጅለውታል።
መኮንኖቹ ዕውቅና የሰጡትን ጉባኤ የምርጫ ቦርድ እንዲሁም ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጌታቸው ረዳና ሌሎች የትህነግ ከፍተኛ አመራሮች እውቅና እንደነፈጉት የሚታወስ ነው። አሁንም በቀነ ገደብ ላይ እንዳለ አይዘነጋም።
አመራሮቹ በደብረፅዮን (ዶ/ር) የሚመራው የህወሓት ቡድን በጊዚያዊ አስተዳደር ያለው 50+1 ድርሻ እንዲረከብ እንደሚፈልጉ ተናግረዋን። ከዚህ በተጨማሪ በትግራይ ያሉ ታጣቂዎች በትግራይ ሰላም እና ፀጥታ ሴክሬታሪያት ስር እንዲሆኑ፣ ከዚህ ውጪ በሆነ ላይ ግን እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል።
ዛሬ መግለጫ የሰጡት የትግራይ ኃይሎች ከፍተኛ ወታደራዊ አመራር እንደሆኑ የገለጹት መኮንኖቹ በግልጽ ለደብረፅዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ቡድን ያደላ አቋም ይዘዋል ፤ ይህ ደግሞ አሁን ላይ በክልሉ ያለውን ሁኔታ አስፍሪ አድርጎታል የሚሉ አስተያየቶች ሲሰጡ መመልከት እንደቻለ ቢቢሲ አመልክቷል።
ትህነግ በአቶ ጌታቸው ረዳ እና ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ለሁለት ተከፍሎ ላለፉት ወራት እጅግ በጣም በከረረ የመግለጫ እና የሚዲያ ምልልስ ተጠምደው መቆየታቸው ይራወሳል። የታጣቂ ኃይሎች እስካሁን በክልሉ ጉዳይ በይፋ አቋማቸውን ሲገልጹ አልታዩም ፤ የዛሬው ለደብረፅዮን (ዶ/ር) ህወሓት ያደላ የድጋፍ መግለጫ ጉዳዩ ወዴት ያመራ ይሆን ? የሚል ስጋት እንደደቀነ ቢቢሲ ታዛቢዎችን ጠቅሶ ምልከታውን አጋርቷል።
ትግራይ በርካቶች ያለቁበትን እጅግ አስከፊ የሆነ ጦርነት አስተናግዳ ከህመሟ ገና ያላገገማች ሲሆን አሁን በክልሉ ያለው መካረር መፍትሄ አለማግኘቱ ብዙዎችን አሳዝኗል።
ለሃያ ሁለት ዓመታት የትግራይን ህዝብና የአገር ድንበር ሲተብቅ በኖረው የአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ በግፍ ጥቃት ከተፈጸመ በሁዋላ በተከታታይ በተካሄደው ጦርነት አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ የትግራይ ተወላጆች ህይወት እንደተቀጠፈ የትግራይ ተፎካካሪ ፓርቲዎችና ጥናት ያደረጉ ማስታወቃቸው አይዘነጋም።
ሻዕቢያም ይህንኑ አጋጣሚ ተጠቅሞ በቃላት ሊገለስ የማይችል ግፍና ውንብድና የፈጸመባት ትግራይ አሁን ዳግም ወደ ጦርነት እንዳትመለስ ፓርቲያርኩም የተማጽኖ ደብዳቤ ልከዋል።
ዶክተር ደብረጽዮንን “የጥፋት አንቴና” ሲል የሚጠራቸው የር ዕዮት ሚዲያ ባለቤት ቴዎድሮስ፣ “ አንሬና ሲግናል እንደሚስብ፣ ደብረርጽዮንም የጥፋትና የጦርነት ሲግናል ይስባል…” ሲል ክፉኛ ትችት ሲሰነዝር “ ያንን ሁሉ ሕዝብ አስጨርሰው በተትኛው ሞራላቸው ነው ህዝብ ፊት የሚቀርቡት” በማለት ነበር። እሳቸው ያልመሯት ትግራይ ቀጣይ እጣ ፈንታዋ ምን ይሆን?