ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኢትዮጵያ ምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ስነምግባር ማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 1162/2011 ላይ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ምክክር እያካሄደ ነው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሮ ሜላትወርቅ ኃይሉ በመድረኩ እንደገለፁት፤ የአዋጅ ማሻሻያው ቦርዱ በሀገሪቱ ፍትሀዊና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ማካሄድ እንዲችል አጋዥ ሆኖ የተሰናዳ ነው።
ማሻሻያው በ2013 ሀገራዊ ምርጫ ወቅት ያጋጠሙትን ክፍተቶች በመለየት የተዘጋጀ ነው ያሉት ወይዘሮ ሜላትወርቅ፤ ከተለያዩ ባለድርሻ አካለት ጋር በሚደረግ ውይይት የተነሱ ሀሳቦች ግብዓት ሆነው በአዋጁ ቀርበዋል ብለዋል።
ቦርዱ በተለያዩ ጊዜያት ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እና ከሲቪክ ማህበራት ጋር በሚያደርጋቸው ውይይቶች ከዚህ ቀደም በነበረው አዋጅ የተካተቱ ድንጋጌዎች መሻሻል የሚገባቸው መሆኑን በመረዳት የተዘጋጀ ማሻሻያ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በቦርዱ የህግ ጉዳዮች ባለሙያ አቶ ኢድሪስ ሰልማን በሰጡት ማብራሪያ፤ የምርጫ አስፈፃሚዎች ቁጥር መጨመር፣ በምርጫ ውሳኔ ቅሬታ ያላቸው ሰዎች ቅሬታ አቅርበው አፋጣኝ ውሳኔ የሚያገኙበት አሰራር መዘርጋት በአዋጁ የተካተቱ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም በማሻሻያው በመላው ሀገሪቱ በእያንዳንዱ ቀበሌ ቢያንስ አንድ የምርጫ ጣቢያ እንዲቋቋም የሚደነግግ ህግ የተካተተ ሲሆን፣ በአንድ የምርጫ ጣቢያ የመራጮች ቁጥር ከአንድ ሺህ የሚበልጥ ከሆነ አዲስ የምርጫ ጣቢያ እንዲቋቋም እንደሚደረግ ተናግረዋል።
ሀገር አቀፍ ፓርቲ ለመመሰረት የሚያስፈልገው የአባላት ስብጥር ከአምስት ክልሎች ወደ ሰባት ክልሎች እንዲያድግ ተደርጎ በማሻሻያው ቀርቧል።
በአዋጁ ከዚህ በፊት የነበረው የምርጫ ቅስቀሳ ምርጫው ከሚደረግበት 4 ቀን በፊት መቆም አለበት የሚለው ድንጋጌ ወደ 48 ሰዓት ዝቅ እንዲል ተደርጓል ብለዋል።
በክብረአብ በላቸው
ኢፕድ