በኢትዮጵያ በብሄር “ነጻ አውጪ” ስም እዛም እዚህም የፈሉ አላገቱም? አግተው አልተደራደሩም? ገንዘብ ከተቀበሉ በሁዋላ ሬሳ አልላኩም? ሰው ገድለው ከሰቀሉ በሁዋላ በድንጋይ አልወገሩም፣ ብር ካልተሰጠን እያሉ የስልክና የቪዲዮን መልዕክት አልላኩም? በጅምላና በተናጠል ምስኪኖችን አላፈኑም? ዛሬ ልክ ከሊቢያ እንደተለቀቀው ዓይነት የጣርና የስቃይ ማስፈራሪያ እዚሁ በወገን ምድር፣ በወገን ተፈጽሞ ለወገን አልተላከም? ይህን ዓይነት አስነዋሪ የማፍያ ተግባር “ትግል ነው” ብለው ያደነቁ አልነበሩም? ለፖለቲካ ገበያ አውለው በህዝብ ስቃይ ዳንኪራ ሲወርዱ የነበሩ ሚዲያዎችና “አክቲቪስት” ተብዬዎች አላየንም … ዛሬ ላይ ከሊቢያ የሚወጡ የጣር ድምጾች በአገራችን በብዛት አለ። እንዲያድግ እየተበረታታ ነው። በትግል ስም ንግድ፣ ይዞ መገኘት፤
“አካሄዱ ገብቶናል” የሚሉ ቡድኖችና ግለሰቦች ኢትዮጵያ እንደ ሊቢያ እንዳትሆን እያሉ በተደጋጋሚ ሲናገሩ ቀልድ የሚመስላቸው ተሳስተዋል። አሁን ኢትዮጵያ ላይ እንዲሆን የሚፈለገውና እየተሰራበት ያለው ይህን የሊቢያን ጣር ኢትዮጵያ ላይ ለመትከል ነው።
በሊቢያ መንግስት ከወደቀ በሁዋላ አሁን ድረስ የሰከነ ነገር የለም። ጎጠኞች ጠብመንጃ ይዘው የጎበዝ አለቃ ሆነውባታል። በጡንቻቸው መጠን የሚለያዩ የጎበዘ አለቆች ልክ እኛ አገር አሁን እንደሚታየው ስፍራ ለይተው ራሳቸውን አንግሰዋል። ይዘርፋሉ። ቀረጥ ይጥላሉ። ያግታሉ። አግተው ገንዘብ ይደራደራሉ። ይረሽናሉ። ወዘተ…
ኢትዮጵያም አሁን የጎበዝ አለቆች በየስርቻው አገንግነዋል። ራሳቸውን የቀቡም አሉ። ራሳቸውን መለኮታዊ አድርገው ከክርስቶስ አዳኝነት ጋር ያመሳሰሉ ተነስተዋል። ሲያሻቸው ኃይማኖተኛ፣ ሲቀጥል “ብሄር አንደኛ” የሚሉ፣ ሲከሽፉ “ኢትዮጵያ” ለማለት የሚዳዳቸው እዛም እዚህም እየተክለፈለፉ ነው። በየስፍራው ማገት፣ አግቶ መደራደር፣ በግደል፣ መረሸን፣ ህዝብ ላይ ቅጣት መጣል፣ የህዝብ ንብረት መብላትና ማውደም … ኢትዮጵያ ውስጥ ዘመናዊው ትግል ከሆነ ሰነባብቷል። ባጭሩ ልክ እንደ ሊቢያ የሰፈርና የቄዬ ንጉሶች ፈልተዋል።
በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በትግራይ በየቀበሌው የተነሱት የጎበዝ አለቆች፣ እነዚህኑ አለቆች የለውጥ ሃዋሪያ አድርገው የሚሰብኩ የተገዙ የሚዲያ ውስጥ አለቆች አንድ ላይ ኢትዮጵያን ወደ ለየለት ሆሊጋሊዝም እየሾፈሩዋት ነው። እየተቀባበሉ በሚከፈላቸው ልክ የጎብዘ አለቆችን፣ የመንደር ጁቴዎችን እያገነኑ ፣ ይህ እንዳይሆን ደሙን እየሰጠ፣ ህይወቱን እየገበረ ያለውን መከላከያን እያንኳሰሱ አገር አልባ እንድንሆን ከሻዕቢያና ሻዕቢያን ለሚልኩ እያገለገሉ ነው። በነገራችን ላይ ከስር ታሪኳ የቀረበው ናሒማን የነዚህ ሁሉ ሰለባ እንደሆነች ልብ ይሏል።
በትግራይ ሲፈጸም የነበረው፣ እየተፈጸመ ያለው፣ በማራ ክልል የሚፈጸመው ግድያ፣ ዝርፊያ፣ እገታ፣ በኦሮሚያ እየሆነ ያለው ተመሳሳይ ግፍ ለምን ይደበቃል? የአገራችን የመብት ተቆርቋሪዎች፣ የመብት ተሟጋቾች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና አመራሮች፣ የኃያማኖት አባቶችና ተቋሞቻቸው፣ ምሁራኖች፣ ለእውነት አድረናል የሚሉ ዜጎች፣ በተለይ በተለይ መረጃው በደንብ ያላችሁ ሚዲያዎች ስለምን እውነቱን አታወጡም? በማስረጃ አስደግፋችሁ ለምን አታጋልጡም?
