የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬው እለት ባካሄደው 14ኛ መደበኛ ጉባዔ የነዳጅ ውጤቶችን ግብይት ሥርዓት ለመደንገግ የተዘጋጀ አዋጅን በሁለት ተቃውሞ፣ በአንድ ድምፀ ተዓቅቦና በአብላጫ ድምጽ አፅድቋል፡፡ የነዳጅ ምርቶችን ከመሸጫ ዋጋ በላይ በሚሸጡ ነጋዴዎች ላይ እስከ 500 ሺህ ብር የሚደርስና ሲደጋጋም ከሶስት ዓመት ጀምሮ በእስር እንዲቀጡ የሚያስገድድ አዋጅ ጸደቀ።
የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ አይሻ ያህያ÷ ማደያዎች ያልተቆራረጠ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስገደድ ነዳጅ በማደያ ውስጥ እያለ የሽያጭ አገልግሎት ያለማቋረጥ የሚል ድንጋጌ በአዋጁ መካተቱን ገልጸዋል፡፡
የተሸከርካሪውን ጉዞ በቴክኖሎጂ ለመከታተል እንዲቻል ማንኛውም የነዳጅ ውጤቶች አጓጓዥ ተሸከርካሪ ጂፒኤስ የመግጠም ግዴታ እንዳለበት በአዋጁ ተደንግጓል ብለዋል፡፡
በአዋጁ መሠረት ከመሸጫ ዋጋ በላይ በመሸጥ ለሚፈጸም የመጀመሪያ ጥፋት ከሶስት መቶ ሃምሳ ሺህ እስከ አምስት መቶ ሺህ ብር ያስቀጣል። ድርጊቱ በተደጋጋሚ ከተፈጸመ የገንዘብ መቀጮው ላይ ከሶስት ዓመት እስከ አምስት ዓመት የሚደርስ የእስር ቅጣት እንደሚኖር አዋጁ ያትታል።
የነዳጅ ውጤቶች ካላቸው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳ አንጻር ስትራቴጂክ ምርቶች በመሆናቸው አቅርቦታቸው፣ ክምችታቸው፣ ስርጭታቸውና ደህንነታቸው ዓለም ዓቀፍ ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን የሚያስችል በመሆኑ አዋጁ እንደተዘጋጀ ተናግረዋል፡፡
የነዳጅ ውጤቶች ከአስመጪ ጀምሮ እስከ ተጠቃሚው ድረስ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ቀልጣፋ፣ ፍትሃዊና ተደራሽ የአቅርቦትና ስርጭት እንዲሁም በነዳጅ ውጤቶች የግብይት ሰንሰለት ውስጥ እየታዩ ያሉ ህገ-ወጥ ተግባራትን ለመቆጣጠር የሚያስችል ምቹ ሁኔታን መፍጠር በማስፈለጉ አዋጁ ወጥቷል ብለዋል።
በአዋጁ መሰረት “የነዳጅ ውጤቶችን ከተፈቀደው ቦታ ውጪ ያከማቸ፣ ሊሸጥ ከሚገባው ሰው፣ ቦታ እና የግብይት ሥርዓት ውጪ ሲሸጥ የተገኘ” ማንኛውም ሰው፤ ከሶስት አመት እስከ አምስት አመት በሚደርስ እሥራት እና ከ350 ሺህ እስከ 500 ሺህ ብር በሚደርስ መቀጮ ይቀጣል። ከዚህ በተጨማሪም የተያዘው የነዳጅ ውጤት እንደሚወረስ አዋጁ ያትታል።የነዳጅ ምርቶችን “ሆን ብሎ” ከባዕድ ነገሮች ጋር በመቀላቀል ለግብይት ማቅረብ ከአምስት አመት እስከ ሰባት አመት በሚደርስ እሥራት እና ከ350 ሺህ እስከ 500 ሺህ ብር እንደሚያስቀጣ አዋጁ ላይ ሰፍሯል።
የነዳጅ እና ኢነርጅ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰሀርላ አብዱላሂ በበኩላቸው÷ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን አሁን ላይ እየታዬ ያለውን ህገ-ወጥነት ለመቆጣጠር ጠበቅ ያለ ህግ እንደሚያስፈልግ የጋራ መግባባት ላይ ደርሰናል ብለዋል፡፡
መንግስት በሚያስቀምጠው ታሪፍ አለመሸጥ በዘርፉ እየተስተዋሉ ካሉ ችግሮች ውስጥ አንዱ መሆኑን በመግለጽ ይሄም አዋጁ ላይ በግልጽ ድንጋጌ እንዲቀመጥ ተደርጓል ነው ያሉት፡፡
የምክር ቤት አባላትም መንግስት ማደያዎች ወደገበያ ለመግባት የሚያደርጉትን ሂደት ቀላል ማድረግ ላይ ትኩረት ቢያደርግ ችግሩን መፍታት እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡
ቀደም ሲል የነበረው አዋጅ 838/2006 ከነዳጅ ውጤቶች ቁጥጥር ጋር ተያይዞ ክፍተቶች እንደነበሩበት የተገለጸ ሲሆን÷ ይህ አሁን የፀደቀው አዋጅ በነዳጅ ግብይት ላይ የሚከሰተውን ብክነትና በነዳጅ ዘርፉ የሚታየውን ችግር ለመቅረፍ ድርሻው ከፍተኛ መሆኑ ተመላክቷል፡፡