ቢቢሲ ሰሞኑን በቪዲዮ ስትሰቃይ የምትታየዋን ናሆንሚን አስመልክቶ ቤተሰቧን አናግሮ የሚከተለውን ዘግቧል። ለሪፖርቱ ምስጋና ይገባዋል።
በሊቢያ ታጣቂዎች በርካታ ስደተኞችን አግተው የማሰቃየት ድርጊት ሲፈጽሙባቸው የሚያሳዩ ቪድዮዎች እና ፎቶዎች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ተሠራጭተው መነጋገሪያ ሆነዋል።
ከእነዚህ ታጋቾች መካከል ነሒማ ጀማል አንዷ ናት። ነሒማ ከኦሮሚያ ክልል ሻሸመኔ በመሰደድ ነው ወደ ሊቢያ ያቀናችው።
‘ሬፊዩጂስ ኢን ሊቢያ’ የተሰኘው ተቋም በኤክስ ገፁ እንዳስታወቀው ነሒማ እና ሌሎች ስደተኞች ኩፍራ በምትባለው የሊቢያ ግዛት በታጣቂዎች ቁጥጥር ሥር ይገኛሉ።
ነሒማ በፎቶዎቹ እና በቪዲዮዎች ላይ አፏ በጨርቅ ተለጉሞ ስቃይ ሲደርስባት ትታያለች።
የነሒማ ቤተሰቦች ለቢቢሲ እንደተናገሩት ቪዲዮዎች እና ፎቶዎች ተልኮላቸው የማስለቀቂያ ገንዘብ እንዲከፍሉ ማስጠንቀቂያ ደርሷቸዋል።
የነሒማ እህት ኢፍቱ ጀማል፤ ነሒማ ከስምንት ወራት በፊት ነበር ከሻሸመኔ ከተማ የ11ኛ ክፍል ትምህርቷን አቋርጣ ወደ ሊቢያ የተሰደደችው ስትል ለቢቢሲ ትናገራለች።
“ፎቶዎች እና ቪዲዮዎች ይልኩልናል። ስትሰቃይ ያሳዩናል። የድምፅ መልዕክትም ልከውልናል። እህታችን ‘ገንዘብ ላኩላቸው ካልሆነ ይገድሉኛል’ ስትል ይሰማል።”
ነገር ግን ኢፍቱ እንደምትለው ቤተሰቡ አጋቾቹ የጠየቁትን ገንዘብ የመላክ አቅም የለውም።
ሬፊዩጂስ ኢን ሊቢያ የተባለው በሊቢያ የሚገኙ ስደተኞችን ጉዳይ የሚከታተለው ተቋም እንደሚለው የ20 ዓመቷ ነሒማ ጀማል ባለፈው ግንቦት ሊቢያ ከገባች ከቀናት በኋላ ነው በታጣቂዎቹ እጅ ውስጥ የገባችው።
በቁጥጥር ሥር ከዋለች በኋላ ስቃይ ሲደርስባት እና ስትደበደብ የሚያሳዩ ፎቶዎች እና ቪዲዮዎች ለቤተሰቦቿ ተልከዋል።
ኢፍቱ እንደምትለው ቤተሰቡ የተጠየቀውን ገንዘብ ለማሰባሰብ እርዳታ ቢጠይቅም እስካሁን ድረስ ሊሞላላቸው አልቻለም።
ቤተሰቡ የነሒማን ድምፅ ከሰማ ሁለት ሳምንት እንዳለፈው እህቷ ኢፍቱ ለቢቢሲ ትናገራለች። “ገንዘቡን ካላገኘን በቀር እንዳንደውልላቸው አስጠንቅቀውናል። በጣም ተጨንቀናል።”
ሬፊዩጂስ ኢን ሊቢያ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ስቃዩና ማስፈራራቱ እንደተጠናከረ እና ይህ ደግሞ ቤተሰቦች ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ እንደሆነ ይገልጻል።

አጋቾቹ ለነሒማ ማስለቀቂያ የጠየቁት ገንዘብ 6 ሺህ ዶላር ነው። የነሒማ ቤተሰብ ይህን ገንዘብ ለማሰባሰብ የሚችለውን ሁሉ እያደረገ ይገኛል።
ለነሒማ ቤተሰብ የተላኩ ቪዲዮዎች በርካታ ስደተኞች በአሰቃቂ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ያሳያሉ።
ነሒማ እጅና እግሯ ተጠፍሮ፤ አፏ በጨርቅ ታፍኖ ትታያለች። ስቃይ ሲደርስባት እና ደም በደም ሆና የሚያሳዩ ቪዲዮዎች እና ፎቶዎችም አሉ።
ድርጅቱ በለቀቃቸው ቪዲዮዎች እና ፎቶዎች ላይ ነሒማ ብቻ ሳትሆን 50 ገደማ ሌሎች የአጋቾቹ ሰለባዎች ከጀርባዋ ተደርድረው ይታያሉ።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በሊቢያ እየተካሄደ ያለውን የባርነት ንግድ ዓለም ረስቶታል ሲሉ ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ይወቅሳሉ።
“ሊቢያ ውስጥ ያለው እውነታ ይህ ነው። ይህን ድርጊት አሰቃቂ ብቻ ብሎ ማለፍ ተገቢ አይደለም” ይላሉ ከዚህ ቀደም ከእገታ የተረፉት እና አሁን የመብት ተሟጋች ሆነው የሚያገለግሉት ዴቪድ ያሚቢዮ።
ዲቨድ እንደሚሉት ነሒማ አሁን ያለችበት ሁኔታ በርካታ ስደተኞች የሚያልፉት አሳዛኝ ክስተት ነው።
የመብት ተሟጋች ቡድኖች ሊቢያ በተለይ ለጥቁር አፍሪካውያን ስደተኞች መካነ መቃብር ሆናለች ይላሉ። አክለውም መሰል የእገታ ድርጊቶችን የሚፈፅሙ ‘ታጣቂዎች ለምንድነው የማይጠየቁት?’ ሲሉ ይጠይቃሉ።
ዴቪድ “ቁጭ ብሎ በመመልከት ፍትሕ ማግኘት አይቻልም። ፍትሕ ሊመጣ የሚችለው ይህ የታጣቂዎች ኔትዎርክ ሲበጣጠስ እንጂ በንግግር አይደለም” ይላል።
የነሒማ እና የሌሎች በሊቢያ የባርነት አረንቋ ውስጥ የሚገኙ ስደተኞች መጨረሻ የዓለም መሪዎች በሊቢያ ያለውን ጭካኔ ካላስቆሙ የሚቆም አይደለም ሲሉ ዴቪድ አሳሳቢነቱን ይገልጻል።
ከዚህ ቀደም በሊቢያ የነበረውን የባርነት ጨረታን የሚያስታውሰው ዴቪድ ልክ እንደ ከዚህ ቀደሙ ለችግሩ ጀርባችንን ከሰጠን ሊቢያ ለአፍሪካውያን መካነ መቃብር መሆኗ ይቀጥላል ሲል ያስጠነቅቃል።
በእርስ በርስ ጦርነት እየታመሰች ወዳለችው ሊቢያ በስደት የተጓዙት ነሒማ እና ሌሎች ስደተኞች መጨረሻቸው ምን ሊሆን እንደሚችል አይታወቅም።
በርካታ ኢትዮጵያውያን እና ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ስደተኞች ሕይወታቸውን ለመቀየር በሚል ወደ አውሮፓ በሚያደርጉት ጉዞ የሜዲቴራኒያን ባሕርን ከማቋረጣቸው በፊት ሊቢያን ይረግጣሉ።